Wednesday, December 5, 2012

ሰው ለሰው



የህይወት ጥያቄዎች

አንድ ሰው ለምንድነው የሚኖረው ?

የህይወት ፈተናዎች ምንድናቸው ? 


ሰው መሆን ጥበብ

ይብዛም ይነስም ማንኛውም ሰው የሚመራበት የራሱ የሆነ የህይወት ፍልስፍና ፣ አስተሳሰብ ፣ አመለካከት አለው ። ህይወታችን ራሱ የአስተሳሰባችን ነፀብራቅ ነው ። ትክክኛውን ፍልስፍናና አመለካከት የያዘ ሰው በህይወት ውሰጥም መርሁ እየሰራለት በስኬት ላይ ስኬትን እየደራረበ ሲሄድ ፣ በአንፃሩ ግን በህይወት ውስጥ ትክክለኛውን ጎዳና ያልያዘ ሰው ግን ወደ አዘቅቱ እየገባ ሲሄድ መመልከት የተለመደ ነው ። ፍልስፍና በህይወታችን ውስጥ ከምናስበው በላይ የተራሱ በጎም ይሁን አሉታዊ ተፅእኖና አሻራ አለው ። ለምሳሌ የምናምንበትን ሀይማኖት ብንወስድ ከታላላቅ ፈላስፎች አለማዊም ሆነ መንፈሳዊ ከሆኑ የሚነሱ በርካታ ፍልስፍናዎች የተደገፈ ሲሆን ፣ ያም እምነት በህይወታችን ፣ በአኗኗራችን ላይ በየቀኑ ሲንፀባረቅ ማየት የተለመደ ነው ።    
      በዚህ ጉዳይ ላይ የተፃፉ ፅሁፎች በአብዛኛው አለም እንዲህ መምሰል አለባት ፣ እንደዚህ መሆን አለባት ፣ ስለዚህ እንደዚህ መሆን አለበት የሚሉ ሲኖሩ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አለም እንደዚህ ነች ፣ አለም ይህቺ ነች በቃ የሚሉም አሉ ። የሁለቱን ልዩነት መረዳት ያሻል ። ለምሳሌ ስነ - ምግባርን ብንወስድ በውስጡ በርካታ የግብረ - ገብ ህግጋት አሉት ፣ ራሱ ስነ - ምግባር ከጋርዮሽ ጀምሮ የነበረ አስተምህሮ ሲሆን ፣ ነገር ግን ገሀዳዊው አለም ግን ከእነኚህ ህግጋት አፈንግጦ ማየት የየእለት ትእይንታችን ነው ። ምንም እንኳን የስነ - ምግባርና የግብረ - ግብ ፈላስፋዎች የተለያዬ ነገርን ቢሉም በተግባር ግን እነሱ የሚሉት ሲጣስ የየእለት ትእይንታችን ነው ።   
