አንድ መሪ የሌሎች ሰዎችን ባህሪና ፍላጎት መረዳት መቻል አለበት ።ባለማወቅ ወይንም ሆነ ብሎ የሌሎች ሰዎችን ስሜት
የሚረጋግጥ ከሆነ ይዘግይም ወይንም ይፍጠንም በሌሎች ሰዎች ያለዉ ተወዳጅነትን እያጣ መሄዱ የማይቀር ነዉ ። ኢሞሽናል ኢንተሊጀንስ
በተፈጥሯቸዉ የታደሉ አሉ ይሁን እንጂ በመማርም ሊገኝ ይችላል።ልክ እንደ ኦቲስቲክ (Autistic) ልጆች አይነት ። በእርግጥ ይህ ችሎታ በቀለም ትምህርት የሚገኝ ነገር አይደለም ። አንድ ሰው በከፍተኛ ደረጃ የተማረ
ቢሆንም እንኳን የዚህ የሌሎችን ስሜት የመረዳት ችሎታው ግን አነስተኛ ሊሆን ይችላል ። ውስብስብ የሆኑ ስለ- ልቦናዊ ባህሪያቶችን
ማወቅ አለበት ።
አንድ መሪ የሀገር መሪ ቢሆን ራሱን ከሀገር ማስበለጥ የሌለበት ሲሆን እንደዛ ካደረገ ግን እንደ ተሞኘ ይቆጠራል ።
ለምሳሌ ሙባረክ ማለት ግብፅ ፣ ተብሎ ይታሰብ የነበረ ሲሆን ልጁም ስልጣኑን እንደሚወርስ ይገመት የነበረ ቢሆንም ያ ቀርቶ በዛ
ምትክ ማንም ከዛ አስቀድሞ ማንም ባላሰበውና ሊያስበው በማይችለው ሁኔታ በሰባት ሺ የግብፅ የነገስታትና የመሪዎች ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ
ሁኔታ መሪዎቹ ፍርድ ቤት ለመቅረብ በቅተዋል ።
መሪው ተከታዮቹን ባህሪ ማወቅ አለበት ፤አንዳንድ ተከታዮች ተባባሪዎችና ቀና አመለካከት ያላቸው ሲሆኑ አንዳንዶች ደግሞ
ቀና አመለካከት የሌላቸውም ሁሉ ሊሆኑ ይችላሉ ፣አንዳንዶች ደግሞ ለመሪው የማይጠቅሙም የማይጎዱም ሆነው ሊገኙ ይችላሉ። ሰዎች መሪው
ከሚሰጣቸው መመሪያ ይልቅ መሪው ማነው ብለው ይጠይቃሉ ።
በአሁኑ ወቅት ከአስተዳደር ባለሙያዎች ትኩረት
እየተሰጠው ያለ ጉዳይ የስብእና ፍተሻ (Personality
Test) የሚባለው ሲሆን ይኀውም የተለያዩ ሰዎች ያላቸውን የተለያየ ተፈጥሯዊ የሆነ ስብእናን
ትኩረት መስጠትና ለአስተዳደር ያለውን በጎም ሆነ አሉታዊ ተፅእኖ በመረዳት ነው ። የቀድሞው የአስተዳደር አስተሳሳብ በሰዎች መሀከል
ያለውን ተፈጥሯዎዊም ሆነ ማህበራዊ ልዩነቶችን ትኩረት የማይሰጥና ሁሉም ሰዎች በባህሪም ሆነ በአስተሳብም አንድ አይነት ናቸው ብሎ
የሚያስብ የነበረ ሲሆን ፣ አሁን በዘመናችን ግን ልዩነቶች ትኩረትን እያገኙ መጥተዋል ። ጥሩ ሌሎችን የመረዳት አስተውሎት ያለው
መሪ እነኚህን የስብእና ልዩነቶችን በሚገባ የሚረዳ ይሆናል ።
ይሁን እንጂ በቡድናዊ
ጠባብ አስተሳሰብ (Group-think) እንዳይታሰርም መጠንቀቅ አለበት ። ብዙውን ግዜ ይሄ አስተሳሰብ በአንድ
ቡድን ውስጥ ለሰፈነ ቡድኑ እሚሰራውን ስህተት ለማየት ያስችለው የነበረውን እይታ ያጠበዋል፤ የምናደርገው ነገር ሁሉ ትክክል ነው
በሚል ቡድናዊ እሳቤ ፣ ገሀዳዊውን እውነታና ከውጪ የሚመጡ ስህተቶችን ነቀፌታዎችን ለመረዳት ሳይችል እንዲቀር ያደርገዋል ። ከውጪ
ያለ ሰው በቀላሉ የሚያያቸውን እንከኖች ለማየት ያስችል የነበረውን እድል ያሳጣዋል ። ይህ ብቻ ሳይሆን ከእውነታው ውጪ የሆነ (Delusional)የሆነ አስተሳሰብ ይፈጠራል ። ይህም ወደ ቅዠት የቀረበ አስተሳብ ሲሆን ከገሀዳዊው እውነታ ውጪ የሆነ አስተሳሰብን
መያዝን ያመለክታል ፤ መሪዎችም ሆኑ ቡድናቸው የዚህ አይነቱ አስተሳሰብ ከሰረፀባቸው ወደ ውድቀትና ወደ ስህተት የማምራታቸው እድል
እየሰፋ ይመጣል ።
No comments:
Post a Comment