Monday, March 11, 2013

የስልጣኔ ዳራዎች



ስልጣኔዎች የሚፈጠሩት ሰዎች ከጥረት ከእልህ ራሳቸውን ጠላት ከሆነ ወገን ለመከላከል ወይንም የሆነ ደረጃ ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት ነው ።በአጭሩ ስልጣኔ የሚፈጠረው ከችግርና ከመከራ ነው ለምሳሌ ከግሪክ ስልጣኔ በኋላ አውሮፓውያን ቀድመው እየሰለጠኑ የመጡበት ምክንያት አገራቸው በበረዶ የተሸፈነ ስለሆነ የሚመገቡትን ምግብ ለማምረት የሚኖሩበትን ቤት ለመስራት ብዙ ማሰብና አእምሯቸውን ማሰራት ነበረባቸው የሚል ንድፈ - ሀሳብ አለ በአንፃሩ ግን የምድር ወገብ አካባቢን ብንመለከት አካባቢው በደን የተሸፈነ ሲሆን አንድ ሰው ቢርበው እንኳን በቀላሉ ወደ ደን ሄዶ አድኖ ወይም ፍራፍሬ ልቅ ለቅሞ መብላት ይችላል ፀሀይ ከአመት እስከአመት ድረስ ትወጣለች አፈሩ ለም ነው የተሰጠውን ያበቅላል ውሀ እንደልብ ነው ስለዚህ ምንም ችግር የለም ለመኖር እንደ በረዷማ አካባቢዎች ብዙ መከራና ችግር የለም


የስልጣኔዎች ውድቀት መነሾው ምንድነው ቢባል ፣ከስኬት መደራረብ ውድቀት ሊመጣ እንደሚችል መርሳት፣ ቀላል ድሎች ይመጣሉ በሚል ወደ አደገኛ መንገድ ውስጥ መግባት ነገሮች በፍጥነት እንደሚቀያየሩ አለመረዳት እና ውሎ አድሮ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን አለማገናዘብ እና ችግሮች እየተደራረቡ ሲመጡ ቁልጭ ያለ መፍትሄውን ባለማስቀመጥ ወደ ተሳሰሰተው አቅጣጫ ለብዙ ጊዜ የቆየ ጉዞን ማድረግ ነው በየትኛውም ዘመን ያሉ ሀያላን ሲያቆለቁሉ ማየት የተለመደ ሲሆን ሀያላኑ የሚገቡበትን ችግርና ተመልሰው መውጣት ሲያቅታቸው በማየት በቀላሉ መረዳት ይቻላል


ስለዚህ ኑሮው ስላልፈተናቸው ነው ወደ ኋላ የቀሩት ወደሚል ድምዳሜ ያመራል ምንም እንኳን በተፈጥሮ ሀብት የምድር ወገብ አካባቢ የታደለ ቢሆንም ነገር ግን ለአውሮፓውያን መሰልጠንና ለተቀረው አለም ለስልጣኔ ወደ ኋላ መቅረት ግን አመርቂ ምክንያት ሊሆን አይችልም ምክንያቱም ከግሪክ ስልጣኔ በሺ አመታት እሚቀድሙ ስልጣኔዎች በአፍሪካም፣ በእስያም ነበሩ ነገር ግን በአጠቃላይ ሲታይምንም እንኳን ግሪካውያን በኋላ ላይ ቢወድቁም አውሮፓውያን ለስልጣኔ መሰረትን እየጣሉና እየተጠናከሩ ሲሄዱ የተቀረው አለም ግን ከአውሮፓውያን አንፃር ከማደግ ይልቅ እንደውም በአንዳንድ የአለማችን ክፍሎች የስልጣኔዎች ማቆልቆልና ወሎ አድሮ ለአውሮፓውያን የበላይነት ስር ሊሆን ችሏል ።

 
ይሁን እንጂ ከአውሮፓውያኑ የግሪካውያንና የሮማውያን ስልጣኔ በፊትም በስተደቡብ በአፍሪካና በእስያ በምድር ወገብ አካባቢ በርካታ ከአውሮፓውያን የቀደሙ ስልጣኔዎች ነበሩ እነኚህ ስልጣኔዎች እየከሰሙ ሲመጡ በኋላ ላይ ግን አውሮፓውያን ገነው ሊወጡ ችለዋል ለዚህም በአውሮፓ እየበዛ ያለው ህዝብ ያለው ሀብትና መሬት ሊበቃቸው ስላልቻለ መሬት ፍለጋና በዘመኑ ዋነው ንግድ የቅመማ ቅመመን ንግድ ሲሆን ወደ ህንድ ያመራ የነበረውን የንግድ መስመሩን ለማግኘት በነበራቸው ፍላጎት ከበርካታ ሙከራ በኋላ የአሜሪካ አህጉርን ለማግኘት በቅተዋል


