Thursday, February 28, 2013

የምጣኔ - ሀብት እድገት አንድምታ



በአሁኑ ጊዜ ከአለም ኢኮኖሚ ጋር ያለን ትስስር እያደገ መጥቷል ። ለምሳሌ ቀድሞ ቢሆን ቡና ላኪዎች ብንሆንም በገበያው ላይ ግን ዋና ወሳኞች አልነበርንም -  አሁንም አይደንም -ይሁን እንጂ የአለም ኢኮኖሚ መቀዝቀዝና የሌሎች አቅራቢዎች መኖር አቅርቦት መጨመርና አለመጨመር ግን ልናገኝ የምንችለውን ገቢ ላይ ተፅእኖን በጎም ይሁን አሉታዊ ይፈጥራል። ነዳጅን ብንወስድ ቀድሞ ብዙ መኪኖችም ፣ ፋብሪካዎች በሀገሪቱ ውስጥ አልነበሩም ፣ በአለም ላይም እንደ አሁኑ አይነት የነዳጅ ጥማት አልተፈጠረም ። በአሁኑ ወቅት ግን የነዳጅ ዋጋ በአንድ ዶላር ቢጨመር ወይም ቢቀንስ በሀገራችንየኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ የራሱ አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ተፅእኖ ይኖረዋል ። በአለም ላይ በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ ያለው የካፒታል ፍሰት (Captal Flow) እና የንግድና የምጣኔ - ሀብት ትስስር ስለጨመረ በየትም የአለም ክፍል የሚፈጠር ችግር ወደ ሌላውም የመትረፍ እድሉ ሰፊ ነው ።
ይህም በርካታ ከአለም አቀፍ ደረጃ የቀረበው ፣ ምንም እንኳን ሰፊ የሆነ ትስስር ገና ባይኖረንም ትስስራችን ግን እየጨመረ እንደሚሄድ ከአሁኑ መገመት ይቻላል ። በአለም ላይ የሚፈጠር የምጣኔ - ሀብት ቀውስም ሆነ ችግር ለሌላው አለም የመትረፍ ሰፊ እንዳለው የታየ ጉዳይ ነው ፣ ለዚህም በአለም ላይ ያለው የነዳጅ ፣ የማዳበሪያ ፣ የብረታ ብረት ዋጋዎች ሲጨምሩ በእኛም ላይ ጭማሪዎች መንፀባረቃቸው አልቀረም ።
 ለዚህም ምክንያቱ የራሳችን ምጣኔ - ሀብት እያደገ በሄደ ቁጥርና ይበልጥ ገበያ መር እየሆነ ሲሄድ በአለምም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የምጣኔ - ሀብት ትይይዝ ሲጨምር ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በአለም ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተፅእኖው እያየለ የመጣው የአለም - አቀፍ ምጣኔ ሀብት ትስስር (Globalisation) በምጣኔ - ሀብትና በሌሎችም ዘርፎች በስፋት እየታየ ያለ ጉዳይ ነው ።  የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሀገራችን በብዛት እየገቡ ሲሄዱ ፣ ወደ ውጪ ሀገራት በርካታ ሸቀጦችንና ምርቶችን መላክ ስንጀምር ከውጪም እንደዘዛው ስናስገባ ፣በዚህ በዚህ ሁሉ ምክንያቶችከእኛ ውጪ ያለውን ነገር መረዳትና እድልም ከሆነ መጠቀም ፣ አደጋን ይዞ የመጣ ከሆነም ለዛ መዘጋጀትና ሊመጡ ከሚችሉ ጉዳቶች ራስን መጠበቅ ይረዳል።
ይህም ትስስር ወደ ፊት ከዚህ ይበልጥ እየተጠናከረ እንጂ እየቀነሰ እንደማይሄድ ግልፅ ነው ። ከዚህም ሌላ ደግሞ የውጪ ኩባንያዎች በሀገራችን መንቀሳቀስ በሚጀምሩበት ወቅት ትስስሩይበልጥ እየጠበቀ ይሄዳል ። አይነተኛ ምሳሌዎቹ የውጪ ባንኮች በሀገራችን መንቀሳቀስ ቢጀምሩ ያገራችንን ምጣኔ ሀብት ከአለም አቀፉ የገንዘብ ስርአት ጋር ትስስርን ሲፈጥር የራሱ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ጎኖች አሉት ። በእነኚህ ምክንያቶች ስለአለም ምጣኔ  - ሀብት አንዳንድ ነገሮችን መረዳት ሊያስፈልግ ይችላል ።ኢትዮጲያ የአለም የንግድ ድርጅት አባል በምትሆንበት ወቅት የተወሰነ የመንደርደሪያ ጊዜ ቢኖርም ከተወሰኑ አመታት በኋላ ግን ዝግ የነበሩትን ዘርፎችን ክፍት ማድረግ አይቀሬ ነው ።  ይሄም በማደግ ላይ ያሉትን አገሮች ብቻ ሳይሆን ያደጉትንና ለብዙ መቶ አመታት የዳበረ የካፒታሊዝም ስርአት ያላቸውን ሀገራት ሁሉ ሲፈታተን ማየት እየተለመደ መቷል ።
ከአውሮፓ ሀብታም ሀገራት ሳይቀር በአለም ሁለተኛዋ የወጪ ንግድን የምትልከው ጀርመንን ብንወስድ በምትልካቸው የኢንዱስትሪ ምርቶች በምታገኘው ገንዘብ ነው የምትመገበውን ምግብ እምትገዛው እንጂ የፍጆታዋን ምግብ ሁሉ ራሷ አታመርትም ። በተመሳሳይም እንግሊዝም በባንክ ፣ እና በፋይናንስ ፣ በኢንዱስትሪዎቿ በመሳሰሉት አገልግሎት ዘርፎች በምታገኘው ገንዘብ አብዛኛውን የምግብ ሰብሏን ከውጪ የምታስገባ ሀገር ነች።ሌሎች ሀብታም የሆኑ ነገር ግን በቂ ለግብርና ተስማሚ የሆነ መሬት የሌላቸው ፣ ሀገራትም እንዲሁ የምግብ ሰብላቸውን ከውጪ የሚያስገቡ ናቸው ፣ ለምሳሌም በነዳጅ ዘይት የከበሩትን የአረብ ሀገራትን ብንወስድ በዚህ አይነት መንገድ ከውጪ የምግብና የግብርና ሰብሎችን እሚያስገቡ ናቸው ። አንዳንዶቹም በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ሰፋፊ መሬትን በመኮናተር ወደ ግብርና ስራ ራሳቸው እየገቡ ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ የግብርና ዘርፋቸውን በከፍተኛ ደረጃ የሚደጉሙ ናቸው ፣ ለምሳሌ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ የሚጠቀሱ ሲሆን እነኚህ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገራት መሬታቸው ጠባብ ከመሆኑ ውጪ የግብርና ምርት በሀገራቸው ቢቀርብ የሀገራቸው ገበሬዎች ከገበያውጪ ስለሚሆኑ የግብርና ዘርፋቸውን ይደጉማሉ ።

