Wednesday, March 13, 2013

የመሪዎች ተጠያቂነትና ሀላፊነት

በታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብለን ብንመለከት የጥንት ነገስታት የአሁኑን አይነት ተጠያቂነት አልነበረባቸውም ። ሰዎችንና አውሬዎችን በማደባደብ በምትታወቀው በጥንታዊቷሮም ፣ የሮማውያን ነገስታት ካሊጉላንና ኔሮን ብንወስድ ካሊጉላ ሮም ከተማን እናቃጥላትና እስኪ ምን እንደምትመስል እንመልከታት ይል እንደነበርናአቃጥሏትም ያለቅስ እንደነበረ ይነገራል ። ካሊጉላ በዚህ ብቻም ሳይወሰን ፈረሱን ለሴኔቱ ምክር ቤት ለማስመረጥም በቅቷል ። ኔሮም እንዲሁ በርካታ ሮማውያንን የገደለ ሲሆን በእርሱም እንደ አንዳንድ የታሪክ ፀሀፊዎች አባባል አእምሮው አብዶ ነበረ እስከማለት ደርሰዋል ። ይህም በጥንት ዘመን የነበረውን እጅግ የላላ ወይንም ጨርሶ ያልነበረን የተጠያቂነት ስሜት ጨርሶ አለመኖርን የሚያሳይ እና ነገስታት የሚመሩትን ህዝብ እንደፈለጋቸው ይጨፈጭፉ እንደነበረ የሚያሳይ ሲሆን ባስ ካለም የተጠያቂነትና የሀላፊነት ስሜት የማይሰማቸው ነገስታትም የሚያደርሱት ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ነው ። 


እንደዛ እንደዛ እያልን ቀረብ ካሉትም ብንወስድ በታሪክ የተፈፀሙ ዘግናኝ የዘር ማጥፋቶች ፣ ጭፍጨፋዎች የመሳሰሉት የተጠያቂነት ስሜት ከመጥፋትና ካለመኖር (Impunity) እና ከእብሪተኝነት ስሜት የመጡ ናቸው ፤ ለምሳሌ ናዚዎች በአይሁዳውያን ላይ ያደረሱት ፍጅት ከዚሁ ተጠያቂነት ካለመኖር ስሜት የመነጨ ነው ፣ ከዛ ወዲህም በአለም ላይ የተከሰቱ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋዎች ከዚሁ ስሜት የተፈፀሙ ናቸው ። አሁን ባለንበት ዘመን ግን ከቀድሞው ዘመናት በአንፃራዊነት የተሻለ ተጠያቂነት የሰፈነበት ዘመን ሲሆን ። አሁን ያለንበት ዘመን ግን መሪዎች በከፍተኛ ደረጃ ተጠያቂነት ሀላፊነት የሚጠየቁበት ዘመን ነው ። የኩባንያ መሪዎችን ብንወስድ የምእራቡ አለም ግዙፍ ኩባንያ ስራ አስኪያጆች ግዙፍ ቦነስ ለራሳቸው እንደሚወስዱ ይታወቃል ። ነገር ግን በቅርቡ ግን የባለአክስዮኖች አመፅና ተቃውሞን (Share Holder Revolt) በማድረግ የኩባንያ መሪዎች የሚወስዱት ቦነስ እንዲቀነስ ማድረግ ችለዋል ። በአሁኑ ወቅት የኩባንያ ሀላፊዎች ጭምር የሚመሩትን ኩባንያ ወደ አላግባብ ወደ ሆነ ችግር ውስጥ ሲከቱና ፣ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ሲንቀሳቀሱ በኮንግሬስና በፓርላማ ጭምር ሀላፊዎቹ ተጠርተው እስከመጠየቅ ደርሰዋል ።

በአሁኑ ወቅት በምእራቡ አለም የግዙፍ ኩባንያ መሪዎች ኩባንያቸውን ችግር ውስጥ በሚጨምሩበት ወቅት ወይም ፣ የማጭበርበር ድርጊቶች በሚፈፀሙበት ወቅት ስራ አስኪያጆቹ ወደ ፓርላማና ኮንግሬስ ተጠርተው እንዲጠየቁ ሲደረግ ፣ ከባድ የቅጣት ከገንዘብ እንዲከፍሉና ባስ ካለም ሀላፊነታቸውን እንዲያጡ ፣ በፍርድ ቤት ጭምር ተጠያቂ እንዲደረጉ መደረግ ተጀምሯል ። ለዚህም ምክንያቱ የአንድ ኩባንያ ኪሳራ ምን ያህል ለአለም የሚተርፍ የምጣኔ - ሀብት ቀውስን እንደሚያስከትል ካለፉት ልምዶች በመረዳት ሲሆን ለምሳሌ በ2008 ለአለም የገንዘብ ቀውስ መንስኤ የሆነው ሊማን ብራዘርስ (Lehman Brothers) የተሰኘው የአሜሪካ አራተኛው ግዙፍ ባንክ ጨርሶ መክሰር ሲሆን ፣ የሱን መውደቅ ተከትሎም ከ1930ዎቹ ወዲህ ለመጀመረያ ጊዜ ለአለም ከባድ የምጣኔ - ሀብት ቀውስን ያስከተለው የ2008 የገንዘብ ቀውስ ተከትሎ ለአመታት የምእራብ ሀገራትን ችግር ላይ ጥሎ ቆይቷል ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ተጠያቂነት የሌለበት የኮርፖሬሽን አመራር (Corporate Governance) የሚፈጥረውን ኪሳራ በማወቅ ነው ። በአብዛኛው የኩባንያዎቹ ቦርዶች ውስጣዊ የአመራር ችግሮችን በመሸፋፈን ስለሚያልፉ በዛም ላይ አምነት ካለመኖሩ ልክ የፖለቲካ መሪዎች በቀጥታ ለህዝብ ተጠያቂ እንደሆኑት ሁሉ ፤ በርካታ የአገርን ሀብት የሚያንቀሳቅሱትና ለብዙ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥሩና ብሎም የሀገር ምጣኔ - ሀብት የተመሰረባቸው ኩባንያዎችን ከውድቀት ለማዳንና ግልፅነት የሰፈነባቸው ለማድረግ የተሻለ አማራጭ ሆኖ ተገኝቷል ። 


በአገር ደረጃ በከፍተኛ የአመራር እርከን የሚቀመጡ መሪዎች ብዙውን ግዜ የህግ ከለላን (Immunity) የሚኖራቸው ሲሆን ይህ ከለላ ግን ሰውየውን ወይንም ግለሰቡን ለመከላከል ሳይሆን መሪው ተግባሩን ያለስጋት በሙሉ የራስ መተማመን መንፈስ እንዲወጣና ስራውን በመስራቱ ወይንም ሀላፊነቱን በመወጣቱ በግል ይመጣብኛል የሚል ስጋት ሳያድርበት ስራውን እንዲሰራ ለማስቻል ነው እንጂ አለአግባብ አንድ ነገርን እንዲያደርግ ወይምን ጥፋትና ወንጀልን እንዲሰራና ከህግ በላይ እንዲሆን ለማበረታትና መሪው እንደ ግለሰብ ራሱን ከህግ በላይ አድርጎ እንዲቆጥር አይደለም ። በእርግጥ በሀገራችን ሰማይ አይታረስ ንጉስ አይከሰስ የሚል ይትበሀል አለ ፣ ነገር ግን ይህ በአሁኑ ተጠያቂነት በስፋት እየሰፈነ ባለበት አለም ውስጥ የሚሰራ አይደለም ።

No comments:

Post a Comment