Thursday, February 28, 2013

በምጣኔ - ሀብት ሙያ ላይ የሚቀርቡ ትችቶች



የምጣኔ-ሀብት የትምህርት ዘርፍ ከተግባር የራቁ ናቸው ተብለው ከሚተቹ የሙያ ዘርፎች አንዱ ነው ። ለምሳሌ ፍልስፍናን ብንወስድ ይህ ዘርፍ ከተግባር የራቀ ነው በሚል በርካታ ቀልዶች ተቀልደውበታል። ምጣኔ ሀብትም እንዲሁ በርካታ ቀልዶች የተቀለዱበት ዘርፍ ለመሆን የበቃው ይሄው ከተግባር መራቁ ነው ። ንድፈ - ሀሳብና ተግባር በተወሰነ ደረጃ መሆን አለበት ። ንድፈ - ሀሳብ ብቻ ከሆነ ከተግባር እየራቀ ይሄዳል ፣ በአንፃሩ ተግባር ብቻ ከሆነ ደግሞ አይለወጤ ከሆኑት ንድፈ - ሀሳባዊ ህግጋት እየራቀና ከእውነታው ወጪ የመሄድ አደጋ ይገጥመዋል ። ስለዚህ ንድፈ - ሀሳብንና ተግባርን አጣጥሞ መጓዝ አስፈላጊ ነው ። ብዙ ጊዜ የምጣኔ - ሀብት የትምህርት ዘርፍ ከሚተችባቸው ነገሮች መሀከል  የሚያነሳቸው እንዲሁም የሚጠቁማቸው መፍትሄዎች በጣም ንድፈ - ሀሳባዊ ናቸው ፣ ከገሀዱ - አለም የራቁ ቅድመ - እሳቤዎች (Assumptions) ይበዙበታል ፣  በተግባር ከሚታየው እውነታ የራቁ ናቸው የሚል ነው ። 

ነገር ግን በምጣኔ - ሀብት ውስጥ ሁሉም የምጣኔ - ሀብቱ ተዋናዮች ምክንያታዊ(Rational) ሆነው ስለሚወስኑ ምጣኔ - ሀብቱ ትክክለኛ እኩልዮሹን (Equlibrium) ይይዛል የሚል ነው ።  በእውነተኛው አለም ውስብስብነትና አስቸጋሪነት አንፃር አለምን ለመረዳት ፣ እነኚህ እሳቤዎች አስፈላጊ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ብናነሳ በእውነተኛው አለም የሌሉ እሚመስሉትን፣ ፍፁም ውድድር የተሞላበት የገበያ ስርአት በእውነተኛው አለም የሌለ ሲሆን ፣ ፍፁም ሁሉንም እሚያውቅ ፍፁም ምክንያታዊ የሆነ ተጠቃሚ ወይም ገዢ (Rational Consumer) በቂ መረጃ ካለመኖር የተነሳ በእውነተኛው አለም የሌለ ሲሆን ፣ አለመኖርም ብቻ ሳይሆን ምክንያታዊ ነው ብለን ብንነሳ ምክንያታዊነቱ ከማን አንፃር ነው ? ከራሱ አንፃር ነው ወይንስ ከሌሎች ጥቅም አንፃር ነው ? ፣ ውሳኔው ትክክለኛ መስሎት ነገር ግን ራሱን የሚያከስር ሊሆን እንደሚችል ፣ ወይንም ደግሞ ውሳኔው ለራሱ ሊያተርፈው የሚችል ነገር ግን ሌሎችን የሚያከስር ከሆነ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑ ከየትኛው አቅጣጫ እንደሚታይ ሊያወዛግብ ይችላል ። አንድ ሰው ፍፁም በምክንያት የሚመራ «Rational» ነው ማለት ያ ሰው በምንም አይነት ስሜት አይመራም ማለት ነው ፣ ሌላው ደግሞ የስነ - ምግባር ጥያቄም ይነሳል ፣ ግለሰብ በምጣኔ - ሀብቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን ትተን ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪዎች በተለይ እያወቁ ውሳኔያቸውን በትክክለኛ ስነ - ምግባር ፣ ህግና ደንብ ላይ ተመስርተው መወሰናቸው ራሱም ከጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችላል ።
በትምህርቱ ዘርፍ ውስጥ ንድፈ - ሀሳባዊ ብቻ ሆነው የሚቀሩ ነገሮች ሲኖሩ ሌሎች  ደግሞ ወደ ተግባር ሊቀየሩ የሚችሉ ነገሮች አሉ ። ተግባርን ለመተንተን የገቡ ነገር ግን በተግባር ላይ እንደማይወሉ የታወቁ ጉዳዮችም እንዳሉ ሳንረሳ ማለት ነው ።  
ሌላው ደግሞ የዘመናችን ምጣኔ - ሀብት ሳይንስ ማህበራዊ ሳይንስ ከመሆን ይልቅ የተፈጥሮ  ሳይንስ ሆኗል የሚል ሲሆን በርካታ ጥናቶች በቁጥር ላይ ብቻ ተመስርተው መሰራታቸው ከትክክለኛው ነባራዊ እውነታ ውጪ ወደሚያመሩ ድምዳሜዎች ሲያመራም በተደጋጋሚ ተስተውሏል ።ይህም ምጣኔ - ሀብት የትምህርት ዘርፍ የማህበራዊ ሳይንስ አንዱ ቅርንጫፍ እንደመሆኑ እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ ወይንም እንደ ፊዚክስ ቁጥሮች ብቻ እሚገልፁት አይደለም ። ለዚህም የሰዎች ስነ - ልቦና ፣ ባህልና ሀይማኖትም የራሳቸው ተፅእኖ አላቸው ። በቁጥር ላይ ብቻ የተመሰረቱ መረጃዎች የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ሊያደርሱ ሲችሉ ፣ ቁጥራዊ ወይም ሂሳባዊ ከሆነው እውነታው ውጪ ያለውም የገሀዱ አለም እውነታም አስፈላጊ ነው ። 

