በቁጣ የተነሳሳን ህዝብ በማረጋጋት የተጠመዱት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር
የህዝብን ቁጣ በማስተንፈስ (በአንገር ማኔጅመንት ) ስራ የተጠመዱት
ውስጥ ለዘመናት ፍትህን ያጣና ሲበደልና ሲበዘብዝ በኖረ ህዝብን ለማረጋጋት ወደ ስልጣን የመጡት አዲሱ ጠቅላይ ሚ/ር በአዋሳ ተገኝተው
ባደረጉት ንግግር ‹‹የዚህን ያህል ቂም የተያያዝን አልመሰለኝም ነበረ››
ሲሉ የተሰማቸውን እውነቱን ተናግረዋል ፡፡ ታምቆ የቆየውና ለአመታት በሰብአዊ መብትም ሆነ በዲሞክራሲና በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ዘርፍ ተገቢውን ምላሽና ግንዛቤን ያላገኘው
ህዝብ በውስጡ ጤናማ ያልሆነ ስሜት መታመቁን መረዳታቸው በራሱ ከእርሳቸው ቀደም ካሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ለየት ያደርጋቸዋል ፤ ይህም
የብዙዎቹን ተስፋ አጭሯል ፡፡ ጠቅ / ሚሩ በተለያየ ሃገራት ታስረውና ለአመታት ተረስተው የኖሩትን በማስፈታት በኩል ስራዎችን የሰሩ
ሲሆን በዚህ ዘርፍ ዜጎች ተረስተው እንደነበረ አመላካች ነው፡፡
የቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች አቶ ሃይለማርያምም ሆኑ አቶ መለስ
ዜናዊ ለህዝብ ጥያቄ ቅርበት አላሳዩም ማለት ይቻላል፡፡ ከላይ በሚሰጥ ትእዛዝ ሃገርን የማስተዳደርንና ጨርሶ የህዝብን ጥያቄን አለማዳመጥ
በሙስና ፤ በአቅም ማነስ የህዝብ ቅሬታ ይቀርብባቸው የነበሩትን አመራሮችን ከስፍራ ስፍራ መለዋወጥ እንጂ የተሻለ አቅም ያላቸውን
ሰዎችን አለመመደብ የህዝብ ጥያቄዎች መፍትሄን ሳያገኙ እየተገላበጡ በእንዲሄዱ ሰበብ ሆኗል ፡፡ ህዝቡ ፍላጎቱን በቅጡ የሚያዳምጠው
አካል በለሌለበት ሁኔታ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህንን የህዝብ ቁጣ ለማስተንፈስና ለማብረድ በተለያዩ የሃገሪቱ አካላት በመገኘት
ከህዝብ ጋር ቀጥተኛ ውይይትን ማድረጋቸው ይበል የሚያሰኝ ነው ፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ በንግግርና በውይይት ብቻ የሚፈታ ሳይሆን በቀጥታ
በፍጥነት ወደ ተግባር መግባትን የሚጠይቅ ሲሆን እንዲሁም ተደጋጋሚ የህዝብ ቅሬታ የቀረበባቸውን ባለስልጣናትን ከሃላፊነታቸው ማንሳትንና
በሙስና የማይጠረጠሩ ሃላፊዎችን መሾምን የሚጠይቅ
ጉዳይ ነው በዚህ ዘርፍ ዶ/ር አቢይ ግማሽ ነጥብን ብቻ ሊያገኙ ይችላሉ ለዚህም ምክንያቱ ጥቂቶቹን በጡረታ አሳርፌአለሁ ቢሉም ነገር
ግን በህዝብ ዘንድ የማይወደዱና በብዙ ሙስና የሚጠረጠሩት ሃላፊዎችን
