በዘመናዊው ዓለም ህግ ማለት የድሮ ሰዎች መሳሪያ
ተማዘው ፊት ለፊት ሽጉጥ ወይም ጎራዴ መርጠው ፣ በመፋለም ያደርጉ የነበረውን ጦርነት በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ማካሄጃ መንገድ
ማለት ነው ፡፡ በጥንት ዘመን አንድ ነገር የኔ ነው ብለው ሁለት ሰዎች ተካሰው ዳኛ ወይም አንድ ገዢ ፊት በሚቀርቡበት ወቅት ተዋጡና
ወይም ተፋለሙና ይለይላችሁ ተብሎ ይፈረድና የሚፋለሙበትን መሳሪያ መርጠው ይፋለሙ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ዘመን ግን የዚህን አይነት
ጦርነት ማካሄጃው መሳሪያ ህግ ነው ፡፡
ከዚያም ሻል ባለው ዘመን ደግሞ በመርማሪ
ችሎት መቋቋም ላይ የተመሰረተ ሲሆን ይም በአውሮፓ በተለይም በስፔን መርማሪ ችሎት (Inquisition) የተሰኘ ራሱ ችሎትም መርማሪም
ፖሊስም ሆኖ የሚሰራ ችሎት ተቋቁሞ በስፔን ቋንቋ ማሮንስ የሚባሉትን የካቶሊክ ሀይማትን ያልተቀበሉ አይሁዳውያንንና መናፍቃንን ለመመንጠር
በስፔን ንጉስ የተቋቋመ የነበረ ነው ፣ በዚህም በርካታ አይሁውያን ስፔንን ለቀው ሲወጡ ስፔንም ከነበራት ሀያል የምጣኔ ሀብት ማእከልነት
ልታዘቀዝቅና የአውሮፓ ምጣኔ ሀብታዊና የንግድ እንቅስቃሴው ወደ ሰሜናዊ አውሮፓ ወደ እንግሊዝና ፣ ጀርመን ሆላንድ ወደ መሳሰሉት
አገራት ሊሄድ በቅቷል ፡፡ ካንጋሮ ፍርድ (Kangaroo Court) ቤትም እንዲሁ በስታሊን ዘመን በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት በስታሊን
ተቃዋሚዎች ላይ ያለምህረት ፍርድ ሲሰጥ የነበረ ነው ፡፡
በተመሳይም (MacCartysm) ማካርቲዝም
በመባል የሚታወቀው ማካርቲ በተባለው ችኩል በነበረው የአሜሪካ ሴናተር የተመሰረተው መንጣሪ ኮሚቴ ኮሚኒዝምን የሚመነጥር ኮሚሽን
ተቋቁሞ እንዲሁ በርካታ የሆሊውድ ጸሀፍትን ፣ የፊልም ዳይሬክተሮችን ከአሜሪካ ምድር ሊያሰድድና በርካቶችን ያለ ጥፋታቸው ሊያሳድዳቸውና
ከአገር ሊያባርራቸው በቅቷል ፡፡
ህግ በራሱ በርካታ አላማዎች ያሉት ሲሆን ከህግ ባለሙያዎች ውጪ የተቀረው ህብረተሰብ እነኚህን አላማዎች
ልብ አይላቸውም፡፡ ብዙውን ጊዜ የህግ ባለሙያዎች የህግ አላማዎች ብለው የሚያስቀምጠዋቸው ህግ ለመቅጣት ወይም ለመበቀል ፣ ለማስወገድና
ለማስተማር ነው ይላሉ ፣ ይሁን እንጂ ህግ በዚህ አይወሰንም አንዱ የህግ አላማ ያለውን ወቅታዊ የሆነውን ነባራዊውን ሁኔታ ‹Status Quo›
ማስጠበቅ ነው ፡፡ ይህ ነባራዊ ሁኔታ በሀይልም በማታለልም ይምጣ በይርጋ የህግ አንቀፆች ባለበት ይርጋ ተብሎ ሲበየን ያለው ሁኔታ
