Wednesday, January 30, 2013

የመሪነት ክህሎት / The Art of Leadership







የመሪነት ክህሎት 

መግቢያ
መሪነት የራሱ የሆኑ ጥበቦችና አካሄዶች ያሉት ሲሆን በአብዛኛው በስነ - ልቦናና ሰፋ ያለውን ማህበረሰብ ባህሉን አኗኗሩን በማየትና በመረዳት ላይ የተመሰረተ ነው መሪነት ማለት አንድ መሪ ሙያውን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ሀላፊነቱ የሚጠይቀውንና ፈተናዎቹንም ጭምር በሚገባ መረዳት ማለት ሲሆን አሁን ባለዉ የሰው ልጅ ግንዛቤና መረዳት ፈታኝ ከሆኑ የሙያ ዘርፎች አንዱ መሪነትን መረዳትና ለብዙሀን በሚጠቅም መንገድ ስራ ላይ ማዋል ነው ።መሪነት ቀላል ያልሆነና እጅግ ውስብስብ መሆኑን   ለመረዳት ባደጉት ሀገራት ሳይቀር የመሪነትጉድለትና የአመራር ዝርክርነት በየቀኑ በመገናኛ ብዙሀን የምንሰማው ነገር ነው። በተለያዩ ግዙፍ ኩባንያዎች የታዩት የአመራር ጉድለቶች ለድርጅቶች መዘጋት ለበርካታ ሰዎች ከስራ መባረርና ለግዙፍ ኪሳራዎች ዳርጓል።ይህም ጉድለት በተለይም በፖለቲካው አለም ታላላቅየምእራብ ሀገራትን ጦርነት ውስጥ ከመዘፈቅ አንስቶ ፣ለትላልቅ በሀገር ደረጃ የተከፈሉ ዋጋዎችን አስከፍሏል።

በምእራብ ሀገራትም እንዲሁ የሀገራትን ወዳልተፈለገ ጦርነት ውስጥ መግባትንና ያንን ተከትሎም እጅግ ከፍ ያለ መስዋእትነትን መክፈልን አስከትሏል እንዲሁም በተሳሳተ የምጣኔ - ሀብት አስተዳደር ስራ አጥነት መስፋፋትን ያን ተከትሎም ወደ ሌሎች ተቀረው አለም ጭምር ወደሚስፋፋ አለም አቀፋዊ ምጣኔ - ሀብታዊ ችግሮች ለመዳረግ በቅተዋል እነኚህ ነገሮች በተደጋጋሚ የታዩ በመሆናቸው አንዳንዶቹን ጨርሶ ማስወገድ ባይቻልም እንኳን ብቃት ባለው አመራር መቀነስ አንዳንዶቹን ጨርሶ ማስቀረትም ይቻሉ የነበሩ ችግሮች በመሪነት አቅም ማነስ ምክንያት በሀገራትም ሆነ በአለማችን ላይ በተደጋጋሚ ሲከሰቱ ታይቷል

መሪነት ራሱን የቻለ ሙያ ነው ከምንግዜውም በበለጠ በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ እጅግ በጣም ውድ የሆነ ነገር ችሎታ ሲሆን ሌላ ማንኛውም ነገር ወርቅ ወይንም አልማዝ ቢሆን ከመሬት ተቆፍሮ ሊወጣ ይችላል የአንድ ነገር የላቀ ችሎታና እውቀት ግን ብዙም የተለመደ አይደለም በቀላሉ ሊተካም ሆነ ሊገኝ አይችልም በዚህም ምክንያት በጣም ብቃት ያለው ኩባንያ መሪዎች ብዙ ካለመሆናቸውም በላይ ለምሳሌ በምእራቡ አለም የአንድ ስራ አስኪያጅ ወደ ኩባንያው መምጣት የኩባንያውን አክስዮን ዋጋ ከፍ ሲያደርግ ኩባንያው መሪውን ማጣቱም የአክስዮን ዋጋ ዝቅ  ማድረግን ሲያስከትል ይስተዋላል ይህም የሆነበት ያለምክንያት ሳይሆን ብቃት ያለው ስራ አስኪያጅ ማለት በትክክል መተዳደርንና የወደፊት ትርፍ መጨመርን የኩባንያው ዋጋ ከፍ ማለትን መዋእለ - ንዋይ አፍሳሾች ስለሚገነዘቡ ነው