መልሰው ቁልፍ በሆኑ ስፍራ መሾማቸው በእርሳቸው ላይ ጥርጣሬን የሚጋብዝ ነው ፤ በቅርቡ በሜቴክ ያደረጉት ሹመት ይህን ጥርጣሬ የሚጋብዝ
ነው ፤በአንጻሩ ደግሞ የፖሊስ አዛዦችን መለዋወጣቸውና መከላከያውን በሪፎርም ለማደስ ማሰባቸውን ግልፅ ማድረጋቸው ደግሞ ለለውጥ
የቆሙና የህዝብ ድጋፍን ለማግኘት የቆረጡ ሆነው እንዲታዩ አድርጓቸዋል፡፡
ሃገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንጻር የህዝብ አመኔታን ለማግኘት ጠቅላይ
ሚ/ሩ ከህዝብ ጥርጣሬ የጸዱ አመራሮችን
መሰየም የተገባው ቢሆንም ነገር ግን ምክንያቱ በማይታወቅ ሁኔታ የቀድሞዎቹን አመራሮችን ወደ ስልጣን መመለስ የፈለጉበት ምነክንያት
አይታወቅም ፤ ምናልባት የቀድሞቹን አመራሮቹን በመሾም ኢህአዴግ ውስጥ ያሉትን ለውጥ ፈላጊ ያልሆኑትን ሃይሎችን ለማስደሰት ‹አፒዝ›
ለማድረግ ብለው ከሆነና ለውጥ ፈላጊዎቹን ያስደሰቱትን ያህል ለውጥ የማይፈልጉትንም በማስደሰት መሃል ላይ ስፍራን ለመያዝ ታክቲክ
ይሁን ግልፅ አይደለም ፤ ነገር ግን ይህ የጠ/ሚሩ አሹዋሹዋም ነባር የኢህአዴግ አካላትን ሊያስደሰት ቢችልም ከህዝብ ፍላጎት አንጻር
ግን የህዝብን ፍላጎትን ማርካቱ አጠያያቂ ነው ፡፡ በዚህም የህዝብን አመኔታን ላለማጣትና ወዳልተረጋጋ ሁኔታ ላለመመለስ ጥንቃቄን
ማድረግ ያስፈልጋል ፡፡
ይህ የአሁኑ ጠ/ ሚር የዶ/ር አቢይ አህመድ ሹመት አሰጣጥ የአሜሪካን
ፕሬዝደንት የነበረውን አብረሃም ሊንከንን ያስታውሰናል፤ ሊንከን ፕሬዝዳንት የነበረበት ዘመን በአንድ በኩል የባርያ ስርአትን መቀጠል
በሚፈልጉና በሌላ በኩል ደግሞ የባርያ ስርአቱ እንዲያበቃ በሚፈልጉ ሁለት ተቃራኒ ሃይሎች ዙሪያውን ተከቦ የነበረ ሲሆን ሊንከን
ሁለቱንም ለማስደሰት ተቃራኒ የሚመስሉ ውሳኔዎችን ይወስን ነበረ ፤ በዚህ በአጭር ግዜ ለውጥ ፈላጊ ያልሆኑትን ሃይሎችን ድጋፍን
እንዲያገኝ አስችሎታል፤ ነገር ግን ዋና አላማው የባርያውን ስርአት መለወጥ የነበረ ሲሆን ይህን በማድረጉ ለውጥ ፈላጊ ያልነበሩትን
ሃይሎችን ፍላጎት በመጠበቁ ከእነርሱ ሊመጣበት ይችል የነበረንን ለውጥን እምቢታንና ጠንካራ ተቃውሞን ማስቀረትና የማይቀረውን ለውጥ ማምጣት ችሏል ተብሎ ይታመናል ፤ አንድ ለውጥን እንዲያመጣ የተሰየመ
ከፍተኛ ስልጣን ላይ ያለ ሰው ለውጥ እምቢ ባዮችንም ሆነ ለውጥ ፈላጊዎችን በአጭር ግዜ ውስጥ ሊያስደስት የሚችል ፖሊሲን መከተል
ሲኖርበት በረጅም ግዜ ግን ለቆመለት ለውጥ ታማኝ በመሆን የህዝብን የለውጥን ፍላጎትን መመለስ ይኖርበታል ፡፡
ራሳቸውን በለውጥ ፈላጊዎችና በለውጥ ተቃዋሚዎች መሃከል ያገኙት
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለህዝቡ ታማኝ ይሆናሉ ወይንስ የህዝብን ድጋፍ ላጣውና ስልጣናቸው ከእጃቸው እያፈተለከ ላሉት የፓርቲያቸው
