Thursday, February 28, 2013

የመሬት ስሪት ስርአትና የመቅራዊ ሽግግር (Transformation)





 በሀገራችን መሬት በከተማም ሆነ በገጠር ዋናው የሀብት ምንጭ መሆኑ አያከራክርም ። ለመንግስትም ሆነ ለግል ድርጅቶች እንዲሁም ለግለሰቦች ዋናው የሀብት ምንጭ መሬት ነው ። በከተማም ሆነ በገጠር መንግስት ከሚሰበስበው ግብር አብዛኛው መሬት የሚያመነጨውን ነው ማለት ይቻላል ። ምጣኔ ሀብቱ መሬት በተፈጠረው ሀብት ላይ እስከተመሰረተ ድረስ ፣ እንዲሁም በእውቀት ላይ የተመሰረተ እስካልሆነና ኢንዱስትሪዎች ተስፋፍተው ፣ ለዜጎች የስራና የገቢ እድሎች እስካልሰፉ ድረስ በመሬት ላይ ኢኮኖሚው መመስረቱ አይቀሬ ነው ።


 የምጣኔ - ሀብት ባለሙያዎችም እንደሚስማሙት ከአዳም ስሚዝ በፊት የነበሩት ፊዚዮክራቶች እንዲሁ ግብርናን እሴትን የሚፈጥር ዘርፍ ብለው የሚያምኑ የነበረ ሲሆን ፣ ከአዳም ስሚዝን ብንወስድ ተፈጥሮ ሰውን ስለሚያግዘው (Nature Labors with Man) አትራፊው የሆነው ዘርፍ ግብርና ነው የሚል እምነት የነበረው ሲሆን ፣ ይህ አስተሳሰብ በተለይም በአሁኑ ዘመን የህዝብ ቁጥር እየናረ ባለበትና ፣ ለእርሻ ይውል የነበረውን መሬት ለከተሞች ማስፋፊያ እየዋለ ባለበት ፣ ለእርሻ አመቺ የነበረው ለም መሬት በአለም ሙቀት መጨመር ምክንያት ምርታማነቱ እየቀነሰ በመጣበት እና የምግብ ዋጋ ንረት በየአመቱ እየተባባሰ ባለበት በዚህ ወቅት የግብርናው ዘርፍ አስፈላጊነት ከምንም ነገር በላይ በልጦ የሚታይ ሀቅ ሆኗል ። ይህ ብቻም ሳይሆን ፣ አንድ ሀገር በእድገት ጅማሮዋ እያለችና ካፒታልን ለማሰባሰብ እና የእድገት ለመሰረትን ለመጣል የግብርናው ዘርፍ ዋነኛ መሰረትና በሌላ ዘርፍም ሊተካ የማይችል ነው ።

 የመሬት ጉዳይ የሀገሪቱ ምጣኔ - ሀብት መዋቅራዊ ለውጥ እያደረገ ሲመጣ ጉዳዩ እየተቀየረ መምጣቱ አይቀሬ ነው ። ሆኖም አሁን ባለው ያገሪቱ ምጣኔ - ሀብት ሁኔታ አወቃቀር ሲታይ በገጠርም ሆነ በከተማ ዋናው የሀብት ምንጭ መሬት መሆኑ ግልፅ ነው ። በአንፃራዊነት ግብርናው ዘርፍ ለአጠቃላዩ ኢኮኖሚ ያለው ድርሻ እየቀነሰ እና የሌሎች ዘርፎች ማለትም የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች እያደጉ ሲመጡ በመሬት ጉዳይ ላይ እሚነሱት ክርክሮች ፖለቲካዊ ከሆነ ይልቅ ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰቦችን እየያዙ ይመጣሉ ።

