ፀሃፊው ስሜነህ ተረፈ
ኢ-ሜይል smofed@hotmail.com
or
smofed@gmail.com
የመብት ተሟጋችነት (አክቲቪዝም) ማለት ለአንድ የለውጥ አላማ መረጃ
መስጠት፤ማንቃት ፤ማስተማር ህዝብን ማደራጀትና ማብቃት ማለት ሲሆን የመብት ተቆርቋዎች (Activist) ሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ
ናቸው እንጂ ወደ አመፅና ብጥብጥ አያመሩም ፣ የመብት መረገጥ ካለ አክቲቪዝም (Activism) ከተቃውሞ (resistance) ወይም
ህዝባዊ እምቢ ባይነት (civil disobedience) ብሎም ወደ አስተዳደራዊ ፖለቲካ (administrative
politics) እየዳበረ መሄድ አለበት ፡፡ከቀድሞዎቹ ትውልዶች በተለየ ሁኔታ የአሁኑ ትውልድ ምንም አይነት ጥይት ሳይተኩሱ አምባገነኖችን
መታገል ብቻ ሳይሆን መጣልም እንደሚችል ይህ ለውጥ አመላካች ነው ፡፡ የሙዳየ ሃሳብ ተቋማት (think thank) ማለት ከዩንቨርስቲዎች
የሚመነጭን ንድፈ ሃሳባዊ የሆነ እውቀትን ልክ አጣፍጠው ቀለል ባለ መልኩ የተግባር ሰዎች ለሆኑት ለፖለቲካና ቢዝነስ መሪዎች የሚያቀርቡ
መለስተኛ የጥናት ተቋማት ናቸው ፤እንደ ጃዋር መሃመድ ያሉት ዋነኛ አክቲቪስት የነበሩት በውጭ የቆዩት የሃሳብ ማጥኛ ተቋማትን ለመክፈት
ሃሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል ጃዋር መሃመድ በሙዳየ ሃሳብ ተቋማት የሚፈልቅን ሃሳብ ለአስፈጻሚው አካል የሚቀርብን ሃሳብ ‹‹አጤሪራ
እንደማጉረስ ነው›› ሲል ይገልጸዋል ፡፡ አክቲቪዝም ወደ ሀሳብን ወደ ማበልፀግና ወደ ምርምር ተቋምነትና የፖለቲካ
ሰዎች የሚመሩባቸውን አስተሳሰቦችን ወደማዳበር ደረጃ ማደግ አለበት እንጂ ወደ አመጸኝነትና ረብሻ ስርአት አልበኝነት (አናርኪ)
ደረጃ መዝቀጥ የለበትም፡፡
በሶማሌ ክልል ‹‹ስልጣንህን ልቀቅ ተብያለሁ፣ስልጣኔን ከምለቅ ብሞት ይሻለኛል›› በሚል
ጸረ-ዲሞክራሲዊ ስሜት አብዲ ኢሌ ወይም አብዲ መሃመድ ኡመር የተባሉት የክልሉ ፕሬዝዳንት የነበሩ ግለሰብ ያሰለጠኗቸው ሄጎ ሲባሉ
ከቄሮ በተቃራኒ ሄጎዎች ለውጥን ለማደናቀፍ በሶማሌ ክልል የተደራጁ ሲሆን ‹‹ሄጎ››
የሚባሉት እነኒህ የወጣት ቡድኖች የሶማሊያን ሪፐብሊክን ሰንደቅ አላማ በመያዝ ‹‹አብዲ ኢሌ ለዘላለም ይኑር››
እያሉ መፈክርን እያሰሙ በሶማሌ ክልል ከተሞች በመዞር በከተሞች ውድመትና የሰው ህይወትን ማጥፋት ፈፅመዋል ፡፡ እንዲሁም በሻሸመኔ
ጃዋር መሃመድን ለመቀበል በወጣው ሰልፍ ላይ 3 ሰዎች ሲሞቱ ወደ 71 ሰዎች ቆስለዋል ፤ ወደ መቀሌ ሊሻገር የነበረን እህል ከመኪና
አውርዶ ለህዝብ ማከፋፈል ከወደ አማራ ክልል የተሰማ ሲሆን እንዲሁም በጎንደር ፣በባሌ፣በጣና በለስ፤በከፋ ሸካ ዞን -በቴፒ፣ በዶምቢዶሎ፣በደብረማርቆስ