ይቀጥል እንደማለት ነው ፡፡ ለዚህም የይርጋ አንቀፆችን ብንመለከት አንድ ፍርድ ለምሳሌ በአስር አመት ውስጥ ካልተፈፀመ ‹‹በይርጋ
ቀሪ ነው የሚሆነው መፈፀሙ ካቆመ ጀምሮ ከአስር አመት በኋላ አይፈፀምም›› ይላል የፍትሀ ብሄር የስነ - ስርአት ህጉ ፣ ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው ሁከት ይወገድልኝ ብሎ ለመጠየቅ
በሁለት አመት ውስጥ መጠየቅ ሲኖርበት በዚያ ጊዜ ውስጥ ካልጠየቀ ግን የተወሰደበትን ነገር በሁከት ይወገድልኝ ማስመለስ የማይችል
ሲሆን ሊያቀርብ የሚችለው ክስ የዛ የተወሰደው ነገር ባለቤት ነኝ የሚል ክስን ነው ፡፡ ይህም በሰበር ሰሚ ውሳኔ የህግ ትርጓሜ
የተሰጠበት ነው ፡፡ ለምሳሌ ቤታቸውን በሀይል በቀበሌም ሆነ በሌላ አካል ያጡ እና በሁከት ይወገድልኝ ለማስመለስ የሞከሩ ሰዎች
ሁለት አመቱ ስላለፈ መጠየቅ አትችሉም በይርጋ ክሳችሁ ቀሪ ሆኗል ተብሎ በስር ፍርድ ቤት ውሳኔ የተሰጠባቸው ሲሆን ሰበር ሰሚ ችሎት
ግን የንብረት ባለቤትነት መብት በይርጋ ስለማይታገድ ባለቤት ነኝ በሚል የባለቤትነት ክርክራቸውን በማቅረብ ቤታቸውን ለማስመለስ
የሚችሉበት እድል አለ ብሎ ጭብጡን ለውጦ ፈርዶበት ወደ ስር ፍርድ ቤት መልሶታል፡፡
ህግ
የረጅም ጊዜውን አርቆ በማየት የተሰደረ ነው ፡፡ በአንድ ክርክር ወቅት ረዘም ያለ ቀጠሮ የሚሰጥበት ምክንያት ተከራካሪ ወገኖች
በዚያ ነገር አንዴ ስለሆነ የሚወሰነው ተዘጋጅተው የህግ ባለሙያ አማክረውም ሆነ ራሳቸው ደህና መልስ ይዘው እንዲቀርቡና አጥብቀው
እንዲያስቡበት እንደሆነም ማንም አይስተውም ፡፡
ህግ
አንድን ሰው ከራሱ አጥፊ ድርጊት ለመጠበቅ የተደራጀ ነው ፡፡ ለምሳሌ በህግ አንድ ሰው ራሱን እንዲገድል ወይንም ራሱን የሚጎዳ
ነገረን እንዲያደርግ አይፈቀድለትም ፡፡ በተሻሻለው የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ በሚያውጀው አዋጅ ላይ አንድ ሰው ራሱ ከፈጠረው
የስነ - ጥበብ ውጤት አይከፈለኝ ማለት አይችልም ፡፡ አንድ ሙዘቀኛ ባቀነቀነው ሙዚቃ ይከፈልህ ሲባል የለም አይከፈለኝ ማለት አይችልም
፣ አንድ ሰራተኛም በሰራተኝቱ ማግኘት የሚገባውን እና ህግ የሚፈቅድለትን ጥቅምም ሆነ መብት በገዛ ፈቃዴ ትቻለሁ ቢል በህግ ፊት
ተቀባይት የለውም ፡፡ አንዳንድ አገራት በእርግጥ አንድ በማይደን ህመም የተጠቃ ሰውን ህይወቱ እንዲጠፋ ወይንም ራሱን በራሱ የማጥፋት
መብት እንዲኖረው ወይንም ሀኪሞች ህይወቱን እንዲያጠፉ ራሱ ወይንም ቤተሰቡ መፍቀድ እንዲችሉ የሚፍቅድ ህግ እንዲፀድቅ የሚጠይቅ
አዋጆች እንዲወጡ ሲጠየቅ እንደ ሆላንድ ያሉ አገራት ላይ በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት ተደርጓል ፡፡
