Monday, May 20, 2013

የአየር ንብረት ለውጥና ምጣኔ-ሐብት



            የአየር ንብረት ለውጥ በምጣኔ-ሀብት እድገት ላይ የፈጠረው አሉታዊ አንድምታ በአሁኑ ዘመን በመታየት ላይ ነው ። ላለፉት በርካታ መቶዎች አመታት አውሮፓውያን የኢንዱስትሪ አብዮትን ካንቀሳቀሱ ወዲህ በአየር ንብረትና በአካባቢ ላይ የደረሰው ውድመት እጅግ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ሳይንቲስቶች እንዳረጋገጡት በአለም ላይ እየታየ ያለው የሙቀት መጨመር ላለፉት 4 ሚሊ ዮን አመታት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ነው ።

               የአየር ንብረት አስከፊ በሆነ ሁኔታ መለወጥ የፖለቲካ ጉዳይ ከመሆኑ አገራትን ሊያስማማ  አልቻለም ። ለምሳሌ ቻይናና አሜሪካ በዚሁ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ላይ በመሐከላቸው ሰፊ ልዩነት ያለ ሲሆን ፣ አሜሪካም በበኩሏ ከራሷ ይልቅ ሌሎች አገራት ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን የልቀት መጠን እንዲቀንሱ ትፈልጋለች ።  

              በአንፃሩ እንደ አፍሪካ ያሉት ደሐ አህጉራት ደግሞ በዚህ የአየር ንብረት ለውጥ በተለይም በከባቢ አየር ሙቀት መጨመር በእጅጉ ተጎጂዎች ናቸው ። በእርሻ ስራ ላይ ምጣኔ-ሀብታቸው የተመሰረተው ገና በማደግ ላይ ያሉት ሐገራት  የአየር ንብረት ሙቀት በሚጨምርበት ወቅት የግብርናው ምጣኔ-ሀብታቸው በእጅጉ እንደሚዳከም የታወቀ ነው ። ይሄውም የህዝብ ቁጥራቸው ሲጨምር ቁጥሩ እያደገ ላለው ህዝባቸው የምግብ ሰብል ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል ። 

            ይህ ሁሉ ሲሆን በአካባቢ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ከጉዳቱ ለማገገም ተፈጥሮ በቀላሉ አያገግምም የሚል የሳይንቲስቶች ግምት አለ ። የአንድ ዲግሪ ሴንትግሬድ የአለም ሙቀት መጨመርን ለመቀነስ አንድ ሺህ አመት ያስፈልጋል ። ይህ ብቻ ሳይሆን የሚጠፉና ተመልሰው የማይገኙ የእንሰሳና የእፅዋት ዝርያዎችም አሉ ።

               ያደጉት ሐገራት ለሚለቁት የካርቦን መጠን  ፣ የካርቦን ግብርን ለመክፈልም ሙሉ ፈቃደኝነትን ማሳየታቸውም አጠራጣሪ ነው ።

No comments:

Post a Comment