Tuesday, April 16, 2013

የኤርትራ የወደፊት እጣ ፈንታ




በምስራቅ አፍሪካ ካሉ ሐገራት ያላት መልከአ-ምድራዊ አቀማመጥ ስልታዊ የሆነችው ኤርትራ ነፃነቷን ካገኘች ወዲህ የሄደችበት አቅጣጫ ብዙዎችን አስገርሟል ። እንደ አንድ በቅርቡ ነፃ እንደወጣ ሐገር ነፃነቷን ካገኘች ወዲህ በእርጋታና በጥንቃቄ ትጓዛለች ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ፤ በአንፃሩ የዚያች ሐገር አካሄድ ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ ሆኖ ቆይቷል ። አደገኛ በሆነው በአካባቢው የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ራሷን በሰፊው የከተተችው ኤርትራ ፣ ሀያላንንም ጭምር በሚጨምረው በዚህ አደገኛ ጨዋታዎች ውስጥ መግባቷ ውሎ አድሮ ለአለም አቀፍ ማእቀቦች ፣ ከአለም አቀፍና ከአካባቢያዊ ድርጅቶች መገለልን ፣ በዲፕሎማሲ አለም አቀፍ መገለልንና መነጠልን «Isolation» አስከትሎባታል ። 


ከጎረቤቶቿ ጋር በሙሉ መሳሪያን የተማዘዘችውና ከዚያም አልፋ ከሳኡዲ አረቢያ በስተቀረ ከየመንም ጭምር ጋር የተጣላችው ፣ እንዲሁም በሱማሊያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ራሱን የአልቃኢዳ ክንፍ ነኝ ብሎ ለሚጠራው ለአልሸባብም ጭምር ድጋፍን ስታደርግ የቆየችው ይህቺው አገር ፣ ከውጪ ለሚመለከቷት ተመልካቾች ወደ መንግስት አልባነት «Failed State»  ደረጃ ትወርዳለች ተብሎ አስግቷል ።

ምንም እንኳን ኤርትራ የቆዳ ስፋቷ ከኢትዮጲያ እጅግ ያነሰ ቢሆንም ፣ ያላት ከአንድ ሺ ማይል በላይ የሆነ በአለም ዋነኛ የንግድ መስመር በሆነው በቀይ ባህር ጠረፍና ለመካከለኛው ምስራቅ ያላት ቅርበት ተፈላጊ ያደርጋታል ። በአንድ ወቅት እንደውም አሜሪካኖች ከኢትዮጲያ ይልቅ ለኤርትራ ነው የሚያደሉት ይባሉ ነበር ። ካላት እጅግ ስልታዊ ከሆነ መልከአ ምድራዊ አቀማመጧ የተነሳ ፣ የውጭ ሀይሎች በዚህችው አገር የውስጥ ጉዳይ መግባታቸው የማይቀር ነው ። ከጎረቤቷ ሱዳን ፣ መካከለኛው ምስራቅ አረብ ሀገራትና ግብፅ ጭምር እንዲሁም እንደ አሜሪካን ያሉ ሀያላን በዚያች ሐገር የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን አይሰዱም ማለት አይቻልም ።

ኤርትራ በነፃነት ትግል ወቅት ኤርትራን ነፃ ለማውጣት እንደ ጀብሀን የመሳሰሉ የነፃ አውጭ ድርጅትች የነበሩ ቢሆንም በትግል ወቅት ጀብሀ ተሸንፎ ከትግል ሜዳ በሀይል ነው የተወገደው ። ይህችው አገር ውስጣዊ አንድነት ራሱ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ የሚችል ነው ። ከአስር በላይ ብሄር ብሄረበሰቦች ያሏት ይህችው አገር የአሰብ ወደብ ባለቤት ጭምር የሆነው የአፋር ፣እንዲሁም የብሌን ፣ የሳሆ ፣ የቤጃን የመሳሰሉ ብሄር ብሄረሰቦች አገር ነች ።