             
አሁን ባለችው አለማችን ካፒታልና እውቀት ናቸው ከፍተኛ ሀብትን መፍጠር የሚችሉት በዚህ ምክንያት ከመሬት የሚመነጨው ሀብትም ያን ያህል እሚያስመካ እንዳልሆነም ይታወቃል ፣ አንዱም ሀገሪቱ ስር የሰደደ ድህነት ምክንያት ምጣኔ - ሀብቱ በአብዛኛው እድገቱ  አዝጋሚ በሆነው መሬት በሚያመነጨው ሀብት ላይ መመስረቱ ነው ። በዚሁ በመሬት ጉዳይ ሌላ ዋነኛ አማራጭ የሆነ የገቢ ምንጭ ስለሌለው መንግስት ፖሊሲዎች በተደጋጋሚ መቀያየሩ ፣ የበለጠ ገቢን በሚያገኝበት መንገድ የመሬት አዋጆችና ደንቦች መለዋወጡ የሚጠበቅ ነው ። በኢትዮጲያ በተደጋጋሚ እንደታየው መንግስታት ሀብትን ለማከፋፈል ሲፈልጉ ወይም ያለውን የፖለቲካና ኢኮኖሚ መዋቅሩን መቀየር ሲፈልጉ መሬትን የሚመለከት ስር ነቀል አዋጆችን ማውጣት የተለመደ ነው ። በንብረት ላይ የተመሰረተ ሀብት የተዛባ የሀብንት ክፍፍልን ከሚፈጥሩ ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ ይታወቃል ። ምክንያቱም አንድ ሀገር የሚኖራት ንብረት ማለትም መሬትም ሆነ ሌላ ከተወሰነ መጠን እንዳማያልፍ ይታወቃል ።

በሀገራችን ታሪክ በ1967 ዓ.ም.ደርግ ያወጣው የመሬት አዋጅና በ2004 ዓ.ም. ኢህአዴግ ያወጣው አዋጆች መሬትን በተመለከተ ስር ነቀል መሆናቸውን በርካታ የመስኩ ምሁራን ይስማሙባቸዋል ። ምንም እንኳንየ 1967ቱ አዋጅ በዘመኑ የነበሩ ወጣቶች የታገሉለትና ስር ነቀል ለውጥን ያመጣና፣ ሀገሪቱን ከፊውዳላዊ የመሬት ስሪት ያላቀቀ ቢሆንም ፣ በአንፃሩ የከተማ ትርፍ ቤቶችን የመንግስት ያደረገው አዋጅ ግን የከተሞችን እድገት ባሉበት እንዲቆሙ ያደረገና ፣ እንደ አዲሳባ ያሉትን ትላልቅ ከተሞች ለመኖሪያነት አመቺ እንዳይሆኑና እድገታቸው የተገታና ፣ በአጠቃላይ የተከተሞችን እድገት የጎተተ ነው ። 


ይህ ብቻም ሳይሆን መሬት አላቂ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት እንጂ የማያልቅ ባለመሆኑ ፣ ለመሬት የሚደረገው ሽሚያና ዋጋውም እንደዛው እየጨመረ መሄዱ አይቀርም ።የመሬት ጉዳይ ህገ - መንግስት ውስጥ ገብቶ መቀመጡ ግን ምናልባት ማሻሻል ቢያስፈልግ ቀላል እንዳይሆን ያደርገው ይችላል ። መሬት በግል ቢያዝ ይሻላል የሚሉ ሰዎች ከሚያቀርቡት ክርክር አንዱ ለምሳሌ አንድ ሰው መሬቱ የግሉ ቢሆን ከአመት እስካመት ድረስ በዝናብ የሚታጠበውን መሬት ባለቤቱ ሊንከባከበውና ከመሸርሸር ሊጠብቀው ይችላል የሚል ነው ። 


በአንድ በኩል ሲታይ ግብርናን መደጎም ተገቢነት ያለው ነው ማለት ይቻላል ። የግብርና ስራ አድካሚና አሰልቺ መሆኑ ፣ ትርፉም እንደሌሎቹ ዘርፎች አስተማማኝ አለመሆኑ፣ ከተፈጥሮና ከአየር ንብረት ጋር በመታገል የሚሰራ ስራ በመሆኑሀብታም ሀገራት የግብርናውን ዘርፋቸውን እንደሚደጉሙ የአደባባይ ሀቅ ነው ። አሜሪካና አውሮፓውያን በተለይም ከአውሮፓ ሀገራት ፈረንሳይ ገበሬዎቿን በመደጎም ትታወቃለች ። ይሁን እንጂ አውሮፓውያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሀገራትም ደግሞ እንደሚሉት ግብርናውን ዘርፍ በመደጎም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትና እና ቻይናንም ጭምር ግብርናቸውን ይደጉማሉ የሚል ቅሬታን ያሰማሉ ። በ2012 ዓ.ም በአሜሪካን ሀገር ምስራቅና በመካከለኛው «Mid West» በሚባለው አካባቢ ለ52 አመታት ተከስቶ የማያውቅ ድርቅ በመከሰቱ ምክንያት የበቆሎና የአኩሪ አተር ዋጋን ሲያንር ፣ ነገር ግን የአሜሪካ ገበሬዎች የመድን ዋስትና ስላላቸው በቀላሉ ገበሬዎቹ የሚፈራውን ያህል ለኪሳራ አይዳረጉም ።  


