የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተግባርን የሚቆጣጠረው (UN Watch) ኤርትራ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ተመልካች ምክር ቤት አባል መኾን አይገባትም ሲል ተቃውሞውን ገለጠ።
ለዚህም እንደ ምክንያት ያቀረበው ኤርትራ ዓለም አቀፍ ድርጅቱ የሚጠይቃቸውን መሠረታዊ መስፈርቶች አታሟላም የሚል ነው። የUN Watch ዋና ዳይሬክተር ኃይለል ኖየር፦ ኤርትራ «የዘፈቀደ እስር፣ ግድያ፣ አስገዳጅ ሥራ፣ ስውር እስር፣ ቁምስቅል፣ ፍትኃዊ የፍርድ ሒደት እጦት፣ የሚፈጸምባት የመናገር፣ የፕሬስ፣ የመሰብሰብ እና የኃይማኖት ነጻነት የሌለባት ሀገር ናት» ሲሉ በትዊተር የማኅበራዊ ድረገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ኤርትራን ጨምሮ ስድስት ሃገራት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ተመልካች አካል ለመኾን በዛሬው እለት ምርጫ እንደሚካሄድ ዓለም አቀፉ ድርጅት ዐስታውቋል። እስካሁን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ተመልካች አካል አባላት ኢራቅ፣ ኩባ፣ ቻይና፣ ኳታር፣ አንጎላ፣ ቡሩንዲ፣ ፓኪስታን፣ ቬኔዙዌላ፣ የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፣ አፍጋኒስታን፣ ሣዑዲ ዓረቢያ እና ዩናይትድ ዓረብ ኢሚሬትስ ናቸው።
«ክፉ የኾነውን የኤርትራ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ዳኛ እንዲኾን መምረጥ ሁሉን በእሳት ካላያያዝኩ የሚልን ግለሰብ የከተማው እሳት መከላከያ ኃላፊ እንደማድረግ ነው» ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተግባርን የሚቆጣጠረው (UN Watch) ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል። ቀደም ሲል ኤርትራን ጨምሮ ስድስት ሃገራት 18ቱ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ተመልካች አካል ውስጥ ሊቀላቀሉ አይገባም ሲሉ በዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ እና አውሮጳ የሚገኙ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ገልጠው ነበር። ተቃውሞ የቀረበባቸው ሃገራት ኤርትራ፣ ባህሬን፣ ባንግላዴሽ፣ ካሜሩን፣ ፊሊፒንስ እና ሶማሊያ ናቸው።
No comments:
Post a Comment