ህግ
የራሱ የጊዜ አቆጣጠርም አለው ፣ ለምሳሌ አንድን ነገር አንድ ተብድያለሁ የሚል
ሰው ሊጠይቅ የሚችልበት ጊዜ ራሱ በህግ የተገደበ ነው ለምሳሌ አንድ በደል የደረሰበት ሰው በሁለት አመት ውስጥ በደሉን ወደ ህግ
ካላቀረበ ከዚያ በኋላ በማንኛውም ጊዜ ተበድያለሁ የሚል ጥያቄን ማቅረብ እንደማይችል የፍትሀ ብሄር ህጉ ይደነግጋል ፡፡ በአሰሪና
ሰራተኛ ህጉም ላይ ከሶስት ወር እስከ አንድ አመት ድረስ የይርጋ ጊዜዎች ተቀምጠዋል፡፡
በ1950ዎቹ
የወጣው የፍትሀ ብሄር እና የንግድ ህግጋት ከወጡ ወደ ስልሳ አመታትን ያስቆጠሩ በመሆኑ ከአሁኑ ዘመን ጋር በሚሄድ መንገድ
መሻሻል እንደሚያስፈልጋቸው ግልፅ ነው ፡፡ ከእዚሁ የፍትሀ ብሄር ህግ ውስጥ መንግስት ለራሱ አሰራር አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን እየነመረጠ
አሻሽሏል ፡፡ ለምሳሌ የሊዝ አዋጅ ፣የቤተሰብ ህግ ፣ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ፣ የግብር አዋጅ የመሳሰሉት ተሻሽለዋል ሆኖም በአጠቃላይ
የፍትሀ ብሄር ህጉም ሆነ የንግድ ህጉ አሁን ካለው የኢኮኖሚና የንግድ እንቅስቃሴና ካለው ማህበረሰባዊና ፖለቲካዊ ለውጦች አንፃር
መቃኘትና መሻሻል እንደሚገባቸው ግልፅ ነው ፡፡
‹‹የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ውሳኔዎች››
በሚል ርእስ ስር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በ2005 እና በ2006 ዓ.ም. ካሳተማቸው በ13ኛው ና በ14ኛው ቅፆች ውስጥ የዚህ አይነት አስገዳጅ የሆነ የህግ ትርጓሜ የተሰጠባቸውን ክርክሮች ውሳኔዎችን ማግኘት ይቻላል
፡፡ ክርክር እንዳለ እያወቁ ዝም ያሉና ክርክር ባለበት ወቅት በክርክሩ ውስጥ ገብተው መብታቸውን ያላስከበሩ ይዞታቸውን እስከማጣት
ድረስ የተወሰነባቸው ግለሰቦች እንዳሉ ከሰበር ውሳኔዎች ማንበብ ይቻላል ፡፡
አንድ ሰው የውርስ መብት አለኝ ብሎ ካለ ውርስ ይጣራልኝ
ብሎ መጠየቅ የሚችለው በሶስት አመት ውስጥ ነው ብሎ ሰበር ሰሚው ችሎት የህግ ትንታኔ የሰጠበት ሲሆን ፣ አንዲሁም አንድ ሰው የስጦታ
ውልን አድርጎ ያደረኩት የስጦታ ውል ይፍረስልኝ ወይም ይፈፀምልኝ ብሎ መጠየቅ የሚችለው በአስር አመታት ውስጥ ነው ብሎ ሰበር ሰሚው
የህግ ትርጓሜን ሰጥቶበታል ፡፡ የዚህ አይነት ህግጋት በግልፅ የስነ ስርአት ህጉ ላይም ሆነ በተለይም የዋናው የፍትሀ ብሄር ህጉ
ላይ በግልፅ መቀመጥ የነበረባቸው ናቸው እንጂ በሰበር ሰሚው የህግ ትርጓሜ ሊሰጥባቸው የሚገቡ አልነበሩም ፣ ምክንያቱም አንድ ሰው