ወዘተ… የታየው ብጥብጥና ረብሻ ግን ከመስመር ያለፈ ነው ፤ በሱማሌ ክልል የጅቡቲ ዜጎች ላይ የደረሰው ጥቃት እንዲሁም በጅቡቲ
ባሉ ኢትዮጲያውያን ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት አግባብነቱን የሳተና አክቲቪዝም ምን ላይ ነው መቆም ያለበት የሚለውን የሚሳስብ
ነው ፡፡አንዳንዶች ይህ የምናየው የደቦ ፍርድ ‹‹በለውጥና ሽግግር ወቅት የሚያጋጥም ነገር ነው››
ሲሉ ሊያቃልሉት ይሞክራሉ ነገር ግን ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ አበው እንደ ቀይ ሽብር
ዘመን ‹‹አስታጥቁን፣አታስጨርሱን›› ደረጃ ላይ ባይደርስም ‹‹ይቺ ባቄላ ካደረች
አትቆረጠምም›› ብሎ በሱማሌ ክልል ከተፈጸመው ትምህርት በመውሰድ መፍትሄ መፈለግ ግን ያባት ነው ፡፡የኢትዮጲያ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክንም ሃይ ባይ ያጡትን አንድ በሉልኝ ስትል ‹‹የመንግስት ትእግስት በዛ››
ስትል አሳስባለች፡፡
ይህ በሃገሪቱ በአሁኑ ወቅት ተጠያቂነት አለመኖርን እንዲሁም መንግስት
የላላ የፀጥታ አጠባበቅንና አንዳንዶች እንዲሁ መንግስት ጠንከር ካላለ ከዚህ የባሰ ይመጣል ብለው የሚሰጉ ወገኖች አሉ ‹‹ለቄሮ እናገራለሁ … ቄሮ ይቀጣችኋል››
የሚሉ አባባሎች ወጣቶች ያለ ተጠያቂነት የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ የሚል ሃላፊነት የጎደለው የተሳሳተ ስሜትን ፈጥሯል ፤ ይህም
ወደ ሃገራችን ይመጣሉ የሚባሉትን የዋጋ ቅናሽ ተደርጎላቸው ወደ ሃገራቸው የዘመን መለወጫን እንዲያከብሩ የተጠሩትን ዲያስፖራና ቱሪስቶችን
ቁጥር እንዲቀንስ የሚደርግ ነው ሲሉ ስጋታቸውን የባህልና ቱሪዝም ተቋማት አመራሮች እየገለፁ ናቸው ፡፡ዋነኛ አክቲቪስት የሆነው
ጃዋር መሃመድ በበኩሉ ይህን በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን ወጣቱ በራሱ ስልጣን እየወሰደ ያለውን እርምጃ ማውገዝና ከህግና ከስርአት
መውጣት እንደሌለበት በይፋ መናገር ይጠበቅበታል፡፡ጆርጅ በርናርድ ሾው እንተናገረው ‹‹ነጻነት ማለት ሃላፊነት
ማለት ነው›› ነጻነት ዋጋ ተከፍሎበት እንደተገኘው ሁሉ ያለተጠያቂነት ዝም ብሎ የህግ የበላይነትን ቸል በማለት
የሚከበር አይደለም፡፡
በመልካም ጎኑ ስናየው አክቲቪዝም ለምሳሌ የባህር ዳር ወጣቶች ከመንግስት
ጋር በተደረገው ግጭት ከተጎዱ ቤተሰቦች ከ17 በላይ ከሚሆኑ ባለሃብቶች ከ2 ሚሊየን ብር በላይ በማሰባሰብ መስጠታቸው በዜና ማሰራጫዎች
ተነግሯል ፡፡ ይህ አክቲቪዝም መልካም ጎኑ ሲሆን ከዚህ ባለፈ ግን ወደ ግጭትና ረብሻ በሃገራችን በተለያዩ ክልሎች የምናያቸው ከመስመሩ
የወጡና በተለይም ወጣቱ ራሱን ጆሮውን ለዚህ መስጠት የለበትም ፣ተከታይ ያፈራ አክቲቪስት በሃላፊነት ስሜት መረጃን የሚያስተላልፍ
