Friday, December 14, 2018

የህወሃት እጣ ፈንታ


#የህወሓት የወደፊት እጣ ፈንታ

#ህወሓት ሁለት ወሳኝ #የፖለቲካ ሀብቶች አሉኝ #ብሎ ያስባል፡፡ የመጀመሪያው የትግራይ ህዝብ ሲሆን ሁለተኛው የቅራኔ ፖለቲካ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት አንደኛውን የፖለቲካ ሀብት ተነጥቆ በሁለተኛው የፖለቲካ ሀብቱ ላይ ወሳኝ ትግል እያካሄደ ይገኛል፡፡

የመጀመሪያው ሀብቱ የሆነው የቅራኔ ፖለቲካ ህወሓት የፖለቲካ የዘር ሀረጉ ከሚመዘዝበት ኮሚኒስታዊ እሳቤው የመነጨ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በኮሚኒስታዊ ፈላስፎች እሳቤ መሰረት በማህበረሰብ ውስጥ እርስ በእርሳቸው የሚፃረሩ ኃይሎች የመኖራቸው ጉዳይ የተፈጥሮ እውነታ ነው፡፡ በእነዚህ ተፃራሪ ኃይሎች መካከል ደግሞ ምንጊዜም ተቃርኖ አለ፡፡ ተቃርኖውም የፖለቲካ ትግሉ ማዕከላዊ ነጥብ ሆኖ ያገለግላል፡፡
በአንድ ልቦለድ የታሪክ አወቃቀር ውስጥ ግጭት ወይንም ኮንፍሊክት ከሌለ ታሪክ የለም” እንደሚባለው በሌኒንስታዊ አስተሳብህም ቅራኔዋ ከሌለች የአንተም ፖለቲካ ሊኖር አይችልም፡፡ እናም በዚህ እሳቤ መሰረት የቅራኔዋን የፖለቲካ ከሰል እያራገቡ እሳቱን ማቀጣጠል የፓርቲ ህልውና ጉዳይ ነው፡፡

ህወሓትም በቀደመው የትግራይ ማርክሲስት ሌኒንስት ወይንም ማሌሊት አስተሳሰቡ ይህች የቅራኔ ፖለቲካ በሚገባ ተክኖባታል፡፡ የቀድሞው ህወሓት መራሹ ኢህአዴግም ቢሆን ይህችን የቆየች ዘመን ያለፈባት የፖለቲካ ካርድ ይዞ በቅራኔ ፖለቲካ ጨዋታ እድሜውን ሲገፋ ቆይቷል፡፡ ነፍጠኛው ፣ትምክህተኛው፣ ጠባቡ፣ ኒኦሊብራሉ የሚሉት ፍረጃዎችና የፖለቲካ ብሂሎች ከዚሁ ከድርጅቱ ኮሚኒስታዊ ባህሪ የመነጩ ናቸው፡፡
የሚታረቅ ቅራኔ ሲሉ ጥልቀት የሌለው ተቃርኖ ሆኖ በውይይትና በድርድር ሊፈታ የሚችል ማለታቸው ሲሆን የማይታረቅ ተቃርኖ ሊፈታ የሚችለው ግን በማሸነፍ እና በመሸናነፍ ብቻ ነው፡፡ በኮሚኒስቶች የፖለቲካ ዶክትሪን መሰረት የፖለቲካ ድርጅት ከሆንክ በህይወት ለመኖር የምትታገለው ደመኛ ጠላት ሊኖርህ ይገባል፡፡ የሚፈረጅ ጠላት ከሌለ ትግል፣ ፖለቲካ፣ ርዕዮተ ዓለም፣ መታገል፣ ማታገል የሚባሉ ነገሮች የሉም፤ አይኖሩምም፡፡ ለዚህ የሚሆን ጠላት ከሌለህ ደግሞ በራስጌም በግርጌም ብለህ አንድ ጠላት መፈጠር አለብህ፡፡ ማርክሲስት ሌኒንስትነት ያለተቃርኖ በህይወት ሊኖር የማይችል ፖለቲካ ነው፡፡
እናም ህወሓት በተካናት የቅራኔ ፖለቲካ በተለይ ትምክህተኛና ጠባብ ብሎ በፈረጃቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል በተፈጠረው የተካረረ ቅራኔ የፖለቲካ የኃይል ሚዛኑን ለሶስት አስርት ዓመታት ያህል አስጠብቆ ማስኬድ ችሏል፡፡ ሆኖም የቅራኔ ፖለቲካው ሴራ ዘግይቶም ቢሆን የገባቸው የቀድሞው የፖለቲካ አጋሮቹ፤ በተለይ በኦሮሞና በአማራ መካከል ምንም አይነት ቅራኔ እንደሌለ በማሳየት የትግሉን አቅጣጫ ከቅራኔ ፖለቲካ መስመር ማውጣታቸው የህወሓትን የቅራኔ ፖለቲካ የበርሊን ግንብ ንዶታል፡፡

No comments:

Post a Comment