ይሄም ከአለም ጋር የሚኖረን የምጣኔ ሀብት ትስስር የፈጠረው ሲሆን እነኚህም የሀገራችንን ኢኮኖሚ ለመረዳት የአለም ምጣኔ - ሀብትን በመረዳት እንደሚጀምር የሚያሳይ ነው ። ከቀድሞው በተሻለ ሁኔታ የአገራችን ምጣኔ - ሀብት ከተቀረው አለም ጋር ትስስርን እየፈጠረ ስለመጣ በምግብና በነዳጅ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የፋብሪካ ውጤቶችና ጥሬ እቃዎችም ጭምር በአለም ዋጋ እሚወሰኑ ሆነዋል ።

በመርህ ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ጠቀሜታ



ይህ ብቻ ሳይሆን በውጪዎቹ አስተሳሰብ ፣ ባህል ፣ ፍልስፍና አወቅነውም አላወቅነውም ተፅእኖ ያሳድርብናል ። አሁን ባለው ቴክኖሎጂና የመገናኛ ዘዴዎች አማካይነት ፣ በውጪው አለም ላይ ላለው አስተሳሰብ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተጋላጭ መሆናችንን መዘንጋት የለብንም።
በነገራችን ላይ አንድ ነገርን ለመፍጠር ምንም እንኳን ያ ነገር ሲጀመር ማህበረሰቡን አስተሳሰብ እሚፃረር ወይንም እሚጎዳ ሁሉ ሆኖ ሊታይ ይችላል ። እሚጎዳ ሁሉ ሆኖ ሊታይ ይችላል ። ይሁን እንጂ ውሎ አድሮ ግን አንድ ነገር በጎ የሆነ ነገር በረጅም ጊዜ ብዙሀኑን ማህበረሰብ እሚጠቅም ነገር ሊገኝበት ይችላል ። ያ ነገር ለማህበረሰብ ምንም ጥቅምን እማያስገኝ ፣ ወይም ጎጂ መሆኑ እየተረጋገጠ ከመጣ ግን ውሎ አድሮ ራሱ መክሰሙ አይቀርም ።
በኛ ሀገር በመርህ ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ (Objective Thinking) ብዙም የዳበረ ወይም የተለመደ አይደለም ። ነገር ግን የትኛውም ሀሳብ የራሱ ጥቅምም ሆነ ጉዳት ሲኖረው ፣ በአንድ በኩል ብቻ ያለውን ተመልክተን በአንደኛው በኩል ያለውን ብናልፈው ውጤቱ ጉዳት ነው እሚሆነው ፣ለምሳሌ ጥቅሙን ብቻ ተመልክተን ጉዳቱን ብናልፈው ተጎጂ ሲያደርገን በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳት ብቻ ነው ያለው ብለን ብንደመድም ደግሞ ልናገኝ የምንችለውን ጥቅም እናጣለን ። በዚህ በኩል ግን ምእራባውያንን ብንወስድ ሰፊ ልምድ ያላቸው ሲሆን አስተሳሰባቸውም በአመክንዮ (Logic) ላይ የተመሰረተ ነው ። ይህ ብቻ ሳይሆን የሀሳብን ጥቅምም ሆነ ጉዳት ተገንዝበዋል ማለት ይቻላል ።
አንደ ነገር ሁሉም ሰው ትክክል ነው ስላለው ትክክል አይሆንም፣ በአንፃሩም ስህተትም ነው ስላለው ስህተትም አይሆንም ። አንድ ነገር ትክክለኝነቱም ሆነ ስህተት መሆኑ በሰዎች ስምምነት እሚሆን ነገር አይደለም ።አንድ ነገር ብዙ ሰዎች ስለተስማሙበት ትክክል አያደርገውም ።እንደውም በአንድ ነገር ብዙ ሰዎች መጀመሪያ እሚስማሙበት ያ ነገር የሆነ ውጤትን ይሰጣል በሚል ሲሆን ፣ ያ ነገር እንደማይሰራ ከተገነዘቡ ግን ለመተው ወይም ለመቀየርም እንደዛው የተጋለጠ ነው ። 
በዚህ ምክንያት ትክክል ወይም አግባብ ያልሆኑ ነገሮች እንደ ትክክለኛ ነገር ተወስደው ስራ ላይ በሚውሉበት ወቅት እሚያስከትሉት ጉዳት ከሚያስገኙት ጥቅም ይበልጣል ። ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳቱ እንደሚበልጥ በምርምርና በሙከራ የተረጋገጠን ነገር እንደ ትክክለኛ ነገር ተደርጎ ቢሰራበት ጉዳቱ ያመዝናል ።
አንድ ነገር ብዙ ሰዎች ስለተስማሙባቸው ትክክል ወይም ብዙ ሰዎች ስላልተስማሙባቸው ደግሞ ስህተት እሚሆኑ ቢሆን ኖሮ በአለም ላይ ብዙ ነገሮች በጣም ቀላል በሆኑ ነበረ ። ምእራባውያን ራሳቸው በርካታ ስህተቶችን የሰሩ ቢሆንም እንደገና እያረሙ በመሄድ የተሻለ የእድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ በቅተዋል ።በዚህ መፅሀፍ ውስጥ ያሉት ብዙዎቹ ሀሳቦች ተግባራዊ ከሆነ አተያይ በመነሳት የተገለፁ ሲሆኑ ንድፈ - ሀሳባዊ መሰረቶችም አልፎ አልፎ ተገልጿዋል ። ይሁን እንጂ አንድ ንድፈ - ሀሳብ ወደ ተግባር ሲቀየር እንደሚገልፀው ሰው አስተሳሰብና ሊገልፀው እንደሚፈልገው ነገር ይለያያል ፣ ተግባራዊ የሆኑ አገላለፆች ሁሉንም ሰዎች እማያስማሙ ሊሆኑ ይችላሉ ።
አንድ ነገር ትክክለኛ ወይም ጥቅም ያለው መሆኑ የሚታወቀው በረጅም ጊዜ በሚሰጠው ጥቅም አንፃር ሲሆን ። ሌላ የአንድን ነገር ጥቅም መለያ መንገድ የሌለ ሲሆን ጊዜን አልፎ ጥቅምን መስጠት የሚችል ነገር ጥቅም አለው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል ። ነገር ግን ጊዜን ወይም የጊዜን ፈተና ማለፍ የማይችል ከሆነና ከተወሰነ ጊዜ በላይ ሳያልፍ ዘላቂ የሆነ ጥቅም የሌለው ነገር ተመራጭ አይደለም ። ከዛ ይልቅ የረጅም ጊዜ ጥቅም ወይም ግልጋሎትን እሚሰጥ ነገር የተሻለ ነው ።
በአገራችን አንድ ትክክል ያልሆነን ነገር ትክክል እንደሆነ፣ተገቢ ያልሆነን ነገር ተገቢ እንደሆነ አድርጎ ተቀብሎ የመኖር ልማድ አለ ። ይህም አንድምታው ቀላል የማይሆን ሲሆን ፣ ትክክል ያልሆነን ነገር መያዝ ተከትሎ የሚመጣውም ነገር ትክክል ያልሆነ ነገርን ማድረግን ያስከትላል ። ይሄም ብዙ ችግራችን መፍትሄ ሳያገኝ ለረጅም ጊዜ እንዲቆይና  ባልተቋረጠ መከራና ችግር ለመኖራችን አንዱ ምክንያት ነው ።
በአሁኑ ጊዜ በሀገራችንም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ችግሮች በጣም ውስብስብ ከመሆናቸው የተነሳ ፣ መፍትሄአቸውን ለማምጣት ብዙ ማሰብን ይጠይቃሉ ፤ይሁን እንጂ በቀላሉ በሀይል ወይንም ግብታዊ እርምጃን በመውሰድ እሚፈቱ ወይም በአንድ ጀንበር በነው እሚጠፉ አይደሉም ። ይህ ብቻ ብዙ ጊዜ አንድ ለውጥን ለማምጣትየሚደረግ እንቅስቃሴ ከሀዲዱ ወቶ አቅጣጫውን ስቶ ፣ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የመሄድ አዝማሚያዎች ታይተዋል ። ትልቅ ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩ ፤ ነገር ግን ከመስመራቸው የሳቱ ሆነው የታሰበላቸውን ውጤት ሳይሰጡ የውሀ ሽታ ፣ ደብዛ ሆነው ቀርተዋል  ። 