ነባር ስልጣን ጠባቂዎች ‹‹ኦልድ ጋርድ›› (old guard) አባላት ታማኝ ይሆናሉ የሚለው
ነው ጥያቄው፡፡ የኢትዮጲያ ህዝብ በተደጋጋሚ ለውጥን እናመጣለን በሚሉ መሪዎች የተታለለና ብዙ የችግርንና ውጣ ውረድን በማየት ችግርን
ያየ ባስ ሲልም የተዘረፈና የተጨፈጨፈ የተካደ ህዝብ ስለሆነ በቀላሉ መሪዎችን የማመን ዝንባሌን አያሳይም፤ ይህንን የህዝቡን ስነ
ልቦና መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትራንስፎርሜሽናል ለውጥ የተማሩ ስለሆነ ለውጥን ለማካሄድ ያሉትን ተፈጥሯዊ ፈተናዎችን
የሚረዷቸው ይመስለኛል ፡፡
በማንኛውም ለውጥ ሊደረግበት በሚገባ ተቋም ውስጥ ሶስት አይነት
አሰላፎች አሉ፤ አንደኛው ቡድን ከነባራዊው (Status Quo) ሁኔታ ‹‹ስታተስ ኩ››
ተጠቃሚ ሆኖ የኖረና ለውጥ እንዲደረግ የማይፈልግ ቡድን ሲሆን ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ከውጭ ወይም ከውስጥ ያለ ሆኖ ነገር ግን ባለው
ነባራዊ ሁኔታ ያልተጠቀመና ለውጥ በቶሎ እንዲመጣለት የሚፈልገው ቡድን ሲሆን ይህም ብዙሃኑን ህዝብና ወጣቱን ይወክላል ፤ ሶስተኛው
ቡድን ደግሞ የለውጥን አስፈላጊነትን በሚገባ የሚረዳ ነገር ግን ለውጥ ይዞት በሚመጣው ጓዝና መዘዝን የሚፈራ አካል ነው ፤ የለውጥ
እምቢ ባይነት ‹‹ሪዚስታንስ ቱ ቼንጅ› (Resistance to Change) ሊመጣ ከሚችልባቸው አቅጣጫዎች አንዱ ይሄ ነው ፡፡ ለውጥን ለመተግበር ተቋማት
የውጭ አማካሪን እስከመቅጠር ድረስ የሚሄዱበት ግዜ አለ ፤ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ግን ውክልና ባላቸው በራሱ አመራሮች ካልሆነ በስተቀረ
የለውጥን ፍላጎት እሚመልስበት እድል የለውም ፤ስለዚህ አመራሩ ራሱ ወቅታዊውን ሁኔታ በመረዳት የለውጡ አካልና ተባባሪ በመሆን ሃገርን
ወደሚቀጥለው እርከን የማሻገር ስራን መስራት አለበት፡፡
ጉዳዩ የዘገየና ለውጥ ቀደም ብሎ መምጣት የነበረበት ቢሆንም
የዚህን አሳሳቢነት በመረዳት ‹‹ጊዜ የለንም በሚል ስሜት
›› መንግስት ስራውን መስራት እንዳለበት ማሳሰባቸው መልካም ሲሆን ከሁኔታዎች ጫፍ መድረስ አንጻር ሲታይ ግን ወደ ለውጥ መሄድና
ፈጠን ባለ ሁኔታ ችግሮችን በመፍታት ለመጪው ሃገራዊ ምርጫ አስፈላጊ
የሆኑትን የመወዳደርያ ሜዳን ከወዲሁ ማዘጋጀት ይገባል፤ ከችግሩ ጥልቅ ከመሆን አንጻር ኢህአዴግ ብቻውን የሚወጣው አይደለም፡፡
የዲሞክራሲ ስርአትን ኮትኩቶ አለማሳደግ ይባስ ብሎም በእኔ አውቅልሃለሁ
ልማታዊ መንግስትነት ሰበብ ዲሞክራሲን ሆነ ብሎ ማቀጨጭ ፤ ሃገርን እያስከፈለ ያለው ዋጋ በዚህ ወሳኝ ወቅት በግልፅ የታየ ሲሆን