ምንም እንኳን ምጣኔ - ሀብት በቁጥሮች ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ማህበራዊ ሳይንስ እንደመሆኑ እንደ ማንኛውም የማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ እሚያጠናው ሰውን ነው ። ስለዚህ ሰውን መረዳት ማለት ደግሞ አካላዊ (ባዮሎጂካል) ከሆኑ ነገሮች ውጪ በአብዛኛው በግልም ሆነ በማህበረሰብ ደረጃ ያለውን ስነ - ልቦናውን መረዳት ማለት ነው ። አብዛኛው ማህበራዊ ሳይንስ የሰውን ልጅ ግላዊም ሆነ ማህበራዊ ስነ - ልቦናውን ወይም አስተሳሰቡን፣ፍላጎቱን ወዘተማጥናትና መረዳት መሰረቱ ነው ። የትኛውም የምጣኔ - ሀብት ፖሊሲም ሲወጣ እሚተገበረው በአገርና በህዝብ ላይ በመሆኑ አንድምታውም እንደዛው ሰፊ ነው ። 
የአንድ ኩባንያን አትራፊነትና ወደ ትክክለኛው መንገድ እየተመራ እንዳለ ለመረዳት ኩባንያው ከሚያወጣቸው የቁጥር መረጃዎች ውጪ ፣ ስለ አስተዳደሩ ባህሪ እና ታማኝነቱ፣ ስለሚወስናቸው ውሳኔዎች አይነትና ሪስክን የመውሰድ ዝንባሌውና ልማዱ ወዘተ የመሳሰሉት ስለ ኩባንያው ትክክለኛና የተሟላ መረጃን ይሰጣሉ ። ኩባንያው የሚያወጣቸውን የቁጥር መረጃዎችን ብቻ በመመልከት ስለኩባንያው ሙሉ ለሙሉ ትክክለኛ የሆነ ስእልን ለመጨበጥ አስቸጋሪ ነው ። ለዚህም አይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው በምእራቡ አለም ትላልቅ ኮርፖሬሽኖች ፣ አማላይ የሂሳብ ምርመራ ውጤትን አሳትመው ለህዝብ ይፋ ቢያደርጉም በተግባር ግን እየከሰሩ ያሉ ፣ ወደ ኪሳራ እያመሩ ያሉ ሆነው የተገኙ በርካታ ግዙፍ ኮርፖሬሽኖች አሉ ።
በአጠቃላይ ግን ምጣኔ - ሀብት የሙያ ዘርፍ ከተፈጥሮ ሳይንስነት ይልቅ ማህበራዊ ሳይንስነቱ በጣም ያመዝናል ። ለዚህም ምሳሌ የሚሆነው አብዛኞቹ የምጣኔ - ሀብት ንድፈ - ሀሳቦች (Economic Theories) ናቸው እንጂ የምጣኔ - ሀብት ህግጋት (Economic Laws) ለመባል የሚበቁ አይደሉም ይባላል ። ምጣኔ - ሀብት በክስተት የሚገለፅ ነው እንጂ በንድፈ - ሀሳብ ለመግለፅ ውስብስብ ሊሆን ይችላል ። በአንፃሩ በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ውስጥ ያሉት የማያወላዱ ህግጋት ናቸው ። የስበትን ህግ ፣ ሀይልን ፣ የፍጥነትን የመሳሰሉትን ህግጋትን ብንወስድ የሰው ልጅ ከመፈጠሩ በፊትና ወደፊትም የሰው ልጅ ህልውናው ባይኖር እንኳን የነኚህ ህግጋት ነበሩም ፣ አሉም መቼም ቢሆን ይሰራሉ ። በማህበራዊ ሳይንስ የዚህ አይነት እርግጠኝነት ላይ መድረስ በእጅጉን አጠራጣሪ ነው ። ማህበራዊ ሳይንስ እንደመሆኑ ያልተጠበቁ ከውስጥም ፣ ሆነ ከውጪ የተለያዩ ክስተቶች መከሰታቸውና ውጤቱን ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ ማሳታቸው አይቀሬ ነው ። ለዚህ ነው በዘርፉ ሊታወቁ ይገባቸው የነበሩ ነገር ግን ለሙያው ራሱ እንግዳ የሆኑ አዳዲስ ክስተቶች በየጊዜው ሲከሰቱ የምናየው ። 
ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው የብሉይንና የኬነስን የምጣኔ ሀብት አስተምህሮዎችን ብንወስድ ምንም እንኳን ሁለቱ የምጣኔ - ሀብት ፍልስፍናዎች የራሳቸው የሆነ አካሄድና የእርስ በእርስ የመቃረን ሁኔታ ሲኖር ከተወሰነ ደረጃ በላይም ሁለቱም ሊሰሩ የማይችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል ።
ለምሳሌ እ.ኤ.አ.የ2008 የገንዘብ ቀውስ ብንወስድ ቀውሱ የተከሰተበት ምክንያት የትላልቅ የባንክ አስተዳዳሪዎችና መሪዎች የወሰኗቸው ውሳኔዎች ለጊዜው እነሱን ትርፍ በትርፍ ቢያደርጓቸውና ግዙፍ ቦነስን እንዲያገኙ ቢያስችላቸውም ውለው አድረው ግን ደንበኞቻቸውን ፣ ራሱን የገንዘብ ስርአቱን ብሎም አጠቃላይ የአለምን ምጣኔ - ሀብት ቀውስ ውስጥ ጨምሯል ። የፖለቲካ መሪዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ከተጠያቂነት ያለመጡ ሲሆን ፣ የአይስላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ ለፍርድ ለመቅረብ ተገደዋል ።
የአለምን የምጣኔ - ሀብት ችግር ወዲያውኑ የሚፈታ አስማታዊ መፍትሄ (Magic Bullet) በአለም ላይ የለም ።አንዱ በአለም ላይ ያለ የምጣኔ - ሀብት ችግርን የሚያስከትል ነገር የምርታማነት መለወጥና አቅጣጫውን መቀየር ሲሆን ፣ ለዚህም በ1990ዎቹና 2000ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በመገናኛ ቴክኖሎጂና በኮምፒውተርና በሶፍትዌርና በኢንተርኔትን በመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ የተመሰረተ ከፍተኛ የምርታማነት የተመዘገበ ሲሆን ፣ የዚህ ዘርፍም ምርታማነት እየቀነሰ ሲሄድም ወደ ሌሎች ዘርፎች ምርታማነቱ መሸጋገር ጀምሯል ። 