አንድ ሀሳብ ቀርቦ ዛሬ ላይ ስናስበው ወደ ተግባር እማይቀየር ወይም እማይጠቅም ቢመስለንም ውሎ አድሮ ግን አንድ ፍሬ እሚገኝበት ሊሆን ይችላል ። ሀሳብ አደገኛም ወይም ጥቅም ያለውም ሊሆን ይችላል ።ምንም እንኳን ለጊዜው ያ ሀሳብ ከባድ ተቃውሞ ሊያጋጥመው ቢችልም ውሎ አድሮ ግን ለማህበረሰብ እሚጠቅም ከሆነ ወዲያውም ባይሆን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ስራ ላይ ሊውል ይችላል ። ልዩነቶች እንዲኖሩ እሚፈለግበት ምክንያትም ይኀው ሲሆን ፣ ያ ሀሳብ እሚጠቅምበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል ።
ተፈጥሯዊ ያልሆነ ነገር ተፈጥሯዊ እንደሆነ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ። ብዙ ነገሮች ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ካልተጀመሩ ሚዛናዊ አለመሆናቸው ሊቀጥል ይችላል ። ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው የአየር በንብረት ለውጥ ሲሆን ሚዛናዊ ባልሆነ መሰረት ላይ መመስረቱ ነው ።


በምጣኔ - ሀብት ሙያ ላይ የሚቀርቡ ትችቶች



የምጣኔ-ሀብት የትምህርት ዘርፍ ከተግባር የራቁ ናቸው ተብለው ከሚተቹ የሙያ ዘርፎች አንዱ ነው ። ለምሳሌ ፍልስፍናን ብንወስድ ይህ ዘርፍ ከተግባር የራቀ ነው በሚል በርካታ ቀልዶች ተቀልደውበታል። ምጣኔ ሀብትም እንዲሁ በርካታ ቀልዶች የተቀለዱበት ዘርፍ ለመሆን የበቃው ይሄው ከተግባር መራቁ ነው ። ንድፈ - ሀሳብና ተግባር በተወሰነ ደረጃ መሆን አለበት ። ንድፈ - ሀሳብ ብቻ ከሆነ ከተግባር እየራቀ ይሄዳል ፣ በአንፃሩ ተግባር ብቻ ከሆነ ደግሞ አይለወጤ ከሆኑት ንድፈ - ሀሳባዊ ህግጋት እየራቀና ከእውነታው ወጪ የመሄድ አደጋ ይገጥመዋል ። ስለዚህ ንድፈ - ሀሳብንና ተግባርን አጣጥሞ መጓዝ አስፈላጊ ነው ። ብዙ ጊዜ የምጣኔ - ሀብት የትምህርት ዘርፍ ከሚተችባቸው ነገሮች መሀከል  የሚያነሳቸው እንዲሁም የሚጠቁማቸው መፍትሄዎች በጣም ንድፈ - ሀሳባዊ ናቸው ፣ ከገሀዱ - አለም የራቁ ቅድመ - እሳቤዎች (Assumptions) ይበዙበታል ፣  በተግባር ከሚታየው እውነታ የራቁ ናቸው የሚል ነው ። 

