Friday, February 6, 2015

ፍትሀ ነገስትና ዘመናዊ የኢትዮጲያ ህግ



ፍትሀ ነገስት ለሃገራች ህግ መሰረት ሲሆን ይሄው ፍትሀ ነገስት መሰረት የሚያደርገው መፅሐፍ ቅዱስን ነው ፡፡ ከቅዱሳን መፅሀፍት ለህግ ልዩ ትኩረትን ይሰጣሉ ፡፡ ማንኛውም ሃይማኖት አንዱ ክፍል የሚሆነው ህግ ነው ፡፡ ለምሳሌ በክርስትና ሃይማኖት በሃገራችን ኦርቶዶክስ ሃይማኖት የፍትሀ ነገስት የህግ መፅሀፍ ሲሆን በእስልምና ሃይማኖትም የሸሪአ ህግና ይህንንንም ለመተርጎም የሸሪአ ፍርድ ቤቶች አሉ ፡፡ በሃገራችን ከሳሽና ተከሳሽ ከተስማሙ ጉዳያቸው በሸሪአ ህግ እንዲታይ መፍቀድ ይችላሉ ካልተስማሙ ግን ወደ መደበኛው ፍርደፍ ቤት ሄደው እንደሚዳኙ የሃገራችን ህግ ይደነግጋል ፡፡
እግዝአብሄር አዳምንና ሄዋንን ከፈጠረ በኋላ መጀመሪያ የሰጣቸው ነገር ህግ ነው እርሱም ከዚያ ከተከለከለችዋ የበለስ ፍሬ እንዳትበሉ የሚል ነበረ ፡፡ አዳምና ሄዋንም ይህንን ህግ በመጣሳቸው ግን ከገነት እንደተባረሩ እና ለምድር ስቃይ እንደተዳረጉ እንረዳለን ፡፡ ፍትህ እጅግ ከባድ ነገር በመሆኗ ስጋ ለባሽ ሊያመጣት እንደማይችል መፅህፍ ቅዱስ ‹‹ከመሀከላቸው አንድስ እንኳን ፃድቅ የለም›› ስለዚህ ያ ፍፁም ፍትህ ሊመጣ የሚችለው ከምድር ስጋ ለባሽ ነገስታት ሳይሆን ከእግዝአብሄር ነው ፡፡ እየሱስ ክርስቶስም በእውነት ለመፍረድ ተመልሶ እንደሚመጣና የፍትህና የሰላም አለቃ እንደሆነ መፅሀፍ ቅዱስ ያስረዳል ፡፡ መፅሀፍ ቅዱስ ለፍትህ ትልቅ ቦታን ይሰጣል ‹‹እውነትና ፍትህ የዙፋንህ መሰረት ናቸው›› መዝሙር ዳዊት ላይ ሲል ፍትሀ ነገስትም ፍትሐ ነገስት አንቀፅ 44 ምእራፍ 4 ላይ ‹‹በወገኖቹ መሐከል በእውነት መፍረድ ይገባዋል›› ይላል፡፡ ያም ሆኖ ግን ፍትህ የነገስታት የዙፋንና የአንድ ህዝብ ውስጣዊ ሰላም መሰረት በመሆኗ ሰው በሚችለው አቅም ከትክክለኛው ፍትህ ማፈንገጥ እንደሌለበትና እንደ እግዝአብሄር ፍፁም ፍትህን ማስፈን ባይችልም የሰው ልጅ ከትክክለኛው የፍትህ መሰረት መውጣት እንደሌለበት ያስገነዝባል ፡፡
