ፀሃፊው በስሜነህ ተረፈ
የፍትህ ስርአቱ ትኩረትን ይሻል
መልካም አስተዳር ለማስፈን ዋነኛ መሳሪያ ከሆኑት ተቋማት መሃከል
ፍርድ ቤቶች ዋነኞቹ ቢሆኑም ነገር ግን ህብረተሰቡ በሚጠበቅባቸው ደረጃ ላይ አለመሆናቸው የፍትህ አሰጣጡ ያለበትን ሁኔታ አሳሳቢ
ደረጃ ላይ አድርሶታል ፤ ፍርድ ቤቶች ተገቢውን ፍትህ ለመስጠት ዝግጁ አለመሆናቸው በአሁኑ ሰአት በፍርድ ቤቶች አካባቢ የሚታየው
የስነ ምግባር ውድቀት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ማንም ፍርድ ቤት የሚመላለስ ሰው በቀላሉ የሚያስተውለው ሆኗል ፡፡ በከተማችን
በሚገኙት ፍርድ ቤቶች አካባቢ የመዝገቦች መብዛት ፤ የቀጠሮ መርዘምና መደጋገም እንዲሁም የአቅም ማነስና በአጭሩ መቅጨት የሚቻሉ
ጉዳዮች አለአግባብ ማንዛዛትና በዜጎች ንብረት መበላሸትና ውድመት እንዲደርስ ማድረግ ፤ የውሳኔዎች ጥራት መጓደል ፤ በተራዘመ ቀጠሮ
ንብረቶች በማይገባው ተከራካሪ እጅ ለረጅም አመታት ያለ ውሳኔ መቆየት ፤ አርዝሞ በመቅጠር ማቆየት አንደኛው ወገን ማግኘት የማይገባውን
ጥቅም እንዲያገኝ ማድረግና ሌላውን ወገን ተጎጂ ማደርግ አድሎአዊ አሰራር፤ እንደዚሁም የስነ ስርአት ህጎቹ የሚያዙዋቸውን አንቀፆችን
አለመጠቀም እና ነገሩን ማሳጠር ሲቻል ነገር ግን ችላ ብሎ በማለፍ ጉዳዩን የሚጓትት አካሄድን መከተል የሚታዩ ጉልህ ጉድለቶች ይሆናሉ
በአሁኑ ወቅት አንድ ዳኛ በፈለገው ቀን እያስረዘመ ቀጠሮን
የሚሰጥ ሲሆን ነገር ግን ያለውሳኔ ለሚያጓትተው ጉዳይ ምንም ተጠያቂነት የለበትም ፡፡ ጠ / ፍ ቤቱ የጉዳዮች አስተዳደር መመርያ
ማለትም የመዝገቦች አቀጣጠር መመርያ ይወጣል ቢባልም ወጥቶ ስራ ላይ አልዋለም ፡፡ የፍርድ ቤት ውሳኔ መጓተት ከሃገር ኢኮኖሚ ላይ
ውድመትን እያስከተለ ሲሆን ፤ በስር ፍርድ ቤት አመራሮች ዘንድ የሚስተዋለው የስነ ምግባር ችግር በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የበላይ ሃላፊዎች ዘንድ ግንዛቤው ጨርሶ አለመኖር ፤ እንደዚሁም
ዳኞችን ከኋላ በስልክ ይታዘዛሉ የሚልም የባለጉዳዮች ጥርጣሬ ያለ ሲሆን በፍትህ ስርአቱ ላይ ከምንግዜውም የወረደ የህዝብ አመኔታ
መኖሩ ግን ወዴት እየሄድን ነው ያሰኛል ፡፡ ለዜጎች
ፍትህ ያሰፍናል ተብሎ የሚታመንበት ተቋም ዜጎች ፍትህን እንዳያገኙ ዋነኛ ባላጋራ ሆኖ መነሳቱ አሳሳቢ ነው ፡፡ በፍ / ቤቶች ለፍትህ
ቆመዋል የሚባሉ ተቋማት እንደመሆናቸው የሚታየው የተበላሸ አሰራር በብዙዎች የአስፈጻሚ መቤቶች እምብዛም የተለመደ አይደለም ፤ ይህም
በመንግስት ላይ የአመኔታ እንዲሸረሸርና ህብረተሰቡ የትም ሄጄ መብቴን በትክክለኛው መንገድ ማስከበር አልችም የሚለው አስተሳሰብ