ብዙዎቻችን ስለመሪነት ያለን አስተሳሰብ ሌሎች መሪዎች ሲናገሩ እና የተለያዩ ነገሮችን ሲያደርጉ በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ከማየትና ከመስማት በስቀተር በተጨባጭ የተሟላ ስለመሪነት በትምህርትም ሆነ መደበኛ በሆነ ሁኔታ የተማርነው ወይም የምናውቀው ነገር የለም ይህም ሌሎች መሪዎች የሚያደርጉትን መመልከትና እና እሱን ስለ አመራር እንደዋና የእውቀት ምንጭ መውሰድ የሌሎችን ሰዎች ስህተት ለመድገም ይዳርገናል ምክንያቱም እንደ ዋና የመሪነት ምንጭ አድርገን የምንወስዳቸው ሰዎች ራሳቸው በአብዛኛው የተሟላ እውቀቱና ልምዱ ላይኖራቸው ይችላል እነሱም በተለምዶ ከሌሎች የወሰዱት ሊሆን ይችላል
 
አለማችን በአብዛኛው የተሞላችው በተከታዮች ሌሎችን አድናቂ በሆኑ ሰዎችና በመሳሰሉት ሲሆን ነገር ግን እውነተኛ የመሪነት ብቃትና ክህሎት ያላቸው ሰዎች ቁጥራቸው ብዙም አይደለም ነገር ግን አንዳንዶች መሪነት የሚያስገኘውን የክብር የስልጣን ወዘተጥቅምን በማየት ራሳቸውን እንደ ብቃት እንዳለው መሪ አድርገው ቢያቀርቡም በተግባር ግን ውጤትን ማሳየት የሚችሉ ጥቂቶች ናቸው በመሆኑም ውጤትን መስጠት ስለማይችሉ ከመሪነት ዙፋን ሳይወዱ በግድ መሰናበት ግድ ይሆንባቸዋል   

በሀገራችንም ብንወስድ አመራርን የሚያስረዳው መፅሀፍ ክብረ-ነገስትና ፍተሐ - ነገስት መፅሀፍት ላይ ሲሆን ዝርዝር የአመራር መንገዶችን አለማዊም መንፈሳዊም መንገዶችን የሚጠቁም ሲሆን የጥንት አባቶቻችን ስለ አስተዳደር ምን ያህል ትኩረትን ይሰጡት እንደነበረ የሚያሳይ ነው ነገር ግን ፍትሐ - ነገስት ለብዙሀኑ ህብረተሰብ እንደ አሁኑ በዘመናዊ ትምህርት መልክ የሚሰጥ ሳይሆን  የነገስታት ልጆች ብቻ ራቅ ብለው የሚማሩት ነበር ይባላል። ነገር ግን በዘመናት እነኛ ጥንታዊ የአስተዳደር ብልሀቶች አንዳንዶቹ በዘመናዊ ህግጋት እየተሻሩ አንዳንዶቹ ምንም እንኳን ጠቃሚ ቢሆንም ትኩረትን የሚሰጣቸው እየጠፋ በመሄዱ ምክንያት ለአስተዳደር መዘበራረቆች አንዱ ምክንያት ሆኗል ነገር ግን ፍትሀ - ነገስት ነገስታት ሲያጠፉ ዝም የሚልም አልበረም ከዚያ ይልቅ በተለያየ ምሳሌ እያደረገ ነገስታቱ ስህተታቸውን አውቀው እንዲያስተካክሉና መልካም አስተዳደርን እደንዲያሠፍኑ የሚጎተጉት ነበረ ፍትህ - ነገስቱን ጥሰው የተገኙ ነገስታት ስልጣናቸውን እንዳጡ ያም ብቻ ሳይሆን ለሀገር መበጥበጥ ምክንያት እስከመሆን እንደደረሱ በርካታ ታሪካዊ ምሳሌዎችን መስጠት ይቻላል በሀገራችንም ሀገርኛ አባባል መካር ያጣ ንጉስ ያላንድ አመት አይነግስ ይባላል