     ሳይንስ እንደየ አመለካከታችን ሊተረጎም የማይችል «Objective» የሆነ ነገር ስለሆነ ለሁሉም ጥያቄዎች ምላሽን አይሰጥም ። ሳይንስ በአመክንዮና በህልዮት ላይ የተመሰረተ ነው ። በማህራዊ ሳይንስ እነኚህ ነገሮች ሊሰሩም ላይሰሩም ይችላሉ ። በመሆኑም ማህበራዊ ሳይንስ ከላይ ሲታይ ቀላል ቢመስልም ይበልጥ ውስብስብና አስቸጋሪ ነው ። ሳይንስ ተጨባጭ በሆኑ እውነታዎች ላይ የተመሰረተ ነው ። ሆኖም ሳይንሳዊ እውነታዎች አይለወጡም የሰው ልጅ ከመፈጠሩ በፊትም የነበሩ ናቸው፣የሚሰሩትም በመሬት ላይ ብቻ ሳይሆን ለመሬት ውጪ  በህዋው እና በአፅናፈ - አለም (Universe) ውስጥ ጭምር ይሰራሉ ። በዚህ አያያዝ ከሄደ የሰው ልጅ የማሰብ ችሎታ ያለው ስለሆነ እና ንቃተ - ህሊና ያለው ፍጡር ስለሆነ በጊዜ ሂደት በርካታ ሳይንሳዊ ሚስጥር የነበሩ ነገሮች እየተገለፁና እየተብራሩ መሄዳቸው አይቀሬ ነው ። 
          ሳይንስ ዋናው ስራው ጥያቄዎችን መመለስ ሳይሆን ጥያቄዎችን መጠየቅ ነው ። ስለዚህ ሳይንስ የማይቆም ሲሆን ፣ የሳይንስ አላማውም ተፈጥሮን የመቆጣጠር ሂደት ነው ። ምንግዜም ቢሆን አዳዲስ ምርምሮች ፣ አዳዲስ ይሄ ለምን እንደዚህ ሆነ የሚሉ ጥያቄዎች ይጠየቃሉ - የአይቆሙም ። በአንፃሩ ሀይማኖት መጠየቅ ሳይሆን መመለስ ነው ። በርካታ ታላላቅ አዳዲስ የሳይንስ ግኝቶች በአለም ላይ ተገኝተዋል ፣ እየተገኙም ነው ። ነገር ግን ለምሳሌ አሁን በቅርቡ ሂክስ ቦዞን ወይንም የእግዜር ቅንጣት በመባል የሚታወቀውን ሂክስ በተባለው እንግሊዛዊ ሳይንቲስት በ 1965 ዓ.ም. ሊኖር የችላል ብሎ የገመተውን በ2012 ዓ.ም. በስዊዘርላንድና በፈረንሳይ ድንበር መሀከል በሚገኝ ላብራቶሪ ውስጥ በምርምር ደርሰውበታል ። ነገር ግን አዳዲስ ግንኝቶች ሲገኙ የሀይማኖት ሰዎችና ፣ በሀይማኖት የማያምኑ ወይንም በእግዝአብሄር መኖር በማያምኑ ሰዎች መሀከል የተለያዩ አመለካከቶች ይንፀባረቃሉ ። አንዳንዶቹ ይህ የእግዝአብሄር መኖር ማረጋገጫ ነው ሲሉ ፣ ሌሎቹ ደግሞ የለም ይህ የእግዝአብሄር አለመኖር የበለጠ ማረጋገጫ ነው በማለት ይከራከራሉ ።

