Thursday, February 28, 2013

የመሬት ስሪት ስርአትና የመቅራዊ ሽግግር (Transformation)





 በሀገራችን መሬት በከተማም ሆነ በገጠር ዋናው የሀብት ምንጭ መሆኑ አያከራክርም ። ለመንግስትም ሆነ ለግል ድርጅቶች እንዲሁም ለግለሰቦች ዋናው የሀብት ምንጭ መሬት ነው ። በከተማም ሆነ በገጠር መንግስት ከሚሰበስበው ግብር አብዛኛው መሬት የሚያመነጨውን ነው ማለት ይቻላል ። ምጣኔ ሀብቱ መሬት በተፈጠረው ሀብት ላይ እስከተመሰረተ ድረስ ፣ እንዲሁም በእውቀት ላይ የተመሰረተ እስካልሆነና ኢንዱስትሪዎች ተስፋፍተው ፣ ለዜጎች የስራና የገቢ እድሎች እስካልሰፉ ድረስ በመሬት ላይ ኢኮኖሚው መመስረቱ አይቀሬ ነው ።


 የምጣኔ - ሀብት ባለሙያዎችም እንደሚስማሙት ከአዳም ስሚዝ በፊት የነበሩት ፊዚዮክራቶች እንዲሁ ግብርናን እሴትን የሚፈጥር ዘርፍ ብለው የሚያምኑ የነበረ ሲሆን ፣ ከአዳም ስሚዝን ብንወስድ ተፈጥሮ ሰውን ስለሚያግዘው (Nature Labors with Man) አትራፊው የሆነው ዘርፍ ግብርና ነው የሚል እምነት የነበረው ሲሆን ፣ ይህ አስተሳሰብ በተለይም በአሁኑ ዘመን የህዝብ ቁጥር እየናረ ባለበትና ፣ ለእርሻ ይውል የነበረውን መሬት ለከተሞች ማስፋፊያ እየዋለ ባለበት ፣ ለእርሻ አመቺ የነበረው ለም መሬት በአለም ሙቀት መጨመር ምክንያት ምርታማነቱ እየቀነሰ በመጣበት እና የምግብ ዋጋ ንረት በየአመቱ እየተባባሰ ባለበት በዚህ ወቅት የግብርናው ዘርፍ አስፈላጊነት ከምንም ነገር በላይ በልጦ የሚታይ ሀቅ ሆኗል ። ይህ ብቻም ሳይሆን ፣ አንድ ሀገር በእድገት ጅማሮዋ እያለችና ካፒታልን ለማሰባሰብ እና የእድገት ለመሰረትን ለመጣል የግብርናው ዘርፍ ዋነኛ መሰረትና በሌላ ዘርፍም ሊተካ የማይችል ነው ።

 የመሬት ጉዳይ የሀገሪቱ ምጣኔ - ሀብት መዋቅራዊ ለውጥ እያደረገ ሲመጣ ጉዳዩ እየተቀየረ መምጣቱ አይቀሬ ነው ። ሆኖም አሁን ባለው ያገሪቱ ምጣኔ - ሀብት ሁኔታ አወቃቀር ሲታይ በገጠርም ሆነ በከተማ ዋናው የሀብት ምንጭ መሬት መሆኑ ግልፅ ነው ። በአንፃራዊነት ግብርናው ዘርፍ ለአጠቃላዩ ኢኮኖሚ ያለው ድርሻ እየቀነሰ እና የሌሎች ዘርፎች ማለትም የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች እያደጉ ሲመጡ በመሬት ጉዳይ ላይ እሚነሱት ክርክሮች ፖለቲካዊ ከሆነ ይልቅ ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰቦችን እየያዙ ይመጣሉ ።

             
አሁን ባለችው አለማችን ካፒታልና እውቀት ናቸው ከፍተኛ ሀብትን መፍጠር የሚችሉት በዚህ ምክንያት ከመሬት የሚመነጨው ሀብትም ያን ያህል እሚያስመካ እንዳልሆነም ይታወቃል ፣ አንዱም ሀገሪቱ ስር የሰደደ ድህነት ምክንያት ምጣኔ - ሀብቱ በአብዛኛው እድገቱ  አዝጋሚ በሆነው መሬት በሚያመነጨው ሀብት ላይ መመስረቱ ነው ። በዚሁ በመሬት ጉዳይ ሌላ ዋነኛ አማራጭ የሆነ የገቢ ምንጭ ስለሌለው መንግስት ፖሊሲዎች በተደጋጋሚ መቀያየሩ ፣ የበለጠ ገቢን በሚያገኝበት መንገድ የመሬት አዋጆችና ደንቦች መለዋወጡ የሚጠበቅ ነው ። በኢትዮጲያ በተደጋጋሚ እንደታየው መንግስታት ሀብትን ለማከፋፈል ሲፈልጉ ወይም ያለውን የፖለቲካና ኢኮኖሚ መዋቅሩን መቀየር ሲፈልጉ መሬትን የሚመለከት ስር ነቀል አዋጆችን ማውጣት የተለመደ ነው ። በንብረት ላይ የተመሰረተ ሀብት የተዛባ የሀብንት ክፍፍልን ከሚፈጥሩ ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ ይታወቃል ። ምክንያቱም አንድ ሀገር የሚኖራት ንብረት ማለትም መሬትም ሆነ ሌላ ከተወሰነ መጠን እንዳማያልፍ ይታወቃል ።

በሀገራችን ታሪክ በ1967 ዓ.ም.ደርግ ያወጣው የመሬት አዋጅና በ2004 ዓ.ም. ኢህአዴግ ያወጣው አዋጆች መሬትን በተመለከተ ስር ነቀል መሆናቸውን በርካታ የመስኩ ምሁራን ይስማሙባቸዋል ። ምንም እንኳንየ 1967ቱ አዋጅ በዘመኑ የነበሩ ወጣቶች የታገሉለትና ስር ነቀል ለውጥን ያመጣና፣ ሀገሪቱን ከፊውዳላዊ የመሬት ስሪት ያላቀቀ ቢሆንም ፣ በአንፃሩ የከተማ ትርፍ ቤቶችን የመንግስት ያደረገው አዋጅ ግን የከተሞችን እድገት ባሉበት እንዲቆሙ ያደረገና ፣ እንደ አዲሳባ ያሉትን ትላልቅ ከተሞች ለመኖሪያነት አመቺ እንዳይሆኑና እድገታቸው የተገታና ፣ በአጠቃላይ የተከተሞችን እድገት የጎተተ ነው ። 