ምንም እንኳን አገራችን በአለም ላይ ካሉ ጥንታዊ ከሚባሉ ጥቂት አገራት አንዷ ብትሆንምና፣ የሶስት ዘመን ታሪክ ያለን ቢሆንም በአመራር በኩል ግን በአብዛኛው ፍፁማዊ በሆኑና ስልጣናቸውን ከላይ ከመለኮት እንደተሰጣቸው አድርገው ይቆጥሩ በነበሩ በፈላጭ ቆራጭ ዘውዳዊ አገዛዞች ሲገዛ የቆየና ሲሆን ከዚያ ውጪ ያለውን የአስተዳደርም ሆነ የአመራር አይነት በመንግስታት ደረጃ ሲፈፀም የማየት እድልን ያገኘ አይደለም በቤተሰብም ሆነበሌሎች አስተዳደራዊ ዘርፎች ቢሆን አባት ፈላጭ ቆራጭ እንደሆነና ያለው ሁሉ ትክክል ተደርጎ የሚቆጠርበት ነው


በተመሳሳይም ጥንታዊ ቻይናዎችን ብንወሰድ ንጉሰ ነገስቱ ሲያጠፋ በቀጥታ አይደለም የሚነገረው ነገር ግን በዘመኑ ያሉ ምሁራን በተለያየ ምሳሌዎች እያደረጉ ንጉሰ ነገስቱ የጣሳቸውን ህግጋት ያበላሻቸውን ስራዎች በምሳሌዎችና በስእሎች እያደረጉ ይገልፁለታል ንጉሰ ነገስቱም ይህንን በመረዳት ከስራዎቹ ራሱን መቆጠብና ወደ ትክክለኛው መስመር ይመጣል መፅሀፍ ቅዱስንም ብንወስድ ትንቢቶች በዚህ መንገድ የተፃፉ ሲሆኑ በወቅቱ ስልጣን ላይ ያሉ ሀይሎች እንዳይበቀሉ ለማድረግ ተመስጥሮ የተፃፈ ነው ።ግሪን ላይ ተመልከት በመፅሀፍ ቅዱ ላይም እንዲሁ በዘመኑ የነበሩ ነገስታትንና መሪዎችንና መንግስታትን ባለመንካት በተለያዩ ምሳሌዎችና ሰምና ወርቅ ቅኔ በለበሱ በተመሰጠሩ ቃላትን በመጠቀም ተፅፎ ይገኛል ይህም በስልጣን ላይ ያሉ ሀይሎችን ላለማስቆጣት እና ለበቀል  እንዳይነሳሱ ለማድረግ ሲባል ነው  እንዲሁም መፅሀፍ ቅዱስም በምሳሌ በተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ የተፃፈ ነው

በአለም ላይ ያሉ ችግሮች ከመቀነስ ይልቅ እየጨመሩ ያሉ ሲሆን ይህም በአለም ላይ ያለውን የመሪነት ጉድለትን (Leadership Deficit) ያመለክታል ።ምእራባውያን ይህን ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረትን የሚሰጡት ሲሆን የተለያዩ ኩባንያዎችን የበላይ አስተዳዳሪዎችንና መሪዎችን ገለል ወዳለ ስፍራ (Retreat) በመውሰድ ተከታታይ ስልጠናዎችን በመስጠት ስልጠናዎችን የሚሰጧቸው ሲሆን ለቁጥር የሚያታክቱ መፅሀፍትም ተፅፈዋል


በአገርም ሆነ በአንድ ኩባንያ አመራር ደረጃ ብንመለከት የፖሊሲዎች ወጥነት (Consistency) ፣መሆን ሲኖርባቸው እቅዶች ደግሞ ቀጣይነት ሊኖራቸው ይገባል ተከትለው የሚመጡ አስተዳደሮችና መሪዎች ቀደምቶቻቸው ያቀዱትን ነገር ከጥቅሙ አንፃር ቀጣይ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል እንጂ በሀገራችን እንደሚታየው ጭራሽ ሁሉንም ነገር አፍርሶ እንደ አዲስ ከምንም ከመጀመር ይልቅ በነበረው ላይ ማከል ይቀላል