     የሰውን ልጅ የታሪክ አካሄድ ልብ ብለው የታዘቡ የታሪክና የፍልስፍና ባለሙያዎች፣ የሰው ልጅ አደገኛ ወደ ሆነው የታሪክ ምእራፍ እየገባ ነው ይላል ። እንደ ሀውኪንግስ አባባል ከሆነ በመሆኑም ሌሎች ፕላኔቶችን መፈለግና በእነሱ ላይ መስፈር (ኮሎናይዝ) ማድረግ አለበት ባይ ነው ። ምድርን አደገኛ የሚያደርጓት እንደ አካባቢ አየር መበከል ፣ የኒውክሊየር ጦርነት ስጋቶች ፣ የመሳሰሉት ናቸው ።

       በዚህች ምድር ላይ በርካታ ባለቤቶች ነበሯት ። ከ60ና ከ70 ሚሊየን አመታት በፊት ዱይኖሰሮችና መሰል ግዙፍ እንሰሳት የዚህች ምድር ባለቤት የነበሩ ሲሆን አሁን ደግሞ ተራው የሰው ልጅ ሲሆን ራሱ በፈጠረው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ራሱን ካላጠፋ ።

ይሁን እንጂ በአጠቃላይ ሳይንሳዊ ግኝቶች እንደሚያመለክቱት የሰው ልጅ ከእርሱ እጅግ የገዘፈና ሀያል የሆነ አለም አካል ነው ። ነገር ግን እስካሁን ድረስ በዚህ ስርአተ - ፀሀይም ሆነ በአፅናፈ - አለሙ ውስጥ ከተፈጠሩት ፍጥረታት ሁሉ ማሰብ የሚችለውና ህሊናዊ ንቃት ያለው ፍጡር የሰው ልጅ ብቻ ነው ። ስለሆነም ራሱን ከተቀረው አለም ጋር አስማምቶ ማኖር ይችላል ። የሰው ልጅ እንደ ዘርም ጭምር እነኚህን የአፅናፈ - አለሙ ህግጋት ሊረዳቸውና ለህልውናው ሲል ሊጠብቃቸው የሚገቡ ናቸው ፣ እንጂ ሊቀይራቸው የሚችላቸው አይደሉም ። ሳይንቲስቶች እንደሚነግሩን እነኚህ ህግጋት የተፈጠሩት ጊዜ ከተፈጠረ ጀምሮ ነው ተብሎ ይታመናል ። ይህ ማለት የሰው ልጅ ራሱ ከመፈጠሩና ፕላኔቶችና ፀሀይም ጭምር ከመፈጠራቸው ጀምሮ እነኚህ ህግጋት ነበሩ ወደ ፊት ከሰው ልጅ ህልውና በኋላም ይኖራሉ ።


    አብዛኛው ሀይላችን የሚገኘው በምናደርገው ነገር ውስጥ ሳይሆን ፣ በማናደርገው ነገር ውስጥ ነው ። ኒቼ ይህንን ሀሳብ አንፀባርቋል ። ሀይል ወይንም የምንፈልገው ማንኛውም ነገር በአለም ላይ በብዛት ያለ ሲሆን አንድ ቦታ ብቻ ያለ ነገርም አይደለም ። በአገርኛው አባባል እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል እንዲሉ ፣ በሌላ ቦታ ያን ነገር በበለጠ ልናገኘው እንችላለን ፣ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ሰዎች ያን ነገር ለማግኘት አስቸጋሪ በሆነ ቦታ ላይ በአንድ ቦታ ላይ ጊዜያቸውን ፣ ጉልበታቸውን ያጠፋሉ ። ያም ሆኖ ግን እኛ ሰዎች መጨረሻ ላይ ተሸናፊዎች ነን ። ብዙ ብንታገልም መጨረሻ ላይ ግን ሽንፈትን መከናነባችን አይቀርም ።

     ማታለል አንድ ሰው በራሱ የሚፈልገውን ነገር ለማግኘት ብቃት እንደሌለው ያለመክታል ። ብዙ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች መድረስ የሚፈልጉበት ደረጃ መድረስ ላይ የማይችሉ ሰዎች የሚፈልጉበት ደረጃ ለመድረስ ማታለል አቋራጭ መንገድ አድርገው ይቆጥሩታል ። ሆኖም ግን ብዙም ርቀት መሄድ ሳይችሉ ይቀራሉ ። በሌላ በኩል አታላይ የሆነ ሰው የእውነትን ዋጋ ያልተረዳ ነዉ ። ቻይናዊው ፈላስፋ ሜንሲየስ  እንዳለው ።

    ሰዎች ችግር ውስጥ ሲገቡ አይታወቃቸውም ። ሆኖም ግን ቀስ እያሉ እየሰመጡ ይሄዳሉ ። አንዴ ከሰመጡና ከዘገየ በኋላ ሙሉ በሙሉ ይነቃሉ ። ከባድ የሆነ ችግር በተለይ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል ። እዚህ ጋር እድልም የራሱ ሚና አለው ። በእድል አንዳንድ ጊዜ ከባድ የሚመስለን ችግር በቀላሉ ይወገዳል አንዳንዴ ደግሞ ቀላሏ ነገር ወደ ከባድ ችግር ትለወጣለች ።  

ስኬታማ ለሆነ ኑሮ ተግባራዊ የሆነ የህይወት ልምድ ያስፈልጋል ። በተለይም በርካታ ችግሮችን ያሳለፈ ሰው ችግሮች አስቀድመው ሊፈጠሩ ሲሉ አስቀድሞ ማየት ይችላል ። በአለም ላይ አይሁዳውያን በርካታ ችግሮችን አሳልፈዋል ። ከትምህርትና በማንበብ እውቀትን ከመሰብሰብ ውጪ አንድ ሰው በህይወት ውስጥ ተሳታፊና በመሆን የህይወት ልምድን ሊቀስም ይችላል ። ብዙ ጊዜ ሰዎች አንድን ነገር ከላይ የሚያዩረትን ነገር እውነት አድርገው ነው እሚቀበሉት ። ሆኖም ግን ወደ ውስጥ ሲገባና ከላይ ሲታይ የተለያየ መሆኑን አይረዱም ።