የፍትሀ ብሄር ህጉን በሚያነብበት ወቅት መሰረታዊ የሆኑ የዚህ አይነት ህግጋትን በዋናው ህጉ ላይ ቁልጭ ብለው መቀመጥ የሚገባቸው
ናቸው እንጂ በህግ ትርጓሜ ሊብራሩ የሚገባቸው አልነበሩም ፡፡ ‹‹ህግን
አለማወቅ ይቅርታን አያሰጥም›› የሚው የፍትሀ ብሄሩም ሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ህጎቹ ላይ በግልፅ የተቀመጠ
በመሆኑ አንድ ሰው አዋጆችን እየገዛ ሊያነብ ይችላል ፣ ነገር ግን በአብዛኛው የህግ ባለሙያዎች ለስራቸው ሲሉ በሚከታተሏቸው እንደ
ሰበር ሰሚ ውሳኔ የመሳሰሉ ሰነዶችን የማግኘት እድሉ አነስተኛ ነው - የዚህ አይነት ሰነዶች የት እንደሚገኙ ማወቁ ራሱ ፈተና ነው፡፡
ይህን እንጂ የዚህ አይነት ክርክሮች በተደጋጋሚ ለሰበር
እየቀረቡ ተመሳሳይ የህግ ትርጓሜ ሲሰጥባቸው ይስተዋላል ፡፡ ሰበር በአንድ ጉዳይ ላይ የተለየ ጭብጥን በመያዝ ከቀድሞው የተለየ
ውሳኔ መወሰን እንደሚችል ግን የፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ ላይ ተደንግጓል ፡፡ ለዚህ አይተኛ ምሳሌ የሚሆነው ሰበር ችሎቱ በአንድ ወቅት የንብረትን የመጠየቅ
መብት በይርጋ ቀሪ እንደሚሆንና በአስር አመት ውስጥ ጠያቂው ካልጠየቀ በስተቀር ከዚያ በኋላ የመጠየቅ እንደማይችል ሲበይን በሌላ
ወቅት ደግሞ በተመሳሳይ ጭብጥ የንብረትን የመጠየቅ መብት በይርጋ ቀሪ እንደማይሆንና በይርጋ ቀሪ የማይሆንበትን የፍትሀ ብሄር ህግን
እና ህገ - መንግስቱ የንብረት ባለቤትነት መብትን ያረጋገጠ መሆኑን ጭምር በመጥቀስና እንዲሁም ይህንን የንብረት ባለለቤትነት መብትን
ከሰብአዊ መብት ጋር እኩል በማድረግ ቤቱ ለባለቤቱ ይመለስ የሚል ውሳኔን ሰጥቷል ፡፡ የማይንቀሳቀስ ንብረትን በተመለከተ የሚቀርብ
የመፋለም ክስ በይርጋ ቀሪ ሆኗል የሚችል ስላለመሆኑ የሰ/መ/ቁጥን 43600 በቅፅ 10 በጥቅምት 2006 ዓ.ም በታመው
የሰበር ችሎት ውሳኔዎች ላይ ታትሟል ፡፡
እንዲሁም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባሳተመው በሰበር
ችሎት ውሳኔዎች ቅፅ ቁጥር 6 ላይ እንደተመለከተው በሰ/መ/ቁጥር 27739 ላይ ከመሬት ሽያጭ ጋር በተያያዘ የሚቀርብ የክስ አቤቱታ
የክስ ምክንያት የሌለውና በፍርድ ቤት ሊስተናገድ የማይችል ስለመሆኑ ሲወስን መሬትን ሊሸጥ የማይችል በመሆኑ በህገ መንግስቱ ላይ የተደነገገ ስለሆነ ነው ፡፡
በኢትዮጲያ የሚወጡ አንዳንድ ህግጋት ‹‹ጥርስ አልባ›› በመሆንም ይታወቃሉ
፡፡ዎልፍ ጋንግ ቮን ጎቴ የተባለው ጀርመናዊ ፈላስፋና ገጣሚ እንደሚለው ‹‹መቅጣት የማይችል ዳኛ ፣ የማታ ማታ የወንጀለኛ ተባባሪ ይሆናል›› ይላል