ይህ ብቻም ሳይሆን መሬት አላቂ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት እንጂ የማያልቅ ባለመሆኑ ፣ ለመሬት የሚደረገው ሽሚያና ዋጋውም እንደዛው እየጨመረ መሄዱ አይቀርም ።የመሬት ጉዳይ ህገ - መንግስት ውስጥ ገብቶ መቀመጡ ግን ምናልባት ማሻሻል ቢያስፈልግ ቀላል እንዳይሆን ያደርገው ይችላል ። መሬት በግል ቢያዝ ይሻላል የሚሉ ሰዎች ከሚያቀርቡት ክርክር አንዱ ለምሳሌ አንድ ሰው መሬቱ የግሉ ቢሆን ከአመት እስካመት ድረስ በዝናብ የሚታጠበውን መሬት ባለቤቱ ሊንከባከበውና ከመሸርሸር ሊጠብቀው ይችላል የሚል ነው ። 


በአንድ በኩል ሲታይ ግብርናን መደጎም ተገቢነት ያለው ነው ማለት ይቻላል ። የግብርና ስራ አድካሚና አሰልቺ መሆኑ ፣ ትርፉም እንደሌሎቹ ዘርፎች አስተማማኝ አለመሆኑ፣ ከተፈጥሮና ከአየር ንብረት ጋር በመታገል የሚሰራ ስራ በመሆኑሀብታም ሀገራት የግብርናውን ዘርፋቸውን እንደሚደጉሙ የአደባባይ ሀቅ ነው ። አሜሪካና አውሮፓውያን በተለይም ከአውሮፓ ሀገራት ፈረንሳይ ገበሬዎቿን በመደጎም ትታወቃለች ። ይሁን እንጂ አውሮፓውያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሀገራትም ደግሞ እንደሚሉት ግብርናውን ዘርፍ በመደጎም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትና እና ቻይናንም ጭምር ግብርናቸውን ይደጉማሉ የሚል ቅሬታን ያሰማሉ ። በ2012 ዓ.ም በአሜሪካን ሀገር ምስራቅና በመካከለኛው «Mid West» በሚባለው አካባቢ ለ52 አመታት ተከስቶ የማያውቅ ድርቅ በመከሰቱ ምክንያት የበቆሎና የአኩሪ አተር ዋጋን ሲያንር ፣ ነገር ግን የአሜሪካ ገበሬዎች የመድን ዋስትና ስላላቸው በቀላሉ ገበሬዎቹ የሚፈራውን ያህል ለኪሳራ አይዳረጉም ።  


በሀገራችን ውስጥ በርካታ አይነት የመልከአ - ምድራዊ እንዲሁም አየር ንብረት ስርጭት ያለ ሲሆን ለምሳሌ ቆላማ የሆኑትን የአርብቶ - አደር አካባቢዎችን ብንወስድነዋሪዎቹ ለከብቶቻቸው የግጦሽ ሳርና ውሀ ፍለጋ በእነኚህ አካባቢዎች በቋሚነት ከአመት እስከ አመት ድረስ የሚንቀሳቀሱባቸው በመሆናቸው መሬት በጋራ እንጂ በግል ለመያዝ አመቺ አይደለም ።በደጋውና ለግብርና አመቺ በሆነው አካባቢ  ደግሞ ደጋማ የሆነና በቂ አመታዊ ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎችም አሉ ። ይሁን እንጂ የሀገሪቱ ተፈጥሯዊ የሆነው የመሬት ሁኔታ በጣም የሚለያይ ስለሆነ አንድ ወጥ ሆነ የመሬት ስሪት ስርአት ለማውጣት አመቺ አይደለም ።


ይሁን እንጂ በደጋው ያለው ህዝብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለመጣ ተደጋጋሚ የመሬት ክፍፍልና ፣ ሽግሽግ ማድረግ ምን ደረጃ ድረስ ሊቀጥል እንደሚችልና ፣ አንዱ አርሶ አደር የሚይዘው መሬትም እያነሰ ስለሚሄድ ውሎ አድሮ የይዞታው ማነስ በምርታማነቱ ላይ አሉታዊ ተፅእኖን ሊያሳድር ይችላል ። በከተሞች አካባቢ የወሰድን እንደሆነ ግን መሬት የግል ንብረት ቢሆን የከተሞችን እድገት ሊያፋጥን ይችላል ።

በአርሶ አደሩ ውስጥ መዋቅራዊ ወይንም የሆነ ስራ አጥነት ሊኖር ይችላል ። ምክንያቱም የስራና መደጋገም ሊኖር ሲችል በርካታ ያገሪቱ ህዝብ በገጠር የሚኖር እንደመሆኑ ያ ሁሉ ህዝብ የስራ እድሉ ጠባብ በሆነ በገጠር አካባቢ የሚኖር መሆኑ በራሱ መዋቅራዊ የሆነ የስራ አጥነት ሊኖር እንደሚችል መገመት ይቻላል ። ጊዜንና ወቅትን ጠብቆ የሚከሰት ስራ አጥነት  (Cyclical Unemployment) የስራ አጥነት አይነቶች ሊኖሩ ይችላሉ። መሬት ውሱን ሀብት እንደመሆኑ መጠን ግን የህዝቡ ቁጥር እየጨመረ ሲሁድ ሀዴሄድ በገጠር የሚኖረው እድል እየጠበበ እንዲሄድ ያደርገዋል ።