ካልሆነ አደጋን ያመጣል፡፡የዶ/ር አቢይ መንግስት በግልፅነት በሃገሪቱ የተፈጸሙትን ለምሳሌ የኢንጂነር ስመኝን ግድያ ፣ የሰኔ
16ቱን ቦንብ ውርወራ የመሳሰሉትን ለህዝብ ይፋ ማድረግና ማሳወቅ ይጠበቅበታል ፡፡ ፖለቲካ ላለማበላሸት በሚል፣የውስጥ ድርድርን
በማድረግ የዚህን የመሳሰሉት ጉዳዮች ሲደበቁና ሲሸፋፈኑ በህዝብ ዘንድ ጥርጣሬን ፣ በወጣቱ ዘንድ ደግሞ በራሱ ህግን ለማስከበር
ሲል የመሰለውን ሊያደርግ ይችላል፡፡ ከዚህም ሌላ የሶሻል ሚዲያ አጠቃቀማችንን መፈተሸና የአክቲቪዝምን ገደብና ድንበርን መለየት
ያስፈልጋል ፤ ህብረተሰቡ የመጣለትን ለውጥ ለማረጋገጥ የየራሱን ድርሻ መወጣት አለበት፡፡በኢንተርኔት የተጻፈን ነገር ሁሉ እውነት
ነው ብሎ መውሰድ ለጥፋት ሊዳርግ እንደሚችል ከሰሞኑ ያየናቸው ግርግሮች ምስክሮች ናቸው ፡፡ በምእራብ አገራትም ጭምር የጥላቻ ንግግሮች
(hate speech) ክልክል ናቸው ፣ እንዲሁም የሚታወቁ እውነታዎችን መካድ፣አልተደረጉም ብሎ መከራከር ለምሳሌ በሁለተኛው የዓለም
ጦርነት ወቅት አይሁዶችን ናዚዎች አልጨፈጨፏቸውም ብሎ የሆሎኮስትን (genocide) መካድ በራሱ በአውሮፓ አገራት ህግ በወንጀል
ያስጠይቃል፣በሃገረ አሜሪካም ጥቁሮችን ወይም ሌላ ዘርን የሚያዋርድ ነገርን መናገር ወይም መጻፍ ያስጠይቃል ፡፡
ለዘመናት በጣም የታፈነ ጩኀት የነበረበት ሃገር እንደመሆኑ ፣ቀድሞ
መጮህ ቢፈለግም መጮህ የማይቻልበት ዘመን ነበር አሁን ግን ህዝቡ ባደባባይ ስሜቱን መግለፅ ይችላል፡፡ባገሩ ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ የኖረ
በመሆኑ ምክንያት አሁን መተንፈሻ ያገኘው ህዝብ በተለይም ወጣቱ በገነፈለ ሁኔታ ስሜቱን እየገለፀ እንዳለ መረዳት ይቻላል፡፡ በሃገራችን
ለውጥን በሰላማዊ መንገድ የመምራት ልምዱ የለንም ማለት ይቻላል፤ከዚህ ቀድሞ የደርግ መንግስት ከሃይለስላሴ ስልጣኑን ሲረከብ እርስ
በእርስ ፍጅት የተካሄደ ሲሆን ኢህአዴግም ደርግን ሲተካ እንዲሁ ስልጣኑን እስከሚያጸና ድረስ ሃይልን ተጠቅሟል ፤ የአሁኑን ለየት
የሚያደርገው ግን ጠ/ሚር ዶ/ር አቢይ ለስላሳ አቋምን በማሳየታቸው ምክንያት ስርአት አልበኝነቱ ሊንሰራፋ በቅቷል ፡፡የህግ የበላይነት
ቀርቶ ሁሉም የፈለገውን አድርጎ ምህረት ይደረግልኛል የሚል ስሜት መኖር የለበትም ፡፡ ድምጻቸውን አጥፍተው የቆዩት ጠ/ሚሩ የመከላከያ
ኮሌጅ ተመራቂዎችን ነሃሴ 12 ፣ 2010 ዓ.ም. ሲያስመርቅ እንደተናገሩት ‹‹የይቅርታው ዓላማ ባለፍንበት መንገድ
ያጣነውን ለማግኘት ነው እንጂ የገነባነውን አገር ለማፍረስ አይደለም… ዘመናዊነት የህግ የበላይነትን ማክበር ነው››
ብለዋል፡፡
እነኚህ ረብሻዎች የሚያመለክቱን ሌላው ነገር ለውጡ መፍጠን እንዳለበት አመላካች ነው ፣ ለውጥ አደናቃፊዎች በዚህ ረብሻ የሚጠረጠሩትን