ነገር ግን በምጣኔ - ሀብት ውስጥ ሁሉም የምጣኔ - ሀብቱ ተዋናዮች ምክንያታዊ(Rational) ሆነው ስለሚወስኑ ምጣኔ - ሀብቱ ትክክለኛ እኩልዮሹን (Equlibrium) ይይዛል የሚል ነው ።  በእውነተኛው አለም ውስብስብነትና አስቸጋሪነት አንፃር አለምን ለመረዳት ፣ እነኚህ እሳቤዎች አስፈላጊ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ብናነሳ በእውነተኛው አለም የሌሉ እሚመስሉትን፣ ፍፁም ውድድር የተሞላበት የገበያ ስርአት በእውነተኛው አለም የሌለ ሲሆን ፣ ፍፁም ሁሉንም እሚያውቅ ፍፁም ምክንያታዊ የሆነ ተጠቃሚ ወይም ገዢ (Rational Consumer) በቂ መረጃ ካለመኖር የተነሳ በእውነተኛው አለም የሌለ ሲሆን ፣ አለመኖርም ብቻ ሳይሆን ምክንያታዊ ነው ብለን ብንነሳ ምክንያታዊነቱ ከማን አንፃር ነው ? ከራሱ አንፃር ነው ወይንስ ከሌሎች ጥቅም አንፃር ነው ? ፣ ውሳኔው ትክክለኛ መስሎት ነገር ግን ራሱን የሚያከስር ሊሆን እንደሚችል ፣ ወይንም ደግሞ ውሳኔው ለራሱ ሊያተርፈው የሚችል ነገር ግን ሌሎችን የሚያከስር ከሆነ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑ ከየትኛው አቅጣጫ እንደሚታይ ሊያወዛግብ ይችላል ። አንድ ሰው ፍፁም በምክንያት የሚመራ «Rational» ነው ማለት ያ ሰው በምንም አይነት ስሜት አይመራም ማለት ነው ፣ ሌላው ደግሞ የስነ - ምግባር ጥያቄም ይነሳል ፣ ግለሰብ በምጣኔ - ሀብቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን ትተን ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪዎች በተለይ እያወቁ ውሳኔያቸውን በትክክለኛ ስነ - ምግባር ፣ ህግና ደንብ ላይ ተመስርተው መወሰናቸው ራሱም ከጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችላል ።
በትምህርቱ ዘርፍ ውስጥ ንድፈ - ሀሳባዊ ብቻ ሆነው የሚቀሩ ነገሮች ሲኖሩ ሌሎች  ደግሞ ወደ ተግባር ሊቀየሩ የሚችሉ ነገሮች አሉ ። ተግባርን ለመተንተን የገቡ ነገር ግን በተግባር ላይ እንደማይወሉ የታወቁ ጉዳዮችም እንዳሉ ሳንረሳ ማለት ነው ።  
ሌላው ደግሞ የዘመናችን ምጣኔ - ሀብት ሳይንስ ማህበራዊ ሳይንስ ከመሆን ይልቅ የተፈጥሮ  ሳይንስ ሆኗል የሚል ሲሆን በርካታ ጥናቶች በቁጥር ላይ ብቻ ተመስርተው መሰራታቸው ከትክክለኛው ነባራዊ እውነታ ውጪ ወደሚያመሩ ድምዳሜዎች ሲያመራም በተደጋጋሚ ተስተውሏል ።ይህም ምጣኔ - ሀብት የትምህርት ዘርፍ የማህበራዊ ሳይንስ አንዱ ቅርንጫፍ እንደመሆኑ እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ ወይንም እንደ ፊዚክስ ቁጥሮች ብቻ እሚገልፁት አይደለም ። ለዚህም የሰዎች ስነ - ልቦና ፣ ባህልና ሀይማኖትም የራሳቸው ተፅእኖ አላቸው ። በቁጥር ላይ ብቻ የተመሰረቱ መረጃዎች የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ሊያደርሱ ሲችሉ ፣ ቁጥራዊ ወይም ሂሳባዊ ከሆነው እውነታው ውጪ ያለውም የገሀዱ አለም እውነታም አስፈላጊ ነው ። 