፡፡ ዳኛው ብቻ ሳይሆን ህጉም ጭምር መቅጣት የማይችል ‹‹ጥርስ
የሌለው አንበሳ›› ከሆነ ወይንም ቆንጣጭ የሆነ ቅጣትን የማያሳርፍ ከሆነ ወንጀል እንደ ቀልድ እንዲሰራና
ህገ - ወጥ ድርጊት እንዲንሰራፋ ያደርጋል ፡፡ አልጠየቅም ወይንም ፍር እስኪመጣ ጊዜን ይወስዳል በሚል ሰዎች ወደ ህገ - ወጥ
ድርጊት እንዲሀቡ ያደርጋል ፡፡
በ1992 ዓ.ም. የወጣው የጠበቆች የስነ - ምግባር ደንብ
አንድ ጠበቃ ከባድ የስነ - ምግባር ጥሰት ቢፈፅም ምንና በምን አይነት መንገድ እንደሚቀጣ ምንም የሚገልጸው ነገር አልነበረም ፡፡
አንድ ጠበቃ የዛን አይነት ጥሰትን ቢፈጽም እና ይህን ያወቀ ጠበቃ ለፍርድ ቤት ወይንም ፈቃድ ለሰጠው አካል መጠቆም እንደሚችል
ብቻ ይገልፃል እንጂ ቅጣቱ ምን ሊሆን እንደሚችል እንኳን የሚገልጸው ነገር የለም ፡፡ ይህም ጠበቆች ሃሰተኛ ምስክሮችን በመጠቀም
ፍርድ ቤቶችን በማሳሳት ውሳኔዎችን ሲያስወስኑና ሲያስፈርዱ በተደጋጋሚ ተስተውሏል ፡፡ ይህን በማየት ይመስላል ይህንን ደንብ ማሻሻሉንና
ሃሰተኛ ምስክሮችን በመጠቀም ፍርድን የሚያስፈርዱ ጠበቆች ላይ ከበድ ያለ ቅጣትን የሚጥል ደንብ ተረቆ እንደተዘጋጀ የፍትህ ሚኒስቴር
ሃላፊዎች የገለፁት፡፡
በሃገራችን የፍርድ ቤት ቀጠሮ ረጅም መሆኑንና እንዲሁም
በአንድ ወቅት የወጣ የአሜሪካ ምገስት ሪፖረውት ርት እንደሚያመለክተው የኢትዮፒያ ፍርድ ቤቶች ፍትሐ ብሄር ሙግት ያላቸው ልምድ
አነስተኛ ነው ሲል ተችቷል ፡፡ አንድ ቀጠሮ በረዘመ ቁጥር ያንን ነገር በይዞታው ስር አድርጊ የሚከራከረው ወገን ያለአግባብ ተጠቃሚ
ሲሂን ሆን በአንፃሩ ነገሩ ትክክለኛ ባለቤት የሆነው ሰው ቆይቶ ቢፈረድለትም ዋናውን ንብረቱን ከአመታት ክርክር በኋላ ማስመለስ
ቢችልም ነገር ግን የሚደርስበት ኪሳራ ግን ሊካካስ የሚችል አይደለም ፡፡ ምናልባት ከውል ውጪ አለአግባብ መበልጸግ የሚሉ የፍትሀ
ብሄር ህግጋት አንቀፆችን በመጥቀስ ድጋሚ መክሰስና ከውል ውጪ ደርሶብኛል የሚለውን ኪሳራ በተወሰነ መልኩ ማካካስ ቢችልም ይህም
ቢሆን ብቁ ላይሆን ይችላል ፡፡ በፍትሀ ብሄር ህግ ስነ ስርአት ህጉ መሰረት በፍርደ ባለእዳ ላይ የሚታሰበው ወለድ ምጣኔ 9 ፐርሰንት
ሲሆን ይህም አሁን ካለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ከፍተኛ የዋጋ ንረት ባለበት ሁኔታ ባንኮች እስከ 17 በመቶ በሚያበድሩበት ሁኔታ
በ1958 ዓ.ም. የወጣው የፍትሀ ብሄር የስነ ስርአት ህግ አፈፃጸምን በሚመለከት ያስቀመጠው የ9 በመቶ ወለድ ምጣኔ ከአሁኑ የኢኮኖሚ
ሁኔታ ጋር መሄዱ ሊገመገም የሚገባው ነው ፡፡
የኢትዮጲያ የህግ ስርአት በጣም ዘገምተኛውንና ቀሰስተኛው