የግሪካውያንን ስልጣኔ ብንወስድ አንድ ሰው ደስታውን ምኞቱንና መሻቱን እሚፈልገው የከተማ መንግስት (City State) ውስጥ ሆኖ ነው ውስጥ ነው የሚል መስመር የተቃኘ የጥንታዊ ግሪኮች ፍልስፍና ነው። በተለይም የአቴን የከተማ መንግስት አስደናቂ የስልጣኔ ሀሳቦች የፈለቁበትና በርካታ ፈላስፋዎችንና በርካታ የሙያ ዘርፍ አሁንም ድረስ ጠቃሚ አስተዋፅኦን ያደርጉ ሰዎች የነበሩበት ከተማ ነበረች በነገራችን ላይ መንግስት የአንድ ሰው የደስታውንም የኑሮውም የሁሉም ነገር ማእከሉ መንግስት ነው ማል ለት ሰፊ አንድምታ ነው ያለው በኋላ ላይ ለነበሩት ለበርካታ አመታት አውሮፓውያን ለስልጣኔያቸው የረዳቸው አሰተሳሰብ ነው


ይህም ከእነሱ በኋላ የመጡት ሮማውያንም ግዛተ - መንግስታትን (Empire) በማቋቋም ይህንኑ የመንግስትን ቦታና አቅም አስፋፍተውታል ታላቁ አሌክሳንደር እስከ ፐርሽያ ድረስ በመንቀሳቀስ በአጭሩ ከተቀጩት ዘመቻዎች ውጪ የጥንቶቹ ግሪኮች እንደ ሮማውያን ሰፊ መሬትን ግዛትን ለመያዝ አልተንቀሳቀሱም ይሁን እንጂ በአስተሳሰብ ግን የምእራቡ አለም ፈር ቀዳጆች ሲሆኑ ሮማውያን ግዛትንና ስልጣንን ሲይዙ በርካታ የግሪኮችን አስተሳሰብና ፍልስፍና ተጠቅመዋል


በታሪክ ውስጥ እንደሚታወቀው ሮማውያን በፍልስፍና ፣በቲያትር ፣በስነ ጥበብ፣ በንግድ በመሳሰሉት በርካታ ጥበቦች ግሪኮችን ባያክሉም ዘመናዊ አስተዳደርን ለአለም በማስተዋወቅ በኪነ -ህንፃና በጦርነት ጥበብና በስትራቴጂ የበኩላቸውን የታሪክ አሻራ በአለም ላይ አሳርፈው አልፈዋል ነገር ግን በዛን ዘመን የነበሩ በርካታ የሮማውያን ከግሪካውያን ባሮች በርካታ እውቀቶችን ወስደዋል ተብለው ይታማሉ የግሪኮች ስልጣኔ ሲፈራርስና በሮማውያን አገዛዝ ስር ሲወድቁ በርካታ የግሪክ ፈላስፎች፣ የቁም ፅህፈት ባለሙያዎች የስነ - ጥበብ ባለሙያዎች ሀኪሞች የመሳሰሉት ባለሙያዎች በሮማውያን የባርነት አገዛዝ ስር  ወድቀዋል ነገር ግን ከተራው ባሪያ ይልቅ የተሻለ አያያዝ የነበራቸው ይሁኑ እንጂ የጥበብ ስራቸው ግን ስራቸው ግን በአብዛኛው በሮማውያን ተወስዷል ።ሮማውያን ራሳቸውን የእነኛ ግሪካውያን ስራዎች ባለቤት አድርገው አቅርበዋል ብዙዎቹ የሮማውያን ፈላስፎችም የግሪኮችን ስራ በመስረቅ ይታማሉ በዚህም ሮማውያን የግሪካውያንን ስራ በመስረቅ (Plagiarism) ይታማሉ