ምንም እንኳን ምጣኔ - ሀብት በቁጥሮች ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ማህበራዊ ሳይንስ እንደመሆኑ እንደ ማንኛውም የማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ እሚያጠናው ሰውን ነው ። ስለዚህ ሰውን መረዳት ማለት ደግሞ አካላዊ (ባዮሎጂካል) ከሆኑ ነገሮች ውጪ በአብዛኛው በግልም ሆነ በማህበረሰብ ደረጃ ያለውን ስነ - ልቦናውን መረዳት ማለት ነው ። አብዛኛው ማህበራዊ ሳይንስ የሰውን ልጅ ግላዊም ሆነ ማህበራዊ ስነ - ልቦናውን ወይም አስተሳሰቡን፣ፍላጎቱን ወዘተማጥናትና መረዳት መሰረቱ ነው ። የትኛውም የምጣኔ - ሀብት ፖሊሲም ሲወጣ እሚተገበረው በአገርና በህዝብ ላይ በመሆኑ አንድምታውም እንደዛው ሰፊ ነው ። 
የአንድ ኩባንያን አትራፊነትና ወደ ትክክለኛው መንገድ እየተመራ እንዳለ ለመረዳት ኩባንያው ከሚያወጣቸው የቁጥር መረጃዎች ውጪ ፣ ስለ አስተዳደሩ ባህሪ እና ታማኝነቱ፣ ስለሚወስናቸው ውሳኔዎች አይነትና ሪስክን የመውሰድ ዝንባሌውና ልማዱ ወዘተ የመሳሰሉት ስለ ኩባንያው ትክክለኛና የተሟላ መረጃን ይሰጣሉ ። ኩባንያው የሚያወጣቸውን የቁጥር መረጃዎችን ብቻ በመመልከት ስለኩባንያው ሙሉ ለሙሉ ትክክለኛ የሆነ ስእልን ለመጨበጥ አስቸጋሪ ነው ። ለዚህም አይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው በምእራቡ አለም ትላልቅ ኮርፖሬሽኖች ፣ አማላይ የሂሳብ ምርመራ ውጤትን አሳትመው ለህዝብ ይፋ ቢያደርጉም በተግባር ግን እየከሰሩ ያሉ ፣ ወደ ኪሳራ እያመሩ ያሉ ሆነው የተገኙ በርካታ ግዙፍ ኮርፖሬሽኖች አሉ ።
በአጠቃላይ ግን ምጣኔ - ሀብት የሙያ ዘርፍ ከተፈጥሮ ሳይንስነት ይልቅ ማህበራዊ ሳይንስነቱ በጣም ያመዝናል ። ለዚህም ምሳሌ የሚሆነው አብዛኞቹ የምጣኔ - ሀብት ንድፈ - ሀሳቦች (Economic Theories) ናቸው እንጂ የምጣኔ - ሀብት ህግጋት (Economic Laws) ለመባል የሚበቁ አይደሉም ይባላል ። ምጣኔ - ሀብት በክስተት የሚገለፅ ነው እንጂ በንድፈ - ሀሳብ ለመግለፅ ውስብስብ ሊሆን ይችላል ። በአንፃሩ በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ውስጥ ያሉት የማያወላዱ ህግጋት ናቸው ። የስበትን ህግ ፣ ሀይልን ፣ የፍጥነትን የመሳሰሉትን ህግጋትን ብንወስድ የሰው ልጅ ከመፈጠሩ በፊትና ወደፊትም የሰው ልጅ ህልውናው ባይኖር እንኳን የነኚህ ህግጋት ነበሩም ፣ አሉም መቼም ቢሆን ይሰራሉ ። በማህበራዊ ሳይንስ የዚህ አይነት እርግጠኝነት ላይ መድረስ በእጅጉን አጠራጣሪ ነው ። ማህበራዊ ሳይንስ እንደመሆኑ ያልተጠበቁ ከውስጥም ፣ ሆነ ከውጪ የተለያዩ ክስተቶች መከሰታቸውና ውጤቱን ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ ማሳታቸው አይቀሬ ነው ። ለዚህ ነው በዘርፉ ሊታወቁ ይገባቸው የነበሩ ነገር ግን ለሙያው ራሱ እንግዳ የሆኑ አዳዲስ ክስተቶች በየጊዜው ሲከሰቱ የምናየው ። 
ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው የብሉይንና የኬነስን የምጣኔ ሀብት አስተምህሮዎችን ብንወስድ ምንም እንኳን ሁለቱ የምጣኔ - ሀብት ፍልስፍናዎች የራሳቸው የሆነ አካሄድና የእርስ በእርስ የመቃረን ሁኔታ ሲኖር ከተወሰነ ደረጃ በላይም ሁለቱም ሊሰሩ የማይችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል ።
ለምሳሌ እ.ኤ.አ.የ2008 የገንዘብ ቀውስ ብንወስድ ቀውሱ የተከሰተበት ምክንያት የትላልቅ የባንክ አስተዳዳሪዎችና መሪዎች የወሰኗቸው ውሳኔዎች ለጊዜው እነሱን ትርፍ በትርፍ ቢያደርጓቸውና ግዙፍ ቦነስን እንዲያገኙ ቢያስችላቸውም ውለው አድረው ግን ደንበኞቻቸውን ፣ ራሱን የገንዘብ ስርአቱን ብሎም አጠቃላይ የአለምን ምጣኔ - ሀብት ቀውስ ውስጥ ጨምሯል ። የፖለቲካ መሪዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ከተጠያቂነት ያለመጡ ሲሆን ፣ የአይስላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ ለፍርድ ለመቅረብ ተገደዋል ።
የአለምን የምጣኔ - ሀብት ችግር ወዲያውኑ የሚፈታ አስማታዊ መፍትሄ (Magic Bullet) በአለም ላይ የለም ።አንዱ በአለም ላይ ያለ የምጣኔ - ሀብት ችግርን የሚያስከትል ነገር የምርታማነት መለወጥና አቅጣጫውን መቀየር ሲሆን ፣ ለዚህም በ1990ዎቹና 2000ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በመገናኛ ቴክኖሎጂና በኮምፒውተርና በሶፍትዌርና በኢንተርኔትን በመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ የተመሰረተ ከፍተኛ የምርታማነት የተመዘገበ ሲሆን ፣ የዚህ ዘርፍም ምርታማነት እየቀነሰ ሲሄድም ወደ ሌሎች ዘርፎች ምርታማነቱ መሸጋገር ጀምሯል ። 



አሁን እየኖርንበት ያለነው አለም አንዱን ችግር ስናልፍ ሌላው ችግር ብቅ ይላል ። ምንም የመጨረሻ የሆነና እና አስተማማኝ የሆነ ነገር የለም ። መገናኛ ብዙሀንን ብናዳምጥ ዜናዎቻቸው በአብዛኛው ምጣኔ - ሀብታዊ ጉዳዮችን እሚያነሱ ሲሆን ምንም እንኳን በአንዳንድ ተቋማት የምጣኔ - ሀብት ባለሙያዎችን እስከማግለልና ፣ ሌሎች ባለሙያዎችን እንደ የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያዎችን (ሶሺዮሎጂስቶን)ና የአካባቢ ሳይንስ ባለሙያዎችን እስከ መቅጠር ደርሰዋል ። የአለም ባንክ ሳይቀር የምጣኔ - ሀብት ባለሙያዎችን በማባረር ፣ ሌሎች የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎችንና የጤና ባለሙያዎችን በብዛት መቅጠርና ብሎም ከፍተኛ የአመራር ደረጃ ላይ ማስቀመጥ ጀምሯል ። ለምሳሌ ከሮበርት ዞሌክ በኋላ የአለም ባንክ ፕሬዝደንት ሆነው የተሾሙት የህክምና ባለሙያ ናቸው ። ምናልባት አንድ ባንክን አንድ የህክምና ባለሙያ ይምራው ሲባል ፣ ለሰው አንዳንድ ሰው ሊገርመው ይችላል ። ነገር ግን ተቋሙ ከአትራፊ ተቋማት ይልቅ፣ ታዳጊ ሀራትን ከድህነት እንዲወጡ እንዲረዳ በማሰብ ሲሆን ፣ በአንፃሩ ግን በምጣኔ - ሀብት ባለሙያዎች ላይ ከቀድሞው ቀነስ ያለ እምነት መኖሩን ያረጋግጣል ። ይህ ይሁን እንጂ የምጣኔ  - ሀብታዊ ችግር በሚፈጠርበት ወቅት የሚጠሩት ያው ኢኮኖሚስቶች መሆናቸው የታወቀ ነው ፣ አንዳንዴ ይህን ችግር ያመጡብን እነሱ ናቸው ቢባልም ፤ ዞሮ ዞሮ ግን  አንድ ምጣኔ - ሀብታዊ ችግር ሲፈጠር መፍትሄ እንዲያመጡ የሚጠበቀው ከምጣኔ - ሀብት ባለሙያዎች ዘንድ ነው ።
ይህንን ክፍተትም ለመሙላት ፤ በርካታ የምጣኔ - ሀብት አዋቂዎች ይህንን ክፍተት ለመሙላት ብዙ ሀሳቦችን አፍልቀዋል ። እርግጥ እነኚህ እሳቤዎች እውነተኛውን አለም ለመረዳት የሚያስችል የንድፈ - ሀሳብ መደላድልን ወይም መሰረትን ጥሏል ። እንደ የኬነስ ተከታይ የሆኑና እንደ ጆሴፍ ስትግሊትዝን የመሳሰሉት ይህንን ክፍተት ለመሙላት በርካታ ሀሳቦችን አፍልቀዋል ።

