Friday, December 14, 2018

eprdf & tplf future survival

የኢህአዴግና የህወሃት እጣ ፈንታ

የህወሓት አመራሮች የትግራይን ህዝብ እንደ ምሽግም እንደ ደጀንም፣ እንደ ሰብአዊ ጋሻም እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ አሁን ባለው የህወሓት አካሄድ የፖለቲካው አቅጣጫ በነበረበት የመርገጥ አዝማሚያ ስለሚታይበት በትግራይ ህዝብ ውስጥ የተፍታታ የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚፈጠርበት ሁኔታ ከሌላ በስተቀር ሁኔታዎች ይበልጥ እየተውሳሰቡ ይሄዳሉ፡፡

የተፍታታ አስተሳሰብ ሲባል ነገሮችን አሁን ካሉበት ወቅታዊ ፖለቲካ በላይ አርቆ ማሰብ፣ ፖለቲካውን በደረቅ የሂሳብ ስሌት ብቻ አለማየት፣ ካሉበት የሥጋት ቆፈን መላቀቅና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ባለፉት ዓመታት የነበረውንና አሁን ያለው ሀገራዊ ፖለቲካ ብቻ ታሳቢ አድርጎ መንቀሳቀስ የነገውን አካሄድ የሚያበላሸው ይሆናል፡፡ የትናንቱን ሀገራዊ ብልሽትና የዛሬውን ችግር ተገንዝቦ ስለነገው መፍትሄ ማሰብ እንጂ፤ በትናንት ችግር ላይ ቆሞ መቆዘም የትግራይን ህዝብ ቀጣይ ፖለቲካዊ አካሄድ አንድ ጋት ወደፊት ሊያስኬደው የሚችል አይደለም፡፡

ሁለተኛው በትግራይ መምጣት ያለበት ለውጥ ነገሮችን ከፓርቲ ቁመና በላይ መመልከት ነው፡፡ ይህች ህወሓት የማይፈልጋት ጎምዛዛ ሀቅ ናት፡፡ በአሁኑ ሰዓት በትግራይ አድራጊ ፈጣሪ የሆነው የክልሉ ገዢ ፓርቲ ህወሓት ነው፡፡ ህወሓት ደግሞ የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡ እንደ ማንኛውም በሰው የተፈጠረ ድርጅት ህወሓት መጀመሪያ ነበረው፤ መጨረሻም ይኖረዋል፡፡ የራሱ የፖለቲካ ፕሮግራምና አላማን አግንቦ የሚንቀሳቀስ አንድ ክልላዊ ፓርቲ ነው፡፡ ህወሓት ከትግራይ ህዝብ ተገኘ እንጂ፤ የትግራይ ህዝብ ከህወሓት አልተገኘም፡፡ የትግራይ ህዝብ ጥንታዊነት ከህወሓት አርባና እና ሀምሳ ዓመት የጎልማሳነት እድሜ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡

የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ የአስተሳሰብ ብዝሀነት ያለው ሲሆን፤ ሕወሓት እንደ ፓርቲ የፖለቲካ አስተሳሰቡ የሚቀዳው ከፖለቲካ ፕሮግራሙና ከርዕዮት ዓለሙ ብቻ ነው፡፡ እርግጥ ነው፤ የአንድ ህዝብ የአስተሳሰብ ብዝሃነትም ሆነ የአንድ ፓርቲ አስተሳሰብ በርዕዮትና በፕሮግራም መታጠር ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ነገር ግን ስህተቱ የሚፈጠረው የአንድ ፓርቲ ፕሮግራምና አላማ የአንድ ህዝብ አስተሳሰብ ሙሉ ውክልና ያለው አድርጎ ማሰቡ ላይ ነው፡፡

ይህ ማለት አንድን ህዝብ በፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራም ቁመና ልክ ዝቅ ብሎ እንዲያስብ መፈለግ ማለት ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ አካሄድ ራስን የሁሉም ህዝብ ብቸኛ ተጠሪና ተወካይ አድርጎ የማሰብ የጠቅላይ አስተሳሰብ አባዜ ሲሆን በውጤቱም የተለያዩ ተፈጥሯዊ የአስተሳሰብ ፀጋዎችን በአንድ ቅርጫት ውሰጥ ገብተው እንዲጨመቁ ማድረግ ነው፡፡

