Tuesday, July 2, 2019

ህሩይ ወልደ ስላሴ

የዛሬው የታላላቅ ሰዎች ዝግጅታችን እውቁን የአማርኛ ስነጽሁፍ አባት ህሩይ ወልደ ስላሴን ይዘክራል፡፡

ባሕር ዳር፡ ህዳር 30 / 2009 ዓ.ም (አብመድ) ህሩይ ወ/ስላሴ ከአባታቸው አቶ ወልደ ስላሴ እና ከእናታቸው አመተ ማርያም ዜና ግንቦት 1 1871 ዓ ም የተወለዱ ሲሆን በአባታቸው በኩል መርሃ ቤቴ በእናታቸው ወገን ደግሞ መንዝ ናቸው ፡፡
የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት አባታቸው ልጃቸውን ለማስተማር ቆርጠው በመነሳታቸው ህሩይን በሰባት አመታቸው እንዲማሩ አቅራቢያቸው ወደሚገኝ ቤተክርስቲያን ላኳቸው ፡፡
በቀለም አያያዛቸው በመምህራቸው ደብተራ ስነ ጊዮርጊስ አድናቆትን ያተረፉት ህሩይ በሁለት አመት ውስጥ የግእዝ ትምህርትን አቀላጥፈው መናገር ሲችሉ የፊደል አጣጣልን ግን ዘግይተው ነው የተለማመዱት ፡፡

የህሩይን ምጡቅ ችሎታ የተረዱት አባታቸው የተሻለ ትምህርት እንዲማሩ እድሜያቸው አስር ዓመት ሲሆን መድሃኒ አለም ወደተባለ የአብነት ትምህርት ቤት በመላክ ለልጃቸው መማር ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡
በጊዜ ሂደትም ህሩይ ውዳሴ ማርያምን እና ሌሎችንም የቅዳሴ መጻህፍት በማጥናት የዲቁና እና የቅስና ማእረግን አግኝተዋል፡፡
ህሩይ በዕውቀት እንዲታነጹ ጉልህ እገዛ ያደረጉላቸው አባታቸው በ53 አመታቸው በሞት ሲለይዋቸው ህሩይ ገና የ13 አመት ታዳጊ ነበሩ ፡፡

ህሩይ በአባታቸው ሞት ቢደናገጡም ትምህርታቸውን በጀመሩበት ትምህርት ቤት አጠናክረው በመቀጠል ከቀለሙ ጎን ለጎን ወደእርሻው ፊታቸውን በማዞር የተዋጣላቸው አርሶአደር ሆኑ፡፡
በግብርናውም ዘርፍ ተጠቃሚ በመሆን ብዙ የቀንድ ከብት እና ፈረሶች ማርባት ችለዋል ፤ምንም እንኳ ጥሩ የፈረስ ጋላቢ ባይወጣቸውም ፡፡
የህሩይ የስነ ጽሁፍ ዕውቀት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ የሰላሌ አገረ ገዥ የደጃዝማች በሻህ የግል ጸሃፊ እስከ መሆን ደርሰዋል ፡፡
በጸሃፊነት ብዙም ሳይቆዩ የንጉስ ሃይለስላሴ አባት የራስ መኮንን ጸሃፊ ሆነው አገልግለዋል ፡፡
በኋላም ወደ ሸዋ - አድአ በርጋ በመጓዝ ለቀኝ አዝማች መቁረጭ በግብር መዝጋቢነት ተቀጥረው ሰርተዋል ፡፡
በዚህም ስፍራ ተወዳጅነት በማትረፋቸው ከአሰሪያቸው ‹ የሆነው ፍሬ ›የሚል ስያሜን አግኝተዋል ፡፡