በሀገራችን ውስጥ በርካታ አይነት የመልከአ - ምድራዊ እንዲሁም አየር ንብረት ስርጭት ያለ ሲሆን ለምሳሌ ቆላማ የሆኑትን የአርብቶ - አደር አካባቢዎችን ብንወስድነዋሪዎቹ ለከብቶቻቸው የግጦሽ ሳርና ውሀ ፍለጋ በእነኚህ አካባቢዎች በቋሚነት ከአመት እስከ አመት ድረስ የሚንቀሳቀሱባቸው በመሆናቸው መሬት በጋራ እንጂ በግል ለመያዝ አመቺ አይደለም ።በደጋውና ለግብርና አመቺ በሆነው አካባቢ  ደግሞ ደጋማ የሆነና በቂ አመታዊ ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎችም አሉ ። ይሁን እንጂ የሀገሪቱ ተፈጥሯዊ የሆነው የመሬት ሁኔታ በጣም የሚለያይ ስለሆነ አንድ ወጥ ሆነ የመሬት ስሪት ስርአት ለማውጣት አመቺ አይደለም ።


ይሁን እንጂ በደጋው ያለው ህዝብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለመጣ ተደጋጋሚ የመሬት ክፍፍልና ፣ ሽግሽግ ማድረግ ምን ደረጃ ድረስ ሊቀጥል እንደሚችልና ፣ አንዱ አርሶ አደር የሚይዘው መሬትም እያነሰ ስለሚሄድ ውሎ አድሮ የይዞታው ማነስ በምርታማነቱ ላይ አሉታዊ ተፅእኖን ሊያሳድር ይችላል ። በከተሞች አካባቢ የወሰድን እንደሆነ ግን መሬት የግል ንብረት ቢሆን የከተሞችን እድገት ሊያፋጥን ይችላል ።

በአርሶ አደሩ ውስጥ መዋቅራዊ ወይንም የሆነ ስራ አጥነት ሊኖር ይችላል ። ምክንያቱም የስራና መደጋገም ሊኖር ሲችል በርካታ ያገሪቱ ህዝብ በገጠር የሚኖር እንደመሆኑ ያ ሁሉ ህዝብ የስራ እድሉ ጠባብ በሆነ በገጠር አካባቢ የሚኖር መሆኑ በራሱ መዋቅራዊ የሆነ የስራ አጥነት ሊኖር እንደሚችል መገመት ይቻላል ። ጊዜንና ወቅትን ጠብቆ የሚከሰት ስራ አጥነት  (Cyclical Unemployment) የስራ አጥነት አይነቶች ሊኖሩ ይችላሉ። መሬት ውሱን ሀብት እንደመሆኑ መጠን ግን የህዝቡ ቁጥር እየጨመረ ሲሁድ ሀዴሄድ በገጠር የሚኖረው እድል እየጠበበ እንዲሄድ ያደርገዋል ።

አፍሪካ ሰፊ ያልታሰረና ገና ያልተነካ መሬት ያላት አህጉር ስትሆን ፣ ይህንን ሰፊና ጥቅም ላይ ያልዋለ መሬት ለውጪ ባለብቶች በተለይም ለእስያውያን ፣ ለአረቦችና አለልፎ አልፎም ለአውሮፓውያን እየተከራየ ይገኛል ። አንዳንዶቹ የምግብ ሰብልን ሳይሆን የነዳጅ ዋጋ በመወደዱ ምክንያት አንደ ጃትሮፋ የመሳሰሉ ምንም አይነት የምግብ ጠቀሜታ የሌላቸውን ሀይል ሊያመነጩ የሚችሉ ሰብሎችን የሚያመርቱ ሲሆን ፣ በምግብ እህል ራሳቸውን ባልቻሉ በእነኚህ ደሃ ሀገራት ውስጥ ከምግብ ሰብል ፋንታ እነኚህን ለገበያ የሚቀርቡ ሰብሎችን ማምረት አወዛጋሚ ሆኗል ።