ህወሓት ፈፅሞ ሊሰማው የማይፈልገውም ጥሬ ሀቅ ቢኖር በትግራይ ምድር ውስጥ ከብዙዎቹ አንዱ ተደርጎ ሊቆጠር የሚገባው መሆኑን ነው፡፡ ራሱን ብቸኛ የስለት ልጅ አድርጎ ማሰቡ በክልሉ ያለውን የፖለቲካ ከባቢ አየር የታፈነ አድርጎታል፡፡ በክልሉ ከህወሓት ሌላ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ እናም ህወሓት ከብዙዎቹ እንደ አንዱ ይሆናል ማለት ነው፡፡

የትግራይን ህዝብ በተጠቂነት የሥነ ልቦና ጫና ውስጥ ከቶ ራስን የዚህ ጥቃት መድህን አድርጎ በመሳል የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ወንዝ የሚያሻግር አይደለም፡፡ እናም ህወሓት ከዚህ ከተቸነከረ ቀኖናዊ አስተሳሰቡ ተላቆ ተነቃናቂና ተራማጅ መሆን ካልቻለ ለፖለቲካ መቅሰፍት የመዳረግ እድሉ ሰፊ ነው፡፡

ኦዴፓና አዴፓ ከፖለቲካ መቅስፍቱ ለመዳን በለውጥ ማዕበል በመታጀብ በማራመድ ላይ ይገኛሉ፡፡ አንድ ፓርቲ ይብዛም ይነስም በአንድ ህዝብ ውስጥ የራሱ የሆነ ማህበራዊ መሰረት ይኖረዋል፡፡ ይህ የፓርቲ ማህበራዊ መሰረት ሰፊ ህዝባዊ ተቀባይነትን ካገኘ ደግሞ የአንድ ክልል ወይንም ሀገር ገዢ የፖለቲካ መስመር ሆኖ ያገለግላል ማለት ነው፡፡ በዚህም ያ ፓርቲ ተከታታይ ምርጫዎችን እያሸነፈ ቅቡልነቱን የሚያረጋግጥበትን ዕድልንም ያገኛል፡፡ ፓርቲው በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ማህበራዊ መሰረቱ እየሳሳ ሲሄድ ደግሞ በሌላ ተፎካካሪ ፓርቲ ብልጫ ተወስዶበት ከገዢነት መንበሩ በመሰናበት በተራው የተፎካካሪነቱን ቦታ ይይዛል፡፡ ይሄ የዲሞክራሲ ተፈጥሮ ባህሪና መለያ ነው፡፡

ከወራት በፊት በኢትዮጵያ የነፈሰው የለውጥ ነፋስ ቀጣዩን የኢትዮጵያን መፃዒ ፖለቲካዊ በዚህ አቅጣጫ የሚያስኬደው ይመስላል፡፡ ኦዴፓም ሆነ አዴፓ በየክልላቸው እየተንቀሳቀሱ ካሉት እንደ ኦነግና አብን ካሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚጠብቃቸው ብርቱ ፉክክር ቀላል እንዳለሆነ ገና ከመነሻው የፖለቲካ መጫወጫ ሜዳውን ክፍት ሲያደርጉ ያውቁታል፡፡ እናም ሜዳውን ከፍተው ብቻ ዝም አላሉም፡፡ ሁለቱም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የምርጫ ጊዜ ሲቀርብ ነገ የሚጠብቃቸውን ብርቱ ፉክክር ታሳቢ በማድረግ ህዝባዊ መሰረታቸውን ሊያሰፉ የሚችሉላቸውን ሰፊ ሥራዎን በመሥራት ላይ ናቸው፡፡

እነዚህ ሁለት ፓርቲዎች ያለፈውን ጥፋት አምነው በቀጣይ ህዝቡን በመካስ መንፈስ በመስራት ላይ ናቸው፡፡ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጪ ሀገራት ላሉ ኢትዮጵያዊያን ያለፈውን የለውጥ ስኬትና መፃኢውን የፖለቲካ አካሄድ በማስረዳት ሥራ ተጠምደዋል፡፡ በዚህም ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ መደላድልን በመፍጠር የተቀባይነት አድማሳቸውን በማስፋት ላይ ይገኛሉ፡፡

የህወሓት አካሄድ ከዚህ ይለያል፡፡

No comments:

Post a Comment