የዲሞክራሲ ስርአትን ማስፈን ጉዳይ ለዚህች አገር ወሳኝ ቢሆንም ነገር ግን በገዢው ፓርቲ በኩል መጀመሪያ አካባቢ የመልካም አስተዳደር
ችግር ነው ፤ ቀጥሎም የመልካም አስተዳደር ችግር ነው በሚል ተደጋጋሚ ምላሽን ቢሰጥም ነገር ግን ችግሩ ግን ከዲሞክራሲ ጥያቄም
በላይ የሰብአዊ መብት ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል ፡፡ ገዢው ፓርቲ እነኚህን ህዝባዊ ጥያቄዎች ፈጠን ብሎ ምላሽ መስጠት የነበረበት ቢሆንም
ምንም አይመጣም በሚል ዝም ብሎ መተኛትን መርጧል ፡፡ ይህም ገዢውን ፓርቲንና ሃገሪቱን በዋጋ የማይተመን ዋጋን አስከፍሏል ፤ እያስከፈለም
ይገኛል ፡፡ ይህም በሃገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ትፅእኖን ሲጋብዝ ፤ ለመቶ ሺሆች መፈናቀልን ፤ ለሰብአዊ መብት ጥሰትንና
ለከባድ አለመረጋጋት ውስጥ አገሪቱን ሊከታት በቅቷል፡፡
የችግሩን ምንጭ በምንመረምርበት ወቅት የምናገኘው ነገር ከጥቂት
አመታት በፊት የምርጫ ውድድር ሰሞን ለችግሩ ከገዢው ፓርቲ ይሰጥ የነበረው ምላሽ የአፈጻጸም ችግር ነው የሚል ነው ፤ ፖሊሲዎቻችን
ፍፁም ትክክል ናቸው ነገር ግን አፈጻጸም ላይ ነው ችግር ያለው የሚለው መልስ ለጊዜው ምላሽ ቢሆንም ነገር ግን ከውስጥ ያለውን
የባሰውን ችግር ግን መሸፈኛ ሆኖ ለጊዜው አገልግሏል ፤ የአፈጻጸም ችግር ከምንድነው የሚመጣው ለሚለው ጥያቄ አንዱ በቃት ያላቸው
አመራሮች በስፍራው አለመመደብ ፤ አመራሮቹን ተጠያቂ የሚያደርግ አሰራር አለመኖርና የፖለቲካ ታማኝነትን ብቻ እንደ ብቃት መስፈርት
በመውሰድ የሙስና ችግሮች ስር መስደድ ሲጀምሩ አይቶ እንዳላየ መታለፋቸው መመለሻ ለሌለው የሙስና ደረጃ ላይ ሃገሪቱን አድርሷል
፡፡ ከዚህም ዋነኛው ትክክለኛ ዲሞክራሲ ቢኖርና በዲሞክራሲ መንገድ ህዝብ መሪዎቹን የመምረጥ እድል ቢሰጠው ግን በሙስና የተዘፈቁትን
ትቶ የተሻለ አቅም ያላቸውንና በሙስና ያልተነካኩት ይመረጡ ነበረ ፤ በየትም ሃገር መሪዎች እንደ ሰው በሚያጠፉበት ወቅት ጠንካራ
ዲሞክራሰ ሲ ያለው ሃር ከሆነ መሪው በህዝብ ድምፅ ከስልጣኑ ይነሳና በሌላ ይተካል ፤ ይሄ ነው ምእራቡ ዓለም አሁን ለደረሰበት
ትልቅ ደረጃ የደረሰው በኢኮኖሚም በፖለቲካም ፡፡
ይሁንና ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ከ97 ዓ.ም ወዲህ ያለፉትን
ሁለት ምርጫዎችን የተቃዋሚዎችን ድምፅ በፓርላማ አልስማ ያለ በሚመስል ሁኔታ በሃገራዊ ምርጫ ወቅት 96 እና ከዛም በላይ በመቶ
ድምፅ አግኝቻለሁ ማለቱና ምንም የተለየ ድምጽን በሚዲያም ሆነ በመንግስት ውስጥ ላለመስማት ዝግ ማድረጉ ገዢውን ፓርቲ በዋጋ የማይተመን