ነገር ግን አንድ ነገር ልብ ማለት ያለብን ነገር በምጣኔ - ሀብት ዘርፍ በርካታ አሳማኝነትና መስህብነት ያላቸው ክርክሮች በበርካታ ሰዎች የቀረቡ ሲሆን ነገር ግን በማህበራዊ ሳይንስ ውስጥ የአንድን ሀሳብ ትክክለኝነት መረዳት የሚቻለው ያ ሀሳብ በተግባር በሚሰጠው ውጤት ብቻ ነው ፣ በተጨባጭ ከሚያስገኘው ውጤት ውጪ የሀሳብ ጠቀሜታ ሊለካ የሚችልበት ሌላ መንገድ የለም ። አንድ ሀሳብ ለተወሰኑ አመታት በስራ ላይ ውሎ ውጤትን እማይሰጥ ከሆነ ፣ ወይም ይባስ ብሎም ጉዳትን እሚያስከትል ከሆነ ከጊዜ በኋላ ውድቅ መደረጉአይቀሬ ነው ።ይህ በምእራባውያን ሀገራት በተለይም  እንዲሁ ለአስርት አመታት በተግባር ውለው ነገር ግን ውጤትን ሳይሰጡ የተጣሉ በርካታ ሀሳቦች አሉ።አንድ ሀሳብም ትክክል ካልሆነ ለተወሰነ ጊዜ ድረስ የዛን ሀሳብ ጉዳቱን ማዘግየት ቢቻልም ፣ ውሎ አድሮ ግን ትክክል እስካልሆነ ድረስ ውሎ አድሮ የተፈራው ነገር መምጣቱ አይቀሬ ሲሆን ፣ ትክክለኛ መሰረት መጣሉ የተሻለ ነው ። 

ነገር ግን አሁን ባለችው አለማችንን ያለምንም እንከን ፍፁም ሆኖ አለምን የሚመራ ሀሳብን ማግኘት አስቸጋሪ ነው ። ለዚህም ምክንያቱ ምን ይመራሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩ በርካታ ሀሳቦችና አስተሳሰቦች በመጨረሻ ውጤትን እንደማያመጡ ሲታወቅ ሊተው የሚችሉ ሲሆን ፤ ለምሳሌ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ የገበያ ሀይሎችብቻ ምጣኔ - ሀብቱን ይመራሉ ቢባልም እሱም ውሎ አድሮ ችግሮችን በመፍጠሩ አማራጭን መፈለግ ግድ ሆኗል ። የአለማችን ዋነኛ ችግር በትክክል ለረጅም ጊዜ የሚሰራ ቋሚ የሆነ ሀሳብን ማግኘት ሲሆን ። ይህም በተደጋጋሚ አንድ ሀሳብ ከተሞከረ በኋላ እየወደቀ ሲሄድ ተስተውሏል ። ለዚህም የምእራባውያን የኢኮኖሚ ፍልስፍና ከ2008 የአለም የገንዘብ ቀውስ ወዲህ አስተማማኝነቱ የቀነሰ ሲሆን ፣ ሌላ መሪ ሀሳብን መፈለግ ፣ ወይም ቀድሞ የነበረውን በተወሰነ ደረጃ ማሻሻልን ግድ የሚልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ። ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በካፒታሊዝም የምጣኔ - ሀብት ስርአት ላይ የተለያዩ ትችቶች መዝነብ የጀመሩበት ዘመን ላይ ደርሰናል ። ምእራባውያኑ ዜጎች  ሳይቀሩ እኛ 99በመቶ ነን በማለት ከሀገራዊ የሀብት ክፍፍል መአድ የተገለሉ ዜጎች ሰልፍ ሲወጡ በአንፃሩም ምእራባውያን የፖለቲካ መሪዎች ሀብታሞች በአግባቡ ግብር እንዲከፍሉ በይፋ መጠየቅ ጀምረዋል ።
በማህበራዊና በፖለቲካ ዘርፍ ዋናው የአለማችን ችግር የፍትህ መጓደል (Injustice) ሲሆን ፣ በብዙ የአለማችን ክፍሎች የሚሰማውና በየቀኑ የአለም መገናኛ ብዙሀን የሚዘግቡት ጉዳይ በአለም ላይ ስለሚታየው ችግርና በየሀገሩ ስለሚከሰቱ የአስተዳደር መዛባቶች ፣ የኮርፖሬሽኖች እምነት ማጉደል ፣ሙስናዎችና በመሳሰሉት ጉዳዮች ናቸው ። ዴራሲሊ የተባለ የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር በአንድ ወቅት እንደገለፀው «አለም የምትመራው ብዙ ሰዎች እንደሚያስቡት በሚታዩ ሀይሎች ብቻ ሳይሆን በማይታዩ ሀይላትም ጭምር ነው» ። እነኚህም በቀጥታ ለህዝቡ ሲወስኑ የማይታዩ ነገር ግን ከጀርባ ሆነው ምጣኔ - ሀብቱንና ፖለቲካውን፣ የህዝብ አስተያየት (Opinion Poll) በመፍጠር የሚዘውሩትን ሀይላትን ያጠቃልላል ፤ በአብዛኛው ባንከሮች ኩባንያዎች ግዙፍ ኮርፖሬሽኖች እና የህዝብ አስተያየትን የሚቀርፁትን ሚዲያዎችን ይጨምራል ።  