ያህል ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝቡ የሚጠብቀው ፈጠን ያለ ለውጥና መንግስት እየሄደ ያለበት የለውጥ ጉዞ ሂደት ያላረካቸው ወገኖች
ትእግስት በማጣት ወደ ግርግር ሊያመሩ እንደሚችሉ መገመት ያሻል በተለይም ወጣት ስራ አጥነት በተንሰራፋበትና የንግድ መቀዛቀዝ እየተስተዋለ
ባለበት ሁኔታ ፤ ፈጠን ያሉ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጦች፣ አጠቃላይ የፍትህ ስርአቱን ማሻሻል፣ ተዛማጅ ህጎችንና አዋጆችን መፈተሽ ፣ተደጋጋሚ
ቅሬታ ሲቀርብባቸው የነበሩ አዋጆች መሻሻልና መተግበር አለባቸው ፣እንዲሁም ሹመት አሰጣጥ ላይ በቀደመው ዘመን በሙስናና በአቅም ማነስ ሲተቹ የነበሩትን ጠ/ሚሩ ስፍራ
ሲያገኙላቸው ይታያል፤የአምባሳደርነት ሹመት አቅመ ቢስ ለሆኑ ባለስልጣናት
ማገገሚያ መሆኑ ቅሬታን የፈጠረ ሲሆን በፓርላማ ደረጃም ተነስቶ ነበረ፤ ‹‹አዲስ ወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ›› እንዳይሆን የህዝብን
የለውጥ ጥያቄን ሊያረካ በሚችል መንገድ አቅም ያላቸውን አዳዲስ አመራሮችን መሾም የሚበጅ ነው፣ በደቡብ ክልል በሸካና ከፋ ዞን
የታየው ከለውጡም በኋላ አመራሩ ራሱን አለማስተካከሉ ችግሩን አባብሷል፡፡
የፌደራል
መንግስቱ ምን ሲፈጠር ነው ጣልቃ የሚገባው ?
ምንም እንኳ የአንድ ክልል አስተዳደር ራሱን የሚያስተዳድር (ኦቶኖሚ)
ቢሆንም ፣ በክልሉ ያለው የዳኝነት ነጻነት መከበር አለበት፤ የክልሉ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤም ይህን የሚያሟላ መሆን አለበት ፡፡
ነገር ግን የዳኝነት ስርአቱና ፖሊስ ህግና ስርአትን በክልሉ ማስከበር በማይችልበት ደረጃ በሚደርስበት ወቅት ፌደራል መንግስቱ ጣልቃ
ሊገባ ይችላል፤ የፌደራል መንግስቱ ለክልሎች የበጀት ድጋፍን የሚያደርግ እንደመሆኑና ከዚህም በተጨማሪ ያገር ሉአላዊነትንና ደህንነትን
የመጠበቅ ሃላፊነት ስላለበት በክልሎች የሚከናወን ህገ ወጥነትን በዝምታ ይመልከት አይባልም፡፡
በሱማሌ ክልል የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በተደጋጋሚ በህብረተሰቡ
ዘንድ ይነሳ የነበረ ቢሆንም ፤ የነዳጅ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት የተገኘበትና ለገበያ መቅረብ የጀመረበት ሲሆን ፣ክልሉ ላለፉት
27 አመታት ተገቢውን የልማት ስራ ያልተሰራበትና በሚገባው መጠን ያላደገ ሲሆን ፤ ሙስናም ተንሰራፍቶ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ሲደርስና
የክልሉ ባለስልጣናት ባጀቱን ሲዘርፉት እንዲሁም የክልሉ ህዝብ ተጠቃሚ ሳይሆን የቀረበት ዘመን ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ የክልሉ