ነገር ግን ትልቁ የግሪካውያን ስለ ፍልስፍና መሰረት የጣሉት ስለ መንግስት በተለይም ዲሞክራሲያዊ ስለሆነ መንግስት በአጠቃላይ መንግስት ምን መምሰል እንዳለበት በሰፊው በነበሯቸው ታላላቅ ፈላስፋዎች አማካኝነት አትተዋል በተለይም ፕሌቶ ከፍተኛ ተፅእኖ ያሳረፈ ሲሆን ከእርሱ በመቀጠል አሪስቶትል ከፍተኛ ሀሳቦችን አበርክቷል ከዚህም በሂሳብ በጂኦሜትሪ እንደ ኢክሊድ፣ ፓይታጎራስና አርኪሜዲስን የመሳሰሉ ታላላቅ የሳይንስና የሂሳብ ሊቃውንትንም አፍርተዋል መንግስትን ማእከል ማድረጋቸው ትልቁ የምእራቡ ስልጣኔ የአስተሳሰብ መሰረት ነው - በተለይም በዘመኑ በነበሩት የከተማ - መንግስታት (City State) አንፃር። ጥንትም ሆነ አሁን እንደ መንግስት ያለ ተቋም ባይኖር ኖሮ በአለም ላይ ስለየትኛውም ስልጣኔም ሆነ እድገት ማሰብ አይቻልም ነበረ ትልቁ ጥንታዊ ግሪኮች ያደረጉት አስተዋፅኦ ስለ መንግስት ያፈለቋቸው ሀሳቦችና በተግባርም ሲሰሩባቸው የቆዩ ሀሳቦች ነው

 
የአቴናውያን ስልጣኔ ብቻ ነው ወዲያው በአንድ ጊዜ ቦግ ያለው የተቀረው አለም ስልጣኔ ግን በበርካታ መቶዎችና ሺዎች አመታት ውስጥ እያበበ የሄደ ነው ለዚህም የሚጠቀሰው የጥንቷ ኢትዮጲያ ማለትም የኩሽ ስልጣኔ እና በፈርኦኖች ይመሩ የነበሩት የግብፅ ስልጣኔዎች ይጠቀሳሉ በአንፃሩ ከዚያ በኋላ ያበበውና በግሪካውያን በተለይም በአቴናውያንየሚወከለው የምእራባውያን ስልጣኔ ግን በአንድ ወቅት ቦግ ብሎ የታየ ነው   


ይህ ብቻ ሳይሆን አውሮፓውያን የግሪክን ስልጣኔ ከፈጠሩ በኋላ ምንም እንኳን የግሪክ ስልጣኔ ኋላ ላይ ቢፈራርስም ይበልጥ ጠንካራና ሰፊ ግዛትን ያስተዳድር በነበረው የሮማውያን አፄ - ግዛት (Empire) ተተክቷል የሮማውያንም ስርአት ሲደክም እንዲሁ በቤዛንታይን ተተክተቷል በሌላው አለም የነበሩት ስልጣኔዎች ግን የመተካካት አቅማቸው አነስተኛ ሆኖ ነው የቆየው በዛ መንገድ ምእራባውያን ቀዝቀዝ ቢልም መጀመሪያ በመካከለኛው ዘመን ከዚያም በህዳሴው እውቀትን በማስፋፋት በንቃት ወይም አብርሆት (The Age of Enlightenment) ዘመን እንዲሁም በኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን እየተቀባበሉ ባልተቋረጠ የእድገት ጎዳና ላይ መጓዝ ችለዋል። አውሮፓውያን ያልተቋረጠ በሚባል ሁኔታ ባላቸው ላይ እየጨመሩ ሲሄዱ በአንፃሩ የተቀረው አለም በባሪያ ንግድ ፣በቅኝመገዛት በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በእርስ በርስ ሽኩቻ በመሳሰለው እድገቱ የኋልዮሽ ሆኖ ቆይቷል

መሰረታዊ የምጣኔ ሀብት ህግጋት



መሰረታዊ የሆነው የምጣኔ ሀብት ህግ የአቅርቦትና የፍላጎት ህግ ሲሆን ይኀውም በመጀመሪያ ሴይ በተባለ ፈረንሳዊ የተገኘውና የሴይ ሀግ በመባል የሚታወቀው የሴይ ህግ ነው። ይህም በአቅርቦትና በፍላጎት መሀከል ያለውን የሚተነትን ሲሆን የብሉይ ዘመን ምጣኔ ሀብት አስተሳሰብ መሰረት ነው ። የእርሱ ህግ የሚለው አቅርቦት የራሱን ፍላጎት ይፈጥራል (Supply Creates its Own Demand) የሚል ነው ። ምንም አንኳን በምጣኔ - ሀብት ውስጥ ህግጋት ቢኖሩም ፣እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ ዝንፍ ሳይሉ በማንኛውም ሁኔታ የሚሰሩ አይደሉም ።