አሁን እየኖርንበት ያለነው አለም አንዱን ችግር ስናልፍ ሌላው ችግር ብቅ ይላል ። ምንም የመጨረሻ የሆነና እና አስተማማኝ የሆነ ነገር የለም ። መገናኛ ብዙሀንን ብናዳምጥ ዜናዎቻቸው በአብዛኛው ምጣኔ - ሀብታዊ ጉዳዮችን እሚያነሱ ሲሆን ምንም እንኳን በአንዳንድ ተቋማት የምጣኔ - ሀብት ባለሙያዎችን እስከማግለልና ፣ ሌሎች ባለሙያዎችን እንደ የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያዎችን (ሶሺዮሎጂስቶን)ና የአካባቢ ሳይንስ ባለሙያዎችን እስከ መቅጠር ደርሰዋል ። የአለም ባንክ ሳይቀር የምጣኔ - ሀብት ባለሙያዎችን በማባረር ፣ ሌሎች የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎችንና የጤና ባለሙያዎችን በብዛት መቅጠርና ብሎም ከፍተኛ የአመራር ደረጃ ላይ ማስቀመጥ ጀምሯል ። ለምሳሌ ከሮበርት ዞሌክ በኋላ የአለም ባንክ ፕሬዝደንት ሆነው የተሾሙት የህክምና ባለሙያ ናቸው ። ምናልባት አንድ ባንክን አንድ የህክምና ባለሙያ ይምራው ሲባል ፣ ለሰው አንዳንድ ሰው ሊገርመው ይችላል ። ነገር ግን ተቋሙ ከአትራፊ ተቋማት ይልቅ፣ ታዳጊ ሀራትን ከድህነት እንዲወጡ እንዲረዳ በማሰብ ሲሆን ፣ በአንፃሩ ግን በምጣኔ - ሀብት ባለሙያዎች ላይ ከቀድሞው ቀነስ ያለ እምነት መኖሩን ያረጋግጣል ። ይህ ይሁን እንጂ የምጣኔ  - ሀብታዊ ችግር በሚፈጠርበት ወቅት የሚጠሩት ያው ኢኮኖሚስቶች መሆናቸው የታወቀ ነው ፣ አንዳንዴ ይህን ችግር ያመጡብን እነሱ ናቸው ቢባልም ፤ ዞሮ ዞሮ ግን  አንድ ምጣኔ - ሀብታዊ ችግር ሲፈጠር መፍትሄ እንዲያመጡ የሚጠበቀው ከምጣኔ - ሀብት ባለሙያዎች ዘንድ ነው ።
ይህንን ክፍተትም ለመሙላት ፤ በርካታ የምጣኔ - ሀብት አዋቂዎች ይህንን ክፍተት ለመሙላት ብዙ ሀሳቦችን አፍልቀዋል ። እርግጥ እነኚህ እሳቤዎች እውነተኛውን አለም ለመረዳት የሚያስችል የንድፈ - ሀሳብ መደላድልን ወይም መሰረትን ጥሏል ። እንደ የኬነስ ተከታይ የሆኑና እንደ ጆሴፍ ስትግሊትዝን የመሳሰሉት ይህንን ክፍተት ለመሙላት በርካታ ሀሳቦችን አፍልቀዋል ።

ነገር ግን አንድ ነገር ልብ ማለት ያለብን ነገር በምጣኔ - ሀብት ዘርፍ በርካታ አሳማኝነትና መስህብነት ያላቸው ክርክሮች በበርካታ ሰዎች የቀረቡ ሲሆን ነገር ግን በማህበራዊ ሳይንስ ውስጥ የአንድን ሀሳብ ትክክለኝነት መረዳት የሚቻለው ያ ሀሳብ በተግባር በሚሰጠው ውጤት ብቻ ነው ፣ በተጨባጭ ከሚያስገኘው ውጤት ውጪ የሀሳብ ጠቀሜታ ሊለካ የሚችልበት ሌላ መንገድ የለም ። አንድ ሀሳብ ለተወሰኑ አመታት በስራ ላይ ውሎ ውጤትን እማይሰጥ ከሆነ ፣ ወይም ይባስ ብሎም ጉዳትን እሚያስከትል ከሆነ ከጊዜ በኋላ ውድቅ መደረጉአይቀሬ ነው ።ይህ በምእራባውያን ሀገራት በተለይም  እንዲሁ ለአስርት አመታት በተግባር ውለው ነገር ግን ውጤትን ሳይሰጡ የተጣሉ በርካታ ሀሳቦች አሉ።አንድ ሀሳብም ትክክል ካልሆነ ለተወሰነ ጊዜ ድረስ የዛን ሀሳብ ጉዳቱን ማዘግየት ቢቻልም ፣ ውሎ አድሮ ግን ትክክል እስካልሆነ ድረስ ውሎ አድሮ የተፈራው ነገር መምጣቱ አይቀሬ ሲሆን ፣ ትክክለኛ መሰረት መጣሉ የተሻለ ነው ። 

ነገር ግን አሁን ባለችው አለማችንን ያለምንም እንከን ፍፁም ሆኖ አለምን የሚመራ ሀሳብን ማግኘት አስቸጋሪ ነው ። ለዚህም ምክንያቱ ምን ይመራሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩ በርካታ ሀሳቦችና አስተሳሰቦች በመጨረሻ ውጤትን እንደማያመጡ ሲታወቅ ሊተው የሚችሉ ሲሆን ፤ ለምሳሌ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ የገበያ ሀይሎችብቻ ምጣኔ - ሀብቱን ይመራሉ ቢባልም እሱም ውሎ አድሮ ችግሮችን በመፍጠሩ አማራጭን መፈለግ ግድ ሆኗል ። የአለማችን ዋነኛ ችግር በትክክል ለረጅም ጊዜ የሚሰራ ቋሚ የሆነ ሀሳብን ማግኘት ሲሆን ። ይህም በተደጋጋሚ አንድ ሀሳብ ከተሞከረ በኋላ እየወደቀ ሲሄድ ተስተውሏል ። ለዚህም የምእራባውያን የኢኮኖሚ ፍልስፍና ከ2008 የአለም የገንዘብ ቀውስ ወዲህ አስተማማኝነቱ የቀነሰ ሲሆን ፣ ሌላ መሪ ሀሳብን መፈለግ ፣ ወይም ቀድሞ የነበረውን በተወሰነ ደረጃ ማሻሻልን ግድ የሚልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ። ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በካፒታሊዝም የምጣኔ - ሀብት ስርአት ላይ የተለያዩ ትችቶች መዝነብ የጀመሩበት ዘመን ላይ ደርሰናል ። ምእራባውያኑ ዜጎች  ሳይቀሩ እኛ 99በመቶ ነን በማለት ከሀገራዊ የሀብት ክፍፍል መአድ የተገለሉ ዜጎች ሰልፍ ሲወጡ በአንፃሩም ምእራባውያን የፖለቲካ መሪዎች ሀብታሞች በአግባቡ ግብር እንዲከፍሉ በይፋ መጠየቅ ጀምረዋል ።
በማህበራዊና በፖለቲካ ዘርፍ ዋናው የአለማችን ችግር የፍትህ መጓደል (Injustice) ሲሆን ፣ በብዙ የአለማችን ክፍሎች የሚሰማውና በየቀኑ የአለም መገናኛ ብዙሀን የሚዘግቡት ጉዳይ በአለም ላይ ስለሚታየው ችግርና በየሀገሩ ስለሚከሰቱ የአስተዳደር መዛባቶች ፣ የኮርፖሬሽኖች እምነት ማጉደል ፣ሙስናዎችና በመሳሰሉት ጉዳዮች ናቸው ። ዴራሲሊ የተባለ የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር በአንድ ወቅት እንደገለፀው «አለም የምትመራው ብዙ ሰዎች እንደሚያስቡት በሚታዩ ሀይሎች ብቻ ሳይሆን በማይታዩ ሀይላትም ጭምር ነው» ። እነኚህም በቀጥታ ለህዝቡ ሲወስኑ የማይታዩ ነገር ግን ከጀርባ ሆነው ምጣኔ - ሀብቱንና ፖለቲካውን፣ የህዝብ አስተያየት (Opinion Poll) በመፍጠር የሚዘውሩትን ሀይላትን ያጠቃልላል ፤ በአብዛኛው ባንከሮች ኩባንያዎች ግዙፍ ኮርፖሬሽኖች እና የህዝብ አስተያየትን የሚቀርፁትን ሚዲያዎችን ይጨምራል ።  