አፍሪካ ሰፊ ያልታሰረና ገና ያልተነካ መሬት ያላት አህጉር ስትሆን ፣ ይህንን ሰፊና ጥቅም ላይ ያልዋለ መሬት ለውጪ ባለብቶች በተለይም ለእስያውያን ፣ ለአረቦችና አለልፎ አልፎም ለአውሮፓውያን እየተከራየ ይገኛል ። አንዳንዶቹ የምግብ ሰብልን ሳይሆን የነዳጅ ዋጋ በመወደዱ ምክንያት አንደ ጃትሮፋ የመሳሰሉ ምንም አይነት የምግብ ጠቀሜታ የሌላቸውን ሀይል ሊያመነጩ የሚችሉ ሰብሎችን የሚያመርቱ ሲሆን ፣ በምግብ እህል ራሳቸውን ባልቻሉ በእነኚህ ደሃ ሀገራት ውስጥ ከምግብ ሰብል ፋንታ እነኚህን ለገበያ የሚቀርቡ ሰብሎችን ማምረት አወዛጋሚ ሆኗል ።

በነገራችን ላይ የኢትዮጲያ ምጣኔ - ሀብት በግብርና ላይ መመስረቱ መጥፎ ነገር አይደለም ። በግብርናላይ ምጣኔ - ሀብታችን ሊመሰረት የቻለው ለግብርና አመቺ የሆነ መሬት ፣ ስላለና በቂ ውሀ እምታገኝ እንዲሁም በርካታ ወንዞች ያላት ሀገር ስለሆነች ነው ። አላቂ በሆነ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ከመመስረት ይልቅ በማያልቅ ሀብት ላይ መመስረት በረጅም ጊዜ የተሻለ ነው ። ሌሎች ሀገራትን ብናይ ቢፈልጉ እንኳን ኢኮኖሚያቸው በግብርና ላይ ሊመሰረት አይችልም ። በተለይም በረሀማ በሆነ አካባቢ ያሉ ሀገራት በአብዛኛው ደግነቱ ነዳጅ ዘይት ወይም የተፈጥሮ ጋዝ የመሳሰለ የተፈጥሮ በረከት ስለሚኖራቸው ፣ አንዳንዶቹም ካላቸው ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ የተነሳ ፣ ለምሳሌ የሰሜን አፍሪካ ሀገራትን ብንወስድ ለአውሮፓ ካላቸው ቅርበት ፣ ለቱሪዝም ሰፊ እድል ያላቸው ሲሆኑ እንደ ቱኒዚያና ግብፅ ምጣኔ - ሀብታቸው የተመሰረተበት ዘርፍ ይኀው ቱሪዝም ነው ። 



ግብፅ ደግሞ የአባይ ወንዝ የሚጎበኛት ሲሆን በአንፃሩ ሊቢያ ፣ ቱኒዚያን የመሳሰሉ የሰሜን አፍሪካ ሀገራት በረሃማና በሰሀራ በረሀ ውስጥ የሚገኙ እንደመሆናቸው የውሀ ምንጭ የላቸውም (ምንም እንኳን የእንግሊዝ ሳይንቲስቶች በ2012 ባደረጉት ምርምር እንዳረጋገጡት በሰሀራ በረሀ ውስጥ መሬት ስር ግዙፍ የውሀ ሀብት እንዳለ አረጋግጠዋል ፣ አውጥቶ መጠቀሙ ግን ከፍተኛ ቴክኖሎጂን ይጠይቃል) ፣ ስለዚህ በግብርናው ዘርፍ የአባይ ወንዝ ከአመት እስካመት የሚፈስባትን የግብፅን ያህል እድል የላቸውም ። 

በአለም ላይ ያሉ ሀብታም ሀገራት እንደ አሜሪካ፣ ካናዳና አውስትራሊያ ያሉት ምንም እንኳን ከብዙዎቹ የአለማችን ሀገራት የበለጠ የተፈጥሮ ሀብት ያላቸው ቢሆን አብዛኛውን ኢኮኖሚያቸውን የሚያንቀሳቅሱት ከተፈጥሮ ሀብታቸው ሳይሆን ከኢንዱስትሪ ምርቶቻቸው ፣ በአገልግሎትናበግብርና ዘርፋቸው ነው ።

በሀገራችን ያሉ አንዳንድ ተለቅ ያለ የንግድ እንቅስቃሴን የሚያደርጉ ሰዎች እንደሚሉት የንግድ እንቅስቃሴው ሞቅ የሚለው የግብርና ምርቱ በሚሰበሰብበት የመኀር ወቅት ላይ ሲሆን ፣ ይህም ዋነኛው የሀገራችን ምጣኔ - ሀብት የተመሰረተበት ዘርፍ ሌሎች ዘርፎችም እሚነቃቁት ግብርና ምርት በሚሰበሰብበት የአዝመራ ወቅት መሆኑ በሌሎች ዘርፎች ላይ እንዲሁም ግብርናው ዘርፍ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ያለውን የመሪነት ድርሻ ያመለክታል ። 

አንዳንዶች የግብርና ኢምፔሪያሊዝም (Agro - Imperialism) ሌሎች ደግሞ የመሬት ሽሚያ (land grab) እያሉየሚጠሩት በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት እየታየ ያለ ክስተት ሲሆን በጣም ውድ የሆነውን መሬት በርካሽ ዋጋ ለብዙ አመታት ማከራየት በረጅም ጊዜ በሀገሮች ላይ አሉታዊ ተፅእኖን ሊያስከትል ይችላል ። በተለይም እነኚህ ሀገራት ፈጣን የህዝብ ብዛት እድገት ያላቸው ስለሆኑ የህዝብ ብዛታቸው እየጨመረ ሲሄድ ፣ የመሬት ፍላጎታቸው እያደገ ስለሚሄድ የራሳቸውን ህዝብ የመሬት ፍላጎት ለማሟላት ራሱ ሊከብዳቸው ይችላል ። ይህ ብቻ ሳይሆን የደኖች መጨፍጨፍና ለቱሪዝም ጠቀሜታ ያላቸው የእንሰሳት መኖሪያ ክልሎችና ፓርኮች ራሳቸው እንሰሳቱም አደጋ ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ ። ግዙፎቹ ኩባንያዎች ራሳቸው በዚህ ወቅት የአፍሪካን ለም መሬት መቀራመት የፈለጉበት ምክንያት ህዝብ እየበዛና ከተሞች እያደጉና እየሰፉ ሲሄዱ መሬት ለመኖሪያም ሆነ ለግብርና ተፈላጊነቱ እያደገ እንደሚሄድ በማስላት ነው ።