ይህም ማለት አቅርቦት እስካለ ድረስ ፍላጎትም ይኖራል ማለት ሲሆን በሌላ አነጋገር የፍላጎት ችግር አይኖርም ማለት ነው ። ስለዚህ በአገር ኢኮኖሚ ደረጃ ስናስበው የአንድ አገር ኢኮኖሚ እንደፈለገው ቢያመርት የገበያ ወይንም የገዢ ችግር አይኖርበትም ማለት ነው ።ይህ አስተሳሰብ የብሉይ (Classical Economics) እጅግ መሰረታዊ የሆነ ፍልስፍና ሲሆን ለብዙ አመታት ያለጥያቄ ተቀባይነትን አግኝቶ ኖሯል ።በተለይም እወሰ ስከ 1930ዎቹ የአለም ምጣኔ - ሀብት ዝቅጠት (The Great Depression) ድረስ የብሉይ አስተሳሰሰብ ገዢ መሰረታዊ ሀሳብ ሆኖ ቆይቷል ። ከ1930ዎቹ ቀውስ በኋላ ግን በኬነስ አማካይነት የኬነዢያን አስተሳሰብ የበላይነቱን ተጋርቶታል ።


ይሁን እንጂ ጉዳዩ ቀላል አይደለም ፣ እንደውም እንደ ማርክሲስቶች አባባል የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም መሰረታዊ የካፒታሊዝም ስርአት ውስጣዊ ቅራኔ ነው ። በአቅርቦትና በፍላጎት መሀከል መጣጣም አለመኖር በአለም ላይ ለታዩት በርካታ የምጣኔ - ሀብት መቀዛቀዞችና መዝቀጦች ዋነኛ ምክንያት ነው ። ምንም እንኳን ልል የሆነ የመንግስት ፖሊሲ ፣ የመዋእለ - ንዋይ አፍሳሾችና ፣ የባንኮች መስገብገብና (Speculation) ባህሪ ችግሩን የማባባበስ ባህሪ ቢኖረውም ጉዳዩ ግን የካፒታሊዝም ስርአት የፈጠረው ችግር ነው የሚል ክርክር በማርክሲስቶች በኩል ይቀርባል ።


የሴይ ህግ የምጣኔ - ሀብት ዋና ንድፈ - ሀሳባዊ መሰረት ሆኖ አሁንም ድረስ የሚያገልግል ነው ። በምጣኔ - ሀብት ውስጥ ምንም እንኳን ከእውነተኛው አለም የራቁ ቢሆንም በጣም ንድፈ - ሀሳባዊ የሆኑ ሀሳቦችን መጠቀም የተመለደ ነው ። በኬነስ በ1936 ዓ.ም በታተመው መፅሀፍ ከመፈተኑ ውጪ ለክፍለ ዘመናት ያለጥያቄ ተቀባይነትን አግኝቶ ቆይቷል ። የሴይን ህግ በመከተልም አልፍሬድ ማርሻል የተባለው ታላቁ እንግሊዛዊ የምጣኔ - ሀብት ሊቅ የአቅርቦትናንና የፍላጎትን ህግ መሰረት እና ሂሳባዊ ስሌቶችን በመጠቀም የአቅርቦትንና የፍላጎትን  ሂሳባዊ ቀመርና በግራፍ አመልክቷል።

የዚህ አስተሳሰብ መሰረት መናድ የጀመረው የታላቁ የአለም ኢኮኖሚ መዝቀጥ (The Great Depression) እ.ኤ.አ.በ1930ዎቹ በተከሰተበት ወቅት ሲሆን ያንን ታላቅና ግዙፍ የሆነ አለም አቀፋዊ የሆነ የምጣኔ ሀብት ችግር በአለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የስራ አጥነትን ፣ የፋብሪካዎች መዘጋትን ፣ ገንዘብ ግሽበትንና ብሎም ለሁለተኛው የአለም ጦርነት አንዱ መነሻ ሊሆን በቅቷል ። በዚህ ወቅት ጆን ሚያራንድ ኬነስ የተባለው እንግሊዛዊ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ቀደምት ከነበረው የብሉይ የምጣኔ ሀብት አስተሳሰብን በመቀየርና ሌላ መስመርን በመቀየስ መፍትሄውን ለማግኘት በቅቷል ።


የኬነስ አስተሳሰብ ቀደምት የነበረውን አቅርቦት የራሱን ፍላጎት ይፈጥራል የሚለውን የሴይን አስተሳሰብ አቅርቦት ቢኖርም ግን የግድ ግን ፍላጎትን ይፈጥራል ማለት እንዳልሆነ ታይቷል ስለሆነም ኬነስ ያቀረበው ሀሳብ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ኢኮኖሚውን በማነቃቃት ፍላጎትን ማሳደግ አለበት የሚል ነው ።