በነገራችን ላይ የኢትዮጲያ ምጣኔ - ሀብት በግብርና ላይ መመስረቱ መጥፎ ነገር አይደለም ። በግብርናላይ ምጣኔ - ሀብታችን ሊመሰረት የቻለው ለግብርና አመቺ የሆነ መሬት ፣ ስላለና በቂ ውሀ እምታገኝ እንዲሁም በርካታ ወንዞች ያላት ሀገር ስለሆነች ነው ። አላቂ በሆነ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ከመመስረት ይልቅ በማያልቅ ሀብት ላይ መመስረት በረጅም ጊዜ የተሻለ ነው ። ሌሎች ሀገራትን ብናይ ቢፈልጉ እንኳን ኢኮኖሚያቸው በግብርና ላይ ሊመሰረት አይችልም ። በተለይም በረሀማ በሆነ አካባቢ ያሉ ሀገራት በአብዛኛው ደግነቱ ነዳጅ ዘይት ወይም የተፈጥሮ ጋዝ የመሳሰለ የተፈጥሮ በረከት ስለሚኖራቸው ፣ አንዳንዶቹም ካላቸው ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ የተነሳ ፣ ለምሳሌ የሰሜን አፍሪካ ሀገራትን ብንወስድ ለአውሮፓ ካላቸው ቅርበት ፣ ለቱሪዝም ሰፊ እድል ያላቸው ሲሆኑ እንደ ቱኒዚያና ግብፅ ምጣኔ - ሀብታቸው የተመሰረተበት ዘርፍ ይኀው ቱሪዝም ነው ። 



ግብፅ ደግሞ የአባይ ወንዝ የሚጎበኛት ሲሆን በአንፃሩ ሊቢያ ፣ ቱኒዚያን የመሳሰሉ የሰሜን አፍሪካ ሀገራት በረሃማና በሰሀራ በረሀ ውስጥ የሚገኙ እንደመሆናቸው የውሀ ምንጭ የላቸውም (ምንም እንኳን የእንግሊዝ ሳይንቲስቶች በ2012 ባደረጉት ምርምር እንዳረጋገጡት በሰሀራ በረሀ ውስጥ መሬት ስር ግዙፍ የውሀ ሀብት እንዳለ አረጋግጠዋል ፣ አውጥቶ መጠቀሙ ግን ከፍተኛ ቴክኖሎጂን ይጠይቃል) ፣ ስለዚህ በግብርናው ዘርፍ የአባይ ወንዝ ከአመት እስካመት የሚፈስባትን የግብፅን ያህል እድል የላቸውም ። 

በአለም ላይ ያሉ ሀብታም ሀገራት እንደ አሜሪካ፣ ካናዳና አውስትራሊያ ያሉት ምንም እንኳን ከብዙዎቹ የአለማችን ሀገራት የበለጠ የተፈጥሮ ሀብት ያላቸው ቢሆን አብዛኛውን ኢኮኖሚያቸውን የሚያንቀሳቅሱት ከተፈጥሮ ሀብታቸው ሳይሆን ከኢንዱስትሪ ምርቶቻቸው ፣ በአገልግሎትናበግብርና ዘርፋቸው ነው ።

በሀገራችን ያሉ አንዳንድ ተለቅ ያለ የንግድ እንቅስቃሴን የሚያደርጉ ሰዎች እንደሚሉት የንግድ እንቅስቃሴው ሞቅ የሚለው የግብርና ምርቱ በሚሰበሰብበት የመኀር ወቅት ላይ ሲሆን ፣ ይህም ዋነኛው የሀገራችን ምጣኔ - ሀብት የተመሰረተበት ዘርፍ ሌሎች ዘርፎችም እሚነቃቁት ግብርና ምርት በሚሰበሰብበት የአዝመራ ወቅት መሆኑ በሌሎች ዘርፎች ላይ እንዲሁም ግብርናው ዘርፍ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ያለውን የመሪነት ድርሻ ያመለክታል ። 