ከዚህም በተጨማሪ የአለም ህዝብ ብዛት እየጨመረና መሬት እየጠበበ ስለሚሄድ የመሬት ዋጋ እየጨመረ ነው የሚሄደው ። እነኚህ ሀገራት ግን በአነስተኛ ዋጋ ለብዙ አመታት ኮንትራት መሬቱን በመያዛቸውና ከግብርና ምርቶች ዋጋ መጨመር አንፃር በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ይሆናሉ ።በሌላ በኩል ደግሞ መንግስታት እድገት ለማፋጠንና ካላቸው ጉጉትና ፣ እነኚህን ሰፋፊ መሬቶች ለማልማት የሚያስፈልገው ገንዘብና ቴክኖሎጂ (Capital) በሀገራቱ ውስጥ ሊገኝ ባለመቻሉ እነኚህን መሬቶዎች ለውጪ ባለሀብቶች ለመስጠት ተገደዋል ።ይሁን እንጂ በደንብ የተጠናከረና በረጅም ጊዜ ጥቅምን የሚያስጠብቅ ድርድርን ማድረግ አስፈላጊ ነው ።

ጨርሶ የውጪ ባለሀብቶች በዘርፉ አይግቡ ባይባልም ፣ መንግስታት ጠንካራ ድርድር ማድረግ ሲጠበቅባቸው ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በግብርናው ዘርፍ እንዲሰማሩ ቅድሚያና ማበረታቻዎችን መስጠት ያስፈልጋል ። ከባለሀብቶቹ ጋር በሚደረግ ድርድርም ያመረቱት አብዛኛውን ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ ፣ እና የሀገር ውስጥ የምግብ ፍላጎት ከተሟላ ብቻ ወደ ውጪ መላክ እንደሚችሉ በቅድሚያ ድርድሮች ውስጥ ማካተት ያስፈልጋል ።

ሌላው ደግሞ አብሮ ተያይዞ እሚነሳ ነገር የሰፈራ ጉዳይ ነው ። ወደ ሌሎች ለም መሬት ወዳለባቸው ቦታዎችም ማስፈር አንድ አማራጭ ሆኖ ሊታሰብ ይችላል ። በተለይም በድርቅ በተደጋጋሚ የሚጠቁና ፣ ረሀብ በሚከሰትባቸው እንዲሁም የግብርናው ዘርፍ አስተማማኝ የገቢ ምንጭ ባልሆነባቸው አካባቢዎች ሰፈራ እንደ አንድ አማራጭ ሊታይ የሚችል ነው ፤ ሰፊ ለም መሬት ወዳለባቸው አካባቢዎች ። 

በሰሜናዊ ኢትዮጲያ በአብዛኛው መሬቱ ለብዙ ሺ ዘመናት ሲታረስ የኖረ እንደመሆኑ ሌሎች አማራጮች መታሰብ ሊኖርባቸው ያስፈልጋል ። በነገራችን ላይ የአክሱም ስልጣኔ ወደቆባቸው ሊሆን ይችላል ፣ወይም ለውድቀቱ ሰበብ ሊሆኑ ተብለው ከሚሰጡት መላ-ምቶች አንዱ የአካባቢ የአየር ለውጥ ማለትም ድርቅ ወይም የአካባቢ ምርት አለመስጠት ሊሆን ይችላል የሚለው አንዱ መላ-ምት ነው።

ኢንዱስትሪን ፣ ማእድንንበማስፋፋት አማራጭ የስራና የገቢ ምንጮችን መፍጠር አስፈላጊ ሲሆን ። በእስያ ሀገራት እንደተደረገው  (Labor Migration) በመባል በሚታወቀው በርካታ ቻይናውያን ኢንዱስትሪ ወደ ተስፋፋባቸው ጠረፋማ አካባቢዎች በመሄድ ገቢ የሚያስገኝላቸውን የስራና እድል ማግኘት የቻሉ ሲሆን ፣ በደቡባዊ አፍሪካ ሀገራትም የማእድን ሀብት ስላላቸው ወደ ማእድን ማውጫዎች ለበርካታ ሰዎች እንዲሁ አማራጭ የስራ እድሎችን እንዳስገኙ የሚታወቅ ነው ። 

ነዳጅና ጋዝ የመሳሰለው የተፈጥሮ ሀብት ያላቸው ሀገራት ፣ ብዙውን ግዜ በግብርና ላይ ከተመሰረቱ ሀገራት የተሻሉ ይመስላሉ ነገር ግን አላቂ በሆነ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ከተመሰረተ ኢኮኖሚ ይልቅ ስራን እሚጠይቅና ቀስ እያለ በሚያድግ የተሻለ የወደፊት እድል አለው ። ትናንሾቹን የመካከለኛው ምስራቅ «ገልፍ» ሀገራትን ብንወስድ ምንም እንኳን አሁን ባላቸው የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ኢኮኖሚያቸውን መገንባትና ከተሞቻቸውን ማድመቅ ቢችሉም ፣ ውለው አድረው ግን ምጣኔ - ሀብታቸውን በሌሎች ዘርፎች ላይ እንዲመሰረት ካላደረጉ በስተቀር ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት ሲጨርሱ ችግር ላይ የመውደቅ አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል ። በአንፃሩ የሀገራችን ተፈጥሮ ብንመለከት ተራራማ ፣ በቂ ዝናብ የሚያገኝ እና በርካታ ወንዞች ያሉትና መሬቱም ለም ነው ። 

ምንም እንኳን የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ምጣኔ - ሀብቱን የሚያንቀሳቅስ ሞተር ሊሆን ቢችልም ፣ ግብርና ብቻውን ዘለቀ ዘላቂና ፍትሀዊ እድገትን ሊያመጣ አይችልም፣ በተለይም የግብርና ምርትን ለማምረት አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች ማለትም ፣ ብድር ፣ ማዳበሪያ የመሳሰሉት ባልተሟሉበት ሁኔታ ።