ካርል ማርክስም አንዱ የካፒታሊዝም ስርአት ችግር ያመረተውን ያህል ገበያ አይኖረውም የሚል ሲሆን ፣ ከፍተኛ አቅርቦት ቢኖርም ፍላጎት ግን የአቅርቦት ያክልን ስለማያድግ የምጣኔ - ሀብት ችግሮች ይከሰታሉ ፣ ይህምምንን ኬነስ በመረዳት የኬነስ አስተሳሰብ ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ በሚገባበት ወቅት ኢኮኖሚዎችን ፍላጎት ማነቃቃት ፍቱንና ትክክለኛ መፍትሄ መሆኑ በተደጋጋሚ የታየ ሲሆን ዋናው ጥያቄ ግን መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ የሚገባው በምን አይነት ሁኔታ መሆን አለበት የሚለውና እስከምን ድረስ ነው መግባት ያለበት የሚለው ነገር ግን ምንግዜም ቢሆን አወዛጋቢ ነው ።ለምሳሌ እ.ኤአ. እ.ኤ.አ በ2008 በአሜሪካን ሀገር በተፈጠረው የገንዘብ ቀውስና የኢኮኖሚ ዝቅጠት ውስጥ መግባት ምክንያት ሁለቱንም የአሜሪካ ዋና ዋና ፓርቲዎች ማለትም ሪፐብሊካኖችም ሆኑ ዲሞክራቶች ኢኮኖሚውን ማነቃቃት እንዳለት ሲስማሙ መጠኑና በምን አይነት ሁኔታ ማነቃቂያው መፈፀም አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ግን ሰፊ ልዩነት አላቸው ።


ሀገሪቱ በእዳ ውስጥ እየተዘፈቀች በነበረበት ወቅት እ.ኤ.አ. ከ2008 በፊት ዘመን አንዳንዶች አሜሪካ እየተዘፈቀችበት የነበረው እዳ ያስገርማቸው የነበረ ሲሆን ፣ ይሄን ያህል እዳ ለመሸከም እና የበጀት ጉድለትን ለማሳየት የሚያስችላት ልዩ የሚያደርጋት ወይም የተለየ ነገር አላት ወይ ብለው እስከመጠየቅ ደርሰው የነበረ ሲሆን ፤ ነገር ግን ከጥቂት አመታት በኋላ የኦባማ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣ ከሁለት አመት በኋላ ግን የእዳ ጣሪያውን ከፍ ለማድረግ በኮንግሬሱ በአስተዳደሩ መሀከል የታየው እሰጥ አገባ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ የችግሩን ጥልቀትና ስፋት ህዝቡ እንዲረዳው አስችሎታል ። 


ነገር ግን ይሄው እዳ ውሎ አድሮ የመንግስት ተቋማትን እንዲዘጉ እስከማሳሰብ ድረስ ደርሷል ፣ አንዳንድ ክፍለ ሀገራትና ከተሞችም ከእዳ ብዛት የተነሳ የኪሳራ መክሰራቸውን እስከማወጅ መክሰራቸውን እስከማሳወቅ (File for Bankruptcy) ድረስ ደርሰዋል ። ይህም ካርል ማርክስ ይህን በውስጣዊ ተቃርኖዎች የተሞላው የካፒታሊዝም ስርአት የራሱን መቃብር ይቆፍራል ይለዋል ።በግብር በሚሰበሰብ ገንዘብ የባንክ ብድርንና ወለድን መክፈል እጅግ ፈታኝና በረጅም ጊዜ ሀብታም ለሆነ ሀገርም ቢሆን ፈታኝ እየሆነ እንደሚሄድ  የታወቀ ሀቅ ነው ።

ኬነስ የአንደኛው የአለም ጦርነት ሲያበቃ አሸናፊ ሀይሎች በቬርሳሌስ ስምምነትአማካይነት በጀርመን ላይ የተጋነነ ትርጉም የለሽ ቅጣትን መጣላቸው ቆይቶና ውሎ አድሮ ችግርን እንደሚያመጣ ከተረዱና እና ካስጠነቀቁ ጥቂት ሰዎች አንዱ ነው ። ይህ ብቻ ሳይሆን የሁለተኛው የአለም ጦርነት እንዳበቃ በጎደለው እሚሞሉ ፣ ባነሰው የሚጨምሩ የምጣኔ - ሀብት አለም አቀፍ ተቋማትን መፍጠርን አስፈላጊነት በመረዳት የአለም የገንዘብ ድርጅትንና የአለም ባንክ እንዲቋቋሙ አስተዋፅኦ አድርጓል ።


... 1930ዎቹ የአለም የታላቁ ምጣኔ - ሀብት ቀውስ ከተከሰተ በኋላ ፣ ቀደም በሎ የነበረው የብሉይ የምጣኔ - ሀብት አስተዳደር በምጣኔ - ሀብቱ ውስጥ ችግር ቢፈጠር የሚለውን ትኩረት አላደረገበትም ማለት ይቻላል ።