በተለይም በወጣቱ ዘንድ ተስፋ መቁረጥን ሲፈጥር ወደ አመፅና ግርግር አገሪቷን ጨምሯል ፡፡
ከህዝብ ቅሬታዎችን የመቀበልና መፍትሄ የመስጠት ስልጣን በአዋጅ
የተሰጠው የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ቢሆንም ጉባኤው ከህዝብ ለሚቀርቡለት ጥያቄዎ በይፋ ምላሽን ሲሰጥ አይታይም ፤ የዳኝነት በደሎች
፤ አድልኦ የመሳሰሉት ባለጉዳዮች ሲያጋጥሟቸው ለጉባኤው ያቀርባሉ ቢባልም ጉባኤው በወር አንዴ ብቻ የሚሰበሰብ ሲሆን አባላቶቹም
በርካታ በሌላ መ / ቤቶች ውስጥ ስራ ያላቸው ስለሆነ ዋነኛው ስራቸው አይደለም፡፡ በሃገሪቱ በሞላ የሚቀርቡለትን ጉዳዮችን የሚመለከተው
ጉባኤው በወር አንዴ ብቻ መሰብሰቡ በቂ ነው ወይ ሊባል ይችላል ፡፡፡
በተለይም በፍርድ ቤት ንብረትን ማስለቀቅ በጣም ከባድ ከመሆኑም
በላይ ለኪራይ ሰብሳቢነት በርን የከፈተ ሲሆን የመንግስትን ትኩረት የሚሻበት ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ያለቀውን ጉዳይ አስከ ሰበር ችሎት
ድረስ ያስቀርባል በማለት በተደጋጋሚ አፈጻጸም በማገድ በተደጋጋሚ በማከራከር ጉዳዮችን በማርዘም በባለጉዳዮች ላይ ይሄ ሃገራችን
ነው ውይ ብለው እስከሚጠራጠሩ ድረስ ግፍ እየተፈፀመ ይገኛል ፡፡
የንግድ ቤቶች አከራዮች እዚህ ላይ ጠንቀቅ እንዲሉ ምክሬን እሰጣለሁ በአሁኑ ወቅት የንግድ ቤት ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ከገባ ቀላል
የአከራይ ተከራይ ጉዳይ ቢሆንም እንኳን አመታትን ሳይፈጁ በቀላሉ ቤቶቹ የማይለቀቁ ሲሆን የመዝገብ ቤት ፀሃፊዎች ጭምር መዝገቡንና
ባለጉዳዩን እንዲለዩት የሚደረግ ሲሆን ከፍተኛ ጉቦ የሚረጭበት ክርክር እንደሆነ በጠበቆች ጭምር በይፋ ይነገራል ፤ በመንግስት ደጋፊዎች
በሆኑ ዘንድ ሳይቀር የዚህ አይነት ክርክሮችን ለመርታት ደህና ገንዘብ እንደሚያስፈልግ በይፋ እየተነገረ ይገኛል ፡፡
በአንድ ወቅት አንድ የህግ ባለሙያ በጋዜጣ ላይ ከሰጡት መግለጫ
እንደሰማሁት የዳኞች ሹመት ግልፅ አለመሆንና በጣም ወጣቶች መሆን በራሱ ችግር እንዳለው ሲለግፁ ሁሉም ደካማ ናቸው ባይባልም ነገር
ግን የእድሜ ገደብ ቢንስ ወደ 30 አመት ከፍ ቢል ከእድሜ ተሞክሮ የተሻለ ዳኝነት ለመስጠት የሚስችል ሲሆን ባለጉዳዮች ሊያፍሩባቸው
የሚችሉ ግለ ጉዳዮች ለምሳሌ የባልና የሚስት የውስጥ ገመና አይነት ክርክሮችን ለመረዳት እድሜ ያበሰለው ሰው ይመረጣል ተብሎ ይታሰባል
፡፡ የትምህርት ዝግጅት ብቻ ሳይሆን የዳኝነት ስራ በባህሪው የእድሜ ተሞክሮ የሚፈልግ ስለሆነ ነው ፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የዳኞች ደሞዝና ጥቅማጥቅም በመንግስት ጭማሪ