 
ዞሮ ዞሮ አንድ መሪ የሚለካው ለተከታዮቹ ወይም ለሚመራው ድርጅት ወይም ሀገር አንድ ውጤትን  ማምጣት ሲኖርበት ይህን ማድረግ ካልቻለ ግን ቀስ በቀስ ያገኝ የነበረውን ድጋፍ እያጣ ይሄዳል ስለዚህ ተጨባጭ ውጤትን ማምጣት ያልቻለ የሌለው አመራር ቀስ በቀስ ግን ያገኘውን ድጋፍ ማጣቱ አይቀሬ ነው ።ለዚህም ራሱ መሪውም መሪው መስዋእትንም መክፈሉ አይቀሬ ነው

በትምህርት ከፍተኛ ውጤትን ማስመዝገብ ፈተናዎችን በጣጥሶ ማለፍ ብቻውን አንድን ሰው ውጤታማ መሪ አያደርገውም አንድ ተማሪ በርካታ ኤዎችን ደርድሮ ትምህርቱን ቢጨርስም የተሳካለት መሪ ይሆናል ማለት አይደለም ይህንን እውነታ በመረዳት በአሁኑ ወቅት ያደጉት ሀገራትም ሆነ ሌሎቹ ሀገራት ወጣቶቻቸውን ከቀለም ትምህርቱ በተጨማሪ ስለአመራር የትምህርት ራሳቸውን የቻሉ ተቋማትን በመክፈት ማሰልጠን ጀምረዋል
 
ይሁን እንጂ መሪነት እውቀትነቱ እንዳለ ሆኖ ጥበብነቱ ያመዝናል ምንም እንኳን በአለም ላይ በርካታ መሪዎችን የሚያሰለጥኑ ተቋማት ቢኖሩም በተግባር ግን በሌሎች ሙያዎች ባለሙያዎችን ማሰልጠን እንደሚቻለው ሁሉ በመሪነት ዘርፍ ግን መሪዎችን በስልጠና ብቻ ማፍራት አይቻልም ከዚያ ይልቅ ጥበብነቱን የጎላ በመሆኑ መሪዎች ጥበቡን ከልምድ ከተግባር ልምምድ ማግኘት ይችላሉ

ሌላው መሪው ሊረዳቸው ከሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ዋነኛው ነገር የሚመራውን ተቋም ወይም ድርጅት እሴትና አላማን መረዳት ነው ለምሳሌ ወታደራዊ ተቋማት ነፃነትን በማስከበር ላይ ሲመሰረት በአንፃሩ ደግሞ የግል ኩባንያዎች ደግሞ ለሰራተኛው የስራ ዋስትናን ለባለቤቶቹ ደግሞ ትርፍን በመስጠት ላይ የተመሰረቱ ናቸው ፣እሴቶቹ ተቋማቱ በተለዋወጡ ቁጥር እየተቀያየሩ ይሄዳሉ
 
ሌላው ደግሞ እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ የሚመስሉ አላማዎች ሊያጋጥመው ይችላል ከላይ እንደተጠቀሰው የአንድ ኩባንያ ባለቤቶች ከፍተኛ ትርፍን ማግኘት ሲፈልጉ ሰራተኞች ደግሞ ደህና ደሞዝን  እንደሚፈልጉ ይታወቃል የዚህ አይነት ተፃራሪ የሚመስሉ ነገር ግን ዞሮ ዞሮ በአንድ መንገድ የሚሳኩ ማለትም የሁለቱም ወገኖች ማለትም የሰራተኞችም ሆነ የባለቤቶቹ ፍላጎት የሚሳካው ኩባንያው ትርፋማ እስከሆነ ድረስ ብቻ ሲሆን ከላይ ሲታይ የማቃረኑ ቢመስሉም ትርፋማ እስከሆነ ድረስ ግን የሁለቱም ፍላጎት ከሞላ ጎደል ይሳካል ስለዚህ ዋናውን ግብ ማሳካት የሚቃረኑ የሚመስሉ ፍላጎቶችን ለማሳካት ያስችላል

መሪነት ምንድነው ?