ይሁን እንጂ የኬነስ ሀሳብ በምጣኔ - ሀብት ሙያ ውስጥ መሰረታዊ የአስተሳሰብ ልዩነትንና ፣ የርእዮተ - አለም መስመር መለያየትን ፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን እሚያሳይ ነው ። የብሉይ አስተሳሰብ ፍልስፍና የኬነስ አስተሳሰብ መሰረታዊ የፍልስፍናዎቹ ልዩነቶች ኬነስ ሙሉ ለሙሉ ገበያ የምጣኔ ሀብትን ችግር እንደማይፈታ የተረዳ ሲሆን ፣ ወደም ባለው በብሉይ የምጣኔ - ሀብት አስተሳሰብ ግን ምጣኔ - ሀብት ውስጥ ችግር ቢከሰት ራሱ ገበያው ያስተካክለዋል የሚለውን ሀሳብ የተቀበሉ ሲሆን ይሄንን አስተሳሳብ ለመፈተን ፣ ወይም ለማቀየር አልሞከሩም ።


ኬነስ ግን ይህንን በመረዳት እ.ኤ.አ. በ1946 ዓ.ም. ባሳተመው ፈር - ቀዳጅ የሆነ መፅሀፍስለ ገንዘብ ፣ ወለድና አጠቃላይ የምጣኔውን እኩልነት የሚያስረዳውን ሀሳብ ማፍለቅ ችሏል ።ይሁን እንጂ የዳግመኛ ብሉይ ምጣኔ - ሀብት አስተሳሰብ (Neo - Classical) አራማጆች(Objective) ነው ተብሎ ሲወሰድ የኬነስና የሱ ዳግመኛ ተከታዮች ግን እንደየሁኔታው (Subjective) ነው ለት ይቻላል ። ከቅርብ ግዜ ወዲህ የኬነስ ተከታዮችና አራማጆች በምጣኔ - ሀብቱ ውስጥ ተደማጭነታቸው እየጨመረ በመምጣቱ በርካታ የኖቤል ሽልማትን ብንወስድ በአብዛኛው የኬነስና የእርሱ ተከታዮች (ኒው ኬነዢያንስ» ናቸው የሚወስዱት ። 

ልጓም የሌለው ካፒታሊዝም ወይም ለኩባንያዎች ጥቅም ብቻ የቆመ የኮርፖሬት ካፒታሊዝም ውጤቱ የማያምር ሲሆን ፤ በምእራቡ አለም እንድታየው ውሎ አድሮ የስርአቱን ህጋዊ ተቀባይነትና ውክልናን ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ሁሉ ሊያደርግ ይችላል ።የምርጫው ስርአት ራሱ በኩባንያዎች እንደፈለገው ሁኖ እሚጠመዘዝ ከሆነ ፣ በምርጫ ስርአቱ ላይ ብዙሀኑ ህዝብ አመኔታ እንዲያጣ ብሎም ስርአቱ ህጋዊ ተቀባይነቱን (Legitimacy) እንዲያጣ ያደርጋል ። 


የኬነስ አስተሳሰብ ግን እንደው ፍፁም ሁልግዜ የሚሰራ ነው አይባልም ። ዋናው የኬነስ እና የእርሱ ተከታዮች ፍልስፍና ችግሩ ፣ መንግስት በምጣኔ - ሀብቱ ውስጥ ያለው ተሳትፎ ምን ድረስ ነው የሚለው ነው ። ይህም እ.ኤ.አ. በ2008 ዓ.ም.ከተከሰተው የአለም የምጣኔ - ሀብት የገንዘብ ቀውስ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ይህንን ችግር ለመፍታት የኬነስ ሀሳብ ነው ዳግመኛ በተግባር ላይ የዋለው ። የቡሽም ሆኑ የኦባማ አስተዳደር ይህንን ሀሳብ የተከተሉ ሲሆን፣ ምን ድረስ ነው መንግስት በምጣኔ - ሀብቱ ውስጥ መሳተፍ ያለበት የሚለው ላይ ግን ስምምነት የለም ። በተለይም ከዚህ ቀውስ በኋላ መንግስታት በተደጋጋሚ የመንግስትን ወጪ ቢጨምሩም ፣ ተጨማሪ ገንዘብ ወደ ምጣኔ ሀብቱ ቢለቁም ፣ ምጣኔ ሀብቱ ግን ካለበት እንኳን ሊንቀሳስ ጭራሽ ወደ ባሰ እዳ ውስጥ መዘፈቅና ፣ የገንዘብ ግሽበትን ማሳየቱ አልቀረም ። 


