ባለዋሽንቱ ዮሃንስ አፈወርቅ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ተዋናይ ወጋየሁ ንጋቱ ለተረከው የደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር ልብወለድ በተጫወቱት የማጀቢያ ሙዚቃ ተለይተው ይታወቃሉ። ቀብራቸውን በአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ለማስፈጸም ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ የሙዚቃ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት ይፍሩ ለDW ተናግረዋል። አቶ ዮሃንስ በስተመጨረሻ ሕይወታቸው "በጣም ተጎድተው፤ መነጋገርም ሆነ መንቀሳቀስ አቅቷቸው" እንደነበር አቶ ዳዊት ተናግረዋል።
የሙዚቃ ባለሙያው ከአንድ አመት ገደማ በፊት በሰጡት ቃለ-መጠይቅ "ኢትዮጵያን በተለያዩ የዓለም አገሮች ዞሬ ባህሏን አስተዋውቂያለሁ። ዛሬ እኔ ምንም ነገር የሌለኝ ሰው ነኝ። የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ኢትዮጵያ ለእኔ አንድ ቤት ቢሰጡ ይጎዳሉን?" ሲሉ ያሉበትን ኹኔታ አስረድተው ነበር። በቅርበት የሚያውቋቸው በተደጋጋሚም ያገኟቸው የአቶ ዮሃንስ ኑሮ ሳይሻሻል መቆየቱን ያስታውሳሉ።
አቶ ተስፋዬ ለማ ለኅትመት ባበቁት የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ የተሰኘ መጽሐፍ "ትሁት፣ ሙያውን አፍቃሪ እና ተግባቢ" ሲሉ አድንቀዋቸዋል። አቶ ተስፋዬ "የኢትዮጵያ የባህል የሙዚቃ ቡድን በተዘዋወረባቸው ሀገሮች ሁሉ በሙያው ታላቅ አገልግሎት የሰጠ ግሩም ሙዚቀኛ" ሲሉ ስለ አቶ ዮሃንስ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
በቀድሞው ጎጃም ክፍለ ሀገር ፍግታ በተባለ ቦታ የተወለዱት ዮሃንስ አፈወርቅ 72 አመታቸው ነበር። በትውልድ ቀያቸው ሸንበቆ ተብሎ የሚጠራውን የሙዚቃ መሳሪያ መጫወት የጀመሩት በእረኝነት ቤተሰቦቻቸውን ሲያገለግሉ
በ1955 ዓ.ም. ከትውልድ ወያቸው ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት ዮሃንስ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሚገኙ ጠጅ ቤቶች እየተዘዋወሩ ሙዚቃ ይጫወቱ፤ ያቅራሩ እና ይፎክሩ ይናገሩ ነበር። በሙያቸው በቀድሞው ፖሊስ ኦርኬስትራ ለሁለት አመታት ሰርተዋል። የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ እና የሕዝብ ለሕዝብ አባልም ነበሩ።
ጥላሁን ገሠሠ፤ ታምራት ሞላ፤ ተፈራ ካሳ፤ ታደሰ አለሙ፤ ለማ ገብረሕይወት እና ሒሩት በቀለን ከመሳሰሉ ሥመ-ጥር ድምፃውያን ጋር ሰርተዋል። ከቀድሞው ትኩል ባንድ እና ሙላቱ አስታጥቄ ጋር ተጫውተዋል።
ጡረታ ከወጡ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ካዛንችስ መናኸሪያ አካባቢ በሚገኘው ፈንድቃ የባሕል ቤት ኢትዮ ከለር ከተባለ የሙዚቃ ባንድ ጋር ይጫወቱ ነበር። አሜሪካ፣ ጣልያን እና ፈረንሳይን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም አገሮች እየተዘዋወሩ ሙዚቃ ተጫውተዋል።👉🏾 @dwamharicbot
No comments:
Post a Comment