ያገር ሽማግሌዎችም (ኡጋሶች) ጭምር እዚህ አዲስ አበባ በመገኘት ለጠ/ሚሩ ተደጋጋሚ ጥያቄውን ቢያቀርቡም ጥያቄያቸው ፈጣን ምላሽን ሊያገኝ አልቻለም፣በተደጋጋሚ ኢሳትን ጨምሮ በክልሉ ያለው የአብዲጊሌ አገዛዝ በክልሉ ኪራይ ብሳቢነትንና
ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣን ማድረጉን ሲገልፁ ቢቆይም ፣ እንዲሁም ሂዩማን ራይትስ ዎች በክልሉ ያለው የልዩ ሃይል እንዲበተን
ቢጎተጉቱም ሰሚ ሳያገኙ ቆይተዋል፤ በሶማሊያ ወረራ እንኩዋን ያልተፈፀመ በደልና ውድመት ደርሷል፤ በዚህም ምክንያት ቀላል የማይባል ዋጋን አስከፍሏል ፡፡
ይህ ሁሉ ጥፋት ከጠፋ በኋላ የሶህዴፓ አመራር ባደረገው ግምገማ መሰረት
‹‹የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች፤ በክልሉ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊና የዲሞክራያዊ መብቶችን ማፈን ፣ በህዝቦች
መሃል ግጭቶችን በመፍጠር፣ ህዝብን ማፈናቀል ፣ የሃሰት መረጃዎችን አመራሩ በማሰራጨት የህዝብ ግጭት እንዲፈጠርና አለመረጋጋት እንዲፈጠር
ማድረግ ፣ ሄጎ የተባሉ ወጣቶችን በማስታጠቅ በማስራጨትና በማስተማር በጅግጅጋ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ከተሞች እንዲሁም በህብረተሰቡና
በተለያዩ የማህበራዊ ተቋማት ላይ ጥፋቶችን መፈጸም፣ ፍፁም ህገ መንግስትን በጣሰ መልኩ ሰዎችን ማሳሰርና ማሰር ፣ የዲሞክራሲን
ማፈን ፣ ህዝቡን ማፈን ፣ ሁሉንም የመንግስት ተቋማትን ሽባ በማድረግ ፣ የጎሳ መሪዎችን በመንግስት መሾምና መሻር ፣ በሃሰት ማስረጃ
፣ መርህ አልባ ግንኙነትን በመፍጠር ፣የከፋ የኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሰራር ፣ የመንግስትን ሃብት ማባከን ፣ ለጎሳ ለዘመድ
ማከፋፈል ፣ ፕሮጀክቶችን ለወዳጅ መስጠት ፣ ንግድን በሞኖፖል መቆጣጠር ፣ ኮንትሮባንድ ንግድ ማካሄድ፣ የሴፍቲኔት ገንዘብን መከፋፈል፣
የአመራር መምከንንና ወደ ገዢ መደብነት መቀየር ፣ በግለሰብ አምባነናዊ አገዛዝ ስር መውደቅ ፣ የመንግስት ተቋማትን ወደ ግል ባለቤትነት
መቀየር ፣በመንግስት ገንዘብ ህገ ወጥ ድርጅቶችንና የማፍያ ኔትርኮችን ማደራጀት፣ የሃሰት ሪፖርት ማሰራጨት፣ በከፋ የስነ ምግባር
ችግር ፍፁም አድርባይትን በማንገስ ፣ ድብቅ የማፍያ ቡድኖች ተደራጅተውና ታጥቀው ፣ ስልጠናም ጭምር ወስዶ ነው ይህ የተደረገው››
ብለዋል፣ የክልሉን መንግስት ከላይ እስከታች እንደገና ማደራጀት ስራ እንደሚከናወን የገለፁት አቶ አህመድ ሽዴ፣ 3 ስራ አስፈጻሚና