ይህ ቀውስም ሆነ በ1930ቹ የተከሰተው ለታላቁ የአለም ምጣኔ - ሀብት አዘቅት (The Great Depression) መነሻቸው አሜሪካ ሆኖ ለተቀረው አለምም የተረፉ ናቸው ሁለቱም ቀውሶች ምንም እንኳን አሜሪካን አገር ውስጥ ቢነሱም ቀጥሎ ወደ አውሮፓ ብሎም ወደ ተቀረው የአለማችን ክፍል ተዛምተዋል ።  ይህም አሜሪካ ካላት ግዙፍ የገንዘብና የምጣኔ - ሀብት አቅም ምክንያት የአለም ምጣኔ - ሀብት በአሜሪካ እድገትና ውድቀት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ እነሱ ችግር ውስጥ ከገቡ ለሌላውም የመትረፍ እድሉ ሰፊ ነው ። ምንም እንኳን አሁን አሜሪካ በ1930ዎቹ ከነበራት ከአለም አመታዊ ምርት ወደ ግማሽ እሚጠጋውን እምታመርት ሀገር የነበረች ቢሆንም ከአውሮፓውያን ጋር ስትደመር በአለም ላይ ያለውን አመታዊ ምርት 80 በመቶውን በዛን ዘመን ያመርቱ የነበሩት አውሮፓና አሜሪካ ነበሩ ። የተቀረው አለም በድህነት ፣ በእርስ በእርስ ጦርነት ፣ በቅኝ ግዛት ፣  በየሚማቅቅበት ዘመን ነበረ ።

የምጣኔ - ሀብት ባለሙያዎች ዘንድ በዚህ ጉዳይ ላይ ሙሉ መግባባት የሌለ ሲሆን፣ በተለይም መንግስት ዝም ብሎ የመንግስት ወጪ ቢያወጣ የዋጋ ግሽበትንና የገንዘቡ የመግዛት አቅም መቀነስን ያስከትላል ። በተለይም እ.ኤ.አ. ከ2008ቱ ቀውስ ወዲህ የምእራብ ሀገራት ከፍተኛ የመንግስት ወጪን በማውጣት ቀጣይነት ያለው ዘላቂ የሆነ የስራ እድል እንዲኖር ማድረግ ግንምን ያህል ድረስ ሊሰራ እንደሚችል አጠያያቂ ነው ።አሁን ባለው የምእራባውያን የምጣኔ - ሀብት አደረጃጀት የመንግስት ገንዘብ ለጊዜው ካልሆነ በስተቀር ፣ዘላቂ የሆነ ቋሚ የስራ እድልን ሊፈጥር አይችልም ። ባደገ የካፒታሊስት ምጣኔ - ሀብት ውስጥ ለጊዜው የግሉ ክፍለ - ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ ከማገዝ በስተቀር ፤ በረጅም ግዜ በመንግስት ገንዘብ ቋሚ የሆነና ለብዙ ዜጎች የሚሆን በርካታ የስራ እድሎችን መፍጠር አይችልም ።

Thursday, March 7, 2013

Monday, March 4, 2013

የአፍሪካ ቀንድ የተወሳሰበ ነባራዊ ሁኔታ



    የአፍሪካ ቀንድ በአለም ላይ ካሉ አደገኛ ከሚባሉ አካባቢዎች አንዱ ነው ። ለዚህም በአንደ መካከለኛው ምስራቅ በአለም ላይ ካሉ አደገኛ ከሚባሉ ቀጠናዎች አንዱ ነው ። ይህ ክልል በተደጋጋሚ በድርቅና እርሱንም ተከትሎ በረሀብ የሚጠቃ ሲሆን በአለም ላይ እጅግ ደሀ ከሚባሉ አካባቢዎችም ዋነኛ ነው ።

    የአፍሪካ ቀንድ አገራት ላለባቸው ችግሮች ምንጭ በርካታ ምክንያቶች አሉ ። አንዳንዱ ችግር ከቅኝ አገዛዝ ዘመን የወረሱት ሲሆን ፣ በአንፃሩ ደግሞ ሌሎች ደግሞ ክልሉ ራሱ ካለው ስልታዊ መልከአ ምድራዊ አቀማመጥ የተነሳ የተከሰቱ ናቸው ። ለዚህም ስልታዊነቱ ለመካከለኛው ምስራቅ ያለው ቅርበት ፣ እንዲሁም የአለም የንግድ ዋነኛ መስመር የሆነው የቀይ ባህር ተዋሳኝ መሆኑ ፣ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ከሰሜን አፍሪካ ለጥቆ የአፍሪካ ቀንድን እጅግ አስፈላጊና ስልታዊ «ስትራቴጂክ» ያደርገዋል ።


