news.et
የአቶ በረከት የቁም እስረኝነት፤ የመጨረሻው መጀመሪያ
Published 1 day ago on December 4, 2018 By Teshome Tadesse
5-7 minutes
የአቶ በረከት የቁም እስረኝነት፤ የመጨረሻው መጀመሪያ | ፀጋው መላኩ በድሬቲዩብ
አቶ በረከት ስምኦን የቁም እስረኛ ለመሆን ተገደዋለ፡፡ ቀኖቹም ለእሳቸው የከፉ ሆነዋል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ከአንዱ የሥልጣን እርካብ ወደ ሌላው የሥልጣን ወንበር እየተሸጋገሩ ከፓርቲያቸው እኩል የስልጣን ዘመን ላይ የነበሩት አቶ በረከት ዛሬ በጭርታና በዝምታ ውስጥ ናቸው፡፡ በመኖሪያ ቤት ጊቢያቸው ከነቤተሰባቸው ሰብሰብ ብለው በሀገሪቱ ብሎም በእሳቸው ቀጣይ እጣ ፋንታ ዙሪያ ሊሆን የሚችለውን በጥንቃቄ በመከታተልና በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡
ዛሬ ትናንት የነበሩ ጓደኞች፣ ወዳጆች፣ ጠባቂ ጋርዶች፣ አሸብሻቢዎች፣ ቬሎ ያዦች ሁሉ የሉም፡፡ የኢህአዴግ የሥልጣን ጉዳይ ከእጅ ያመለጠ ብርጭቆ ሆኗል፡፡ የአሁኑ ኢህአዴግ አቶ መለስ ከመሩት ኢህአዴግ በብዙ ማይልስ የራቀ ነው፡፡ የአሁኑ ኢህአዴግ ከቀድሞው ኢህአዴግ በሰዓት በብዙ ማይልስ ፍጥነት በመጓዝ ርቀቱን እያሰፋ ይገኛል፡፡ አሁን ያለው የለውጥ ፍጥነትና ርቀት በዚሁ ከቀጠለ የአሁኑ ኢህአዴግ ምንአልባትም ለጥቂት ጊዜ ይዞ ሊቀጥል የሚችለው ኢህአዴግ የሚለውን ስም ብቻ ይዞ ነው፡፡ እሱንም ቢሆን የቀድሞው ብአዴን እና ኦህዴድ ስማቸውንና አርማቸውን በመቀየር የግንባሩ ስያሜና አደረጃጀት ሳይቀር የሚቀየርበት ሂደት አይቀሬ መሆኑን እያሳዩን ነው፡፡
የለውጡ ፍጥነት አቶ በረከትን የመሳሰሉ የፖለቲካ ሰዎች ከሩጫው ተቆርጠው እንዲቀሩ አስገድዷቸዋል፡፡ ተቆርጦ መቅረትም ብቻ ሳይሆን ከውድድሩ ውጪ በመሆን ከመወዳደሪያ ሜዳው ወጥቶ ወደ ቤት ለመመለስም አስገድዷል፡፡ እናም አቶ በረከት የአብዮታዊ ዲሞክራሲን ርዕዮተ ዓለም ወንጌል ሰብከው ብዙዎችን ካጠመቁበት፣ካዳቆኑበትና ካቀሰሱበት የኢህአዴግ የፖለቲካ መቅደስ ተባረው የመጨረሻቸውን መጀመሪያ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡
አቶ በረከት በሁለት መልኩ የቁም እስረኛ ለመሆን ተገደዋል፡፡ በአንድ መልኩ ከፖለቲካ ለውጡ ጋር በተያያዘ በየትኛወም ሁኔታ በሚኖራቸው እንቅስቃሴ “ከግለሰቦች ወይንም ከቡድኖች ጥቃት ይረድስብኛል” ብለው በመስጋታቸው ሲሆን፤ ይህም ደግሞ አጠቃላይ ባላቸው ማህበራዊ መስተጋብር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እያሳደረ ይገኛል፡፡
በመሆኑም አቶ በረከት ፈረንጆቹ ሰልፍ አይዞሌሽን (Self Isolation) እንደሚሉት በራሳቸው ማህበራዊ መስተጋብር ላይ እቀባ በማድረግ በቁጥብ ማህበራዊ ግንኙነት ራሳቸውን አግልለው እንዲኖሩ አስገዳጅ ሁኔታን ፈጥሮባቸዋል፡፡ ይህ ራስን የቁም እስረኛ ማድረግ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡
አቶ በረከትን ለዚህ ያበቃቸው በተለይ በ2010 ማብቂያ “እሳቸው በዚህ ወጡ በዚያ ገቡ” እየተባለ በአማራ ክልል ሲደረግ የነበረው አሰሳና በደብረማርቆስ ከተማ እሳቸው ነበሩበት በተባለው ጎዛምን ሆቴል ሆቴል የደረሰው ጥቃት ነው፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎ በነበሩት ጊዜያት አቶ በረከት በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች በአንፃራዊ ነፃነት የሚንቀሳቀሱ ሰው ነበሩ፡፡
አቶ በረከት ህላዊ ዮሴፍን ከመሳሰሉ የቀድሞ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች “ለውጡን ለመቀልበስ እየሰሩ ነው” በሚል ከዚህ ቀደም በህዝቡ ክትትል ሲደረግባቸው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በአጠቃላይ ሲታዩ አቶ በረከት ራሳቸውን በቁም እስረኝነት እንዲያስቀምጡ የሚያስገድዷቸው ሆነዋል፡፡