እንዲደረግና ይህንንም ለማድረግ የበጀት እጥረት እንዳለ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዳኜ መላኩ በሚዲያ የገለፁ ሲሆን ጠቅላይ
ፍ / ቤቱ የራሱ ቦታ እንደተሰጠው ተሰምቷል የቢሮ እጥረቱን የሚቀርፍለት ሲሆን የዚህ እነኚህ ጅምሮች የሚበረታቱ ናቸው ፡፡ ጠቅላዩ ፍርድ ቤቱ በኮምፒተር መረጃዎችን የመያዝ ፤ መዝገብ የመክፈትና
ክፍያዎችን የመፈፀም በተመለከት ማሻሻሉ ፤ በበርካታ መስኮቶች ባለጉዳዮች ያለወረፋ ማስተናገድ መጀመሩ መልካም ቢሆንም ነገር ግን አስፈላጊ የሆኑ መመሪያዎች አለመውጣታቸው በራሱ ችግርን እንደፈጠረ
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሃላፊዎች በሚዲያ የተናገሩ ሲሆን አንድ ጉዳይ ወደ ይግባኝ ሲሄድ ያስቀርባል ወይስ አያስቀርብም የሚለው ግልፅ
የሆነ መመሪያ አለመኖሩ በራሱ ችግርን እንደፈጠረ የስር ፍርድ ቤት በትክክል የፈረዳቸው ማለቅና መቆም ሲገባቸው ያስቀርባል ተብለው
ውሳኔዎቹም ላይቀየሩ ነገር ግን የዜጎች ንብረት አፈጻጸም ታግዶ አለአግባብ እንደሚንከራተቱ ይታያል ፤ አንዳንዴ ደግሞ ሊያስቀርቡ
የማይገቡ ሆነው ነገር ግን በአድላዊ አሰራር አፈጻጸማቸው ታግዶ ይቆይ ለሰበር ይቅረብ ተብለው ፣ ትክክለኛ የሆነው የስር ፍርድ
ቤት ውሳኔዎች በግፍ ሲሻሩ ይስተዋላል ፤ ሌላ ግዜ ግልፅ ያልሆኑና የተምታቱ ውሳኔዎችን የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ሲሰጥ ይታያል
፡፡ ይሁንና የሰበር ችሎት የመጨረሻው ይግባኝ ሰሚ ፍ/ ቤት ነው እንጂ ህገ መንግስታዊ ፍ / ቤት አለመሆኑ የሚታወቅ ፤ ነገር
ግን በተደጋጋሚ ሰበር ችሎት እንደ ህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት ሆኖ ሲሰራም ይስተዋላል ፡፡ የፌ/ጠ/ ፍ/ ቤት ሰበር ችሎት ለስር
ፍ / ቤት አስገዳጅ የሆኑ ሃያ በላይ ቅፆችን ያሳተመ ሲሆን ይህም የሚያሳየው በተለይም የፍትሃ ብሄር ህጉ ውስጥ በርካታ ግልፅ
ያልሆኑ ነገሮች ስላሉ እነዛ ሰበር ችሎቱ አንዳንድ ግዜም እንደ ህግ አውጭ ፓርላማ ስራን እየሰራ ነው ማለት ይቻላል ነገር ግን
ሰበር ችሎቱ በአንድ ወቅት የያዘውን ኣቋም በሌላ ግዜ
መለወጥ መቻሉ ነው ከህግ አውጭው የሚለው ፤ ከዚህ ይልቅ ግን ሰበር አስገዳጅ የህግ ትርጉም የዚህን ያህል መዝገቦች መብዛታቸው
በራሱ ህጉ መፈተሸና መሻሻል እንዳለበት አመላካች ነው ፤ ህጎቹ ግልፅ ቢሆኑ ኖሮ የዚህን ያህል የበዙ ጉዳዮች አስገዳጅ የህግ ትርጉም
ባልተሰጠባቸው ነበረ ፡፡