ምንም አሁን በኢትዮጲያ ውስጥ የሀብት ክፍፍሉ ያን ያህል የሰፋ ባይሆንም ፣ ውሎ አድሮ ግን በአለም ላይ ሰፊ የሀብት መዛባት ከሚታይባቸው ሀገራት ልትሆን እንደምትችል ዛሬ ላይ ሆኖ መገመት ይቻላል ። ለዚህም ምክንያቱ ይኀው የመሬት ጉዳይ ሲሆን ብዙሀኑ ህዝብ በሀገሩ ዋነኛው የሀብት ምንጭ የሆነውን የመሬት ባለቤት አይደለም ። 

 
የምግብ ዋጋንም ብንወስድ በአለም ላይ ያለው የምግብ ዋጋ እየናረ መሄድ እድሎችንም ፣ ስጋቶችንም ይዞ መቷል ። ስጋቱ የህዝባችን ቁጥር እያደገ በመሄድ ላይ ስለሚገኝ የምግብ ዋጋ መወደድ በህዝቡ ኑሮ እንዲሁም በሀገሪቱ ውስጣዊ መረጋጋት ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅእኖ ሊኖረው ሲችል በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጲያ ሰፊ መሬትና ወንዞች ያላት ሀገር እንደመሆኗ በርካታ የግብርና ምርቶችን ለአለም ዋጋ ለማቅረብ ሲያስችል ፣ ለብዙ መቶ አመታት ኋላ ቀር ሆኖ የኖረው የግብርናው ዘርፍ እንዲያንሰራራና ወደ ዘመናዊነት እንዲሸጋገር እድልን በመክፈትየግብርናውን ዘርፍ አዋጪ አንዲሆን ያስችለዋል ።

የታሪክ ጠባሳ የሚፈጥረው አሉታዊ ጥላ




            ብዙ ጊዜ ተገዢ ወይንም ተጨቋኝ ውሎ አድሮ የሞራል የበላይነትን ያጎናፅፋል ። ገዢው ስልጣኑን ወይንም ሀብቱን ለመከላከል ሲል በሚያደርጋቸው ድርጊቶች ሳያስበው ስህተቶችን ይፈፅማል ። እነኚህም ስህተቶች ውለው አድረው ጉዳት የደረሰበት ወገን የሞራል የበላይነትን እንዲይዙ ያደርጉታል ። ሲጀመር ፍትህን ይዞ የተነሳው ገዢ ቀስ በቀስ  ራሱ ወደ ቀድሞው ፣ራሱ ወዳስወገደው አይነት ፈላጭ ቆራጭነት ይመለሳል ። በዚህ የሞራል የበላይነቱን ልእልናን ወደ ተገዢዎቹ ወይም ወደ ተጨቋኞቹ ይተላለፋል ።በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ገዢና ተገዢ ቦታቸውን የሚቀያየሩ ሲሆን  ፣ ገዢ የሆኑት ዎች ይህንን ነባራዊ እውነታ ካልተረዱ ።  ለለውጡም ሁኑታ ቅድመ ሁኔታ እሚያስፈልጉት ህሊናና እየተዘጋጁ ይሄዳሉ ።
           ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ ስርአት የሚፈጥረው ማህበረሰብ ራሱ ውሎ አድሮ ከስርአቱ ጋር ሆድና ጀርባ የመሆን እድልም አለ ። ለምሳሌ በብዙ ሀገራት ቀድሞ መካከለኛ መደብ ያልነበረባቸው ፣ እንዲሁም የዲሞክራሲ ስርአትም ያልነበራቸው ሀገራት ፣ በመሪዎቹ ፖሊሲ ምክንያት ሀገራቱ የምጣኔ - ሀብት ብልፅግናን ሲያመጡ መጀመሪያ ላይ ከመካከለኛው መደብ ጠንካራ ድጋፍን ሲያገኙ ውለው አድረው ግን ያ የተፈጠረው የመካከለኛው መደብ ጥያቄዎቹ እያደጉ መጥተው ካለው ስርአት ጋር  የሚቃረኑ እና ስርአቱ እንዲለወጥ ወይንም እንዲሻሻል ፍላጎት ይፈጠራል ። ይህም ለምሳሌ በሩስያ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ የፑቲን አስተዳደር ስርአትን በማስፈንና ፣ በእዳና በምጣኔ - ሀብት ዘቅጣ የነበረችውን ሀገር ወደ ቀድሞው ገናናነቷ መመለስ ቢችልም እንዲሁም መካከለኛው መደብ ቢደግፈውም ፣ ከተወሰኑ አመታት በኋላ ግን ስርአቱ ለመካከለኛው መደብ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችልና ለእድገቱም እንቅፋት እንደሚሆን  የተረዳው ህብረተሰብ ድጋፉ እየቀዘቀዘ መምጣቱ አልቀረም ፤ በቻይናም የዚህ ምልክቶች በመታየት ላይ ናቸው ።

               በአሜሪካ አፍሪካ አሜሪካውያን አሁን ወደ ከፍተኛ ስልጣን ደረጃዎች እየመጡ ሲሆን ፣ከዚህ ቀደም እንኳን ለመመረጥ ቀርቶ መምረጥ እንኳን እማይችሉበት ጊዜ ነበረ ። በደቡብ አፍሪካም እንዲሁ ጥቁሮች እንደ ሁለተኛ ዜጋ ይቆጠሩ የነበረ ሲሆን የዘር መድልኦ በራሳቸው ሀገር ይደረግባቸው የነበረ ቢሆንም የኋላ ኋላ ግን የገዛ ሀገራቸው ባለቤትና አስተዳዳሪዎች ለመሆን በቅተዋል ። 

ይህ ክስተት በተደጋጋሚ በታሪክ የታየ ሲሆን ምእራባውያን ካለፉት ልምዶቻቸው ይህንን ስለሚያውቁ በርካታ ጥንቃቄዎችን እሚያደርጉት ። በባሪያ ንግድ ፣ በቅኝ ግዛት  እና በከዚያም በኋላ በዘረኝነትና በመሳሰለው በርካታ ጉዳትን ስላደረሱ በዛም ለበርካታ የሞራል የበላይነታቸውን ስላጡ ያንን ላለመድገም በእጅጉ የሚጠነቀቁት ። ጆርጅ ኦርዌል የተባለው ታዋቂው እንግሊዛዊ ደራሲ ያለፈውን የሚቆጣጠር የአሁኑን ይቆጣጠራል፣ የአሁኑን የሚቆጣጠር የወደፊቱንም ይቆጣጠራል ይላል ። ያለፈውን የተቆጣጠረ የአሁንን ብሎም የወደፊቱን መቆጣጠር ይችላል ።

ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት ከዚህ በፊት እንደ አናሳ ዜጋ ይታዩ የነበሩት ጥቁሮች በአሜሪካን ሀገር ከፍተኛውን የስልጣን ደረጃ ውስጥ እየገቡ ሲገኙ ፣ ይሄም ለዘመናት ተገዢ የሆኑት ጥቁሮች ገዢም ፣አስተዳዳሪም ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው ። በምእራቡ አለም በርካታ መፅሀፍት በየአመቱ ይታተማሉ ። ቁጥራቸው ቀላል እማይባሉት ግለ - ታሪኮች የመሳሰሉት ናቸው ። ነገር ግን አንድ ሰው መፅሀፍ ሲፅፍ ካለፈው በመነሳት ፣ታሪክን በራሱ መንገድ በመተርጎም የወደፊቱን ሰው በተረዳው መንገድ ለመቅረፅ ካለው ጉጉት በመነሳት የሚያደርገው ጥረት ነው ።
ያለፈውን እሚቆጣጠር ፣ ባለፈው እንደዚህ ስለተደረኩ ነው አሁን እንደዚህ እማደርገው ወይም አሁን እንደዚህ መሆን ያለበት እሚል ክርክር ሲያቀርብ ፣ አሁን እሚደረግ ማንኛውም ነገር ደግሞ ለወደፊት ለሚሆነው በጎም ሆነ ጥሩ ነገር መሰረትን ይጥላል ። ለዚህም ነው ታሪክ ላይ ብዙ መራኮትና ታሪክን ሁሉም በየራሱ መንገድ ለመተርጎም የሚጥረው ።

ነገር ግን እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር ባለፈው የተደረገ ወይም የተከሰተ መጥፎ ነገር አሁን ለሚደረግን ትክክል ወይም አግባብ ያልሆነ ነገር እንዲደረግ ፣ ትክክለኛ (Justify) አያደርገውም ።በተለምዶ ሁለት ስህተቶች አንድን ነገር ትክክል አያደርጉትም እንደሚባለው መሆኑ ነው ። ለምሳሌ እስራኤላውያን በአውሮፓውያን ለብዙ ክፍለ ዘመናት መሰቃየታቸው ብሎም አለምን ለመቆጣጠር እያሴሩ ነው በሚል በሁለተኛው የአለም ጦርነት በጀርመን ናዚዎች መፈጀታቸው ፣ እነሱ ፍልስጥኤም ላይ የሚያደርጉትን ማንኛውንም ነገርወይም እሚያደርሱትን ችግር ትክክለኛ ወይም ፍትሀዊ አያደርገውም ። ወይም አውሮፓውያን እስራኤልን በፍልስጥኤም ላይ እምታደርገውን ነገር በጭፍን ቢደግፉ እነሱ ለብዙ ክፍለ ዘመናት በአይሁዶች ላይ ያደረሱትን ስቃይና ግፍ አያጥበውም ። አንዳንዶች እንደውም እስራኤል በዚህ ድርጊቷ የኋላ ኋላ መልካም ውጤትን እንደማያመጣላት እየገለፁ ይገኛሉ ። 

ጀርመኖችንም ብንወስድ ምንም እንኳን እሁዳውያንን መጥላት ለብዙ መቶ አመታት በአውሮፓ የነበረና የተለመደ ቢሆንም አሁንም ድረስ ያለ ቢሆንም ናዚዎች ግን ይሄንን ነገር ወደ ከፍተኛ ጥግ በመግፋት እሁዳውያንን በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት እሁንዳውያንን በመጨፍጨፋቸው ፣ እስካሁን ድረስ እያፍሩበት ያሉበት ጉዳይ ነው፣ ጀርመን በዚህ ምክንያት በርካታ ዋጋን ከፍላለች ። በርካታ ገንዘብም ለጦር ጉዳት የከፈሉ ሲሆን ይሄንን ድርጊትን የካደ ራሱ በህግ እንዲጠየቅም ጭምር ጀርመን ደንግጋለች ፣ ይሄንን ድርጊትን የካደ ራሱ በህግ እንዲጠየቅም ጭምር ደንግጋለች ፣ ይሄ ብቻ ሳይሆን ጀርመን ከሁለተኛው የአለም ጦርነት የደረሳባትንና ያለፈችበትን ያንን በመፍራት እንደ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት በአለም ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ተሳትፎ የላትም ፤ ለምሳሌ እንግሊዝና ፈረንሳይን ብንወስድ ምንም እንኳን ከጀርመን ከእነሱ የበለጠ የምጣኔ - ሀብት አቅም ቢኖራትም የእነሱን ያክልግን ተሳትፎን አታደርግም ።

ምንም እንኳን ቱርክ ብታስጠነቅቅም ፣ ፈረንሳዮችም በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ አርሜንያውያን በቱርኮች የተጨፈጨፉበትን ድርጊት የካደ ማንኛውም ሰው በህግ እንዲጠየቅ እነሱም ደንግገዋል ። በነገራችን ላይ ይህ የአብዝሀው አናሳዎቹን መጨቆን ፣ ውሎ አድሮ በተራው የአናሳዎቹን አገዛዝ ፍትሀዊ ወይንም ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ያደርገዋል ። ነገር ግን የዚህ አይነቱ አገዛዝ ችግሩ ግን የአናሳዎቹ አገዛዝ ራሱን ከብዙሀኑ ጋር ማዋሀድ «አሲሚሌት» ማድረግ ይኖርበታል ፣ አለበለዚያ በረጅም ጊዜ ህልውናውን አስጠብቆ መቆየት አይችልም ። ቢያንስ ፍትሀዊነትን መላበስ ይኖርበታል ። ለምሳሌእስራኤልን ብንወስድ ምንም እንኳን የአረብ ህዝብ ቁጥሩ ስለሚያይል በአረብ ህዝብ መዋጥ ባትፈልግምና እስራኤልን የአይሁዶች ብቻ አገር የማድረግ ፍላጎት ያላት ብትሆንም ፣ በረጅም ጊዜ ግን በአካባቢው በሰላም ለመኖር ያስችላት ዘንድ ፣ ከጎረቤቶቿ ፍልስጥኤሞችን ሆነ አረቦች ጋር ያላት ግንኙነት የተሻለ ፍትሀዊነት የሰፈነት መሆኑ ግድ ነው ። 