መሪነት ወይንም አመራር የሚባለው ነገር የፖለቲካዊ ፍልስፍና አካል እንደመሆኑ መጠን አላማው በማህበረሶች ብሎም በአለም ላይ ስርአትን ማስፈን ነው ስርአትን ለማስፈን ፍትህን ማስፈን ስርአት አልበኝነትን ከህግ ማፈንገጥንና ወንጀልን በመከላከል ማህበረሰባዊ እድገትን ማምጣት ነው   ማህበረሰባዊ ስርአትና ህግ እስከሌሉ ድረስ የግለሰቦች አበርክቶ ብቻውን የአንድን ህብረተሰብ እድገትን አያመጣም ጉዳዩ የህዝቦች የህልውና ጉዳይ እንደመሆኑ በየዘመናት የተነሱ ፈላስፋዎች ስለዚህ ጉዳይ አጥብቀው አስበውበታል።   

በርካታ የአለማችን ፈላስፎች ስለመሪነት የተለያዩ ነገሮችን ብለዋል ከፕሌቶ ብንጀምር   መምራት ያለባቸው ፈላስፎች ናቸው የሚል ፅኑ አቋም ያለው ሲሆን ይህንን ያለበት ምክንያት ብዙሀኑ ህዝብ ሶቅራጥስ ላይ እንዴት ሞት እንዳስፈረደበት በማየቱና፣በብዙሀኑ ዳኝነት ላይ ለተመሰረተው ዲሞክራሲ ፍቅር ስላልነበረው ነው መንፈሳዊ መሪዎችም እንዲሁ እየሱስ ክርስቶስን ብንወስድ «እውር እውርን ሊመራው ይችላልንብሎ ይጠይቃል ይኊውም ለመምራት ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን ሲያሰምርበት ሲሆን ባሀኡላም «እውቀት ለሌለው ሰው ስልጣንን ከመስጠት የበለጠ ምንም አደገኛ ነገር የለም » ይለናል መምራት የሚችለው እውቀት ያለው ብቻ ነው ወደሚል መደምደሚያ ያመራል፣ ይህም ፈላስፎች ናቸው መምራት ያላቸው ከሚለው ከፕሌቶ ጋር ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ነው ከአውሮፓውያን ፈላስፎችም ብንወስድ ኒቼን ብንወስድ የስልጣን ፍላጎትን ያሰምርበታልነገር ግን ኒች ስልጣን አስደሳች እና የሚጥም ነገር መሆኗን ይናገራል እንጂ ስለ ስልጣን ገደብ የሚለው ነገር የለም የኒቼ ፍልስፍና በናዚዎች በተሳሳተ መንገድ የተተረጎመ ፍልስፍና መሆኑን ሳንረሳ ማለት ነው ሄግልን ብንወሰድ ለሄግል መሪን የሚመራው መንፈስ ነው የሚል ነው ማርክስም በሄግል ሀሳብ ይስማማል ነገር ግን ማርክስ ይህንኑ ፍልስፍናውን ወደ ሰራተኞች አምባገነናዊነት አገዛዝን ማስፈን ይለዋል


ነገር ግን ማርክስና ሄግል በውስጠ ታዋቂ የወሰዱት እሳቤ አለ እርሱም ምንድነው ቢባል መሪዎቹ የበቁ የነቁ እና አስፈላጊውን እውቀት ሁሉ የያዙ ናቸው ከሚል ቅድመ - ግምት በመነሳት ነው ነገር ግን በተግባር በታሪክ እንደታየው ብቃት የሌላቸው እምገነናዊ መሪዎች ስልጣን ሊይዙና ጥፋትን አጥፍተው ሲያልፉ በብዙ ሀገራት የታየ እውነታ ነው ነገር ግን እውቀት ሱባል ሲባል የግድ ከዩንቨርስቲ መመረው ወይንም የከፍተኛ ትምህርት መቅሰምን የግድ አያመለክትም ከዚያ ይልቅ በተፈጥሮውና በአስተዳደጉ ማስተዋልና ጥበብ ያለው ሰው ምንም እንኳን ዘመናዊ ትምህርትን ባይማርም ለመምራት ህግን ጥበብን እንደታደለ ሊቆጠር ይችላል