         አለማወቅ ራሱ ሰዎች ደስተኛ ሆነው እንዲኖሩ የሚያስችል ነገር ሲሆን ፣ ከተማሩ ሰዎች ይልቅ ያልተማሩ ሰዎች ደስተኛ ሆነው እሚገኙበት ጊዜ አለ ። እውቀት ብዙውን ጊዜ ከነገሮች ጋር ያለንን ትስስርን ስለሚፈጥር ፣- ማወቅ ትስስርን ይፈጥራል ስለዚህ- የሰዎችን ደስታ ይቀንሳል ።

       በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ልሂቃን የሚባለው የህብረተሰብ ክፍል የሚሆኑት ሰዎች ለመምራት የሚያስፈልገውን እውቀትን የሰበሰቡና ተግባር ላይ የሚያውሉ ናቸው ። ብዙሀኑ ህብረተሰብ ክፍል ይህንን እውቀት ሊያሰባስብ ሳይችል ሲቀር ጥቂቶች ግን የሄን ማድረግ የቻሉ ግን በማህበረሱ ላይ ከፍ ያለ ቦታን ይይዛሉ ።

             የሰው ልጅ ጥረት ለራሱ ያለውን ስሜት (Ego) ማርካት ነው ። ሰዎች ትልቅ ስልጣንን ፣ ብዙ ሀብትን በማግኘት ወይም ባለቤት በመሆን ራሳቸውን ትልቅ በሚሉት ቦታ በማዋል ለራሳቸው ያላቸውን አመለካከት ለማርካትና ስሜታቸውን ለማስደሰት ይመጥራሉ ። ነገር ግን እነኚህ ሁሉ ነገሮች በጊዜ ሲያልፉ ወይም ባልተጠበቀ ሁኔታ በነው ሲጠፉ ሊያዩም ይችላሉ ። ሰዎች ብዙውን ግዜ በጣም ሲቆለማመጡ (Flatter) ሲደረጉ ይቀበላሉ ። ይህም ላላቸው ቦታ ሌሎች ሰዎች እንዲቀበሏቸው ከመፈለጋቸው የተሳ ብዙውን ግዜ በስልጣንና በሀብት ያሉ ሰዎች ይህንነን ይፈልጉታል ለዚህም ምክንያቱ የሌሎች ሰዎችን ተቀባይነትን ለማግኘት ካላቸው ጉጉትና ፍላጎት የተነሳ ነው ።  

            አንዳንዴ ሲታሰብ ማንኛውም ነገር በሚያልፍበትና በሚረሳበት አለም ለነገሮች ያን ያህል ክብደት መስጠት አስፈላጊ አይደለም ያስብላል ። ለምሳሌ ዛሬ በጣም ትልቅ ቦታን የምንሰጠው ነገር ነገ ከነገ ወዲያ የሚረሳና ብሎም የሚወገዝ ሁሉ ሊሆን ይችላል። ዛሬ እውነት ነው ፣ ትክክል ነው የምንለው ነገ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ውሸት ነው ሊባል ይችላል ። ብዙ ሰዎች ግን ዛሬ እውነት ነው ፣ ትክክል ነው ለሚሉት ነገር ሊሞቱለትና ለገድሉለት ዝግጁዎች ናቸው ይሁን እንጂ ያ ነገር ፍፁም ትክክል ስለመሆኑ በበቂ የሚያውቁት ነገር የለም ፣ ወይም ዛሬ ትክክል ነው ቢባልም ነገ ከነገ ወዲያ ጥፋት ሆኖ ሊገኝ ይችላል ። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በተደጋጋሚ የታየ ሀቅ ሲሆን ። ስፒኖዛ የተባለው ታላቁ የሆላንድ ፈላስፋ በተደጋጋሚ የሚጠቀስለት አባባል እንዳለው «እውነት የራሷም ፣ የሀሰትም ማስረጃ  ነች» ብሏል ።