            እስራኤል በበኩሏ  ይህንን ችግር ለመጋፈጥ ወታደራዊ ጡንቻዋን ማፈርጠሙን እንደ ዋና አማራጭ ወስዳዋለች ማለት ይቻላል ።የመከላከያ ባጀቷን ከቱርክ በ73 እጥፍ  ከእንግሊዝ በ 11 ጊዜ እጥፍ ታንሳለች አመታዊ 16ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ወይም 288 ቢሊዮን የኢትዮጲያ ብር በጀት ትመድባለች ። ነገር ግን እስራኤል ከግብፅ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ላይ የደህንነት ጥበቃ ሰውራ ስራዋን ለመስራት ፣ እንዲሁም የአረብ አመፅ አካባቢው መናዊ ወጡ የእስራኤልን ስጋት አንሮታል ። የካይሮን ቃል በመተማመኛነት ተቀብላ ከመቀመጥ ይልቅ ፣ የራሷን የመከላከያ ባጀቷን ማሳደግንና ራሷን መከላከልን መርጣለች ። በወታደራዊ በአለም 10ኛ ስትሆን 10 የኒውክሎሊየር አረሮች ባለቤትም ነች ። ከዚህም በተጨማሪ  በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦርነቶች ፣ የጦር መርከቦች ያሏትም ሀገር ነች ።


የምእራባውያን የስትራቴጂ ፈተናዎችና ስልቶች



                    ምእራባውያን ራሳቸው አልፎ አልፎ ቢደነቃቀፉም ቢሉም ብዙ ጊዜ ግን መርሆቻቸውና ፍልስፍናዎቻቸው ሰርተውላቸዋል - በመርህ የሚመሩ መሆናቸውም በእጅጉ ሳይጠቅማቸው አልቀረም ። ለመርህ ተገዢ መሆን ለጊዜው ችግር ቢያጋጥም እንኳንካለው ችግር አንፃርከመርህ ለመውጣት ሊፈታተን ቢችልም ፤ በረጅም ጊዜ ግን በመርህ ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ አሸናፊና ጠንካራ ሆኖ ይወጣል ።.
                    በተለይም ከዲሞክራሲ ፣ ከሰብአዊ መብት ጋር በተያያዘ ከሌሎች ሀገራት በተሻለ የነሱ መርሆዎች በበለጠ የሚሰሩ ሆነው ተገኝተዋል ። ነገር ግን እነሱም በቀላሉ እዚህ ደረጃ አልደረሱም በርካታ ስህተቶችን ሰርተው ነው ። በባሪያ ንግድ እና በግኝ ግዛት ዘመን በሌሎች ህዝቦች ላይ ካደረሷቸው ሰቆቃዎች፣ ከአንደኛውና ከሁለተኛው የአለም ጦርነቶች ፣ በየሀገሮቻቸው ከነበሩ የመብት ትግሎች ለምሳሌ ጥቁሮች በአሜሪካን አገር የሰብአዊ መብታቸውን ለማስከበር ካደረጓቸው ትግሎች እና ከሌሎችም ብዙ ትምህርቶችን ቀስመው ነው እዚህ አሁን ለደረሱበት የሰብአዊ መብትን ማክበርና ወደ የዲሞክራሲ ደረጃ የደረሱት ።
                 ከቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ጋር ባደረጉት ትግል የቀዝቃዛው ጦርነት ፣ ሶቭየት ህብረትም ከአሜሪካ ጋር ተመጣጣኝ የጦር መሳሪያ እና ወታደራዊ አቅም የነበራት ሀገር ነበረች ። ይሁን እንጂ በ1963 ተከስቶ የነበረው የኩባው የሚሳይል ቀውስ አደገኛ ሁኔታን ለአለም ከመፍጠሩ የተነሳ ፣ ቀውሱ በሰላም ባይፈታ ኖሮ አለማችን የዛሬዋን አለማችንን አትሆንም ነበረ ።በአለም ላይ አሁን ባለው የሰው ልጅ በታጠቀው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ፊት ለፊት ሊደረጉ የሚችሉ ጦርነቶች አለማችንን አንዴ ብቻ ሳይሆን ደግመው ደጋግመው ማጥፋት እሚችሉበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ ተደርሷል ።
              ይህን የተረዱት አሜሪካኖች ግን የሶቭየት ህብረትን ግዙፍ አቅም በአመታት ውድድር በማድረግ ፣ ያንን ውድድር መቋቋም ሲያቅተው ራሱ ስርአቱ ከውስጡ ሊፈራርስ ችሏል ። የኮኮቦች ጦርነት(Star Wars) የተሰኘው አሜሪካን የጀመረችው ሶቭየት ህብረት ከነበራት የገንዘብም ሆነ የቴክኖሎጂ አቅም አንፃር በአጠቃላይ ከአሜሪካንም ሆነ ከምእራብ አውሮፓውያን ጋር መወዳደር ባለመቻሏ ልትፈራርስ በቅታለች ። ይህ ብቻ ሳይሆን የሶሻሊስት ስርአት እንደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት መሪዎችን እየቀያየረ ፣ የፖሊሲ ለውጥ እያደረገ የመሄድ አቅምና ብቃትም ስላልነበረው መሪዎቹ በእድሜ እያረጁና አንዳንዶቹም እየሞቱ የነበሩትየሶቭየት መሪዎችን ውስጥ ችግሮቻቸውን በተለይም የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመፍታት ሳይችሉ ቀርተዋል ። ይባስ ብሎም በወቅቱ የገቡበት የአፍጋኒስታን የጦርነት ክፉኛ ጎድቷቸዋል ። ሌላው ደግሞ የሶቭየት ስርአት ከፍተኛ አመራሩ ተቋማዊ ሳይሆን መቅረቱ ለውድቀቱ ትልቅ አስተዋፅኦን አድርጓል ።   