          ሙሴ ምናልባትም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በጣም ስኬታማ ከሆኑ መሪዎች አንዱ ነው ይኊውም በአንድ በኩል አይሁዳውያንን በግብፅ ሀገር ከነበሩበት ከአስጨናቂው የባርነት ቀንበር ማላቀቅ ሲሆን በአንድ በኩል ሰዎቹ ሲያጠፉ በመቅጣት በሌላ በኩል ደግሞ ሊያገኙ የሚችሉትን ነገር ተስፋ በመስጠት ከመስመር እንዳይወጡም ትእዛዝ አክባሪዎች እንዲሆኑ በማድረግ አልፈው ተርፈው በሚያጠፉበት ወቅትም በመቅጣት ነው ይሁን እንጂ በአለም ላይ ከተፈጠሩ ታላላቅ መሪዎች መካከል የተወሰኑቱ ዲሞክራሲያዊ ያልነበሩ ናቸው ሙሴም ለዚህ አይነተኛሰ ምሳሌ ነው የብዙሀኑን ህዝብ የግንዛቤ ደረጃን የተረዳ እንደሆነ አያጠራጥርም ይህንንም ለምሳሌ በመዝሙሮቹ ላይ ገልፆታል ይሄውም «ደንቆሮና አላዋቂ የሆንክ ህዝብ ሆይ የምንልህን ስማ » የሚል አነጋገር ቃና አለው። እንዲሁም ከፍተኛ ወታረደራዊ ድሎችን ያስመዘገቡና አገራቸውን ከውድቀት የታደጉ መሪዎችም እንዲሁ ከዲሞክራሲ ከመሆን ጋር የተገናኙ ላይሆኑ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም


ከዚህ በመነሳት መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉ እነርሱም አንድ የመሪነት ወሰኑ ምን ድረስ ነው ? ሌላው ደግሞ የነቃና ያወቀ መሪ ማለት ምን ማለት ነው ? የበቃና ያወቀ መሪ እሚባለውስ ማነው ? የሚሉት ጥያቄዎች መሰረታዊ ጥያቄዎች ናቸው ከላይ እንደተጠቀሰው ኒቼን ብንወሰድ ምንም እንኳን ስልጣን የሚጥም ነገር መሆኑን እንዲሁም ስልጣንን መጠቀም እንደሚጥም ቢገልፅም በተግባር ግን አንድ ሰው ምን ድረስ ነው ስልጣኑን መጠቀም ያለበት የሚለው ጥያቄ አልተነሳም ይህንንም ለማየት ብዙዎች ስልጣናቸውን አለአግባብ የተጠቀሙ ነገር ግን በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት ማረፊያቸውን ያደረጉ ከሀላፊነታቸው የተባረሩ የኩባንያ መሪዎችን ብንወስድ ይኊው ምን ድረስ ስልጣናቸውን መጠቀም እንዳለባቸው ካለማወቅና መስመር ከማለፍ የመጣ ነው ስለዚህ የአንድ መሪ ስልጣን ምን ድረስ ነው የሚለው ጥያቄ መልሱ በዋናነት የስነ - ምግባር ብሎም የህግ ጥያቄ እንደሚሆን መገመት ይቻላል

 
መሪነት ማለት ለምሳሌ አንድ መርከብን ብንወስድ የመርከቧ ካፒቴን የመርከቧ መሪ ሲሆን ከሱ ቀጥሎ ያሉት የሱን ትእዛዝ የሚያስፈፅሙት መርከበኞች ደግሞ አስተዳዳሪዎች ወይንም የአመራር ሰዎች ናቸው በአንድ ኩባንያ ደረጃ ስናስበው የኩባንያው ወይንም የድርጅቱ ቦርድ አባላት የድርጅቱ መሪዎች ሲሆኑ ድርጅቱ የሚሄድበትን አቅጣጫ የሚወስኑና ፖሊሲ የሚያወጡ ሲሆኑ ከነሱ ቀጥሎ ያሉት የየክፍሉ ሀላፊዎች ደግሞ ከዋናዎቹ መሪዎች የመጡትን ግቦችና መመሪያዎች ከየቀን ተቀን ውሎ ጀምሮ እየተከታተሉ የሚያስፈፅሙ ናቸው በአጭሩ መሪነት ማለት አዲስ አቅጣጫን መቀየስ ማለት ነው