ሀብታም አሜሪካኖች ፤ ትላልቅ የሆኑ ቁጥራቸው 250 የሚሆኑ ቢሊየነሮች ግማሹን ብቻ ሲከፍሉ ፤ ከፍተኛ የኮርፖሬት ግብር ያላት ሀገር ብትሆንም «Tax Watch Amerci» የተሰኘው ተቋም በጥናቱ ላይ ገልፆታል ። በእውቀትም ሆነ በገንዘብ ኮርፖሬሽኖች ከፖለቲካ መሪዎች የበለጠ አቅም  እንዳላቸው የታወቀ ሲሆን ፣ሚዲያዎችን በመቆጣጠር ፣ የትምህርት ስርአቱን በሚመቻቸው መንገድ በመቅረፅ ፣ እንዲሁም ለዩንቨርስቲዎችና ለተለያዩ የምርምር ተቋማት የገንዘብ ድጋፍን በማድረግ ከነሱ አላማ ጋር አብሮ የሚሄዱ ጥናቶችን በማድካሄድና ውጤቶቹንም በማሰራጨት በአጠቃላይ በምጣኔ - ሀብቱም ፣ በባህልም ሆነ በፖለቲካው መስክ የራሳቸውን ተፅእኖ ለዘመናት በሰፊው ሲያሳርፉ ኖረዋል ። በተለይ የፖለቲካውን አለም ከፖለቲከኞች ኋላ ሆነው መቆጣጠር አስችሏቸዋል ። ይህ ሁሉ ይሆን የነበረው በብዙሀኑ ህዝብ ኪሳራ ሲሆን ህዝቡ በሚነቃበት ወቅምትም ብዙ ነገር ከተበላሸ በኋላ ሊስተካከል ይችል የነበረበት ጊዜ ካለፈ በኋላ ሆኗል።

ነገር ግን አለምን የሚመራ ሀሳብ ከአንድ ሰው ወይም በአንድ ፓርቲ ወይም በአንድ አስተሳሰብ ወይም ፍልስፍና ውስጥ ብቻ የሚገኝ ነገር አይደለም ። አለምን ወይም አገራትን የሚመሩ ሀሳቦች በተለያዩ አስተሳሰቦች ፣ አመለካከቶችና ፍልስፍናዎች ውስጥ ተሰራጭተው የሚገኙ ናቸው ። ችግሮች በአንድ ጊዜ የሚፈቱ ወይም የሚታወቁ ላይሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ታይቷል ። ለምሳሌ በምእራቡ አለም ጥንካሬው በዚህ በኩል ከፍተኛ ሲሆን ፣ አንዱ ፓርቲ ሀሳብ በሚጨርስበት ወቅት ፣ በሌላው እየተተካካ በተለያዩ አስተሳሰቦችን በመጠቀም ይቀጥላሉ ፣ በዚህ በኩል እድለኛ ናቸው ማለት ይቻላል ይኀውም በርካታ የማህበራዊ ሳይንስ፣ የፖለቲካ ሳይንስ ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ ሊቃውንትን ያፈሩ ስለሆኑ ሌሎችን በርካታ ሀገራት የነሱን ፈላስፋዎችን ሀሳቦች የተቀረውም አለም በብዛት ተቀባይነትን ያገኙና ተፅእኖን ማሳረፍ የቻሉ ናቸው  
አንዱ አልሰራ ሲል አንዱን ፣ አንዱም ውድቀትን ሲያስከትል የሱ ተቃራኒ የሆነውን አስተሳሰብ በመጠቀም ፖሊሲዎቻቸውን እየለዋወጡ ከችግራቸው ለመውጣት ጥረትን ሲያደርጉና ሲሳካላቸውም ታይቷል ። ይኀውም በ1930ዎቹና እንዲሁም በ2008 የአለም የገንዘብ ቀውስ ፣ እንዲሁም በ2012 በተከሰተው ወቅት አዋጪ ናቸው ያሏቸውን የኢኮኖሚ ፍልስፍናዎችና መርሆዎችን ተግባራዊ አድርገዋል ። በእርግጥ የፖሊሲ ለውጥበን ለማድረግ ፣ የአመራር ለውጥን የሚየተይቅ ሲሂን ሆን «አዲስ መጥረጊያ የተሻለ ያፀዳል እንዲሉ» ምእራባውያን አገራት አንድ ችግር ሲገጥማቸውና ፣ ፖሊሲው አልሰራ ሲል  ጠንካራ የዲሞክራሲ ስርአት ስላላቸው መሪዎቻቸውን ይለውጣሉ ። ለምሳሌ የዩሮ የእዳ ቀውስን ለመፍታት መጀመሪያ ላይ ወጪን መቀነስን «ኦስተሪቲ» እንደ አማራጭ ይዘው የነበሩ አንዳንድ የአውሮፓ መሪዎች እንደ ፈረንሳዩ ሳርኩዚ ያሉት በምርጫ ስልጣናቸን ሲያጡ ፣ ወጪ መቀነስን እንደ አማራጭ የማይከተሉ መሪዎች ተቀባይነትን አግኝተዋል ።

 ቻይናን ኢኮኖሚ ከሶሻሊዝም ወደ ካፒታሊዝም ያመጡት ፣ የቀድሞው የቻይና መሪ ዴንግ ዚያዎፔንግ እንዲሁ እንደሚሉት ፣ዋናው ነገር ድመቷ ጥቁር ወይም ነጭ መሆኗ ሳይሆን አይጥ መያዝ መቻሏ ነው ።
አንድ ለብዙ ጊዜ ሲሰራበት የኖረ አስተሳሰብ መቀየር በሚፈልግበት ወቅት ማሻሻል ፣ ማስተካከል የሚያስፈልግ ሲሆን ማህበረ- ኢኮኖሚና- ፖለቲካዊ ዳራዎች በሚቀየሩበት ወቅት ግን በአንድ በኩል ከነበረው ወቅታዊ ሁኔታ ተጠቃሚ የሆኑ ወገኖች ያ ነገር እንዳይለወጥ በመፈለግ ሲከላከሉለት ፣ በሌላ በኩል ለውጡን ካለመረዳትና ነገሮች እንደቀድሞው ሆነው ይቀጥላሉ ከሚል የተሳሳተ እምነት ምክንያት የቀድሞ ሀሳቦች ስራ ላይ ቢውሉም በተደጋጋሚውድቀትን ሲያስከትሉ ተስተውሏል ። ያም ሆኖ ግን ከዚህ አይነት ጉዳዮች ከጀርባቸው ትልቅ ፖለቲካ አለ ።