ሳይሆን አይቀርም ፡፡ እንደ ቀልድ ፍርድ ቤት የተከፈተች መዝገብ አመታትን ባለጉዳዮችን ስታመላልስ ትስተዋላለች ፡፡ ይህ በሌሎችም
አገራት የሚታይ ነው እንደ ጃፓን ባሉ አገራትም ጭምር ፍርድ ቤት የገባ ነገር አመታትን እንደሚወስድ ይነገራል ፡፡ በተለምዶ ‹‹የዘገየ ፍትህ እንደ ተነፈገ ይቆጠራል›› የሚል
አባባል አለ፣ ህብረተሰቡ በተለምዶ ጉዳዮች የሚፈጁትን ረጅም ጊዜ በማስተዋል ‹‹ከሳሽ ከመሆን ፣ ተከሳሽ መሆን ይቻላል›› ሲል ይሰማል
፡፡ የአንድ ፍርድ ምንም እንኳን ሰበር ሰሚው ጋር ደርሶ ትክክለኛው ቢፈረድም እዛ ደረጃ ለመድረስ አመታትን ወስዶ ነው ፡፡ ሲፈፀም
ደግሞ ለማስፈረድ ያለውን ድካም ቸል የማለትና ፍርዱን እንደ ምንም ያለመቁጠር ሁኔታ የሚታይ ሲሆን ፣ ይህም አፈፃጸሙ ለአንድ ተበዳይ
ለሆነ ሰው በራሱ ሌላው ራስ ምታት ነው ማለት ይቻላል ፡፡
ክፉ ስራ ቶሎ አለመቀጣቱና የፍርድ መዘግየት ከጥንትም
ጀምሮ ሰዎች ክፉን እንዲያደርጉ የሚያበረታተ እንደሆነና ጠቢቡ ሰለሞን ‹‹በክፉ ስራ ላይ ፈጥኖ ፍርድ አይፈረድምና፣
ስለዚህ በሰው ልጆች ውስጥ ልባቸው ክፉን ለመስራት ጠነከረ›› መፅሀፈ መክብብ ምእራፍ 8 ፣ ቁጥ 11 ፣ነገር
ግን ሃጢአተኛ መቶ ጊዜ ክፉን ቢሰራ ፣ ዘመኑም ረጅም ቢሆን ለፃድቃን እንጂ ለሃጢአተኞች ደህንነት እንደሌለ ጠቢቡ አክሎበታል ፡፡
እዚህ ላይ ሁለት እስረኞች አንድ ሱልጣን አንድ የተለየ
ነገር እንዲያደርጉ ይጠይቃቸዋል ፡፡ አንደኛው የሞት ፍርድ የተፈረደበት እስረኛ የሱልጣኑን ፈረስ በአንድ አመት ውስጥ መብረር ሊያስምር ቃል ይገባል ፡፡ ጓደኛው እስረኛም በመገረም እንዴት ፈረስ መብረር
አስተምራለሁ ትላለህ ይለዋል ፡፡ ቃል የገባው ጓደኝየው ሲመልስም እስከዛው ወይ ፈረሱ ይሞታል ፣ ወይ እኔ እሞታለሁ ወይንም ራሱ
ሱልጣኑ ይሞታል ብሎ መለሰለት ይባላል ፡፡ ይህም በፍትህ ስርአት
ውስጥ ጊዜ ምን ያህል ፍትህ ላይ ተፅእኖ እንዳለው የሚያሳይ ሲሆን በጊዜ ያልተሰጠ ፍትህ ለጥፋተኛው ከፍርድ ማምለጥን ያስከትላል
፡፡
የዚህ አይነት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሱ ክርክሮችን ውሳኔዎችን
ማንበብ የሚፈልግ ስድስት ኪሎ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ የሚሸጠውን እና በየአመቱ የሚታመውን እንዲሁም በፌደራል ጠቅላይ
ፍርድ ቤት ድረ - ገፅ (www.fsc.gov.et) ላይ
በነፃ የሚገኘውንና ወደ ኮምፒውተር ገልብጦ ማንበብ የሚቻለውን ‹‹የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ውሳኔዎች›› የሚለውን የህግ ትንታኔ የተሰጠባቸውንና በየአመቱ
የሚታሙትን ቅፆች ማንበብ ይቻላል፡፡