             አንዳንድ ሰዎች በተቋም ደረጃ ሊሆኑ ይችላሉ ። በራሳቸው በችሎታቸው ፣ በስብእናቸው እና በአቅማቸው እንደ አንድ ተቋም ሊቆጠሩ የሚችሉ ሰዎች አሉ ። በአብዛኛው ሰዎች ቁሳዊ ነገርን በመፍጠር በኩል ነው የህይወታችንን አብዛኛውን ዘመን የምናሳልፈው ማለት ይቻላል ፣ የአብዛኛው ሰዎች ጥረትም በዚሁ ዘርፍ ሲሆን  ። ነገር ግን ቁሳዊ ነገርን ከመፍጠር አልፈው ለሰው ልጅ ብርሀንን የቀደዱ ፣ ለሌላው ብርሀን የሆኑ ሰዎች በመቶዎች ከሚቆጠሩ አመታት ውስጥ በጣት የሚቆጠሩ የዛ አይነት ሰዎች ናቸው የሚገኙት ቢባል ማጋነን አይሆንም ።

             ማንኛውም በተፈጥሮ ሲሆን በሰዎች የተፈጠረ ነገር በሰዎች በቀላሉ ሊፈርስ ይችላል ። ለምሳሌ ሀገርን ብንወስድ በሰዎች የተፈጠረ ነገር ሲሆን ተፈጥሮ አህጉራትን ሲፈጥር ሰዎች ደግሞ አህጉሩን ተከፋፍለው ከዚህ እስከዚህ ድረስ ያንተ ከዚህ መልስ የኔ ብለው ነው ሀገር የምንለው ነገር የተፈጠረው ። ስለዚህ ይሁን እንጂ ሀገር ማለት ደግሞ የዛ ሀገር ዜጎች የመኖር ህልውና መሆኑ ደግሞ እማይዘነጋ እውነታ ነው ። በአለም ላይ ሀገር የሌላቸው ሰዎች ምን ያህል እንደሚሰቃዩ ሁላችንም የምናውቀው ሲሆን ያለሀገር የአንድ ሰው ህልውና አይታሰብም ። ይሁን እንጂ ሀገርን ላፍርስ ብሎ አንድ ሰው ቢነሳ ደግሞ ሊያደርግ የሚችለው ጉዳት ቀላል አይሆንም ሀሳቡ ባይሳካም እንኳን ።

               ፍልስፍና በሁለት ዋና ዋና አቅጣጫዎች ሊታይ ይችላል ። በአንድ በኩል ተቋማትን ፣ መንግስትን ፣ ሀይማኖትን ፣ ከቤተሰብ ጀምሮ ያሉ ተቋማትን በመገንባትና በእነዛ ተቋማት አማካይነት የሰው ልጅ እዚህ ደረጃ ደርሷል ። ነገር በግን እነዚህ ተቋማት ባይኖሩ ኖሮ የሰው ልጅ ስልጣኔ፣ የቴልክኖሎጂ ግስጋሴና እመርታ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ አይችልም የነበረ ሲሆን ። በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች ከፍተኛ እውቀትና ክህሎት ያላቸው ሰዎች በየትኛውም ትውልድና ሀገር ውስጥ ይገኛሉ ። ነገር ግን እውቀትን ለማሰባሰብ ፣ አዳዲስ ነገሮቸን ለመፍጠር ሰዎች በጋራ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የተሻለ ውጤትን ይሰጣል ። አንዱ አይነት አካሄድ አለምን እንደዚህ ነች ብሎ መግለፅና ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አለም እንደዚህ መምሰል አለባት ወይንም እንደዚህ መሆን አለባት የሚል ነው ። ፕሌቶ የኔ ማስወታወሻ በመጪዎቹ ትውልዶች ውስጥ የሚኖረኝ የባለውለታነት ሰሜት ነው ብሏል ።