ይህ ብቻ አይደለም ህግን የመተርጎም እንደ ህገ መንግስታዊ
ፍ / ቤት ሆኖ ስልጣን የተሰጠው ለፌዴሬሽን ም/ ቤት መሆኑ በራሱ ለህግ አተረጓጎም ችግርን ፈጥሯል ፤ ፌ/ ም ቤት ራሱ የአስፈጻሚው
የገዢው ፓርቲ አካል ሆኖ መልሶ ከፍ / ቤቶች በላይ ህግ ተርጓሚ መሆኑ ህገ መንግስታዊ ትርጉም ያስፈልጋቸዋል የሚባሉ ጉዳዮች ወደ
ም/ቤቱ የሚሄዱ ሲሆን የህግ አውጭውን ፤ የአስፈጻሚውንና የህግ ተርጓሚ የመንግስት አካላት ስራን የሚያደበላልቅ ነው ፡፡ ከዚህም
አልፎ በቅርቡ ስራውን የጀመረው የህገ መንግስታዊ አጣሪ ኮሚሽን የተባለው ተቋም ስራ መጀመሩ መልካም ሲሆን በርካታ የህግ ክፍተቶች
ባሉት የፍትህ ስርአቱ ፍርደ ገምድል ውሳኔ ተወስኖባቸው አጣሪ ኮሚሽኑ ያስተካከላቸው እንዳሉ ይታወቃል ፤ ይሁንና ይህ ተቋም የበላይ
ሃላፊዎቹ ፍርዱን የፈረደው ተቋም የጠ/ፍ / ቤት ሃላፊዎች መሆናቸው ራሱ ፍርድን የሰጠው ሰው መልሶ ቅሬታውን የሚያየው መሆኑ አሁንም
የአጣሪ ኮሚሽኑን ነጻነቱንና ተጠያቂነት አጠያያቂ ያደርገዋል ፡፡
ለመልካም አስተዳደር መጠናከር ዋነኛው የፍትህ ስርአቱን መፈተሸና
የዳኝነት ስርአቱን በተደጋጋሚ ማሻሻል አስፈላጊ ቢሆንም በከፍተኛ የመንግስት አካላት ሳይቀር ተገቢውን ትኩረት አላገኘም ፡፡ አንዳንዶቹ
ህጎች ከወጡ ረጅም አመታት ያለፋቸውና ለአሁኑ ዘመን እንዲያሰሩ በሚገባ መሻሻል የነበረባቸው ቢሆንም ሳይሻሻሉ ለበርካታ አስርት
አመታት የዘለቁ እንዲሁም ከህገ መንግስቱ በላይ እድሜ ያላቸውና በስራ ላይ ካለው ህገ መንግስት ጭምር ጋር የሚጣረሱ ሆነው ሳለ
ነገር አሁንም እየተሰራባቸው ነው ለምሳሌ ከ60 አመታት በፊት የወጣው የፍትሃ ብሄር ህጉ በርካታ ክፍተቶች ያሉበትና ጉዳዮች በቀላሉ
እንዲቋጩ የሚያደርግ ካለመሆኑም በላይ ዜጎች በቀላሉ በፖሊስ ሊያልቁ የሚችሉና የሚታወቁ ነገሮች ላይ አመታት በይግባኝ እንዲጓተቱ
የሚያደርግና ለዳኛው ከሚሰጠው ሰፊ ስልጣን አንጻር ለኪራይ ሰብሳቢነት በርን የከፈተ ነው ፡፡ የንግድ ህጉም ቢሆን የቆየ ሲሆንም
እሱንም ለማሻሻል ስራ እየተሰራ እንደሆነ በጠቅላይ አቃቤ ህግ የተገለፀ ቢሆንም ተሻሽሎ አልወጣም፡፡ አሁን ሃገሪቱ ካለችበት ፈጣን
የኢኮኖሚ እድገት አንጻር ህጎች ከዘመኑ ጋር መሄድ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም ነገር ይህ ሲሆን አይታይም ፡፡
ፍትህ ስርአቱ የሚወስናቸው ውሳኔዎች በሃገሪቱ የፖለቲካ ጉዞ
ላይ መልካምም ሆነ አሉታዊ ተፅእኖ ያለው ሲሆን ቀጥተኛ የፖለቲካ አስተዳደሩን ህልውና በበጎም ይሁን በመጥፎ ይወስናል ፡፡ በሃይለስላሴ