5 ማእከላዊ ኮሚቴ አባላትን መታገዳቸውንና ፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ለፍርድ የማቅረቡ ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አክለዋል
፣ግምገማው ፍፁም ዲሞክራሲያዊና ግልፅ ነበረ ብለዋል፡፡ ጥያቄው ግን ይህ ሁሉ ሲሆን ፌደራል መንግስቱ በወቅቱ ለምን እርምጃ አልወሰደም
የሚል ነው ፡፡
ከዚህ ሁሉ በኋላ ጣልቃ የገባውን የፌደራል መንግስቱን የሶማሌ ክልልን
ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣኑን ደፍሯል የሚሉ አሉ - ነገር ግን የህግ ባለሙያዎች እንዳስታወቁት ከላይ የተጠቀሰው በሱማሌ ክልል
የተፈፀመው ግዙፍ የሰብአዊ መብት ጥሰት ‹‹ግሮስ
ሁውማን ራይት ቫዮሌሽን›› ነው በዚህ ሁኔታ ፌደራል መንግስቱ እጁን አጣጥፎ መቀመጥ እንደሌለበት የታወቀ
ነው ፡፡ በክልሉ የተነሳው ረብሻ በክልሉ በሚኖሩ ዜጎች ቤትና ንብረት ላይ ዘረፋ ሲፈፀም ፤ በዚህ ብቻ ሳይወሰን በአብዲ ኢሌ የተመራው
የክልሉ መንግስት እገነጥላለሁ በማለቱ ምክንያት የመከላከያ ሰራዊቱ ሊገባ ችሏል ተከትሎም ከሌላ ክልል የመጡ ብቻ ሳይሆን ጅቡቲዎችና
ሱማሌዎች ጭምር የክልሉን ከተሞች በመልቀቅ ወደ ስደት ገብተዋል ፡፡
የክልሉን ፀጥታና ደህንነትን እንዲያስክብር ሃላፊነት የተጣለበት ራሱ
የክልሉ ፖሊስና ልዩ ሃይል ጸጥታን ከማስከበር ይልቅ ራሱ ዝርፍያና ውድመት ውስጥ በመግባቱ የፌደራሉ ሃይል ጣልቃ ገብነት አስፈልጓል፡፡
በመጀመሪያ የፌደራል መንግስቱ ወደ አንድ ክልል ጣልቃ ሊገባ የሚችለው
ምን ሲሆን ነው? የሚለውን መመልከት ያሻል፤ ሌላው ደግሞ ጣልቃ መግባት ማለት ምን
ማለት ነው? የሚለው ሲታይ ወታደራዊ በሆነ መንገድ ነው ወይንስ ኢኮኖሚዊ ወይስ
ሌላ ከሆነ በምን መንገድ ነው ጣልቃ መግባት ያለበት? የሚለው አነጋጋሪ ሊሆን ይችላል፤ ለምሳሌ በድሬዳዋ የተሰበሰቡ ተሰብሳቢዎች
አብዲ ኢሌ በጀቱ ሊያዝበት ይገባል ሲሉ ባወጡት የአቋም መግለጫ ላይ አውጥተዋል፤በርካታ በክልሉ ነዋሪ የሆኑ ዜጎችም ከዚህ በኋላ
በክልሉ ለመኖርና ለመስራት ምን ዋስትና አለን ሲሉ ጠይቀዋል ፡፡
ህገ መንግስቱ ምን ይላል ብለን ስንጠይቅ አንቀፅ 15 መሰረት ማንኛውም
ሰው በህይወት የመኖር መብት አለው ፤ እንዲሁም ‹‹በህግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ህይወቱን
አያጣም›› ይላል ስለዚህ አንድን ሰው ፀጉረ ልውጥ ነው በሚል ብቻ መግደል ወይም መደብደብ ህገ መንግስታዊ መብቱን
መጻረር ነው ፡፡ እንዲሁም በአንቀፅ 28/1 መሰረት ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ መውሰድ ይቅርታም ሆነ ምህረትን የማያሰጥ ሲሆን፣
ክሱም በይርጋ የማይታገድ መሆኑን ፤ የሞት ቅጣት ቢፈረድበት እንኳን አጥፊው ርእሰ ብሄሩ ወደ እድሜ ልክ ብቻ ዝቅ ከማድረግ ውጪ