አንዳንዶች የግብርና ኢምፔሪያሊዝም (Agro - Imperialism) ሌሎች ደግሞ የመሬት ሽሚያ (land grab) እያሉየሚጠሩት በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት እየታየ ያለ ክስተት ሲሆን በጣም ውድ የሆነውን መሬት በርካሽ ዋጋ ለብዙ አመታት ማከራየት በረጅም ጊዜ በሀገሮች ላይ አሉታዊ ተፅእኖን ሊያስከትል ይችላል ። በተለይም እነኚህ ሀገራት ፈጣን የህዝብ ብዛት እድገት ያላቸው ስለሆኑ የህዝብ ብዛታቸው እየጨመረ ሲሄድ ፣ የመሬት ፍላጎታቸው እያደገ ስለሚሄድ የራሳቸውን ህዝብ የመሬት ፍላጎት ለማሟላት ራሱ ሊከብዳቸው ይችላል ። ይህ ብቻ ሳይሆን የደኖች መጨፍጨፍና ለቱሪዝም ጠቀሜታ ያላቸው የእንሰሳት መኖሪያ ክልሎችና ፓርኮች ራሳቸው እንሰሳቱም አደጋ ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ ። ግዙፎቹ ኩባንያዎች ራሳቸው በዚህ ወቅት የአፍሪካን ለም መሬት መቀራመት የፈለጉበት ምክንያት ህዝብ እየበዛና ከተሞች እያደጉና እየሰፉ ሲሄዱ መሬት ለመኖሪያም ሆነ ለግብርና ተፈላጊነቱ እያደገ እንደሚሄድ በማስላት ነው ።

ከዚህም በተጨማሪ የአለም ህዝብ ብዛት እየጨመረና መሬት እየጠበበ ስለሚሄድ የመሬት ዋጋ እየጨመረ ነው የሚሄደው ። እነኚህ ሀገራት ግን በአነስተኛ ዋጋ ለብዙ አመታት ኮንትራት መሬቱን በመያዛቸውና ከግብርና ምርቶች ዋጋ መጨመር አንፃር በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ይሆናሉ ።በሌላ በኩል ደግሞ መንግስታት እድገት ለማፋጠንና ካላቸው ጉጉትና ፣ እነኚህን ሰፋፊ መሬቶች ለማልማት የሚያስፈልገው ገንዘብና ቴክኖሎጂ (Capital) በሀገራቱ ውስጥ ሊገኝ ባለመቻሉ እነኚህን መሬቶዎች ለውጪ ባለሀብቶች ለመስጠት ተገደዋል ።ይሁን እንጂ በደንብ የተጠናከረና በረጅም ጊዜ ጥቅምን የሚያስጠብቅ ድርድርን ማድረግ አስፈላጊ ነው ።

ጨርሶ የውጪ ባለሀብቶች በዘርፉ አይግቡ ባይባልም ፣ መንግስታት ጠንካራ ድርድር ማድረግ ሲጠበቅባቸው ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በግብርናው ዘርፍ እንዲሰማሩ ቅድሚያና ማበረታቻዎችን መስጠት ያስፈልጋል ። ከባለሀብቶቹ ጋር በሚደረግ ድርድርም ያመረቱት አብዛኛውን ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ ፣ እና የሀገር ውስጥ የምግብ ፍላጎት ከተሟላ ብቻ ወደ ውጪ መላክ እንደሚችሉ በቅድሚያ ድርድሮች ውስጥ ማካተት ያስፈልጋል ።

ሌላው ደግሞ አብሮ ተያይዞ እሚነሳ ነገር የሰፈራ ጉዳይ ነው ። ወደ ሌሎች ለም መሬት ወዳለባቸው ቦታዎችም ማስፈር አንድ አማራጭ ሆኖ ሊታሰብ ይችላል ። በተለይም በድርቅ በተደጋጋሚ የሚጠቁና ፣ ረሀብ በሚከሰትባቸው እንዲሁም የግብርናው ዘርፍ አስተማማኝ የገቢ ምንጭ ባልሆነባቸው አካባቢዎች ሰፈራ እንደ አንድ አማራጭ ሊታይ የሚችል ነው ፤ ሰፊ ለም መሬት ወዳለባቸው አካባቢዎች ። 

በሰሜናዊ ኢትዮጲያ በአብዛኛው መሬቱ ለብዙ ሺ ዘመናት ሲታረስ የኖረ እንደመሆኑ ሌሎች አማራጮች መታሰብ ሊኖርባቸው ያስፈልጋል ። በነገራችን ላይ የአክሱም ስልጣኔ ወደቆባቸው ሊሆን ይችላል ፣ወይም ለውድቀቱ ሰበብ ሊሆኑ ተብለው ከሚሰጡት መላ-ምቶች አንዱ የአካባቢ የአየር ለውጥ ማለትም ድርቅ ወይም የአካባቢ ምርት አለመስጠት ሊሆን ይችላል የሚለው አንዱ መላ-ምት ነው።

