Thursday, April 11, 2013

የወሲብ ስሜትን «በማፈን» የተገኘው ስልጣኔ



ሲግመን ፍሮይድ ይህ የሠው ልጅ ስልጣኔ የሰው ልጅ «የወሲብ ስሜቱን በማፈን ያገኘው ነው» ሲል እንዲሁም ፍሬደሪክ ኒችም ይህ ስልጣኔ «ራስን በማሰቃየት የተገኘ ነው» ሲል ገልጿል ። ለዚህ የኒች አባባል ማስረጃ የሚሆነው ማርክስ «ዳዝ ካፒታል» በተሰኘው መፅሀፉ በዝርዝር እንደገለፀው ካፒታሊዝም ስርአት በመጀመሪያው የእድገት ዘመኑ እጅግ አነስተኛ ደሞዝ እና በጣም አስቸጋሪ በሆነ የስራ ሁኔታ የሰራተኞችን ብሎም የህፃናትን ጉልበት ጭምር ያለ ምህረት ይበዘብዝ  ፣ እንደነበረ ይገልፃል ።

የወሲብ ስሜት ልክ እንደ ማንኛውም እንሰሳ ለሰው ልጅም ራሱን እንዲራባና ዘሩን ተክቶ እንዲያልፍ የሚያስችል ነው ። ብዙውን ግዜ ታላላቅ ሀይማኖቶች ሰው ራሱን እንዲገዛ ከሚያስተምሩባቸው ምክንያቶች በአንድ በኩል የሰው ልጅ የወሲብ ስሜቱን ካልተቆጣጠረ ወደ ሌላ አላማ ሊውል የሚችል እምቅ ሀይሉን ያዳክማል ፣ በሌላ በኩል ግብረ-ገባዊ የሆነና ስርአትና ወግን የተከተለ ማህበረሰብን ለመፍጠር አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራል ። በምእራቡ አለም አንድ የፖለቲካ ሰው ከሚስቱ ውጪ ከማገጠ እና በማስረጃ ከተረጋገጠ የፖለቲካ ህይወቱ ያበቃለታል ። የወሲብ ስሜቱን መቆጣጠር የማይችል ሰው ለከፍተኛ የሀላፊነት ደረጃ አይታጭም ማለት ይሆን ?


የወሲብ ስሜት በሁለት እርስ በራሳቸው ተቃራኒ በሆኑ አቅጣጫዎች የሚመራ ነው፣ አንደኛው የወሲብ ስሜት ሀይል ሲሆን ፣ በአለም ላይ ከፍተኛ ስኬትን የሚቀዳጁ ሰዎች ከፍተኛ የወሲብ ስሜት ያላቸው ሰዎች ናቸው ። አንዳንዶቹ እንደ አይዛክ ኒውተን ያሉት ታላላቅ ሰዎች ደግሞ በድንግልና ኖረው የሞቱ ናቸው ። በተቃራኒው የወሲብ ሰሜት ካልተገራና ወደ ሌላ ጠቃሚ ወደ ሆነ ነገር ካልተለወጠ በስተቀር ፣ የሕይወት ብክነትን ይፈጥራል ።
የወሲብ ስሜት እንደ ማንኛውም እንሰሳ ለሰው ልጅ የተሰጠው ራሱን እንዲያራባበት  ነው ። ይህም ማለት የወሲብ ስሜት አንድ እምቅ ሀይል ነው ። ይህ ሀይል አለልክ ሲባክን የዛን ሰው የህይወት ግብ ያመክናል ። ሲታፈን ደግሞ እንዲሁ የተቆጣና የተናደደ ሰውን ይፈጥራል ። ናፖሌዎቸን ሂል የተባለው ፀሀፊ እንዳስቀመጠው «አንድ ሰው ከአርባ አመቱ በፊት ስኬታማ አይሆንም» ፣ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አንድ ሰው ከአርባ አመት እድሜው በፊት የወሲብ ስሜቱን መቆጣጠር ስለማይችል ነው ።

በዝግመተ-ለውጥ አስተሳሰብ መሰረት አንድ ሰው ወጣትና ለተቃራኒ ፆታ መስህብ የሚኖረው በወጣትነቱ ዘመን ብቻ ነው - ይህም ለመራባትና ራሱን መተካት አንዲያስችለው ነው ። የወጣትነቱ ዘመን ሲያልፍ ተፈጥሮ እንሰሳው ወይም ተክሉ ራሱን አንደተካ በማመን ለእርሱ እምትሰጠውን እንክብካቤ ማለትም ወጣትነቱንና ሀይሉን ውበ አማላይ አካላዊ ገፅታውንና ጥንካሬውን በአጠቃላይ የአንድ ሰው ትልቁ ፀጋ እሚባለውን ወጣትነቱን ቀስ በቀስ ትወስድበታለች ። ከዚያም እያረጀ ፣ እያረጀ ይሄድና ወደ ተፍፃሜ - ህይወቱ ማለትም ወደ ሞት ያዘግማል ።

No comments:

Post a Comment