የትኛውም ዘርፍ በመሪዎች የሚመራ ሲሆን ከፖለቲካው፣ምጣኔ - ሀብቱ ንግዱ ስነ-ጥበብ ስፖርት እንዲሁም ማንኛውም ነገር በራሱ መሪዎች አመራርና ክትትል የሚመራ ነው አሁን ባለንበት አለም በብዙ ዘርፎች የመሪዎች እጥረት ያለ ሲሆን በአሁኑ ሰአት እያደገ ካለው የሀገራችንም ሆነ የአለም የምጣኔ - ሀብት እና ዘርፈ - ብዙ ከሆነ እንቅስቃሴ አንፃር በርካታ ብቁ መሪዎች ያስፈልጋሉ


የንግድ ትምህርት ቤት (Business School)መምህራን እንደሚናገሩት «ገንዘብ የሚሄደው በጣም ጥሩ ምርቶችና አገልግሎቶች ወደሚገኙበት ሳይሆን እጅግ በጣም ጥሩ መሪዎችና የአመራር ቡድን ወዳለበት ነው »፣በንግዱ አለም ብቻ ሳይሆን የተሻለ እውቀት ባለሙያዎች ደንበኞች እንዲሁም የህዝብ ድጋፍ ጭምር ማንኛውም የምናስበው ዘርፍ ሁሉ ከስፖርትና ከስነ- ጥበብ ዘርፍ ሳይቀርየሚጎርፈው ጥሩ መሪዎች ወደሚገኙበት አቅጣጫ ነው በፖለቲካው መስክ ብንወስድ ብቃት ያላቸው መሪዎች ያሉት የፖለቲካ ድርጅት ሰፊ የህዝብ ተቀባይነትንና ድጋፍን ብሎም በምርጫ ወደ ስልጣን የሚመጣበት እድል የሰፋ ነው ይህንንም ለመረዳት በሀገራችንም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ብቁ መሪዎች ያሏቸው ድርጅቶች ብቁ መሪዎች ከሌሏቸው የፖለቲካ ድርጅቶች በተሻለ ወደ ስልጣን የመምጣትና ከመጡም በኋላ በርካታ ጠቃሚ ስራዎችን ለማከናወንና ብሎም ረዘም ላለ ጊዜ የመቆየት እድል ይኖራቸዋል  


መሪነት ከሌሎች ተከታዮቹም ሆነ ከብዙሀኑ ህዝብ በተሻለ የሚንቀሳቀስበትን ከባቢ እውነታውን እና ገሀዳዊውን አለም መረዳት መቻል አለበት በነባራዊው አለም ውስጥ ክስተቶች እየተከታተሉና እየተደራረቡ ነው የሚሄዱት እንጂ የግድ በሳቢያና በውጤት ላይ ተመስርተው አይደለም አንድ ነገር እየሆነ ሌላው ያልተጠበቀ ክስተት ሊከተለው ሲችል ወይም እሱን ተከትሎ ደግሞ ከየት መጣ ሳይባል ያልታሰበ ነገር ይሆናል በአብዛኛው ገሀዳዊው አለም በእንደዚህ አይነት መንገድ ነው እሚሄደው እንጂ የግድ በምክንያት ላይ ተመስርቶ ላይሆን እንደሚችል መረዳት አለበት እነኚህ ሳይጠበቁ እሚመጡ ክስተቶች ለመሪው አዲስ እድልን ይዘው ሊመጡ ይችላሉ ወይም ደግሞ ያልታሰበ ፈተናን ይዘው ከተፍ ሊሉ ይችላሉ የመሪው ስኬታማነት ላይም ቀላል ያልሆነ አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ነገሮችን ሊያመጡ ይችላሉ


ለምሳሌ ዝም ብለን እንኳን ለተወሰኑ ጊዜያቶች በመገናኛ ብዙሀን ርእሰ - ዜናዎችን ብንከታተል የምንሰማው የምናየው ነገር ሊያስገርመን ይችላል እርስ በእርሳቸው እሚገናኙም እማይገናኙም ነገሮች እዚህም እዚያም ተከሰቱ ሆኑ ሲባል እንሰማለን ። ይሆናል ያልታሰበው ሲሆን አይሆንም የተባለው ሲሆን ወዘተእያለ ነው ነባራዊው አለም የቀን ተቀን ጉዞውን እሚቀጥለው መሪም የዚህን የገሀዳዊውን አለም እውነታ አይጨበጤነት (Unpredictability) በሚመራው ተቋም ላይ የሚኖራቸውን ተፅእኖ መረዳት አለበት