Thursday, December 27, 2018

የቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ሕይወቱ እና ትምህርቱ አጭር ዳሰሳ

                                                                             የቅዱስ አትናቴዎስ ዜና ሕይወት

ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ በ298 ዓ.ም በእስክንድርያ ተወለደ፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ በህጻንነቱ በጨዋታ ሜዳ ከህጻናት ጋር እርሱ አጥማቂ እነርሱ ተጠማቂ እየሆኑ ሲጫዎቱ ፓትርያርክ እለእስክንድሮስ አይቶ ወደ መንበረ ፕትርክናው በመውሰድ እንዳሳደገው ሩፊኖስ የተባለው የዚያን ዘመን ታሪክ ጸሐፊ ዘግቧል፡፡
እለእስክንድሮስ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እና ሥርዓት እንዲሁም ሌሎችን የዘመኑ ዕውቀቶች እያስተማረ ካሳደገው በኋላ ለመዓርገ ምንኩስና በቃ፡፡ በቅድስናው፣ በሞያውና በግብረ ገብነቱ እንከን የሌለው ወጣቱ አትናቴዎስ በ23 ዓመቱ ሊቀ ዲያቆን ሆነ፡፡ በዚያ ዘመኑ መዓርግ “ሊቀ ዲያቆን” ማለት የሊቀ ጳጳሱ አፈ ጉባኤ፣ እንደራሴ እንደ ማለት ነበር፡፡ (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፣ አባ ጎርጎርዮስ (ጳጳስ)፣ 1978 ዓ.ም.፣ ገጽ 94)
በአጠቃላይ የአራተኛው መቶ ዓመት የቤተ ክርስቲያን ተጋድሎ ከአርዮሳውያን እና ተረፈ አርዮሳውያን ጋር የተደረገ እንደነበረ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስንም ጎልቶ እንዲወጣ እና ታላቅነቱ እንዲታወቅ ያደረጉት በዚሁ ዘመን የነበረው የአርዮሳውያንና ተባባሪዎቻቸው ሁከትና ሴራ ነው፡፡
አርዮስ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ላይ የክህነት ኃላፊነት ተሰጥቶት ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲያስተምር ተሹሞ የነበረ ሊቢያዊ ቄስ ነበር፡፡ በኋላ ግን “ወልድ በመለኮቱ ፍጡር ነው” የሚል ትምህርት እያስተማረ እና የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባባት ለዚሁ ትምህርቱ በሚረዳው መልኩ እየተረጎመ ምንፍቅናውን በታላቅ ትጋት በማስተማሩ እርሱ እና መሰሎቹ ቤተ ክርስቲያንን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ አውከዋታል፡፡
በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ ጉባኤ አድርጋለች፡፡ ይህ ጉባኤ በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ አስተባባሪነት እና በእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ በእለእስክንድሮስ መሪነት በ 325 ዓ.ም በኒቅያ (አሁን ቱርክ ውስጥ ባለች ቦታ) ተካሄደ፡፡ በጉባኤው 318 ጳጳሳት ብዛት ካላቸው ቀሳውስት እና ዲያቆናት ጋር ተገኝተዋል፡፡ በጉባኤው የአርዮስን ምንፍቅና በማጋለጥ እና ትክክለኝውን የቤተ ክርስቲያን ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት በሚገባ ከገለጡ ሊቃውንት መካከል ለጊዜው በሊቀ ዲያቆንነት እለእስክንድሮስን ተከትሎ የሄደው በኋላ እለእስክንድሮስ ሲያርፍ በእስክንድርያ መንበር በሊቀ ጳጳስነት የተሾመው ቅዱስ አትናቴዎስ ዋናው ነበር፡፡ በተለይ አርዮስን በጉባኤው ፊት ተከራክሮ በመርታቱ እና አርዮሳውያን መሠረቱን ሊንዱት የጣሩትን የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ትምህርት በጽሑፍና በቃል በማስተማር በማስጠበቅ ኃላፊነቱን በሚገባ የተወጣ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን አባት ነው፡፡
ቅዱስ አትናቴዎስ በአርዮሳውያን ሴራ አራት ጊዜ የተሰደደ እና ብዙ መከራ የተቀበለ ሲሆን ለትውልድ እየተላለፉ ቤተ ክርስቲያንን የሚያለመልሙ ድንቅ የነገረ ሃይማኖት መጻሕፍትን ጽፏል፡፡ ከነዚህ መካከል “በእንተ ሥጋዌ”፣ “የአርዮሳውያን መቃወሚያ (Against Arians)”፣ “በእንተ ስደት” ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በተጨማሪም የቅዱስ እንጦንስን ገድል የጻፈው ቅዱስ አትናቴዎስ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ይህ አባት ሌሎች በርካታ መጻሕፍትን እየጻፈ እና ከነገሥታት እና ባለሥልጣናት ሳይቀር የሚመጣበትን መከራ እየተቀበለ ለቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መጠበቅ እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ ታግሏል፡፡ በዚህ ጽናቱም “ዓለሙ አትናቴዎስን ጠልቶታል፤ አትናቴዎስም ዓለሙን  ጠልቶታል” ለመባል በቅቷል፡፡ ዘመን ገጠሙ የነበረው ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ “የቤተ ክርስቲያን ዓምድ” ይለዋል፡፡ የግሪክ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ “የኦርቶዶክሳዊነት አባት (Father of Orthodoxy)” ትለዋለች፡፡
ይህ ታላቅ የሃይማኖት አርበኛ በሰባ አምስተኛ ዓመቱ በአርባ ስድስተኛ ዓመተ ፕትርክናው ግንቦት 7 ቀን 373 ዓ.ም ድካምና ውጣ ውረድ የተመላውን የዚህን ዓለም ሕይወት በአስደናቂ ሁኔታ ፈጸመ፡፡
(ከዲያቆን ያረጋል አበጋዝ “ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ሕይወቱ እና ትምህርት።      

"ጌታ ለዘለዓለም አይጥልምና፤ ያሳዘነውን ሰው እንደ ይቅርታው ብዛት ይምረዋል" ሰቆቃወ ኤርምያስ ፫ ፥ ፴፩
                                   

No comments:

Post a Comment