ሀብታም አሜሪካኖች ፤ ትላልቅ የሆኑ ቁጥራቸው 250 የሚሆኑ ቢሊየነሮች ግማሹን ብቻ ሲከፍሉ ፤ ከፍተኛ የኮርፖሬት ግብር ያላት ሀገር ብትሆንም «Tax Watch Amerci» የተሰኘው ተቋም በጥናቱ ላይ ገልፆታል ። በእውቀትም ሆነ በገንዘብ ኮርፖሬሽኖች ከፖለቲካ መሪዎች የበለጠ አቅም  እንዳላቸው የታወቀ ሲሆን ፣ሚዲያዎችን በመቆጣጠር ፣ የትምህርት ስርአቱን በሚመቻቸው መንገድ በመቅረፅ ፣ እንዲሁም ለዩንቨርስቲዎችና ለተለያዩ የምርምር ተቋማት የገንዘብ ድጋፍን በማድረግ ከነሱ አላማ ጋር አብሮ የሚሄዱ ጥናቶችን በማድካሄድና ውጤቶቹንም በማሰራጨት በአጠቃላይ በምጣኔ - ሀብቱም ፣ በባህልም ሆነ በፖለቲካው መስክ የራሳቸውን ተፅእኖ ለዘመናት በሰፊው ሲያሳርፉ ኖረዋል ። በተለይ የፖለቲካውን አለም ከፖለቲከኞች ኋላ ሆነው መቆጣጠር አስችሏቸዋል ። ይህ ሁሉ ይሆን የነበረው በብዙሀኑ ህዝብ ኪሳራ ሲሆን ህዝቡ በሚነቃበት ወቅምትም ብዙ ነገር ከተበላሸ በኋላ ሊስተካከል ይችል የነበረበት ጊዜ ካለፈ በኋላ ሆኗል።

ነገር ግን አለምን የሚመራ ሀሳብ ከአንድ ሰው ወይም በአንድ ፓርቲ ወይም በአንድ አስተሳሰብ ወይም ፍልስፍና ውስጥ ብቻ የሚገኝ ነገር አይደለም ። አለምን ወይም አገራትን የሚመሩ ሀሳቦች በተለያዩ አስተሳሰቦች ፣ አመለካከቶችና ፍልስፍናዎች ውስጥ ተሰራጭተው የሚገኙ ናቸው ። ችግሮች በአንድ ጊዜ የሚፈቱ ወይም የሚታወቁ ላይሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ታይቷል ። ለምሳሌ በምእራቡ አለም ጥንካሬው በዚህ በኩል ከፍተኛ ሲሆን ፣ አንዱ ፓርቲ ሀሳብ በሚጨርስበት ወቅት ፣ በሌላው እየተተካካ በተለያዩ አስተሳሰቦችን በመጠቀም ይቀጥላሉ ፣ በዚህ በኩል እድለኛ ናቸው ማለት ይቻላል ይኀውም በርካታ የማህበራዊ ሳይንስ፣ የፖለቲካ ሳይንስ ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ ሊቃውንትን ያፈሩ ስለሆኑ ሌሎችን በርካታ ሀገራት የነሱን ፈላስፋዎችን ሀሳቦች የተቀረውም አለም በብዛት ተቀባይነትን ያገኙና ተፅእኖን ማሳረፍ የቻሉ ናቸው  
አንዱ አልሰራ ሲል አንዱን ፣ አንዱም ውድቀትን ሲያስከትል የሱ ተቃራኒ የሆነውን አስተሳሰብ በመጠቀም ፖሊሲዎቻቸውን እየለዋወጡ ከችግራቸው ለመውጣት ጥረትን ሲያደርጉና ሲሳካላቸውም ታይቷል ። ይኀውም በ1930ዎቹና እንዲሁም በ2008 የአለም የገንዘብ ቀውስ ፣ እንዲሁም በ2012 በተከሰተው ወቅት አዋጪ ናቸው ያሏቸውን የኢኮኖሚ ፍልስፍናዎችና መርሆዎችን ተግባራዊ አድርገዋል ። በእርግጥ የፖሊሲ ለውጥበን ለማድረግ ፣ የአመራር ለውጥን የሚየተይቅ ሲሂን ሆን «አዲስ መጥረጊያ የተሻለ ያፀዳል እንዲሉ» ምእራባውያን አገራት አንድ ችግር ሲገጥማቸውና ፣ ፖሊሲው አልሰራ ሲል  ጠንካራ የዲሞክራሲ ስርአት ስላላቸው መሪዎቻቸውን ይለውጣሉ ። ለምሳሌ የዩሮ የእዳ ቀውስን ለመፍታት መጀመሪያ ላይ ወጪን መቀነስን «ኦስተሪቲ» እንደ አማራጭ ይዘው የነበሩ አንዳንድ የአውሮፓ መሪዎች እንደ ፈረንሳዩ ሳርኩዚ ያሉት በምርጫ ስልጣናቸን ሲያጡ ፣ ወጪ መቀነስን እንደ አማራጭ የማይከተሉ መሪዎች ተቀባይነትን አግኝተዋል ።

 ቻይናን ኢኮኖሚ ከሶሻሊዝም ወደ ካፒታሊዝም ያመጡት ፣ የቀድሞው የቻይና መሪ ዴንግ ዚያዎፔንግ እንዲሁ እንደሚሉት ፣ዋናው ነገር ድመቷ ጥቁር ወይም ነጭ መሆኗ ሳይሆን አይጥ መያዝ መቻሏ ነው ።
አንድ ለብዙ ጊዜ ሲሰራበት የኖረ አስተሳሰብ መቀየር በሚፈልግበት ወቅት ማሻሻል ፣ ማስተካከል የሚያስፈልግ ሲሆን ማህበረ- ኢኮኖሚና- ፖለቲካዊ ዳራዎች በሚቀየሩበት ወቅት ግን በአንድ በኩል ከነበረው ወቅታዊ ሁኔታ ተጠቃሚ የሆኑ ወገኖች ያ ነገር እንዳይለወጥ በመፈለግ ሲከላከሉለት ፣ በሌላ በኩል ለውጡን ካለመረዳትና ነገሮች እንደቀድሞው ሆነው ይቀጥላሉ ከሚል የተሳሳተ እምነት ምክንያት የቀድሞ ሀሳቦች ስራ ላይ ቢውሉም በተደጋጋሚውድቀትን ሲያስከትሉ ተስተውሏል ። ያም ሆኖ ግን ከዚህ አይነት ጉዳዮች ከጀርባቸው ትልቅ ፖለቲካ አለ ።