ህሩይ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ይህ ስማቸው በመግነኑ የተነሳ በርካታ መኳንንቶች ለማሰኮብለል ጥረት ቢያደርጉም ህሩይ ግን በቀላሉ የሚደለሉ አልሆኑም ፡፡
የቀኝ አዝማች መቁረጭ እና የህሩይ መለያየት ቁርጥ የሆነው የጣሊያንን ወረራ ለመመከት ዳግማዊ ዓጼ ምኒልክ በ1887 ዓ.ም የክተት አዋጅ ባሳወጁበት ወቅት ነው ፡፡
አዋጁን ተከትለው ቀኝ አዝማቹ ጠላትን ለመፋለም ወደጦር ግንባር በመዝመታቸው የስራ ግንኙነታቸው ተቋረጠ ፡፡
ህሩይ በጣሊያን ወረራ ወቅት ከጽህፈት ስራቸው በመነጠል ለተወሰነ ጊዜ በትውልድ ቀያቸው ቆይተዋል ፡፡

ከጦርነቱ በኋላ ህሩይ የመጽሃፍ ቅዱስ ጥናት በእንጦጦ ኪዳነምህርት አከናውነዋል ፡፡
የህሩይ የስነ ጽሁፍ ስራ እየናኘ በመምጣቱ የዳግማዊ ምኒልክ የግል ታሪክ ጸሃፊ የሆኑት ጸሃፌ ትዕዛዝ ገብረ ስላሴ አስጠርተዋቸው ከተወያዩ በኋላ አንድ ቁና እህል ወይም 5 ኪሎ ግራም እህል በወር እየተሰጣቸው ለመስራት ወሰኑ ፡፡

በሁለት አመት ቆይታቸው ህሩይ 27 ያህል መጽሃፍትን በማጥናት መተርጎም ችለዋል፡፡
ይህን እንዳጠናቀቀቁ ከዳግማዊ ምኒልክ አራት ያህል ሽልማቶችን ከአንድ የእጅ ሰአት ጋር ተሸልመዋል ፡፡
ህሩይ የተለያዩ የስነጽሁፍ መጻህፍትን እና ፍትሃ ነገስት የተባለውን ታሪካዊ መጽሃፍ አጥንተዋል ፡፡
ቤተሰብ ለመመስረት የተነሱት ህሩይ የጸሃፈ ትዕዛዝ ገብረስላሴን ልጅ እንዲያገቡ ቢታጭላቸውም በድህነታቸው ምክንያት ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡
ይሁን እንጂ ሃሳባቸውን ለማሳካት ወደ ቀዬአቸው ደን አቦ በመመለስ ሚስት ሲያፈላልጉ ከቆዩ በኋላ ግንቦት 17 1895 ዓ.ም. ጎጆ ወጡ፡፡

ህሩይ ሚስታቸው ባተሌ የቤት እመቤት ከሚባሉት ተርታ በመሆናቸው ለስኬታቸው ቁልፍ ሆነዋል ፡፡
በ1882 ዓ ም. በኢትዮጵያ ድርቅ ተከስቶ በርካታ እንሰሳት በማለቃቸው ንጉስ ምኒልክ ከፈረንሳይ ሃገር የእንሰሳት ዶክተሮችን ለማስመጣት ወሰኑ ፡፡
ሆኖም ወደፈረንሳይ ተጉዞ ለመደራደር ብቃት ያላቸው ህሩይ መሆናቸውን ወልደ ጻድቅ የተባሉ የቤተመንግስት ሰው በመጠቆማቸው እንዲሰሩ ግዳጅ ተሰጥቷቸው ወደ ፈረንሳይ አቅንተዋል ፡፡
እዚያም የተሰጣቸውን አደራ በብቃት ለመወጣት ቡድኑን አስተባብረው ተልዕኳቸውን አሳክተዋል ፡፡
በ1890 ዓ.ም. ህሩይ ወርሃዊ ደመወዛቸው ወደ 10 ብር ከፍ ብሎላቸው የተጣለባቸውን የስራ ሃላፊነት በተሻለ መንገድ ወደ መስራት ተሸጋገሩ ፡፡

ቀጣዩን ክፍል ሳምንት እናቀርብላችኋለን

ለህብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!
የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት

No comments:

Post a Comment