የምጣኔ ሀብት የትምህርት ዘርፍ ከሌሎች የትምህርት ዘርፎች ጋር ሲነፃፀር የቅርብ ጊዜ ሙያ ነው ማለት ይቻላል ። መስኩ ደርዝ በያዘ መንገድ የተወለደው እንግሊዝ ሀገር አዳም ስሚዝ በተባለ የስኮትላንድ ተወላጅ ሰው ሲሆን ከዚያም በርካታ ታላላቅ አሳብያንና ለማህበረሱ ኑሮ መሻሻል የጋለ ፍላጎት በነበራቸው ምሁራን ዳብሮ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ደርሷል  - አሁንም ድረስ እየዳበረ ይገኛል።
የምጣኔ - ሀብት የትምህርት ዘርፍን የሚስብ የሚያደርገው አንዱ ነገር የማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ሆኖ በተወሰነ ደረጃ ደግሞ እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ የሚያስቆጥሩት ሁኔታዎች ሲኖሩት ከሌሎች የማህበራዊ ሳይንስ የትምህት ዘርፎች በትለየ ሁኔታ በሂሳብ ፣ በስታትስቲክስና በኢኮኖሜትሪክስላይ የተደገፈ ነው ። ከዚህም ሌላ የምጣኔ - ሀብት ዘርፍ ስራ ላይ የሚውለው በሀገርና በህብረተሰቡ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ በመሆኑ የሚሞከረው በተግባርሲሆን የሚወጡ ፖሊሲዎች ከልተሳኩ የሚያስከፍሉት ዋጋ በአገርም ሆነ በግለሰቦች ኑሮ እጅግ ከባድ ነዉ ።

ይሁን በዚህ መስክ የአንድን ሀገርም ሆነ የአለምን ምጣኔ - ሀብት አቅጣጫን ለማየትና ለመምራት የዛን ኢኮኖሚ የሚሄድበትን አቅጣጫ ለማየትና የመረዳት ችሎታን ይጠይቃል ። ነገር ግን የዚህ አይነት ባለሙያዎች ቁጥራቸው ብዙም ባይሆንም በተለይ በአገር ደረጃ ፖሊሲን የሚያወጡ ሰዎች ያ ኢኮኖሚ የሚሄድበትን አቅጣጫ ማየት የቻሉና ወዴት እያመራ እንዳለ ፣ ወዴት መሄድ እንዳለበት የሚወስኑ ሰዎች ናቸው ። ይህ ብቻም ሳይሆን የግል ድርጅቶችና ባንኮች የመሳሰሉትም ተቋማትን ለመምራት የዚህ አይነት አጠቃላይ ምጣኔ - ሀብቱን የመረዳት ችሎታ ነው ኩባንያዎች ትርፋማ ሆነው ሊመሩ የሚችሉት ። 

ማንኛውም ሀገር ጠንካራ ምጣኔ ሀብትን ሲገነባ ብቻ ነው ሌሎች ዘርፎች እሚነቃቁት ። ለምሳሌ ስነ- ጥበብን ፣ ሙዚቃን ፣ ፍልስፍናን ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ፣ ብንወስድ ጠንካራ ምጣኔ ሀብት ያላቸው ሀገራት በእነዚህ ዘርፎችም እየዳበሩና እየፋፉ ሲሄዱ ለዛ የሚበቃ የኢኮኖሚ አቅም የሌላቸው ሀገራት ግን በእነዚህም ዘርፎች ወደ ኋላ ቀርተው ማግኘት ያለባቸውን ትሩፋት ሲያጡ ይታያሉ ።
ይህ ሙያ ለብቻው የቆመ ሳይሆን ከሌሎች ሙያዎች ጋር በምርምርም ሆነ በተግባር የተያያዘ ነው ይሁን እንጂ ከምንም በላይ ወደ የትኛውምየፖለቲካ አቅጣጫ ሊቀየር የሚችል ነው ። ለምሳሌ የትኛውንም የምጣኔ - ሀብት ክርክር ከየትኛውም ፖለቲካአስተሳሰብ አንፃር መደገፍም ሆነ መቃወም ሲቻል ፣ በየትኛውም ሀገር ያሉ የፖለቲካ መሪዎች የነሱ ፖሊሲና አመራራቸው ትክክል እንደሆነ ለማሳየት በዋናነት የሚጠቀሙበት ከምጣኔ - ሀብት መስክ ያስመዘገቡትን ውጤት በመጥቀስ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞበተቃዋሚነት የተሰለፉ የፖለቲካ መሪዎችም ደግሞ በበኩላቸው ስልጣን ላይ ያለውን ወይም ገዢ የሆነውን ፓርቲ እሚያብጠለጥሉት ደግሞ በኢኮኖሚ መስኮች ያሉትን ችግሮች እንደ ስራ አጥነትን ፣ የኑሮ ውድነትን የመሳሰሉትን ችግሮች በመጥቀስ ነው ።
በምጣኔ - ሀብት ዘርፍ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች የሚፈቱት በሰዎች አማካይነት ሲሆን ከሰው በላይ የሆኑም አይደሉም ። ችግሮቹ የሚፈጠሩትም በሰዎች ሲሆን መፍትሄም ሊያገኙ የሚችሉትም በሰዎች ነው ። ሌላ የተፈጥሮ አደጋዎችን  መሬት መንቀጥቀጥን ፣ ሱናሚን ብንወስድ ከሰው ልጅ ቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ ሲከሰቱ የኢኮኖሚ ችግሮች ግን ከሰው ልጅ አቅም በላይ ሊሆኑ አይችሉም ።          

የናይል ወንዝ ፖለቲካ


የናይል ወንዝ ግብፅንና ኢትየጲያን በታሪክ ፣ በፖለቲካ በሀይማኖት እንዲሁም በጂኦ - ፖለቲካዊና ስትራቴጀጂያዊ ሁኔታዎች ያስተሳሰረ ነው ። ቀደምት የታሪክ ሰነዶች እንደሚያመለክቱት ግብፃውያን ፈርኦኖች በከፍተኛ የስልጣኔ እርከን በነበሩበት ወቅት ሳይቀር በዚያን ወቅት ኩሽ ተብላ የምትታወቀው ኢትዮጲያ የግብፅ ዋነኛ ወዳጅ የነበረች ሲሆን ፣ በዚያን ወቅት ኢትዮጲያውያን ለፈርኦኖች ወታደር ሆነው ያገለግሉ እንደነበረ ፣ አንዳንደ ድ ጊዜም ራሳቸው አስተዳዳሪ ሆነው ያገለግሉ እንደነበረ በታሪክ ሰነዶች ላይ ሰፍሯል ። ድሪሱላ ሂውስተን (Drusilla Dunjee Houston, 1876-1941)  «The Wonderful Ethiopians» በተባለ መፅሀፏ አሜሪካዊቷ ፀሀፊ በመፅሀፏ ውስጥ ዘርዝራዋለች ። የኢትዮጲያውያንና የግብፃውያን ወዳጅነትና ትውውቅ ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ ነው ።
      በአንፃሩ ግን ግብፃውያን የህልውናቸው ምንጭ የአባይ ወንዝ መሆኑን ካወቁ ወዲህ የህልውናቸው ምንጭ የሆነው ወንዝ ለሚነሳባት ኢትዮጲያ በጎ አመለካከት እንደሌላቸው የታወቀ ነው ።


