#ገናን በላልይበላ እናሳልፍ ።
የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙት ሰሜን ወሎ ዞን ከባህር ዳር ጋሸና 236 ኪ.ሜትር ከጋሸና ላልይበላ 64 ኪሎሜትር ከወልዲያ ሰሜን ምዕራብ 18ዐ ኪ/ሜ ርቀት ላይ ከምትገኘው ከላልይበላ ከተማ ነው፡፡
ውቅር አብያተክርስቲያናቱ በ12ኛው ክፍለ ዘመን በቅዱስ ላልይበላ ከአንድ አለት ተፈልፍለው የታነጹ ሲሆኑ በሶስት ምድብ የተከፈሉ ናቸው፡፡
ምድብ አንድ ፦ ቤተመድሃኒዓለም፣ ቤተ ማርያም፣ ቤተ ሚካኤል / ቤተ ጐለጐታ/፣ ቤተ መስቀል፣ ደብረ ሲና እና ቤተ ደናግል ይገኛሉ።
#ምድብ ሁለት መካከል፦ ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ መርቆርዮስ፣ ቤተ ገብርኤል ሩፋኤልና ቤተ አባሊባኖስ ይገኛሉ።
ከሁለቱም ምድቦች ፈንጠር ብሎ የሚገኘው #ቤተ ጊዮርጊስ ደግሞ በምድብ ሶስት ይመደባሉ፡፡
በላሊበላ በርካታ በዓላት አሉ የተለየው ግን ትልቁ ክብረ በአል ታህሳስ 29 ቀን የሚከበረው የገና በአል ነው፡፡
ለበአሉ ታላቅነት ሌላው ተጨማሪ ምክንያት ደግሞ በቅዱስነታቸው የሚታወቁት የቅዱስ ላሊበላ የልደት ቀን ጭምር መሆኑ ነው፡፡
የገና በዓል በላልይበላ በልዩ ልዩ ሀይማኖታዊ ዝግጅቶች ለበርካታ ቀናት ይከበራል፡፡
በተለይም በገና ዋዜማ በሌሊት የሚከናወነው የቤዛ ኩሉ ሀይማኖታዊ ስርአት እንደእርጥብ ሸንበቆ ወገባቸው የሚተጣጠፈውን የደብረ ሮሃ ካህናት ዝማሜ ማየት እጅግ ያስደስታል፡፡
ጥምቀትም በላሊበላ ሌላው ትልቅ በአል ነው፡፡
የእነዚህን ሁለት ትላልቅ በአላት አከባበር በአካል ለመመልከት እና ከበዓላት ውጭም ውቅር አብያተክርስትያኑትን የህንፃ ጥበብ ለማየት እና ለማድነቅ ብዛት ያለው ምእመን፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጐብኝ ወደ ላሊበላ በየአመቱ ይጎርፋል።
በርካታ ቅርሶችን የያዘ ቅዱስ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱትን ሲሰራ የተጠቀመበት መጥረቢያን ጨምሮ በርካታ ቅርሶች በሙዚየም ተደራጅተዋል እንዲሁም ባማረ ህንፃ የተደራጀው የላልይበላ የባህል ማዕከልም የአካባቢውን ወግና ባህል በሚያሳይ መልኩ ሙዚየም ተደራጅቶ ለጉብኝት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
ከ11ዱ ውቅር አብያተክርስትያናት በተጨማሪ በቅርብ ርቀት በርካታ ጥንታዊና ታሪካዊ አብያተ ክርስትያናት ይገኛሉ፡፡
ከእነዚህም ውስጥ ይምርኸነክርስቶስ ፣ ገነተማርያም ፣ ናአኩቶለአብ ፣ ብልብላጊዮርጊስ፣ ብልብላ ቂርቆስ ፣ እመኪናመድሀኒዓለም ፣ አሸተን ማርያም ፣ አቡነ ዬሴፍና ሌሎችም ይገኛሉ፡፡
ውድ የአገር ውስጥና የውጭ ምዕመናን ገናን በላልይበላ በመገኘት እነዚህን ውድ የአገር ሀብትና ኩራት የሆኑትን ቅርሶች በመጐብኘት ደስታችን እጥፍ ድርብ እናድርግ፡፡
No comments:
Post a Comment