ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን
(1929 -1998 ዓ.ም)
"የማይነጋ ህልም ሳልም
የማይድን በሽታ ሳክም
የማያድግ ችግኝ ሳርም
የሰው ሕይወት ስከረክም
እኔ ለኔ ኖሬ አላውቅም"
"የዛሬ 57 ዓመት 1943 ዓ.ም ጃንሆይ የመጀመሪያ ቴአትሬን የዳኒስዮስ ዳኝነትን አምቦ ትምህርት ቤት አዳራሽ አይተው ስሜ በአዲስ ዘመንና በኢትዮዽያን ሄራልድ "ወጣት ደራሲ" ከተባለ ጀምሮ ጋዜጠኞች የሕይወት ታሪኬን እንዳስለፈለፉኝ ነው። ስለሕይወቴና ስለስራዎቼ አጫጭር ሐተታዎች ከፃፉት ከክቡር አሐዱ ሳቦሬ፥ ከብርሃኑ ዘሪሁን፥ከተገኘ የተሻወርቅ ከዻውሎስ ኞኞ ከከፈለ ማሞ፥ ከፍቅረ ማርያም ይፍሩ፥ከሙሉጌታ ሉሌ፥ከስዩም ወልዴ፥ከአጥናፍ ሰገድ ይልማ በተለየና ዘርዘር ባለመልኩ በአሉ ግርማ "የፀጋዬ ዝምታ" በሚል ርዕስ መነን መጽሔት ላይ፥ ማዕረጉ በዛብህ "የቦዳ አቦ የስለት ልጅ" በሚል ርእስ ከእንግሊዘኛው "መስከረም መፅሔት ላይ፥ ሪቻርድ ፓንክረስት "ፀጋዬ" በሚል ርእስ በእንግሊዘኛው "selamta" ላይ፥ አሳምነው ገ/ወልድና ነጋሽ ገ/ማርያም በኢትዮዽያ ሬዲዮና በኢትዮዽያ ቴሌቪዥን ላይ የፃፉትንና የተረኩት ጎላ ብለው ይታወሱኛል። -- ከዚህ ይልቅ ከሕይወት ታሪኬ ውስጥ ለኔ በጣም ጎልተው የሚታዩኝን፥ ሞቼ የተነሳሁባቸውን ዓይነት ልዩ ትዝታዎቼን ለመነሻ ያህል ልጥቀስላችሁ።
" እኔ የስለት ልጅ ነኝ። የስለት ልጅ ደሞ እኔ ባላምንበትም ትክዝተኛና ሕልመኛ፥ ሰበበኛና ሞገደኛ ነው ይባላል። ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ቁሴ ዲነግዴ በተወለዱበት ቦዳ አቦ ከአሰቦ በስተደቡብ ሜጫ ገጠር መንደር ነው እኔም የተወለድኩት 1929 ዓ.ም። አባቴ "ፀጌ፥ቁሴ" ይሉኝ ነበር ቁሴ ማለት በኦሮምኛ "ትክዝያለ" ወይም "ትክዝተኛ" ማለት ነው። እናቴ እኔን እንድትወልድ የተሳለችለትና ክርስትናም የተነሳሁበት ቦዳ ደረባ አቦ ቤተክርስቲያንን የተከሉት ሀብተጊዮርጊስ ናቸው። እና የመጀመሪያው የማይረሳና ትዝታዬ ፥ገና የሁለት ወር ጨቅላ ሁኜ አባቴ ከማይጨው ጦር ሜዳ ሳይመለሱ፥ ቤታችንን ባንዳ አቃጥሎት እናቴ በርራ እሳቱ መሀል ገብታ እንዴት እንዳወጣችኝ ታላቅ እህቴ ወ/ሮ አስካለ ገ/መድኅን ትንሽ ልጅ ሆና "የቦዳ አቦ ተአምር" እያለች ደጋግማ ያጫወተችኝ ታሪክ ነው።
"ሁለተኛው የዛሬ 27 ዓመት 1973 ስኳር በሽታ ዳያቤቲስ በድንገት ጥሎኝ አምስት ቀን ሙሉ "ኮማ" ውስጥ ገብቼ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ICU አጣዳፊ ጣዕር ህክምና ክንፍ ተኝቼ ጥቁር አንበሳ ተብሎ በሆለታ ልጆች መታሰቢያነት እንዲሰየም ለደርግ መንግሥት ጥናት ያቀረብነው አለቃዬ ክቡር ተክለፃዲቅ መኩሪያና እኔ ነን ፥ የነፕሮፌሰር ዕደማርያምና ጀማል፥ በነዶክተር ብሩ፥ባዩ፥ ገብረህይወትና መስፍን ልዩ ጥረት ከመንቃቴ በፊት፥ ስለስለትና ስለእሳት ስለምላጭና ስለብሽሽት፥ ስለሞትና ከሞት በኋላ በህልሜ ያየሁትንና በእንቅልፍ ልቤ የተናገርኩትን ታሪክ ነው።