ግዜ በ1953 ዓ.ም. ተሞክሮ በከሸፈው የጄኔራል መንግስቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግስት ወቅት ጄኔራሉ ለምን መፈንቅለ መንግስት ሊያካሂዱ
እንደተነሳሱ ፍ / ቤት ቀርበው በተናገሩት ንግግግር ላይ ህዝቡ በትክል ዳኝነትን እንደማያገኝ እስከ 20 እና 25 አመት ድረስ
ፍርድ ቤት ሲመላለስ እንደሚኖር እንደዚሁም በንብረት፤ በመሬት ክርክሮች አስርት አመታትን በሚፈጅ የፍርድ ቤት ሙግት ቤተሰብ እንደሚፈራርስ፤
ልጆች እንደሚበታተኑ እንደዚሁም ለንብረቱ ሲባል በተከራካሪው ወገን ላይ እስከ መገደልና ንብረቱን በህግ ማስመለስ በሚያቅተው ወቅት
በሰውየው ህይወት ጭምር አደጋ እንደሚጋረጥ ፤ ይህ ሁሉ ሲሆን መቁዋጫ በሌለው የአመታት ሙግት ህዝቡ ሲሰቃይ ማየታቸውንና ንጉሰ
ነገስቱም ለማሻሻል ጥረት አለማድረጋቸውን ነገር ግን ህብረተሰቡ ለህግ በነበረው አክብሮት ግን ለአመታት ይመላለስ እንደነበረ ተናግረዋል
፡፡ የዙፋን ችሎት ተብሎ ዛሬ እንዳለው የሰበር ችሎት የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ችሎቱ ላይ ይቀመጡ የነበሩት ራሳቸው ንጉሰ ነገስቱ
ስለነበሩ እርሳቸው ካለባቸው የመንግስት ስራ ጫና የተነሳ ጉዳዩ ዙፋን ችሎት ደረጃ ለመድረስ አመታትን ይፈጅ እንደነበረ መገመት
ይቻላል፤ እንደዚሁም ንጉሰ ነገስቱ አስፈጻሚው አካል ሆነው መልሰው ህግ ተርጓሚ ዳኛ መሆናቸው ራሱ የህግ ጥያቄን ሊያስነሳ ይችላል
፡፡ የፍትህ በወቅቱ አለመስፈን የቤተሰብ ብሎም የህብረተሰቡ ሰላም እንደሚያናጋ አሁን በቅርቡ በሃገራችን ያየናቸው አስፈሪ የህዝብ
ተወቃውሞ እንቅስቃሴዎች አስረጂዎች ናቸው ፡፡
በየትም ሃገር እንደሚደረገው ሁሉ አንድ የፍትህ ስርአት ውስጡ ችግሮች ካሉበት መሻሻል እንዳለበት የታወቀ ሲሆን መንግስታት
የህዝብን ጥያቄዎችንና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን ለመመለስ በፍትህ ስርአታቸው ላይ ትኩረትን በማድረግ በየጊዜው አዳዲስ ህጎችን
በማውጣ ህጎቻቸውን በተደጋጋሚ ሲያሻሽሉ የምንሰማ ቢሆንም በሃራችን ግን አንድ ህግ አላሰራ ማለቱና መሻሻል እንደሚያስፈልገው እየታወቀ
ሳይሻሻል ለረጅም ጊዜ እንዲሰራበት በማድረግ ብዙ ችግርን ከፈጠረ በሁዋላ ወደ ማሻሻል ሲገባ ይስተዋላል ፡፡ አንድ መንግስት ስራው
አስተዳደር ብቻ ሳይሆን ጥናት እያደረገ ነባሮቹን ማሻሻልና አዲስ ህጎችን ማውጣት ነው በተለይም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋነኛው
ስራው ህጎቹን ማውጣት ለህግ ተርጓሚው አሻሚ ያልሆኑ ህጎችን መደንገግ ነው ፡፡ ጭራሽ ህችን ካለማውጣት ደግሞ አንድ ህግ ወጥቶ
