ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር፤ የጸረ-ሽብር ሕጓን መልሳ ሥራ ላይ በማዋል እና የኢንተርኔት ግልጋሎትን በማቋረጥ ወደ ቀደመው የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት አፈና የመመለስ አደጋ እንደተጋረጠባት የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ፣ (CpJ ) አስጠነቀቀ።
በአሁኑ ወቅት በትንሹ ሦስት ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ (CPJ) አስታውቋል። ሌሎች ሦስት ጋዜጠኞች ታስረው ቢፈቱም አሁንም የፍርድ ቤት ሙግት እንደሚጠብቃቸው ከሰሐራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሃገራት የድርጅቱ ተወካይ ሞቶኪ ሙሞ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
ሞቶኪ ሙሞ እንደሚሉት ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ሥራቸውን በአግባቡ ለመከወን ፈተና በዝቶባቸዋል።
ሞቶኪ ሙሞ «ባለፈው ሰኔ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን እጅግ ጎድቷል።
ጋዜጠኞች ሥራቸውን ለመሥራት፣ ከመረጃ ምንጮቻቸው ለመገናኘት፣ መረጃዎቻቸውን ለማጣራት ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት ለማተም ፈተና ሆኗል። በግንቦት እና በሰኔ ወራት የታሰሩ ጋዜጠኞች አሉ።
ቢያንስ አንድ ጋዜጠኛ እና ባልደረባው በሥራቸው ሳቢያ ክስ ተመስርቶባቸዋል። በቅርቡ ከዚህ ቀደም ለመገናኛ ብዙኃን ብዙ ችግር ሲፈጥር በቆየው የጸረ-ሽብር ሕግ ጋዜጠኞች መታሠራቸውንም ደርሰንበታል።» ብለዋል ።
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ባለፈው አንድ ዓመት የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት መሻሻል ቢያሳይም የመንግሥቱ የቀደሙ ልምዶች የማገርሸት ምልክት ማሳየታቸውን ተናግረዋል።
የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በጀመራቸው ማሻሻያዎች ለውጥ ይደረግበታል የተባለው የጸረ-ሽብር ሕግ መልሶ ጋዜጠኞችን ለማሰር ግልጋሎት ላይ መዋሉ አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመዋል። ሞቶኪ ሙሞ «አዎንታዊ መሻሻል ወደታየበት፣ መንግሥት ጋዜጠኞችን ወደማያስርበት እና ኢትዮጵያ የመገናኝ ብዙኃን ነፃነት የተከበረባት አገር ትሆን ዘንድ ሊያረጋግጥ ወደሚችለው የማሻሻያ እርምጃ እንመለስ ማለት እንፈልጋለን።
በእርግጥ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት መፃኢ እጣ-ፈንታ አሳስቦናል፤ የዛኑ ያህል የታዩ ለውጦችንም እንረዳለን። የምናነሳቸው አሳሳቢ ጉዳዮች ምላሽ አግኝተው ኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት የተከበረባት አገር ትሆናለች ብለን ተስፋ እናደርጋለን።» ሲሉ በአጽንዖት ተናግረዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ Amnesty International ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መንግሥት እርምጃ አገሪቱ ባለፈው አንድ ዓመት ገደማ ያሳየችውን መሻሻል ሊቀለብስ እንደሚችል በትናንትናው ዕለት አስጠንቅቆ ነበር። ወደ ኅንላ እንዳንመለስ ጎበዝ።
No comments:
Post a Comment