       ይህ ብቻም ሳይሆን ለምእራባውያንም ሆነ በአረቡ አለም ሁነኛ ስልታዊ የሆነችው ግብፅ ህልውና የሆነው የናይል ወንዝም እሚነሳው ከዚሁ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ሲሆን ፣ ግብፅም በበኩሏ የራሷ የሆነ መሰረታዊ ህልውናዋ ከዚሁ ክልል ጋር የተያያዘ ነው ።   


    አንዳንዶቹ የአፍሪካ ቀንዱ አገራት በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ሲኖሯቸው እንደ ኢትዮጲያና ኬንያና ዩጋንዳ ያሉት ፣ በአንፃሩ ደግሞ እንደ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ያሉት ደግሞ በጎሳ ላይ የተመሰረተ ማህበረሰባዊ አወቃቀርን ይከተላሉ ።


    በአፍሪካ ቀንድ ከተከሰቱ ዋና ዋና ሁነቶች መሀከል በኢትዮጲያ ውስጥ ለበርካታ አስርት አመታት ሲካሄድ የቆየው ጦርነትና ማብቃትና ይህን ተከትሎም የኤርትራ ራሷን የቻለች አገር መሆን ፣ በሱዳንም እንዲሁ  በሰሜንና በደቡብ ሱዳን መሀከል ሲደረግ የቆየው ጦርነት ማብቃትና እንዲሁም ደቡብ ሱዳንም ራሷን የቻለች ሀገር ሆና መወለድ ፣ የክልሉን ጆኦ - ፖለቲካዊ አሰላለፍ ከለወጡ ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው ። ከዚህም በተጨማሪ ቀድሞ የተረጋጋች ሀገር ሆና ከቅኝ አገአዛዝ ነፃ ከወጣች ወዲህ በአንፃራዊ ሰላም የኖረችው ኬንያ ባልተጠበቀ ሁኔታ ምርጫዎችን ተከትሎ በእርስ በርስ ውዝግብ ውስጥ መግባት መጀመሯ ለአካባቢው አንደ ስጋትን የጨመረ ጉዳይ ነው ። 



        በአንፃሩ በእርስ በርስ ጦርነትና በአምባገነናዊ አገዛዝ ስር የነበሩት ኢትዮጲያና ፣ ኡጋንዳ በተረጋጋ ሁኔታ ምጣኔ - ሀብቷን ማሳደግ መጀመራቸው ፣ ተጠቃሽ ከሆኑ የአፍሪካ ቀንድ ሁነቶች ዋነኞቹ ናቸው ። ይህ ክልል ለምጣኔ- ሀብት እድገት ትልቅ እምቅ አቅም ያለው ክልልም መሆኑ የታወቀ ነው ። በርካታ ወንዞችን አቅፎ የያዘና ለግብርና አመቺ የሆነ አካባቢ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ደቡብ ሱዳን ያሉት የነዳጅ ሀብት ባለቤትም ጭምር ናቸው ። 

      የወደፊት እድገቱን በተመለከተ የማደግ እምቅ አቅሙ ከፍተኛ ሲሆን ፣ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ካላቸውና ህዝባቸው እያደጉ ካሉ አገራትም ይገኙበታል ።

       ይህም በመሆኑ የምእራባውያን ትኩረት በዚህ ክልል እያደገ የመጣ ሲሆን ፣ በተለይም በሶማሊያ የባህር ጠረፎች የተከሰተው የባህር ላይ ውንብድና ፣ አልቃኢዳን መሰል አክራሪዎች በአካባቢው ማቆጥቆጥ ሌላው የሀያላኑን ትኩረት እንዲስብ ሰበብ ሆኗል ።

     የሀያላኑን ትኩረትን መሳቡ በአንድ በኩል አካባቢው አለም አቀፋዊ ትኩረትን እንዲያገኝ ሲያደርገው ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሩቅ ያሉ ሀያልላን ጥቅማቸውን ለማስከበር በሚያደርጉት ድርጊት ለአካባቢው አለመረጋጋት የራሱን አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይችላል ። የአሜሪካ በፓኪስታን ፣ በአፍጋኒስታንና በየመን መግባቷ አካባቢዎቹን ማተራመሱ እና መረጋጋት ማጣታቸው የታወቀ ሲሆን ፣ በድሮኖች (drons) አማካይነት አሜሪካ በአካባቢው የምትፈፅማቸው የአየር ጥቃቶች ለበርካታ ሲቪሎች መገደልና ለሀገራቱ የውስጥ ፖለቲካ አለመረጋጋት ዋነኛ ምክንያት መሆኑም ይታወቃል ። ምስራቅ አፍሪካም ምእራባውያኑ በዚህ መንገድ የሚገቡ ከሆነ መረጋጋቱን የማጣት አደጋ ውስጥ ሊገባ ይችላል ።