መፍረድ እጅግ ከባድ የሆነ ነገር ነው ፡፡ በሃዲስ ኪዳን መፅፍ አንዲት ሴት ዝሙትን ፈጽማለች ብለው አይሁዳውያን ለእየሱስ ክርስቶስ በድንጋይ ተወግራ እንድትገደል ዘንድ  እንዲፈርድባት ለእየሱስ ክርስቶስ ያመጡለታል ፡፡ አይሁዳውያኑም የተለመደው ፍርድ በድንጋይ ተወግራ መገደል ነው እንደዛም ብሎ ይፈርዳል በሚል ድንጋይ ከምረው በእጃቸው እያነጠሩ ውገሯት እስከሚል ድረስ ይጠብቃሉ ፡፡ እየሱስ ግን የጠየቃቸው ከእናንተ መሀል ንፁህ የሆነ ሃጢአት የሌለባት ይውገራት ብሎ ፈታኝ ጥያቄ አቀረበላቸው ነገር ግን ከእነርሱ አንዳቸውም እጃቸውን በእርሷ ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆን አንድ በአንድ ጥለው ሄዱ፡፡ ‹‹አትፍረድ ይፈረድብሃል›› የሚለው የመፅሀፍ ቅዱስ አባባልም የሚያስረዳው ይሄንን ነው ፡፡   
ሃዋርያው ጳውሎስ በኦሪት ዘመን የታወቀ የህግ መምህር በነበረው በገማልያ እግር ስር ሆኖ ህግን ያጠና ሲሆን የኦሪትንም ሆነ የሙሴን የአይሁዳውያን እንደ ብርቅና አይነኬ አድርገው የሚያዩዋቸውን ህግጋት የተማረና ያጠና ሰው ነበረ ፡፡ ለሮሜ ሰዎች በላከው መልእከት ላይም ሮሜ ምእራፍ 2 ፣ ቁጥር 12 - 16 ላይ እንዲህ ይላል ፡፡
‹‹ያለህግ ሃጢአትን ያደረጉ ያለህግ ይጠፋሉ፣ ህግም ስላላቸው ሃጢአት ያደረጉ ሁሉ በህግ ይፈረድባቸዋል ፣ በእግዝአብሄር ፊት ህግን የሚደርጉት ይፀድቃሉ እንጂ ህግን የሚሰሙ ፃድቃን አይደሉምና ›› 
ከዚህ አባባል የምንረዳው ያለህግ ስልጣኑን ተመክቶ ሃጢአትን የሚሰራ እርሱም በተራው ሌሎች ከእርሱ የበለጠ ስልጣን በእጃቸው ሲገባ እርሱ ያደረገባቸውን መልሰው ያደርጉበታል ሲሆን ህግ አለኝ ብሎ ህግ በኔ ወገን ነው በሚል ትምክህት ራሱ ያወጣውም ለራሱ እንዲመቸው አድርጎ ራሱ ባወጣው ህግ ሌሎችን ሲዳኝ ፣ ሲቀጣ ራሱ በሰራው እስር ቤት ሲያጉር ኖሮ እርሱም በተራው ሲሻር ህጉ የህጉ ስልጣንና ሃይል በሌሎች እጅ ሲገባ እርሱ ህጉን ጠቅሶ ሌሎች ላይ ያደረገውን ሌሎችም ያንን ህግ መልሰው ጠቅሰው እርሱ ላይ መልሰው ይቀጡታል ፣ ይህ በዓለምና በሃገራችን ታሪክ በተደጋጋሚ የታየ ሃቅ ነው ፡፡ ትክክለኛውን  ህግ በእግዝአብሄር ፊት የሚያደርግ ግን ይፀድቃል ፣ የተመሰገነ ይሆናል ፡፡   
እግዝአብሄር ህዝቡ ‹‹ከጠላቶቻቸው ስቃይና መከራ ሲደርስባቸው›› አምላክ እንዳዘነ መሳፍንት 2፣18 እንዲሁም ‹‹ንፁህ ደም ያፈሰሱ እጆች›› ምሳሌ 6፣16 ፣17 ላይ በአምላክ ዘንድ የተጠሉ እንደሆኑ መጽሀፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡

No comments:

Post a Comment