                    መፈላሰፍ፡- ሁለንተናዊ ተሞክሮ
        
ያም ሆነ ይህ እኔ የምለው የአንድ ሕዝብ ፍልስፍና ያንን ፍልስፍና ከሚያቀነቅኑት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተመራማሪዎች ጋር ጥቂት ወይም ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም ነው፡፡ መፈላሰፍ ሁለንተናዊ ወይም ዓለምአቀፋዊ ተሞክሮ ነው፡፡ እያንዳንዱ ባህል የራሱ የሆነ አመለካከት አለው፡፡ የፍልስፍና ታሪክ ካጠናችሁ የምትገነዘቡት ነገር ቢኖር የፍልስፍናን ትርጉም በተመለከተ ምንም ዓይነት ስምምነት እንደሌለ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ፍልስፍና የእውቀት ፍቅር ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ እውነትን መፈለግ ነው ይላሉ፡፡ የተቀሩት ደግሞ የመደነቅ ስሜት ነው ይላሉ፡፡ በአጠቃላይ ፍልስፍናን በተመለከተ የተደረሰበት ስምምነት ቢኖር በዙርያችን ባለው ዓለም ውስጥ በተለያዩ ክስተቶች አንፃር ሥርዓትን ለማስፈን መሞከሩ ነው፡፡ እነዚህ የተለያዩ ክስተቶች ምንድናቸው? ነገሮች፣ ድርጊቶች፣ ክንዋኔዎች፣ ልንረዳው የምንችለው ዓለም፣ ሥነ ምግባራዊ ዓለም እንዲሁም ሜታፊዚካዊው ዓለም ናቸው፡፡  (ዮሴፍ ቢ፤ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ፈላስፋዎች፣ 2001 ..)

             ፍልስፍና ስለ ሰው የሚያወራ እንደመሆኑ የሰውን ልጅ ስነ - ልቦናን ማወቅ ለፍልስፍና መሰረት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም ።የፍልስፍና ዋና አላማው ምንድነው ቢባል ከላይ እንደተጠቀሰው ስርአትን ማስፈን ነው ። ይህንንም ስነ - ምግባርን በማስረፅ ይሆናል ። ሀሳዊ - ፍልስፍና (ሲዶ ፍልስፍና) በመባል የሚታወቅ ፍልስፍናም አለ ። ነገር ግን ይሄ ፍልስፍና ሃሳዊ በመሆኑ ብዙም አያዛልቅም ። ዋናው የፍልስፍና አላማ ሰዎችን በሰለማዊና ፣ ፍትሀዊ በሆነ ህብረተሰብ ውስጥ እንዲኖሩ ማስቻል ነው ። ለምሳሌ ታላላቅ ሀይማኖቶችን ብንወስድ ዋናው አላማቸው የሰው ልጅ እርስ በእርሱ እንዳይበጣበጥ ፣ ፍትህ እንዳይዛባ በማድረግ ላይ የተመሰረተ ነው ።  ይሄም ፍትህ ባይኖር ፣ ሰላም ባይሰፍን ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ፣ ውድመት ፣ ጦርነትን በመፍራትና ከመምጣቱ በፊት ለማስቀረት ነው ።    

                   የፍልስፍና መሰረታዊ ጥያቄ የሚባሉት ውስጥ አንዳንዶቹን ብንጠቅስ ቁስ አካል ነው ወይስ መንፈስ (Idea) ነው እሚቀድመው? በዚህ ህዋው ውስጥ ከሰው ልጅ ሌላ ህይወት ያለው ህሊና (Conscious) ያለው ፍጡር አለን? የህይወት ትርጉም ምንድነው ? ነፍስ ወይም መንፈስ አለን ካለስ በምን መንገድ ነው ያለው ? የሰው ልጅ ለምን ይሰቃያል? የመሳሰሉት መሰረታዊ የፍልስፍና ጥያቄዎች ሲሆኑ እስካሁን ድረስም የሰው ልጅ ባለው ቴክኖሎጂና በደረሰበት ሳይንስ ቁልጭ ያለ መልስ የተሰጠባቸው አይደሉም ። ለምሳሌ የአሜሪካውን የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳን ብንወስድ ፣ ከአሜሪካ ግብር ከፋዮች በሚሰበሰብ ገንዘብ በርካታ ምርምሮችን በማድረግ ፣ የሰው ልጅ ስለጠፈር ያለውን እውቀት አሳድጎታል ። ቀድሞ ዝንባሌውና ችሎታው ያላቸው ሰዎች ቀደምት ሳይንቶስቶች በመነሳት እንደ እነ ጋሊሊዮ ፣ ኮፐርኒከስ ፣ የመሳሰሉት በግላቸው ምርምርን፣ ጥረትና ስራ በርካታ ፈር - ቀዳጅ ስራዎችን አበርክተዋል ። ነገር ግን አሁን የሰው ልጅ ከዛሬ 5 እና 4 መቶ አመታት የተሻለ ደረጃ ላይ በመድረሱ ምክንያት እነኚህ ምርምሮች በተቋም ደረጃ እድገት ማሳየት ችሏል የሰው ልጅ ስለ እሚኖርበት ጠፈር ያለውን ግንዛቤ ከፍ በማድረግ ፣ ኑሮውንም በአንድ እርምጃ ማራመድ ችሏል  