በነገራችን ላይ የአቶ በረከት ምናኔ በቀድሞው ጓዶቻቸው ሳይቀር ከመገለል ጋር የተያያዘም ጭምር ነው፡፡ አቶ ደመቀ መኮንንና ሌሎች የቀድሞዎቹ ወዳጆቻው ሳይቀሩ በአቶ በረከት ላይ ፊታቸውን ማዞራቸው ይነገራል፡፡ አቶ በረከት ተቀባይነታቸውና የቀደመ የባለስልጣን ተፈሪነት ግርማ ሞገሳቸው ተገፎ በግልፅ አቅም እያጣ ከመጣ ዋል አደር ብሏል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የአቶ መለስ ህልፈተ ህይወት ለአቶ በረከት የቁልቁለት ጉዞ መጀመሪያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡
አቶ በረከት በተለይ በምርጫ ዘጠና ሰባት ከተቃዋሚዎች ጋር ሽንጣቸውን ገትረው በመከራረከር፣በማስፈራራትና በህዝባዊ አመፁም ወቅትም በኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ቲም ክላርክ፤ እንደዚሁም ከህብረቱ ታዛቢዎች ቡድን መሪ አና ጎሜዝ ጋር ብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ የገቡ የኢህአዴግ ቀኝ እጅ ነበሩ፡፡
ከዚያ በኋላም ኢህአዴግ የተቃዋሚ መሪዎችን በጅምላ አስሮ የስልጣን ወንበሩን እንዲያደላድል በማድረጉ ረገድ የአቶ በረከት ሚና እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም፡፡ አቶ በረከት በምርጫ 97 ማግስት በነበሩት ተከታታይ ዓመታት ኢህአዴግ የአገዛዝ ልጓሙን ሲያጠብቅ የሥልጣን ኮርቻው ላይ በሚገባ ሲጋልቡ ከነበሩት ጥቂትና ወሳኝ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ካህናት መካከል አንዱ ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ ሰው ናቸው፡፡
ከዚያ በኋላ በነበሩት ጊዜያት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም የሥልጠና ሰነዶችንና ማንዋሎችን በማዘጋጀት ሀገሪቱን በስብሰባ ማዕበል እንድትናጥ ሲያደርጉ የቆዩ ፖለቲከኛም ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ በተለይም የመንግስትና የፓርቲ መዋቅር እንዲደበላለቅ በማድረጉ ረገድ ሰፊ ሚናን መጨዋታቸውም ይነገራል፡፡
አቶ በረከት ባላቸው የፖለቲካ ስብዕና ነገር የሚይዙ፣ፊታቸው የማይፈታ፣መቼ አጥቅተው መቼ መከላከል እንደሚገባቸው በሚገባ የሚያውቁ የሴራ ፖለቲካ አዋቂ ናቸው የሚባልላቸው ሰው ናቸው፡፡
ይሁንና በ2008 ዓ.ም የተጀመረው ህዝባዊ አመፅ ለአቶ በረከት የሚሆን አልነበረም፡፡ በተለይ ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የራሱን መልክ እየያዘ የመጣው የአማራ ብሄርተኝነት ብአዴንን ከአቶ በረከት መዳፍ ፈልቅቆ አውጥቶታል፡፡ የአቶ በረከትን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ቁርባን መመነኛ ገዳም ያሳጣውም የብአዴን የቀድሞዎቹ አመራር ምሽግ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መናዱን ተከትሎ ነው፡፡
የተቀባይነት ማጣት ታሪኩ በአቶ መለስ ህልፈተ ህይወት ማግስት ቢጀምርም የአቶ በረከት ተቀባይነት መሸርሸር “ሀ” ብሎ የጀመረው በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ዘመን ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ አቶ በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል የኢንዱስትሪ ዘርፍ መሪ ሚኒስትር ሆነው ባገለገሉባቸው ዓመታት ያቀርቧቸው የነበሩት ሀሳቦች ተቀባይነትን እያጡ በመሄዳቸው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቂያ እስከማስገባት የደረሱባቸው አጋጣሚዎች እንደነበሩ የሚታወስ ነው፡፡