     በአንፃሩ ግን ግብፆች ብቻ ሳይሆኑ አረቦችም ጭምር ኢትዮጲያ በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን እውቅና መስጠት አይፈልጉም ። ለዚህ የሳኡዲው ልኡል ካሊድ ቢን ሱልጣን «Khalid bin Sultan» የተባሉ የሳኡዲ አረቢያ የመከላከያ ሚኒስቴትር ሳይቀሩ ወታደራዊ ሀይልን መጠቀምን እንደ አንደ አማራጭ መጠቀምን በሱዳንና በግብፅ ውሀ ላይ ጣቶቻቸውን ለማሳረፍ የሚፈልጉ የኢትዮጲያውያንን ሀይ ማለት ይገባል ይላሉ ።  ከዚህም በተጨማሪ ልኡሉ ፣ ያለውን ውሀን በተመለከተ የተደረጉ ነባር ስምምነቶች የማይከበሩ ከሆነ ወታደራዊ ሀይልን መጠቀም እንደ አንደ አማራጭ መታየት አለበት ባይ ናቸው ። ከዚህም ነበተጨማሪ የህዳሴን ግድብ ከሱዳን ድበንበር 12 ኪ.ሜ ርቀት ላይ መሰራቱ በራሱ ኢኾኮኖሚ ጥቅም ሳይሆን ፖለቲካዊ አንድምታም ጭምር አለው የሚል ትንታኔን ሰጥተዋል ።


      በነገራችን ላይ የአባይ ውሀ ማለት በሰሀራ በረሀ ውስጥ ለምትገኘው ግብፅ ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ሌሎች በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የአረብ ሀገራት ይህ ነው የሚባል የዝናብና የወንዝ ምንጭ የሌላቸው እንደመሆኑ ፣ የነዳጅ ሀብት ያላቸው ስለሆነ የውቅያኖስ ውሀን በከፍተኛ ሀይል እያጣሩ ነው እሚጠቀሙት ። ነገር ግን ከአረብ ሀገራት ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ያላት ፣ እንዲሁም በወጣት ስራ አጥነት እና ቀላል የማይባል ህዝቧ በድህነት ለሚኖርባት ግብፅ እንደ ሌሎቹ በነዳጅ እንደከበሩት ሀገራት ከፍተኛ ወጪን አውጥታ የውቅያኖስ ውሀን ማጣራት ፈታኝ ነው ። ስለዚህ ለግብፅ የአባይ ውሀ ማለት የህልውናዋ ምንጭ ነው ።
      
         በተጨማሪም በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአለም ላይ ወደፍ ፊት ከነዳጅም በበለጠ ከገፍተኛ የጂኦ- ፖለቲካዊ ግጭቶች ምንጭ ይሆናል ተብሎ እሚጠበቀው ለውሀ የሚደረገው ፉክክር እንደሆነ በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ የገለፁት ጉዳይ ነው ። ለዚህም ምክንያቱ ነዳጅን በፀሀይ ፣ በንፋስ ፣ በመሳሰለው ሀይል  ለመተካት እንቅስቃሴዎችና ሳይንሳዊ ምርምሮች እየተደረጉና አበረታች ውጤትን እየሰጡ ሲሆን በአንፃሩ ለሰው ልጅ ጥቅም ተስማሚ የሆነን ውሀ ግን መተካት የማይታሰብ ነው ።  

ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታዎች
               የአባይ ወንዝ ከዚህ ቀደም ግብፃውያን ኢትዮጲያ የአባይ ወንዝን ብትነካ ጦር አዘምታለሁ ብላ የምታስፈራራበት ጊዜ ነበረ። ይሁን እንጂ አሁን ባለው አለም ግብፃውያን ወታደራዊ እርምጃን እንውሰድ ቢሉ በአለም ላይ ተቀባይነት እማይኖረው ሲሆን ፣ ጉዳቱም የጋራ ነው እሚሆነው ። ስለዚህ የኢትዮጲያ መጎዳት የግብፅም መጎዳት መሆኑ ግልፅ ነው ።ሀገራችን በአለም ላይ ካሉ ቁልፍ ስትራቴጂክ ከሆኑ አገራት አንዷ ናት ። ልክ እንደ ግብጽ ፣ እስራኤል ፣ ሳኡዲ አረቢያ ፣ ኢራቅና ሶሪያ በአለም ላይ ቁልፍ ሀገራት ተርታ ልትመደብ የምትችል ናት ። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ ለምሳሌ ለመካከለኛው ምስራቅ ቅርብ መሆኗ ፣ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያ መሆኗ ፣የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗ ፣ የራሷ ፊደል ባለቤትና የቅኝ አገዛዝ ያልተገዛችና መሆኗና በታሪክ ጉልህ ስፍራ ከሚደሰጣቸው የአለማችን ጥቂት አገራት አንዷ መሆኗ ፣ በአፍሪካ ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ካላቸዉ ሀገራት እምትመደብ መሆኗና አሁን ደግሞ በአፍሪካ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት እየሆነች መምጣቷና የጎረቤት ከሀገራት ህልውና የሆኑ ህልውና የሆኑ በርካታ ወንዞች ባለቤትና መፍለቂያ መሆኗ፣ ሰፊ ጥቅም ላይ ያልዋለ ያልታረሰ መሬት ባለቤት መሆኗና በታላላቅ ሀይማኖቶች ስሟ የተጠራና ታሪካዊና ቀደምት የሀይማኖቶቹ ተቀባይ ሀገር መሆኗና የጥንታዊ ስልጣኔዎች ሀገር መሆኗ ለየት ያለች ሀገር ያደርጋታል።