ተሰርቶበት በስራ ሂደት ያለው ድከመት ታይቶ ማሻሻል የበለጠ ተመራጭ ነው ፡፡ እኛ ግን ህግን ለማውጣትም ሆነ ለማሻሻል የምንፈራ
እንመስላልን ፤ ምናልባት በመንግስት በኩል እነኚህ ነጻነትን የሚገድቡ ህጎች በቀደሙት መንግስታት ዘመን የወጡ ስለሆነ ነገር ግን
ባሻሽላቸው ስልጣኔን የተወሰነው ይቀንስብኛል የሚል ስጋት ሊኖረው ይችላል ብለን ብናስብ እንኩዋን ፤ አሁን ባለው በሃራችን ተጨባጭ
ሁኔታ ለመንግስት ስጋት የሚሆነው የመልካም አስተዳር አለመስፈን ስለሆነ የበለጠ ዋጋን እንደሚያስከፍል መረዳት ይቻላል ፡፡ እንደውም
መንግስት አሁን ካለው አሳሳቢ ከሆነው የሃገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በመነሳት ህዝቡ ፈጣን ምላሽንና መሻሻልን የሚጠብቅ በመሆኑ የህግ ክፍተት ያለባቸውን ህግጋት በባትሪ ብርሃን እየፈለገ ማሻሻል ያለበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ ክፍተት ያለባቸውን ህጎች እንደሚያሻሽሉ
፤ እንደዚሁም በተደጋጋሚ የህዝብ ቅሬታ የሚቀርብባቸውን የመንግስት መስሪያ ቤት ሃላፊዎችን እንደ የአመራር ለውጥ እንደሚያደርጉ
መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን ፍርድ ቤቶች ዋነኛ የህዝብ ቅሬታ ማእከል ከሆኑ ቆየት ብሏል ፤ እንደዚሁም ብሄራዊ ባንክ ቅሬታ የሚቀርብበት
ቢሆንም እነኚህ ሁለት ወሳኝ ተቋማት በጠቅላይ ሚ/ሩ የመጀመሪያ ሹመት የአመራር ለውጥ ሳይደረግባቸው ቀርተዋል፡፡
አንድ ሰሞን ዋነኛ የህግ ክፍተት ከሚታይባቸው ዘርፎች አንዱ
የሆነው የአከራይ ተከራይ ፤ የሪል ስቴትና የቤቶች ግዢና መግዛትን የሚመለከት ህግ ይወጣል ቢባልም ሊወጣ ጫፍ ደርሶ ሲያበቃ በማይታወቅ
ምክንያት ህጉ ሳይወጣ ቀርቷል ፡፡ መንግስት ለዜጎች ለአመታት ደክመው የሰሯቸውን ቤቶች ንብረት ለድርድር የማይቀርብ የህግ ከለላና
ጥበቃ ማድረግ አለበት ፡፡ አሁን በስራ ላይ ያለው የፍትሃ ብሄር ህግ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ካለመሆኑም በላይ አንድ አይነት
አለመግባባት ቢፈጠር የዜጎች ውል የመዋዋል መብትንና ከውል የሚመነጭ መብታቸውን ለማስከበር ፤ እንደዚሁም ግዴታዎችን ለማስፈጸም
አስቸጋሪና የተንዛዛ የአመታት የፍርድ ቤት ምልልስን የሚፈጥር ነው ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ኮንዶሚኒየም ቤት ቢገዛና ከሻጩ ጋር
አለመግባባት ቢፈጠር ነገሩን ለማስተካከል ወደ ህግ ክርክር ከሄደ ውሳኔ ለማግኘት አመታትን የሚወስድ ነው ፡፡ ይህ አዋጅ ለዚህ
አይነት ጉዳዮች ፍቱን መድሃኒት ሊሆን የሚችል የነበረ ሲሆን መዘግየቱ ግን ተገቢ አለመሆኑን መረዳት ይቻላል ፤ ይህን በመፍራት