የምጣኔ ሀብት የትምህርት ዘርፍ ከሌሎች የትምህርት ዘርፎች ጋር ሲነፃፀር የቅርብ ጊዜ ሙያ ነው ማለት ይቻላል ። መስኩ ደርዝ በያዘ መንገድ የተወለደው እንግሊዝ ሀገር አዳም ስሚዝ በተባለ የስኮትላንድ ተወላጅ ሰው ሲሆን ከዚያም በርካታ ታላላቅ አሳብያንና ለማህበረሱ ኑሮ መሻሻል የጋለ ፍላጎት በነበራቸው ምሁራን ዳብሮ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ደርሷል  - አሁንም ድረስ እየዳበረ ይገኛል።
የምጣኔ - ሀብት የትምህርት ዘርፍን የሚስብ የሚያደርገው አንዱ ነገር የማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ሆኖ በተወሰነ ደረጃ ደግሞ እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ የሚያስቆጥሩት ሁኔታዎች ሲኖሩት ከሌሎች የማህበራዊ ሳይንስ የትምህት ዘርፎች በትለየ ሁኔታ በሂሳብ ፣ በስታትስቲክስና በኢኮኖሜትሪክስላይ የተደገፈ ነው ። ከዚህም ሌላ የምጣኔ - ሀብት ዘርፍ ስራ ላይ የሚውለው በሀገርና በህብረተሰቡ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ በመሆኑ የሚሞከረው በተግባርሲሆን የሚወጡ ፖሊሲዎች ከልተሳኩ የሚያስከፍሉት ዋጋ በአገርም ሆነ በግለሰቦች ኑሮ እጅግ ከባድ ነዉ ።

ይሁን በዚህ መስክ የአንድን ሀገርም ሆነ የአለምን ምጣኔ - ሀብት አቅጣጫን ለማየትና ለመምራት የዛን ኢኮኖሚ የሚሄድበትን አቅጣጫ ለማየትና የመረዳት ችሎታን ይጠይቃል ። ነገር ግን የዚህ አይነት ባለሙያዎች ቁጥራቸው ብዙም ባይሆንም በተለይ በአገር ደረጃ ፖሊሲን የሚያወጡ ሰዎች ያ ኢኮኖሚ የሚሄድበትን አቅጣጫ ማየት የቻሉና ወዴት እያመራ እንዳለ ፣ ወዴት መሄድ እንዳለበት የሚወስኑ ሰዎች ናቸው ። ይህ ብቻም ሳይሆን የግል ድርጅቶችና ባንኮች የመሳሰሉትም ተቋማትን ለመምራት የዚህ አይነት አጠቃላይ ምጣኔ - ሀብቱን የመረዳት ችሎታ ነው ኩባንያዎች ትርፋማ ሆነው ሊመሩ የሚችሉት ። 

ማንኛውም ሀገር ጠንካራ ምጣኔ ሀብትን ሲገነባ ብቻ ነው ሌሎች ዘርፎች እሚነቃቁት ። ለምሳሌ ስነ- ጥበብን ፣ ሙዚቃን ፣ ፍልስፍናን ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ፣ ብንወስድ ጠንካራ ምጣኔ ሀብት ያላቸው ሀገራት በእነዚህ ዘርፎችም እየዳበሩና እየፋፉ ሲሄዱ ለዛ የሚበቃ የኢኮኖሚ አቅም የሌላቸው ሀገራት ግን በእነዚህም ዘርፎች ወደ ኋላ ቀርተው ማግኘት ያለባቸውን ትሩፋት ሲያጡ ይታያሉ ።
ይህ ሙያ ለብቻው የቆመ ሳይሆን ከሌሎች ሙያዎች ጋር በምርምርም ሆነ በተግባር የተያያዘ ነው ይሁን እንጂ ከምንም በላይ ወደ የትኛውምየፖለቲካ አቅጣጫ ሊቀየር የሚችል ነው ። ለምሳሌ የትኛውንም የምጣኔ - ሀብት ክርክር ከየትኛውም ፖለቲካአስተሳሰብ አንፃር መደገፍም ሆነ መቃወም ሲቻል ፣ በየትኛውም ሀገር ያሉ የፖለቲካ መሪዎች የነሱ ፖሊሲና አመራራቸው ትክክል እንደሆነ ለማሳየት በዋናነት የሚጠቀሙበት ከምጣኔ - ሀብት መስክ ያስመዘገቡትን ውጤት በመጥቀስ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞበተቃዋሚነት የተሰለፉ የፖለቲካ መሪዎችም ደግሞ በበኩላቸው ስልጣን ላይ ያለውን ወይም ገዢ የሆነውን ፓርቲ እሚያብጠለጥሉት ደግሞ በኢኮኖሚ መስኮች ያሉትን ችግሮች እንደ ስራ አጥነትን ፣ የኑሮ ውድነትን የመሳሰሉትን ችግሮች በመጥቀስ ነው ።
በምጣኔ - ሀብት ዘርፍ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች የሚፈቱት በሰዎች አማካይነት ሲሆን ከሰው በላይ የሆኑም አይደሉም ። ችግሮቹ የሚፈጠሩትም በሰዎች ሲሆን መፍትሄም ሊያገኙ የሚችሉትም በሰዎች ነው ። ሌላ የተፈጥሮ አደጋዎችን  መሬት መንቀጥቀጥን ፣ ሱናሚን ብንወስድ ከሰው ልጅ ቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ ሲከሰቱ የኢኮኖሚ ችግሮች ግን ከሰው ልጅ አቅም በላይ ሊሆኑ አይችሉም ።