                ነገር ግን ምእራባውያን ኢትዮጲያን የሚፈልጓት ኢትዮጲያ ውስጥ እንደ ናይጄሪያ ወይንም እንደ ሊቢያ በገፍ የሚቀዳ ነዳጅ ዘይት ወይንም ሌላ ማእድን ኖሯት አይደለም ። ከዚያ ይልቅ ምስራቅ አፍሪካን ለመቆጣጠር በዙሪያዋ ካሉት ሀገራት ሁሉ ኢትዮጲያ አመቺ በመሆኗ ነው ። ለምሳሌ ሶማሊያ ውስጥ ያንሰራራውን የአልቃኢዳ አጋር ነኝ ብሎ ያወጀውን አልሸባብን ለመቆጣጠር ከሶማሊያ ጋር ረጅም የጋራ ድንበር ያላት ኢትዮጲያ ስትሆን ፣ ከደቡብና ከሰሜን ሱዳንም ጋር ረጅም የሚያዋስናት ድንበር ያላት ከምስራቅ አፍሪካ ሀገር ኢትዮጲያ ብቻ ነች ።ሌላው ደጋማና የተራራ እንዲሁም ከፍተኛ ዝናብ የምታገኝ ሀገር እንደመሆኗ የግብፅ እና ህልውና የሆነው የታላቁ የአባይ ወንዝ ባለቤት መሆኗ ነው ። የአባይ ወንዝ ብቻ ሳይሆን የጎረቤት ሀገራት በሶማሊያን ፣ ሱዳንን እንዲሁም ኬንያን ወደ እነኚህ ሀገራት የሚፈሱ ታላላቅ ወንዞች መነሻ ሀገርም ነች ። ለምሳሌ ኤርትራን ብንወስድ በቀይ ባህር ከ1400 ማይል በላይ ባለቤት ስትሆን ይህም ኤርትራን ስልታዊ  ያደርጋታል ።

Wednesday, February 27, 2013

የካፒታሊዝም ስርአት ተግዳሮቶች (Challenges of Capitalism)



የካፒታሊዝም ስርአት ከቀደምቶች ከብሉይ የምጣኔ - ህሀብት ፈላስፋዎችሁሉ በስርአቱ ውስጥ ያሉትን ተቃርኖዎች አስቀምጠዋል ። ዴቪድ ሪካርዶ ይህንን ተቃርኖ የተረዳ ሲሆን ፣ ካርል ማርክስ በአንፃሩ ይህን ተቃርኖውንና በስርአቱ ውስጥ ያሉትን ተግዳሮቶቸን በዝርዘሮ ያስቀመጠ የብሉይ የምጣኔ - ሀብት ፈላስፋ ነው ። የካፒታሊዝም ስርአት ሁለት ዋና ዋና ችግሮች ያሉበት ሲሆን በአንድ በኩል ራሱ ስርአቱ ያለበት ውስጣዊ ተቃርኖዎች (Inherent Contradictions)  ያሉት ሲሆን ሌላው ደግሞ ከአስተዳደርና ከቁጥጥር እና ከአመራር ግድፈቶች የሚመነጩ ችግሮች የተጋለጠ መሆኑ ነው ። ለምሳሌ በ1930ዎቹ የተከሰተው የምጣኔ - ሀብት ቀውስና በ2008 የተከሰቱት ቀውሶች ከስርአቱ ውስጣዊ ተቃርኖ የመነጩ ብቻ ሳይሆኑ በዋናነት የመንግስት ተቋማት በአግባቡ ባለመቆጣጠራቸው የተፈጠረ ነው ፣ የላላ ቁጥጥር ፣ እና የፋይናንስ ተቋማት ከልክ ያለፈ ለትርፍ መስገብገብ የፈጠረው ነው ። 


ሌላው ግን ከካፒታሊዝም ስርአት ውስጣዊ ተቃርኖ የሚመነጨው ዋናው ነገር የሀብት ክፍፍል መዛባት ነው ። እ.ኤ.አ. በ 2011 ጥቅምት ላይ በአሜሪካን አገር የተደረገው ህዝባዊ ሰልፍም (Occupy Wall Street) በመባል የተጀመረውን ቀጥሎም ወደ ተቀረው አሜሪካ የአለም ሀገራት ከተሞች የተስፋፋው የሚታወቀው ይህንን የኑሮ አለመመጣጠንና ብሎም የግብር ከፋዩ ገንዘብ እነኚህን የገንዘብ ቀውስ እንዲከተል መነሾ የሆኑትን ኮርፖሬሽኖችና ባንኮችን ከኪሳራ ለማዳን በመዋሉ ነገር ግን የተጠበቀው ውጤት ሳይመጣ መቅረቱን ፣ ይባስ ብሎም የስራ አጥነትና የዋጋ ንረትና የመሳሰሉ ሌሎች የኢኮኖሚ ችግሮች እየተባባሱ በመሄዳቸው ነው ። በዚያኛው ፅንፍ ደግሞ «Tea Party» እንቅስቃሴ በመባል የሚታወቀው ደግሞ በቀኝ አክራሪዎች የሚመራ እና ከሰራተኞች እንቅስቃሴ ከሚባለው ከዎል ስትሪትን መቆጣጠር (Occupy Wall Street) የሚባለው ጋር ተቃራኒ ነው ።


በርካታዎቹ የአሜሪካን ኩባንያዎች በተለይም የፋብሪካ ስራዎችን ወደ ርካሽ ጉልበት ወዳለባቸው ሀገራት በማዛወራቸው ምክንያት ፣ በምእራብ ሀገራት ያለውን የስራ እድል እያጠበበው ሄዷል ፣በተለይም የፋብሪካና የማምረት ስራዎች ። ለኩባንያዎቹ ግን ርካሽ ጉልበትና አነስተኛ ግብር ወደሚከፈልበት ሀገር ስለሚሄዱ አትራፊ ቢሆንላቸውም ለአገራቱ ዜጎች ግን የስራና ለመንግስታቱም የገቢ ማጣትን አስከትሏል ።ይሁን እንጂ አሜሪካ ይህንን የነፃ ገበያ መርህ በሁለትዮሽ ስምምነት ወደ ተጨማሪ ሌሎች የእስያ ሀገራት እንደ ደቡብ ኮርያና ጃፓን ወዳሉት እያስፋፋች ሲሆን በተለይም ካላት ሰፊ መሬትና ብዙ የግብርና ምርቷ አንፃር በግብርና ምርት ሰፊ ገበያን እንደሚከፍትላት ይጠበቃል ።


ሌላው ምክንያት የካፒታል መከማቸት በጥቂቶች እጅ እየገባ መሄድ ሲሆን ይህም የካፒታሊዝም እድገት እየቀጠለ በሄደ ቁጥር በጥቂት ኩባንያዎች እጅ እየተከማቸ ይሄዳል ። ይሄም አብዛኛው ነባር የነበረውም ሀብት ጭምር በካፒታሊስቶች እጅ ተጠቅልሎ እየገባ ሲሄድ አዲስ የተፈጠረውም ሀብትም ቢሆን በአብዛኛው ወደ ትላልቆቹ ኩባንያዎቹና ኮርፖሬሽኖች እጅ እየገባ ነው የሚሄደው ። ይሄ እንዳይሆን መንግስታት በተለያየ መንገድ መታገል ሲኖርባቸው ፣ ከታክስ ስርአቱ ጀምሮየተለያዩ ፖሊሲዎችን በሚገባ መጠቀም አለባቸው ። ነገርግን ፖለቲከኞች በንግዱ ሰዎች በቀላሉ እሚደለሉና ለኩባንያዎቹ ብቻ ተስማሚ የሆነ ፖሊሲን ካወጡ ውሎ አድሮ ኩባንያዎቹ በብዙሀኑ ህዝብ ኪሳራ የሚያተርፉ እየሆኑ ይሄዳሉ ።