             የቻይና የኮሚኒስት ፓርቲን ብንወስድ ለማኦ ሞት በኋላ በቶሎየአመራር ስፍራውን ወደ ተቋማዊነት አደረጃጀት ስለቀየሩት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የሶሻሊዝምን ውድቀት መትረፍ ችሏል ። ይህንም በመሆኑ ምጣኔ - ሀብታዊ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግናስላስቻለው በሌሎች የኮሚኒስት ስርአቶች ያጋጠመው መፈራርረስ ሳያጋጥመው ቀርቷል ። ወደ ተቋማዊ አደረጃጀት መቀየር አንድ ስርአት ለዘብ «flexible» ለዘብ እንዲሆን ያስችለዋል ።በአመራሩ ላይ የሚመጡ የተለያዩ ሰዎች ስለሚኖሩ የተቋማዊ ፣የተለያዩ የአመራር ስልቶች ስራ ላይ የመዋልና አስፈላጊ የሆኑ የፖሊሲ ለውጦችን ለማድረግ እድልን ይሰጣል ።
                      በወቅቱ የሶቭየት ህብረት መሪ የነበሩት ሚካኤል ጎርባቾቭ ፔሬስትሮይካና ግላስኖት በተባሉት የግልፅነትና የሶቭየት ህብረትን ስርአት ለማሻሻል ነው እንጂ ስርአቱን ለማፍረስ አልነበረም አላማቸው ። ይሁን እንጂ ነገሮች ተቀያይረው ባልተጠበቀ ሁኔታ ስርአቱ ፍርስርሱ ወጥቷል ። ምእራባውያን ከ20ኛው ክ/ዘመን ታላላቅ ሰዎች አንዱ ናቸው እሚሏቸው ጎርባቾቭን ሲሆን እንደ ተወዳጅ ታዋቂ ሰው አድርገው ነው እሚወስዷቸው - ያንን ያስፈራቸው የነበረን ግዙፍ ስርአት ስላፈራረሱላቸው ሊሆን ይችላል ።  ይሁን እንጂ ትልቁ ነገር የምእራባውያን ትእግስትና ፣ ፊት ለፊት በወታደራዊ ጉልበት ለመጋፈጥ አስቸጋሪ የሆነን ስርአት ለመጣል የተጠቀሙበት ስልት ግን እሚደነቅ ነው ። 



                            አንዱ የምእራባውያን የጥንካሬ የዲሞክራሲ ስርአት ሲሆን የፖለቲካ አመራራቸው ተቋማዊ ሲሆን ፣ የምጣኔ - ሀብት አስተዳደራቸውም ተከታታይነት ባለው እቅድ የሚመራ ነው ። የማእከላዊ ባንኮችን ብንወስድ ነፃና በራሱ የምጣኔ - ሀብትን ማለትም የገንዘብ ፖሊሲዎችን መውስድ የሚችል ሲሆን ከፖለቲከኞች ቀጥታ ስልጣን እና ቁጥጥር ውጪ ነው ። በነገራችን ላይ ነፃ የሆነ የማእከላዊ ባንክ ምጣኔ - ሀብት ሲያድግ የሚሆን ሲሆን እንግሊዝ እንኳን በቅርቡ ነው ባንክ (Bank of England) ነፃ ያደረገችው ። ስለዚህ ነፃና ከፖለቲካ አመራሩ ገለልተኛ የሆነ ማእከላዊ ባንክ እንዲኖር ያደረገ እንደ ቅድመ ሁኔታ የገንዘብና የአክስዮን ገበያዎች መኖር አለባቸው ።



                   ይሁን እንጂ ምእራባውያን ሁልግዜ መርሆዎቻቸው ይሰሩላቸዋል ማለት አይደለም ። ምእራባውያን ከተደነጋገሩባቸው «ስታምብል» ካደረጉባቸው የኢራቅና የአፍጋኒስታን ጦርነቶች ምሳሌዎች ናቸው ። አሜሪካን ውስጥ ጦርነት ሲመጣነው ጂኦግራፊን የሚማሩት ይባላል። እንጂ ከዛ በፊት ወጣቶቹ ስለአለም በሚገባ እውቀትን ይዘው አለማደጋቸው በፖለቲከኞቹም ላይ የሚንፀባረቅ ነው  ። ከዚህ ቀደም አሜሪካ ራሷን እንደ አለም ማእከል አድርጋ ትወስድ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ያንን በመረዳት አለምንም ራሳቸውንም በተለየ መንገድ ማየት ጀምዋል ።በታወጀው በሽብር ላይ ጦርነት (War on Terror) ከጓናታናሞ ቤይ በፊት ሽብርተኝነትን በአሜሪካ ላይ በፈፀሙ ላይ በመደበኛ ፍርድ ቤት ታይቶ ለምሳሌ አይነስውሩ ግብፃዊ ላይ ጨምሮ ፍትህ የተሰጠ ቢሆንም ሆንም በቡሽ ዘመን ግን ጓንታናሞ ቤይን በመክፈት የሰብአዊ መብትን የሚጥስ ፍርድ ቤትን ለመክፍትና በአለም አቀፍ ደረጃም ስለሰብአዊ መብት የነበራትን መልካም ስም ለማጉደፍ በቅታለች ። ይህ ብቻ ሳይሆን ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩ በርካታ ፖለቲከኞቿ የቀድሞውን ትንሹ ቡሽን ጨምሮ በቂ የአለም አቀፍ እውቀት እንደሌላቸውና ፣ በርካታ ስህተቶችን ሲሰሩ ታይተዋል ። አንድን የአለም ሀያል የሆነ አገርን የሚመሩ የፖለቲካ ሰዎች ስለአለም አቀፋዊ እውነታዎች በቂ ግንዛቤና እውቀት ሊኖራቸው እንደሚገባ ግልፅ የሆነ ጉዳይ ነው ።