ነገሮች ዋል አደር እያሉ ሲመጡ ደግሞ ተቀባይነት ከማጣት ስልጣንን ወደማጣት ተሸጋገረ፡፡ ቆየት ብሎ ደግሞ ስልጣንን ማጣቱ ወደ መገለል ደረጃ አደገ፡፡ ነገርየው እየበሰለ ሲሄድ ደግሞ ከመገለል ወደ ተጠያቂነትም ደረጃ ከፍ እያለ ይገኛል፡፡
ሁለተኛው የቁም እስረኝነት የሚመጣውም እዚህ ጋር ነው፡፡ አቶ በረከት በአማራ ክልል የኢንድዎመንት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ በነበሩበት ወቅት ከጓዳቸው አቶ ታደሰ ካሳ ጋር በመሆን በተዝረከረከ አሰራር ድርጅቱን በቢሊዮን የሚቆጠር ብር አክስረዋል በሚል ስማቸው በጥብቅ እየተነሳ ይገኛል፡፡
በአማራ መገናኛ ብዙኋን ድርጅት በየሳምንቱ እየታተመ የሚወጣው በኩር ጋዜጣ በህዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም ዕትሙ እንዳስነበበው ከሆነ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአቶ በረከት ላይ ክስ ለመመስረት ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከዚህ ቀደም በተጠርጣሪዎች አያያዝ ዙሪያ ሲናገሩ አንድ ቁምነገር ማስተላለፋቸው የሚታወስ ነው፡፡ ቁምነገሩ “አስረን ሳይሆን የምንመረምረው፤ አጣርተን ነው የምናሰረው” የሚል ነበር፡፡ ይሁንና እስከዚያው ግን መንግስት የሚጠረጠሩ ሰዎችን አይኑን ጥሎ በአይነ ቁራኛ የሚከታተላቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አከል አድርገውም ተናግረዋል፡፡
እናም በኩር ጋዜጣ አቶ በረከት መጠርጠራቸውን ከዘገበልን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ የሚጠረጠሩ ሰዎች በመንግስት አይነ ቁራኛ ሥር ሆነው ክትትል የሚደረግባቸው መሆኑን ከነገሩን፤ ሁለቱን ስንደምራቸው የምናገኘው የመጨረሻ ውጤት ቢኖር አቶ በረከት በአይነቁራኛ ሥር ያሉ የቁም እስረኛ መሆናቸውን ነው፡፡
ለቁም እስረኝነት የተዳረጉት ደግሞ በመነሻችን ጠቆም እንዳደረግነው በደረሰባቸው መገለልና የእንቅስቃሴ ዋስትና ማጣት የተፈጠረው ራስን ማቀብ ወይንም ሰልፍ አይዞሌሽን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመንግስት የቅርብ ርቀት አይን ክትትል የሚደረግባቸው መሆኑ ነው፡፡
አቶ በረከት ባለፈው በተካሄደው የቀድሞው ብአዴን የባሀርዳር ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ በክልሉ የፀጥታ ዋስትና እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም ዋስትና የሚሰጣቸው ሰው ባለማግኘታቸው ከሰብሰባው መቅረት ግድ ብሏቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ የስብሰባውን ሂደት ከአዲስ አበባ በስልክ ለመከታተትል ያደረጉት ጥረትም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የቀድሞ አጋሮቻቸው ስልክ አንስቶ ለማናገር እንኳን ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነበር፡፡
እናም አቶ በረከት በጊዜው ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ መታገዳቸውን የሰሙት እንደማንኛውም ሰው በመገናኛ ብዙኃን ነበር፡፡ እነዚህ በአቶ በረከት ላይ እየደረሱ ያሉት ማህበራዊና አመራራዊ መገለሎች እሳቸውም በሥነልቦና ጫና ወድቀው ራሳቸውን በማግለል በቁም እስር ውስጥ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ የቁም እስሩ አካላዊም ስነልቦናዊም መሆኑ ደግሞ ፈተናውን ያከብደዋል፡፡ ሲያልቅ አያምር ይሏል ይህ ነው፡፡
በሶስተኛው ዓለም ፖለቲካ፡- የጨዋታ ህግ ስለሌለ በጥሎ ማለፉ ፖለቲካ በልተህ ታልፋለህ፤ አንተ በተራህ በሌላ ትበላለህ፡፡
አብዮት ልጇን ትበላለች ማለት ይህ ነው፡፡
** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ
No comments:
Post a Comment