ነገር ግን ካርል ማርክስ በአንድ በኩል ፣ አብዮት እንዲሳካ በትክክለኛው ጊዜና ሰአት መካሄድ ያለበት ሲሆን ይህ ትክክለኛ ጊዜ እንዴት ይታወቃል ? በ1871 የተካሄደው የፓሪስ ኮሚዩን ምንም እንኳን ማርክስ ራሱ በህይወት እያለ የተካሄደና ተስፋ ጥሎበት የነበረ ቢሆንም መክሸፉ ይታወቃል ። ሌላው ደግሞ አብዮቱ ከተደረገ በኋላ በአልተፈለጉ ሰዎች እጅ ድሉ ቢገባስ ይህ በተደጋጋሚ የሶሻሊስት አብዮት አካሂደናል ባሉ ሀገራት የታየና አንዱ የኮሚኒዝም ስርአት በተሳሳተ መንገድ ስራ ላይ እንዲውል ምክንያት የሆነ እና ስርአቱ በብዙ ሀገራት ውድቀት የተዳረገበት ምክንያት ይህው ትክክለኛ መሪዎችም ማግኘት አለመቻሉ ነው ። በሊበራል ዲሞክራሲ የሚመራው የካፒታሊዝም ስርአት ራሱን ከሁኔታዎችና ከወቅቱ ጋር የማስማማትና የማዛመድ አቅሙን ማርክስ አሳንሶ ገምቷል ።

ድርቅ



1965/66 እና 1977 ረሀቦች መነሻቸው ድርቅ የነበሩ ሲሆን በሀገሪቱ ህዝብ ስነ - ልቦና ላይ እንዲሁም በሀገሪቱ ብሄራዊ አለም አቀፋዊ ገፅታ (National Image) ላይ አሉታዊ ተፅእኗቸውን አሳርፈው አልፈዋል ። በተለይም በሀገሪቱ አለም አቀፋዊ ገፅታ ላይ ያስከተለው አሉታዊ ተፅእኖ በቀላሉ እሚገመት ካለመሆኑም በላይ ይህንን ሙሉ በሙሉ ለመፋቅም ቀላል እንደማይሆን መገመት ይቻላል ። ረሀብ በኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ ከዚህ ቀደምም የነበረ ቢሆንም ካለፉት አርባ አመታት ወዲህ ግን ዋና አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኗል ። የመሬት ይዞታ ጉዳይ ላይ በርካታ ክርክሮች ያሉ ሲሆን የመሬት ጉዳይ ተዘግቶለታል ለማለት ግን አያስደፍርም ። በ2003 / 4 . . 60 አመታት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ ቢከሰትም ከ30 አመት በፊት የተከሰተው ሁኔታ ግን አልተደገመም ።

ድርቅ መከሰቱ ተፈጥሯዊ ጉዳይ በመሆኑ ማስቀረት ባይቻልም በአሁኑ ወቅት ግን ይበልጥ በድርቅ ተጋላጭ የሆኑት አርብቶ አደሩ  በብዛት እሚኖርባቸው አካባቢዎች ናቸው ። መንግስት ሰብአዊ ቀውስ እንዳይደርስ ማድረግ ሲሆን ፣ በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢ ያለው ህዝብ እንደ ቀድሞው በአርብቶ አደርነት ብቻ ኑሮውን መግፋት ሊያስቸግረው ይችላል ። የህዝብ ብዛቱ እየጨመረ በመሆኑ ፣ በአለም ላይ እየተከሰተ ባለው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እንደ ቀድሞው ሳይሆን በአሁኑ ወቅት የውሀና የዝናብ ምንጮች ፣የተፈጥሮ እፅዋት እየተመናመኑ በመምጣታቸው ተደጋጋሚ ድርቆች ሊገጥሙት እንደሚችሉ መገመት ይቻላል ።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ አማራጭ የሆኑ ሌሎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በአካባቢው መዘርጋት ሲኖርባቸው ፣ ከእነዚህም ውስጥአንድ ቦታ ሰፍሮ ግብርና እንዲጀምር ማድረግ ፣ ለከብቶቹ በዘመናዊ መንገድ ህክምናና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን እንዲጠቀም ማድረግ ፣ የተቀረውን ወደ ከተሞች በመምጣት የስራ እድል መፍጠር እና የስራ እድሎችን እንዲያገኝ ማድረግ ያስፈልጋል ። የውሀ ምንጮችን ማጎልበት ፣ የመስኖ እርሻን ማስፋፋት አስፈላጊ ጉዳዮች ናቸው ። በተለይም የህዝብ ብዛቱ እየጨመረ ስለሚሄድ ይበልጥ ችግሩ እየተባባሰ ሊሄድ ይችላል ።ድርቅ በቻይናም በአሜሪካም በአውስትራሊያም ሊከሰት የሚችል ሲሆን ።
19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ አፄ ምንሊክ በነገሱበት ወቅትም ረሀብ ተከስቶ የነበረ ሲሆን ምክንያቱ ግን በወቅቱ ተከስቶ በነበረው የአባ ሰንጋ አንትራክስ በሽታ ምክንያት የእርሻ በሬዎችና ከብቶች በማለቃቸው ምክንያት ነው ። ከዚያ በኋላም በእጅ እየተቆፈረ እየተዘራ ችግሩ እየተቃለለ ሄዷል ።
ቀደም ባሉት የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ህትመቶች ረሀብ በሚለው ቃል ፍቺ ሲሰጥ የኢትዮጲያን ስም ያነሳ የነበረ ሲሆን ። ከዛ ቀደም ባሉ የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ህትመቶች ብንመለከት ረሀብ በሚለው ቃል ስር ትርጓሜውን ሲሰጥ ህንድን ምሳሌ ያደርግ ነበረ ። በእርግጥ መዝገበ- ቃላቱ በእንደዛ አይነት ሁኔታ የአንድን ሀገር ስም ማንሳቱ የሀገራቱን ገፅታን ማበላሸቱ የታወቀ ሲሆን ህጋዊ ውዝግብም ሊያስነሳበትም ይችላል ። ይሁን እንጂ መዝገበ - ቃላቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚያወጣቸው ህትመቶች የየትኛውንም የሀገር ስም አያነሳም።