ኢንዱስትሪን ፣ ማእድንንበማስፋፋት አማራጭ የስራና የገቢ ምንጮችን መፍጠር አስፈላጊ ሲሆን ። በእስያ ሀገራት እንደተደረገው  (Labor Migration) በመባል በሚታወቀው በርካታ ቻይናውያን ኢንዱስትሪ ወደ ተስፋፋባቸው ጠረፋማ አካባቢዎች በመሄድ ገቢ የሚያስገኝላቸውን የስራና እድል ማግኘት የቻሉ ሲሆን ፣ በደቡባዊ አፍሪካ ሀገራትም የማእድን ሀብት ስላላቸው ወደ ማእድን ማውጫዎች ለበርካታ ሰዎች እንዲሁ አማራጭ የስራ እድሎችን እንዳስገኙ የሚታወቅ ነው ። 

ነዳጅና ጋዝ የመሳሰለው የተፈጥሮ ሀብት ያላቸው ሀገራት ፣ ብዙውን ግዜ በግብርና ላይ ከተመሰረቱ ሀገራት የተሻሉ ይመስላሉ ነገር ግን አላቂ በሆነ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ከተመሰረተ ኢኮኖሚ ይልቅ ስራን እሚጠይቅና ቀስ እያለ በሚያድግ የተሻለ የወደፊት እድል አለው ። ትናንሾቹን የመካከለኛው ምስራቅ «ገልፍ» ሀገራትን ብንወስድ ምንም እንኳን አሁን ባላቸው የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ኢኮኖሚያቸውን መገንባትና ከተሞቻቸውን ማድመቅ ቢችሉም ፣ ውለው አድረው ግን ምጣኔ - ሀብታቸውን በሌሎች ዘርፎች ላይ እንዲመሰረት ካላደረጉ በስተቀር ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት ሲጨርሱ ችግር ላይ የመውደቅ አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል ። በአንፃሩ የሀገራችን ተፈጥሮ ብንመለከት ተራራማ ፣ በቂ ዝናብ የሚያገኝ እና በርካታ ወንዞች ያሉትና መሬቱም ለም ነው ። 

ምንም እንኳን የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ምጣኔ - ሀብቱን የሚያንቀሳቅስ ሞተር ሊሆን ቢችልም ፣ ግብርና ብቻውን ዘለቀ ዘላቂና ፍትሀዊ እድገትን ሊያመጣ አይችልም፣ በተለይም የግብርና ምርትን ለማምረት አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች ማለትም ፣ ብድር ፣ ማዳበሪያ የመሳሰሉት ባልተሟሉበት ሁኔታ ።

ምንም አሁን በኢትዮጲያ ውስጥ የሀብት ክፍፍሉ ያን ያህል የሰፋ ባይሆንም ፣ ውሎ አድሮ ግን በአለም ላይ ሰፊ የሀብት መዛባት ከሚታይባቸው ሀገራት ልትሆን እንደምትችል ዛሬ ላይ ሆኖ መገመት ይቻላል ። ለዚህም ምክንያቱ ይኀው የመሬት ጉዳይ ሲሆን ብዙሀኑ ህዝብ በሀገሩ ዋነኛው የሀብት ምንጭ የሆነውን የመሬት ባለቤት አይደለም ። 

 
የምግብ ዋጋንም ብንወስድ በአለም ላይ ያለው የምግብ ዋጋ እየናረ መሄድ እድሎችንም ፣ ስጋቶችንም ይዞ መቷል ። ስጋቱ የህዝባችን ቁጥር እያደገ በመሄድ ላይ ስለሚገኝ የምግብ ዋጋ መወደድ በህዝቡ ኑሮ እንዲሁም በሀገሪቱ ውስጣዊ መረጋጋት ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅእኖ ሊኖረው ሲችል በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጲያ ሰፊ መሬትና ወንዞች ያላት ሀገር እንደመሆኗ በርካታ የግብርና ምርቶችን ለአለም ዋጋ ለማቅረብ ሲያስችል ፣ ለብዙ መቶ አመታት ኋላ ቀር ሆኖ የኖረው የግብርናው ዘርፍ እንዲያንሰራራና ወደ ዘመናዊነት እንዲሸጋገር እድልን በመክፈትየግብርናውን ዘርፍ አዋጪ አንዲሆን ያስችለዋል ።

No comments:

Post a Comment