ይቅርታም ሆነ ምህረትን ማድረግ እንደማይችልም በ28/2 ተደንግጓል፡፡
በህገ መንግስቱ ስለ አስፈጻሚው አካል በሚደነግግበት አንቀፅ 51 ንኡስ
አንቀጽ 14 መሰረት ‹‹ከክልል አቅም በላይ የፀጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሰረት የመከላከያ
ሃይሉን ያሰማራል›› ይላል በህገ መንግስቱ መሰረት ፌደራል መንግስቱ
ወደ አንድ ክልል ጣልቃ ገብ ሆኖ ሊገባ የሚችለው አንድም ክልሉ ራሱ ሲጠይቅ ወይንም ደግሞ በአንቀፅ 62 / 9 መሰረት ‹‹ማንኛውም
ክልል ህገ መንግስቱን በመጣስ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌደራሉ መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ያዛል››
ይላል፤ ጣልቃ መግባት ማለት ምን ማለት ነው ፣በምንስ መንገድ ነው ጣልቃ ገብነቱ የሚለውን ህገ መንግስቱ አያብራራውም፡፡ ከዚህም
በተጨማሪ ስለ ፌዴሬሽ ምክር ቤት ስልጣን ሲዘረዝር አንቀፅ 62 ንኡስ አንቀጽ 6 መሰረት ፣‹‹በክልሎች መካከል
ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሄ ይፈልጋል›› ይላል፡፡
በህገ-መንግስቱ በአንቀፅ 77/ 9 መሰረት የሚኒስትሮች ም/ቤት ‹‹ህግና
ስርአት መከበሩን ያረጋግጣል›› አስፈጻሚው አካል ይህ ሃላፊነት ተጥሎበታል፡፡‹‹ህግና ስርአትን
የማያከብር የመንጋ ፖለቲካ ኢትዮጲያ ውስጥ መቆም ይርበታል…በመንጋ በሚሰጥ ፍርድ የፍትህ ስርአቱን በግል ስሜት መንዳት የለብንም…
ህግ አልባና አመፅ የሚታገስ ስርአት እንደ አገር መቆጠራችንን ከንቱ ስለሚያደርግ አገራዊ አንድነታችንን በህግ አግባብ ማስጠበቅ
የዘወትር ተልእኳችን ይሆናል…የህግ የበላይነት ህዝቦችን በጋራ የሚያስተሳስር መሰረት መሆኑን፣…መንግስት የህግ የበላይነትን ለመጣስ
እየታዩ ያሉትን አዝማሚያዎችን እንደማይታገስ›› ተናግረዋል ፡ በሱማሌ ክልል የተነሳውን አይነት ሁከት በጋምቤላ ክልል ሊደገም እንደነበረና መከላከያ ሰራዊቱ
እንዳከሸፈው ጠ/ሚር ዶ/ር አቢይ አህመድ የመከላከያ መኮንኖችን ሲመርቁ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በተከሰተው ግጭት የፌደራል መንግስቱ በፍጥነት ያልገባና የማረጋጋትንና
ዜጎችን የመጠበቅ ስራንና እርዳታን በቶሎ የማድረስ በቶሎ ያልሰራ ሲሆን እንደ ቀብሪደሃር ባሉ ከተሞች ዜጎች ለከፋ አደጋ ሲጋለጡ
ምግብና ውሃ በማጣት ለቀናት ማንም ሊደርስላቸው አለመቻሉ መንግስትን አስተችቷል ‹‹ሄሊኮፕተር የለም እንዴ›› ብለው አንዳንድ ዜጎች ጠይቀዋል ፡፡ በተጨማሪ
በክልሉ የተነሳው ያልተጠበቀ ረብሻ በዶ/ር አብይ ለሚመራው የፌደራል መንግስት የመጀመሪያው ፈተና ሆኗል፡፡
No comments:
Post a Comment