              በፍልስፍና ውስጥ ሁለት አይነት አስተሳሰቦች ምንግዜም ቢሆን ትግልን ሲያደርጉ ይኖራሉ ። አንዱ ያለውን ወቅታዊውን ነባራዊ ሁኔታን ስታተስ ኩን የሚደግፉ እና እርሱ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ሲሆኑ እነኚህም በአብዛኛው ከዛ ስርአት ውስጥ ተጠቃሚ የሆኑ ናቸው ። እነኚህም የፖለቲካ የሀይማኖት ፣ በተለያየ የኢኮኖሚያዊ አመራር ላይ ያሉ ናቸው ። በእርግጥ ስርአቱ ምን አይነት ስርአት ነው የሚለውም ራሱን የቻለ ጥያቄ ነው ፣ ዲሞክራሲያዊ  በሆነ አመራር ውስጥ ቁንጮ ላይ ያሉ ሰዎች በምርጫ ሊቀያየሩና ፣ አዳዲስ ሰዎች የራሳቸውን አዳዲስ አስተሳሰብ ይዘው ሊመጡ ይችላሉ ፣ በአንፃሩ ዲሞክራሲ ከሌለ ግን የተወሰኑት ቁንጮነቱን ይዘው አንለቅም ሊሉና ፣ እንዲሁም የመሪነት ህጋዊ ተቀባይነታቸውና ብቃታቸው ጥያቄ ውስጥ ስለሚገባ በውጥረት የተሞላ ስርአት ሊሆን ይችላል ። 

                በሌላ በኩል ደግሞ ስርአቱ እንዲቀየርና በመሰረታዊነት ልዩነታቸውን የገለፁ ናቸው ለዚህ አይነተኛ ዋቢ የሚሆኑት ማርክስ ፣ ስፒኖዛ ፣ ኔቼ የመሳሰሉት ሲሆኑ ከእነሱ ውስጥም አንዳንዶቹ የተሳካላቸው ናቸው ለምሳሌ እንደ ሉተር ቀዳማዊ አይነቶቹ ሉተር ጂኒየርም ምንም እንኳን በዘመኑ አስተሰሳቡ ስር ነቀል ቢሆንም ውሎ አድሮ የተሳካላቸውም አሉ ለምሳሌ ሁለቱ ሉተሮች ለዚህ አይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው ።

             ሌሎች የመንግስታት ፣ የሀይማኖት ተቋማትን ብንወስድ ደግሞ ተመሳሳይ ነው ። በተቃራኒው ደግሞ ብንሄድ እነኚህ ነገሮች ባይኖሩ ኖሮ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ባልተቻለም ነበረ ።