"ሦስተኛው የዛሬ ዘጠኝ ዓመት 1991 ዓ.ም ሀዋርድ ዩኒቨርስቲ Ethiopia Foot Print of Time ኢትዮዽያ የጊዜ እግር አሻራ የተባለውን ሁለተኛ ቅፅ የእንግሊዘኛ መጸሐፌን ከዩስተን ቴሶሬ ጋር ያዘጋጀነውን የመጀመሪያውን ቅፅ ሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ በፊልም ቀርፆታል አጠናቅሬ፥ ሁለተኛውንም በፊልም እንዳስቀርፅ ጋብዞኝ አሜሪካ እንደደረስኩ በቤተሰቤ ግፊት ደንገተኛ ምርመራ ተመርምሬ ኩላሊትህ ፈንድቷል ተብዬ ብሽሽቴን በተቀደድኩበት እኩለ ሌሊት የግማሽ እውንና የግማሽ ህልም እይታዬ ታሪክ ነው።
"ጎልተው ይታዩኛል የምላቸው እነዚህ ሦስት ትዝታዎች፥ በሕይወቴ ከእሳት የተረፍኩበት ሰዓት ጀምሬ ሌሊትና ቀን ስጮህ ብሽሽቴ አብጦ በሁለተኛው ቀን ወ/ሮ ስመኝ የሚባሉ ማህበርተኛ የነበሩ፥ የሴትና ወንድ ሕፃናትን ብልት ገራዥና የተለምዶ መድኃኒት አዋቂ መበለት ከሩቅ ቦዳ ዳርቻ ተጠርተው ደርሰው ብሽሽቴን በምላጭ በጥተው ነው አሉ ዝም ያሰኙኝ።
ገና በዘጠኝ አመቱ የተወነ፥ በ13 ዓመቱ ተኩሉ ድንቅ የተሰኘ ተውኔቱን የደረሰው በ26 ዓመቱ የአፍሪካ አንድነት አህጉራዊ መዝሙር ሥነግጥም ደርሶ ዕፁብ የተሰኘው በ29 ዓመቱ የሀገር የአማተራዊ ሽልማቶችን የተጎናፀፈው ፀጋዬ ገ/መድኅን በኢትዮዽያ፥ በአፍሪካና በዓለም ሥነጽሑፍ ህዋ ላይ - በጥበባት ሞገድ እንደ " አውሎ ሐሳብ " ተዥጎድጉዶ የካቲት 18 ቀን በምድረ አሜሪካ በ69 ዓመቱ፥ አፀደሥጋው አረፈ በሚወዳትና በተሟገተላት ውድ ሀገሩ አርፏል።
ደራሲው ሥራዎች
1. እሳት ወይ አበባ(ግጥምና ቅኔ)
2. የዳኒሲዩስ ዳኝነት(ተውኔት)
3. በልግ(ተውኔት)
4. የደም አዝመራ(ተውኔት)
5. እኔም እኮ ሰው ነኝ(ተውኔት)
6. የከርሞ ሰው(ተውኔት)
7. የእሾህ አክሊል(ተውኔት)
8. ክራር ሲከር(ተውኔት)
9. አስቀያሚ ልጃገረድ(ተውኔት)
10. እኝ ብዬ መጣሁ(ተውኔት)
11. ቴዎድሮስ(ተውኔት)
12. ምኒልክ(ተውኔት)
13. ጴጥሮስ ያቺን ሰአት(ተውኔት)
14. ዘርዓይ ደረስ(ተውኔት)
15. ጆሮ ገድፍ(ተውኔት)
16. ሀሁ በስድስት ወር(ተውኔት)
17. እናት ዓለም ጠኑ(ተውኔት)
18. መልእክተ ወዛደር(ተውኔት)
19. አቡጊዳ ቀይሶ(ተውኔት)
20. ጋሞ(ተውኔት)
21. ሀሁ ወይም ፐፑ(ተውኔት)
22. ቴራቲረኞች [ የምፀት ኮሜዲ፥ አልታየም ] (ተውኔት)
23. ዐፅም በየገጹ (ተውኔት)
24. ሰቆቃወ ዼጥሮስ(ተውኔት)
25. ትንሣኤ ሰንደቅ ዓላማ(ተውኔት)
26. የመቅደላ ስንብት(ተውኔት)
27. ጥላሁን ግዛው(ተውኔት)
28. ዐፅምና ፈለጉ(ተውኔት)
ምንጭ:ብርሀነመስቀል ደጀኔ 2000ዓ.ም ብራና.ማ.ቤ ካሌንደር።