Friday, December 7, 2018

somali region massacare

የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ መሐመድ ይናገራሉ፡-
– በሶማሌ ክልል ለተፈጠረው ኢ- ሰብዓዊ ግፍ ጠንሳሾቹ ጄኔራል አብርሃ (ኳርተር) እና አባይ ጸሐዬ ናቸው አሉ፣

– በዘመድ አዝማድ ስም ባዶ መሬት አስይዘው ባንኮችን በማራቆትም ከሰዋቸዋል፣

በሶማሌ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ግፍ እና ጭፍጨፋ ከፈጸሙት መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት የምስራቅ ዕዝ አዛዡ የነበረው ጄነራል አብርሃ (ኳርተር) እና ከእነሱ ጀርባ እነአባይ ጸሐዬ ናቸው ሲሉ የሶማሌ ክልል ም/ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ መሐመድ ዑመር መናገራቸውን ሸገር ታይምስ መጽሔት በዛሬ ዕትሙ ዘገበ፡፡ ም/ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ልዩ ቃለምልልሳቸው ሁለቱ ግለሰቦች የሶማሌ ህዝብ ዘላለማዊ ጠላት እና በፍጹም የማንረሳቸው ደመኞቻችን ናቸው ብለዋል፡፡

እነዚሁ ግለሰቦችና ግብረአበሮቻቸው በክልሉ በኢንቨስትመንት ስም መሬት ከወሰዱ በኃላም ምንም ዓይነት ልማት ሳያካሂዱ ከባንኮች ገንዘብ ተበድረው የሚሰወሩበት ሁኔታ ማጋጠሙንም አቶ ሙስጠፌ ተናግረዋል፡፡ “…ሰዎቹ ዝም ብለው መጥተው መሬት ለክተው የኔ ነው ይላሉ፡፡ ከዚያም ከባንክ ብር ወስደው ይጠፋሉ፡፡ እንደተመለከትነው በቦታው ላይ ሕዝብን የሚጠቅም አንዳችም ኢንቨስትመንት አልሰሩም፡፡ ይህ ግልጽ ሌብነት ነው፡፡”

ወደ ሥልጣን ከመጡ ገና የሶስት ወራት አጭር ጊዜ የቆጠሩት ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ሙስጠፋ መሐመድ አያይዘውም ባለፉት ጊዜያት በክልሉ ሲፈጸሙ የነበሩ ግጭቶችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጀርባ የእነአባይ ጸሐዬ እጅ መኖሩንም አጋልጠዋል፡፡ “…በአገር አቀፍ ደረጃ የፖለቲካ መገፋፋት ሲፈጠር ታዳጊ ክልሎች የሚባሉ እና በወቅቱ በኢህአዴግ የተያዙ ነበሩ፡፡ ከእነዚህ አንዱ የሶማሌ ክልል ነው፡፡ ሶማሌ ክልልን ሲያሽከርክሩ የነበሩ ሰዎች በወቅቱ ከነበረው የኦሮሞ መነሳሳት ላይ ጫና ለመፍጠር በምስራቅ በኩል ጦርነት ለመክፈት ያቀዱት ፕሮጀክት ነው፡፡ …ከማስተር ፕላን ገር ተያይዞ አዲስአበባ ውስጥ ከፍተኛ ተቃውሞ መነሳት ሲጀምር ሌላ የቶርነት ግንባር እንክፈት ከሚል የፖለቲካ ቀመር የመጣ ጥቃት ነበር፡፡ በዋናነት የዚህ አስፈጻሚ የነበሩት የሶማሌ ክልል የቀድሞ ሹማምንት እና ሐረር ከሚገኘው የመከላከያ አዛዥ ጋር እጅና ጓንት የሆኑ መሆናቸውን ተራው ሕዝብም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ሀኃላ እዚህም እዚያም ሰው ሲሞት ነገሩ በነዋሪው መካከልም እየተስፋፋ ሄደ” ብለዋል፡፡

በሶማሌ ክልል የአንድ ሰው አምባነንነት በመስፈኑ ምክንያት ለስደት መዳረጋቸውን አስታውሰው በተደጋጋሚ በማህበራዊ ሚድያ ትችት በማቅረባቸው ብቻ እሳቸውን ለመበቀል ወንድማቸውን እንደገደሉባቸውና በቤተሰባቸው ላይ እንግልት እና የንብረት ውድመት እንዳደረሱባቸው አቶ ሙስጠፋ ተናግረዋል፡፡

No comments:

Post a Comment