ብዙዎች ከመግዛትና መሸጥ ሲታቀቡ ታይቷል ፡፡ በነባሩ የፍትሃ ብሄር
ህግ መሰረት አንድ ሰው ተከራይ ሆኖ የሰው ቤት ገብቶ ነገር ግን ካርታና ሰነድ ለውጦ የቤት ባለቤት የሚሆንበት ሰፊ የህግ ክፍተት
ያለ ሲሆን እንደዚሁም የሪል ስቴት ኩባንያዎች ቤቶችን ለማስራት ከደንበኞቻቸው ገንዘብን ከሰበሰቡ በሁዋላ አንዳንዶቹ እጅግ ዘግይተው
ቤቱን ሰርተው የሚያስረክቡ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ጭራሽ ገንዘቡን በማበባከን ቤት ገዢዎችን በነጻ እንዲወጡ ያደረጉ እንዳሉ በሚዲያ
የምንሰማው ጉዳይ ነው ፡፡ በነባሩ የፍትሃ ብሄር ህግ ሪል እስቴት የሚባለው ቃሉ ራሱ የማይታወቅ ሲሆን በአንድ የሪል ስቴት ቤት
ገዢና ሻጭ መሃከል አለመግባባት ቢፈጠር በተለይ ቤት ሰርቼ አስረክባለሁ ብሎ ገንዘብ የተከፈለው አካል ተጠያቂ የሚሆንበት የህግ
አሰራርም ሆነ የህግ ማእቀፍ ወይም መመሪያም ሆነ አዋጅ የለም ፡፡ በአንድ የሪል ስቴት ኩባንያና በደንበኞቹ መሃከል በተፈጠረ አለመግባባት
ላይ አንዱ ደንበኛ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ የለብንም ሲል ተሰምቷል ይህም ሪል እስቴት ግልፅ የሆነ አዋጅ ስለሌውና በፍትህ ስርአቱ
ላይ አመኔታ ባለመኖሩ ንብረቱ በአፈጻጸም ታግዶ በይግባኝ ለአስር አመታት ሊቀጥል ስለሚችል ባለው ፍራቻ ነው ፤እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ
ያሉ የህግ ክፍተቶች ናቸው ፡፡
ነገር ግን ለዚህ ሁሊ መፍትሄ ሊሆን ይችል የነበረው የሪል
ስቴት አዋጅን ማውጣት ቢሆንም አዋጁ እንደገና እንዲስተካከል በሚል ሳይወጣ ቀርቷል ፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር መልካም አስተዳርን
ለማስፈን ጥረት አድርገው የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በፍትህ ስርአቱ ላይ ትኩረትን አለማድረጋቸው ሳይሳካላቸው እንዲቀር ምክንያት
ሆኗል ፡፡ ከዚህ ቀደም በአቶ ለማ መገርሳ የተመራው ኦህዴድ በኦሮሚያ ክልል የፍትህ ስርአቱን መልሶ ያዋቀረ ሲሆን ይህም በፌደራል
ቢደገም መልካም ነው ማለት ይቻላል ፡፡ የአሁኑ አዲሱ ጠቅላይ ሚ/ ር የህግ ክፍተቶችን በመድፍን ወደ ስራ በመግባት እንደዚሁም
መቼም ቢሆን ከፍትህ ስርአቱ ላይ አይናቸውን መንቀል የለባቸውም ፤ ለቀድሞው ጠ / ሚር አስተዳደር አለመሳካትና የህዝብ ቅሬታ ምንጮች
በመሆን ፍ / ቤቶች ዋነኛ አሉታዊ አውዳሚ ሚናን መጫወታቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው ፡፡