             በፍልስፍና አለም ውስጥ በአንድ በኩል ሓሳዊ - ፍልስፍና (Pseudo-Philosophy) ሲኖር ይህም የእውነት መሰረት የሌለው እና ሊሰራ የማይችል ፍልስፍና ተብሎም ሊጠራ የማይችል ነው ። በሌላ በኩል ደግሞ ሳብጀክቲቭ የሆነ የፍልስፍና አር ዘርፍም አለ ። ይህ ዘርፍ ፍልስፍና ሲሆን ሊሰራ የሚችልም ነገር ነው ። ነገር ግን የሚሰራው ለተወሰኑ ቡድኖች ፣ ልሂቃን ወይንም ከፍተኛ የማሰብ ፣ እና ግንዛቤ ላላቸው ሰዎች ብቻ ይሆናል ። ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ የሚሆኑት አን ራንድ የተባለችው አሜሪካዊነት አይሁድ ፈላስፋ ፣ የኒቼ ፍልስፍና እንዲሁም እንደ ሮበርት ኪዮሳኪ ያሉ በዘመናችን ያሉ ፀሀፊዎች የጠቆሙት ፣  ከዚህ ዘርፍ የሚመደብ ነው ። ለምሳሌ አን ራንድ የሊበራሊዝም ፍልስፍና መሰረት የሆኑ በርካታ ሀሳቦችን የጠቆመች ቢሆምንም በዋናው የፍልስፈና አስተምህሮ ውስጥ ግን አልተካተተም ።  የኒቼንም ልእለ-ሰብ «Superman» ብንወስድ ሊሰራ የሚችለው በዛ ደረጃ ላሉ ሰዎች ብቻ ሲሆን ፣ ለብዙሀኑ ማህበረሰብ ግን ሊሳራ ሰራ የማይችል ነው ። በነገራችን ካይ ላይ ይህንን ፍልስፍና ናዚዎች ልክ ለብዙሀኑ እንደተነገረ አድርገው ለፖለቲካ አላማቸው ተጠቅመውበታል፣ ነገር ግን በኒቼ ልእለ - ሰብ ማለት ማህበሰረብን ወይንም አንድ ዘርን የሚወክል ነገር አይደለም ፣ በነገራችን ካይ ላይ ይህንን ፍልስፍና ናዚዎች ልክ ለብዙሀኑ እንደተነገረ አድርገው ለፖለቲካ አላማቸው ተጠቅመውበታል ነገር ግን በኒቼ ልእለ - ሰብ ማለት ማህበሰረብን ወይንም አንድ ዘርን የሚወክል ነገር አይደለም ፣ ከዚያ ይልቅ ግን ጥቂት ላቅ ያለ ክህሎት ወይም ያላቸውን ጥቂት ልሂቃንን የሚወክል ነው ።      

            እኔ እኔን የሆንኩት ባንተ ምክንያት ነው የሚል ታዋቂ የደቡብ አፍሪካውያን አባባል አለ ። ይህም የሰው መድሀኒቱ ሰው መነው ከሚለው ሀገርኛ አባባል ጋር ተመሳሳይ ነው ። በብዙ ታላቅ ሀይማኖቶችም እምናገኘው ወርቃማው ህግ ማለትም በራስህ ላይ እንዲሆን እማትፈልገውን በሌሎች ላይ አታድርግ የሚ ል ነው ። አን ራንድ የራስ ወዳድነት ፀጋዎች በሚል የሊበራሊዝም መሰረት የሆኑ ሀሳቦችን አንፀ ባርቃለች ።

ሁላችንም በመጀመሪያ የምንኖረው ለራሳችን ሲሆን ሌሎችን እንምንጠቅመው ከዚያ በኋላ ነው ። አንድ ሰው ማድረግ የሚፈልገውን በራሱ ጊዜና ሁኔታ ማድረግ ሲችል አላስፈላጊ በሆነ ሁኔታ ሌሎች ሰዎችን መጠበቅ የለበትም ። ጊዜ እያለፈ ስለሚሄድ ማድረግ የምንፈልገውን ነገር በቅጡና ፣ በአግባቡና በጊዜው ማድረግ በጣም ጠቃሚ ነው ። በተለይም ለወደፊት ህይወታችን ጠቃሚ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ይበልጥ ትኩረትንና ጥረትን ማድረግ ይጠበቅብናል ። ሌላውንም እኮ ልንጠቅም የምንችለው መጀመሪያ ላይ የራሳችንን ህልውና (Survival) መጠበቅ ስንችል ነው ።

               አለም በአንድ አፅናፈ - አለም አእምሮ ነው የምትመራው ። ይህ ዪኒቨርስ ነገር ግን ውድድርን ብንወስድ መወዳደር ማለት ከአንዱ ውድቀት የአንዱ ስኬት ነው የሚል ፅንሰ - ሀሳብ የሚነሳ ነው ። 

1 comment: