Thursday, August 15, 2013

ምጣኔ-ሐብት ማዘመን



የንግድ ስርአቱን ማዘመን
በሀገራችን ያለ የንግድ ስርአት ዘመናዊ መሆንና ይበልጥ በገበያው አንፃር መቃኘት መቻል ይኖርበታል ። በአሁኑ ወቅት ያከው ለው የንግድ ስርአት አንድ ነጋዴ ወይንም የተወሰኑ ነጋዴዎች ተሰብስበው ገበያውን ለተወሰነ ጊዜ የዋጋ ግሽበትን ሊያስከትሉበት ይችላሉ ። ነገር ግን ዘላቂ የሆነ የዋጋ ግሽበትን ሊያስከትሉ እንደማይችሉ ግን ግልፅ ነው ። በአንድ ወቅት ገበያ ላይ ያለውን ጨው ከገበያ በማስወጣትና በመደበቅ የጨው ዋጋ ሶስትና አራት እጥፍ ሊያድግ መቻሉና ገበያ ትርምስን መፍጠሩ የሚታወስ ነው ።
የንግድ ስርአቱ ዘመናዊ አለመሆኑና አንድ ደርዝ አለመያዙ ለመንግስትም ቢሆን ንግዱን በሚፈልገው የፖሊሲ አቅጣጫ ለመምራት እንዳላስቻለው ግልፅ ነው ። የንግድ ስርአቱ ሰንሰለት መርዘም ፣ መሀል ላይ የደላላ መግባት አንዲሁም የትራንስፖርት ዋጋው መናር ፣ እንዲሁም አግባብ የሆኑና ዘመናዊ የሆኑ የማቀዝቀዣና የማስቀመጫ ፣ የተመረተው የግብርና ምርት ሳይበላሽ ለገበያው የሚቀርብበት የተፋጠነ መንገድ አለመኖር ፣ በምርት ወቅት የሚደርስ ብክነት ከውጭ ከመጣው የዋጋ ንረት በተጨማሪ በሀገራችን ላለው የምግብ ዋጋ እየናረ መሄድ ዋነኛ ውስጣዊ ምክንያቶች ናቸው ።
    በዚህም የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት መሰናከሉ ያሳሰበው መንግስት አለም አቀፍ ቸርቻሪዎችንና ትላልቅ ሱፐር ማርኬቶችን ለማስገባት እስከ ማሰብ ደርሷል ። በነገራችን ላየጥ  ይ ህንድ በሀገሯ ተመሳሳይ የዋጋ ንረትና የአቅርቦት እጥረት ስላጋጠማት ዓለም አቀፍ ሱፐር ማርኬችን በሀገሯ እንዲሰሩ ለመፍቀድ ተገዳለች ። ተቃውሞ ቢገጥመውም የህንድ መንግስት ግን ፖሊሲውን ተግባራዊ በማድረግ ለሸማቿቾቹ የተሻለ አማራጭን ለማቅረብ ችሏል ። ዘርፉ ዋነኛ አትራፊ አንደመሆኑ የውጭ ባለሀብቶች በዚህ ዘርፍ እንዲገቡ የአገር ውስጥ ቸርቻሪዎች  ደስተኛ እንደማይሆኑ ግልፅ ነው ።
የውጭዎቹ አቅራቢዎች ትላለቅ እንደመሆናቸው አነስ ባለ ዋጋ ፣ እንዲሁም ከአለም ገበያ በሚገዙበት ወቅት አነስ ባለ ዋጋ ስለሚገዙ የተሻለ የዋጋ ቅናሽን ለሸማቹ ሊያቀርቡ ይችላሉ የሚል  ግንዛቤ አለ 
   
የአክስዮንና የካፒታል ገበያዎችን መክፍት
ሀገራችን የአክስዮን ገበያ በሀይለስላሴ ስርአት የነበረ ቢሆን «ካፒታሊዝም ሊያቆጠቁጥ ሲል ደረስኩበት» በሚለው የደርግ ዘመን እንደ ሌሎቹ የግል የአክስዮን ኩባንያዎች በመወረሱ ምክንያት ገበያው የለም ። ነገር ግን በአሁኑ  ወቅት ምጣኔ-ሀብቱ እደያደገ ባለበት ሁኔታ የአክስዮን ገበያ ቢኖር በአንድ በኩል ኩባንያዎች አዳዲስ ኢንቨስትመንትን ለማካሄድ ፣ የሚፈልጉትን ካፒታል በቀላሉ ከገበያው ማሰባሰብ ያስችላቸዋል ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአክስዮን ገበያውን እንቅስቃሴ በማየት የምጣኔ-ሀብቱን እንቅስቃሴ መቆጣጠርና መመልከት ይቻላል ። በምእራቡ ዓለም የአክስዮን ገበያው ጥሩ አእንቅስቃሴ ላይ ካለ የኢኮኖሚውን ጤነኛነት ሲያሳይ በአንፃሩ አክስዮን ገበያው መውደቅ ኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ችግር ለመንግስትም ሆነ ለመዋእለ-ንዋይ አፍሳሾች ይጠቁማል ።
ከዚህም በተጨማሪ የውጭ ባለሀብቶች በቀላሉ መዋእለ-ንዋያቸውን በአክስዮን ገበያው አማክነት የሚፈልጉትን ኩባንያ አክስዮኖችን በመግዛት ወደ ሀገሪቱ ኢንቨስት ማድረግ ያስችላቸዋል ። የአክስዮን ገበያ በአውሮፓ እንኳን ከተጀመረ ለምሳሌ በኔዘርላንድ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረና በጣም ረጅም እድሜን ያስቆጠረና የሀገራትን ኢኮኖሚ ሀይል እየሰጠ የሚያሞቅና እድገትን የሚያፋጥን ነው ።
የውጭ ኢንቨስትመንቱን የማፋጠን ሚናንም ሊጫወት ይችላል ። ይህም በተዘዋዋሪ መንገድ ኢኮኖሚውን ለውጭ ይበልጥ ክፍት ማድረግ ማለት ነው ይህን አንድን ኢኮኖሚ ለው ጭ ክፍት ሲያደርገው ከውጭ የሚፈጠር መልካምም ሆነ ጥሩ አጋጣሚ የራሱ ተፅእኖ እንዲጨምር ማድረጉ የማይቀር መሆኑ ግልፅ ነው ። ይህንም የውጭ ምንዛሬ እጥረት ላለባትና የውጭ መዋእለ - ንዋይ በበቂ ሁኔታ እየገባ ያለባት ሀገር በሆነችው ሀገር እጥረት በበቂ ሁኔታ ላልገባባት ኢትዮጲያ የአክስዮን ገበያ መክፈቱ ለውጭ መዋእለ-ንዋይ መፍሰስና ለውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የተሻለ አቅምን የሚፈጥር ነው ።  
የውጭ ኢንቨስተሮች በአንድ ጊዜ ገንዘባቸውን በሚያወጡበት ወቅት -  ክፍት ማድረጉ ከውጪ ለሚመጡ የኢኮኖሚ ቀውሶች የመጋለጥ እድልን የሚያሰፋ ቢሆንም የቀውስ ዘመናት  አጭር እንደመሆናቸው ዘግቶ ከመቀመጥ ክፍት አድርጎ ከአለም አቀፍ ብለፅግና መጋራት የተሻለ ነው ።         
ኢ-ኮሜርስን (E-Commerce) እና የዘመናዊ ክፍያ ስርአትን ማዘመን
በሀገራችን ያለው የየክፍያ ስርአት ገንዘብን ፣ ቼክንና የክፍያ ማሽንን «ኤቲኤምን » የሚጠቀም ነው ። ነገር ግን እስካሁን ድረስ የክፍያ ስርአቱ ወደ ክሬዲት ካርድ (Credit Card) እና ዴቢት ካርድ ደረጃ አልደረሰም ። በዚህም ምክንያት በሀገራችን የኢ-ኮሜርስ (E-Commerce) እሚባል ነገር የለም - የክፍያ ስርአቱ ባለመኖሩ ምክንያት ነው ።
የድረ-ገፅ መገበያየት ደረጃ ባንደርስም ነገር ግን ወደዛ የሚደረገውን ሽግግር ለማጠናከር የሚሰሩ ስራዎችን ከአሁኑ መስራትና ቀስ በቀስ በድረ - ገፅ አማካይነት ግብይቶችን በማካሄድ በአንድ በኩል በሀገር ውስጥ የቀለለ የግብይት ስርአትን መፍጠር ሲቻል ከውጭ ሀገር ሆኖ ወደ ሀገር ቤት ማንኛውንም ነገር መግዛት ለሚፈልግ በቀላሉ ካለበት ሀገር ሆኖ ግዢን በመፈፀም ለሀገሪቱ ተጨማሪ ውጭ የውጭ ምንዛሬን ማስገኘት ይቻላል ።
ለዚህም ተአማኒ የሆነ ስርአትን በመዘርጋት ለገዢም ሆነ ለሻጭም ሁለቱም የሚተማመኑበት የግብይት ስርአትን ለመፍጠር ህጎችን ማውጣትና አስፈላጊ የሆኑ የግልና የመንግስት ተቋማትን መፍጠርን ይጠይቃል ።
በአሁኑ ወቅት ምሳሌ ብንወስድ መፅሀፍት ገበያ በአብዛኛው የሚከናወነው በድረ - ገፅ አማካይነት ሲሆን እንደ አማዞን ያሉ ድረ-ገፆች አማካይነት በአለም ላይ አንድ ሰው የዱቤ «ክሬዲት» ካርድ እስካለው ድረስ የሚፈልገውን መፅሀፍ ማዘዝና መግዛት ይችላል ። ይህም በመሆኑ ንግዱ እጅግ የተሳካ በመሆኑ ምክንያት በተለያዩ የምእራብ ሀገራት ባሉ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ በርካታ የመፅሀፍ መሸጫ ሱቆች እየተዘጉ ሲሆን ፣ የሱቆቹ መዘጋት መልካም ነው ለማለት ሳይሆን ኢ-ኮሜርስ ምን ያህል ሀይልና አቅም እንዳቀለው ለማሳየት ነው ። ኢ-ኮሜርስ (E-Commerce) ለሀያ አራት ሰአታት የሚሰራ ሲሆን አንድ ሰው ተኝቶ እንኳን በሌላ ከተማ ቀን ከሆነ  ምርቱን ወይም አገልግሎቱን ያለማቋረጥ ሊሸጥ ያስችለዋል  
ሀገራችን ም ከዚህ እጅግ ዘመናዊ ከሆነበ ቴክኖሎጂ የንግድ ስርአት ተጠቃሚ ብትሆን በአገራዊ ምርቷ ላይ ጭማሬን ሊያስገኝና ለምርቷም ሰፊ ወደ ሆነው የአለም ገበያ ሊያስገባት ይችላል ። በጅማሬው ላይ ከሀገር ውስጥ ወደ ውጪ መግዛትን በማገድ ነገር ግን ከውጪ ሆኖ አንድ ሰው ወደ ሀገር ቤት የሚፈልገውን እንዲገዛ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ግኝታችንን ለማሳደግ ያስችላል ።  
 በድረ - ገፅ ግብይት አማካይነት መፅሀፍትን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም በቀላሉ በፖስታ ሊላኩ የሚችሉ እንደ ጫማ ፣ ከልሲና ፣ ሸሚዝ የመሳሰሉትንም ጭምር አንድ ሰው ከቤቱ ተቀምጦ ዋጋ በማነፃፀር መግዛት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል - ባደጉት አገራት ። ይህንን ቴክኖሎጂ አዲስ አሰራርን በማስተዋወቅ የአለም የንግድ በድርጅት አባል በመሆን የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ ይቻላል ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ ሀገራችን የባህር በር የሌላት አገር እንደመሆኗ ይህን ለማካካስ እንዲረዳት እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የመገናኛ ፣ የኢንተርኔት ፣ የስልክ መሰረተ - ልማት ሊኖራት ይገባል ። ለዚህም ምክንያቱ የባህር የሌለው አገር ከውጪ ጋር ለመገናኘት እንደሌላው አገር ወደብ እንዳለው አገር በወደቡ ሊተማመን ስለማይችል ያለው አማራጭ እነኚህን የመገናኛ መንገዶች በመጠቀም ነው ንግዱንም ሆነ ከሌላው ሌላው ዓለም ጋር ያለውን ግንኙነት ማቀላጠፍ የሚችለው ።   
ከአውሮፓ እንደ ስዊዘርላንድ ምንም እንኳን የራሷ ወደብ ባይኖራትም ከኢትዮጲያ እጅግ ያነሰ የቆዳ ስፋትና የተፈጥሮ ሀብት ያላትና ተራራማ አገር ሆና ነገር ግን ከአውሮፓ ቀዳሚ የኑሮ ደረጃ ካላቸው አገራት አንዷ ለመሆን የበቃችው ያለባትን የተፈጥሮ ገደብን ማለትም በየብስ የተከበበችና ተራራማ ወደብ አልባ ብትሆንም እጅግ ዘመናዊ የመሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት እንዲሁም ፣ በእውቀት ላይ የተመሰረቱ የኢንዱስትሪዎችን ማለትም በአለም የታወቀ የሰአትና የመድሀኒት የመሳሰሉት ኢንዱስትሪዎች ባለቤት ስትሆን በአገልግሎት ዘርፉም ከአለም እጅግ ስመ-ጥር የሆነና ተአማኒ የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ባለቤት ፣ እንዲሁም ምንም እንኳን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት አባል አገር ባትሆንም ፣  ከአውሮፓ አገራት ካሉ ዋነኛ አለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መናኀሪያም ጭምር ለመሆን የበቃች ነች - ይህ ከኢትዮጲያ ጋር ተመሳሳይ ያደርጋታል ።
ለዚህ ሁሉ የስዊዘርላንድ ስኬት በአውሮፓ መሀል መገኘቷ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በእውቀት ላይ የተመሰረተ ፣ ዘመናዊ ኢኮኖሚን በመገንባቷ እና የተፈጥሮ ጉድለቷን ማካካስ በመቻሏ ወደብ አልባ አገራት እንኳን ሊደርሱ ከሚችሉት በላይ የላቀ የኑሮ ደረጃ ባለቤት ለመሆን የበቃች ነች ።          

No comments:

Post a Comment