ኪሳራን አስከፍሏል፡፡ ነገር ግን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ግረን መከላከያ አዛዦችን ሰብስበው እንደተናገሩት ‹‹ኢህአዴግ ፖለቲካዊ ስራውን መስራት አቅቶት በራሱ ስንፍና
የወደቀ እንደሆነ የመከላከያ ሠራዊቱ ሕዝብ ከመረጠው ፓርቲ ጋር መቀጠል የሚችል ሠራዊት መሆን አለበት››
ሲሉ በግልፅ ማስቀመጣቸው መልካም ነው፡፡ይህ አባባላቸው ፓርቲው የህዝብን ድጋፍ ማግኘት ባይችል መከላከያው የወደቀ ፓርቲን ለማዳን
መስዋእትነትን መክፈል የለበትም ህዝብ ለመረጠው ፓርቲ ድጋፉን መስጠት አለበት ሲሉ በተዘዋዋሪ ማስረዳታቸው ለዲሞክራሲ መሰረት መልካም
ጅምር ሲሆን መከላከያው እንደ ተቋም ህልውናውን ለማስቀጠል የፓርቲ ወገንተኛ አለመሆን መሰረታዊ ጉዳይ ነው ፡፡
ዲሞክራሲ በሚሰፍንበት ወቅትም የሰብአዊ መብት ጥያቄዎችም በተሻለ
ምላሽን ያገኛሉ ፤ ለሰብአዊ መብት ጥሰት ዋነኛው ምክንያት የዲሞክራሲ አለመኖር ነው፤ ዲሞክራሲ ቢኖር ዜጎች ትክክለኛውን ፍትህ
ስለሚያገኙ የሰብአዊ መብታቸውና ክብራቸው አይደፈርም፡፡ የህግ የበላይነት በሰፈነባቸው ሃገራት የማንም ዜጋ መብትን ለመድፈር የሚነሳ
የለም ፤ ስለዚህ ከሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በምንመለከትበት ወቅት የዲሞክራሲ መስፈን ሊቀድም ይገባዋል ፤ አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትርን
ዶ/ር አቢይን የመረጣቸው ፓርቲያቸው ነው እንጂ ህዝቡ ወጥቶ አይደለም፤ እስካሁን ድረስ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ህዝቡ መሪዎቹን መርጦ
አያውቅም ማለት ይቻላል ፤ አዲሱ ጠቅላይ ይህን እድል ሃገሪቱን ወደ ዲሞክራሲ ስርአት ለማሸጋገርና የዲሞክራሲ አባት ለመባል ትልቅ
እድል ከእጃቸው ይገኛል ፡፡
አሁንም ቢሆን ገዢው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች መጪው ምርጫ ሌሎቹም
በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሳትፈውበት በህዝብ ይሁንታ ብቻ ወደ ስልጣን የሚመጣበትን የፖለቲካ ስርአትን ከመመስረት ውጪ ሌላ አማራጭ
የላቸውም ፤ በረጅም ግዜ ሃገሪቱን ሊያረጋጋና ቀጣይ የህዝብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን መፍጠርና ለወጣቶች የስራ እድልን በመፍጠር የተረጋጋ
ሃገርን ለትውልድ የሚተላለፍ ዲሞክራሲያዊ የሆነና የህዝብ ድምፅ የሚሰማበት ስርአተ መንግስትን መገንባት ያሻል፡፡
2 Attachments