በአንፃሩ በስልጣን ክፍፍል እኚህ አናሳ ብሄረሰቦች ተገቢውን የስልጣን ውክልና አላገኙም ። ኤርትራን ነፃ በማውጣት በኩል አሸናፊ ሀይል ሆኖ የወጣው በአብዛኛው በክርስትያኖች የበላይነት የሚንቀሳቀሰው ሻእቢያ ነው ከዚህም በተጨማሪ በእስልምና እና በክርስትና እምነት ተከታይ ኤርትራውያንም የቆየ የስልጣን ትግልም እንዳለ በነፃነት ትግል ወቅት ጀምሮ የታወቀ ነው ። ስለዚህ በዚያች ሐገር ያለው መንግስት ሀገሪቱን ማስተዳደር ቢያቅተው ሊከተል በሚችለው የስልጣን ክፍተት አደገኛ የሆነና ለብዙ አሰርት አመታት የቆየው የተዳፈነው የስልጣን ሽኩቻ ሊቀሰቀስ ይችላል ። ካላት እጅግ ስልታዊ ከሆነ መልከአ-ምድራዊ አቀማመጥም የተነሳ የውጭ ሀይሎችም በሰፊው እጃቸውን ሊሰዱ ይችላሉ ።

የዚህ ውጤትም ለአፍሪካ ቀንድ የባሳ አለመረጋጋትን ሊፈጥር ሲችል ፣ ገና በእግሯ መቆም ከጀመረችው ሶማሊያ ሌላ መንግሰት አልባ የሆነ አገር ሊፈጠር ይችላል በሚል ምእራባውያንን ክፉኛ አሳስቧል ። ከዚህም በተጨማሪ ከኢትዮጲያ ጋር ያለው የድንበር ውዝግብ ገና መቋጫ ያላገኘ ከመሆኑ አንፃር ከኢትዮጲያ ጋር ያለው ሁኔታ ወዴት ሊያመራ  እንደሚችልም አንዱ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው ።

Thursday, April 11, 2013

እስያናና ምእራባውያን





በእስያውያን ምጣኔ-ሀብታቸው በዚህ ፍጥነት ያንሰራራል ተብሎ ተጠብቆ አልነበረም ። ነገር ግን ካለፉት ከ1970 እና 80 ዎቹ ወዲህ ግን ምጣኔ-ሀብታቸውን በፍጥነት በማሳደግ ወዳ ልተጠበቀ የሀብት ፈጠራና የምጣኔ - ሀብት እድገት አምርተዋል ። ይህ በእንደ አንድ በኩል ምእራባውያን መንግስታትን ሲያስደነግጥ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እነኚህ ግዙፍ ህዝብ ያላቸው የእስያ ሀገራት ፣ ለምእራባውያን ግዙፍ ኮርፖሬሽኖች ተዝቆ የማያልቅ ገበያንና ርካሽ ምርቶችን የማምረት የሚያስችል እድልን ፈጥሮላቸዋል ።


ምእራባውያን በተለይም የቻይና የምጣኔ-ሀብት እድገት የተምታታ ስሜትን ፈጥሮባቸዋል ። በአንድ በኩል ቻይና የመገበያያ ገንዘቧን ሆነ ብላ ዝቅ በማድረግ ምርቶቿን በርካሽ ለአለም ገበያ በማቅረብ የሌሎች አገራት ምርቶች በገበያው ላይ ተወዳዳሪ አንዳይሆኑ አድርጋለች ብለው ሲተቿት ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ይሄው የቻይና የገንዘብ ስርአት የንግድ ሚዛናችንን አዛብቷል ብለው ምእራውያን ቅሬታ ገብቷቸዋል ። 

ምእራባውያን የቻይና ዲሞክራሲ አለመስፈኑ ያቺ አገር አንድ ውስጣዊ አለመረጋጋት ቢገጥማት ከባድ ችግር ሊገጥመን ይችላል ብለው ይሰጋሉ ።በአለም ላይ የግዙፍ ምጣኔ-ሀብት ባለቤት ለመሆን የበቃችው ቻይና ውስጣዊ ዲሞክራሲ የሌላትና ከአንድ ዲሞክራሲ ካላደገበት አፍሪካዊ አገር ያልተሻለ ሲሆን ዲሞክራሲዋ ፣ ይህም አንድ የፖለቲካ አለመረጋጋት ቢፈጠር በቻይና ሊከሰት የሚችለው የፖለቲካ ቀውስ በአለም ላይ የምጣኔ-ሀብት መናጋትን ሊያስከትል የሚችል ነው ።

ከዚህም በተጨማሪ ቻይና የፈረጠወመውን ክንዷንም ለማሳየትም ሆነ ለማንሳት የማትቦዝን ሐገር መሆኗ ሌላው የምእራባውያን ራስ ምታት ነው ። በደቡብ ምስራቅ ቻይና ባሉት የደሴቶች ይገባኛል ጥያቄ ጉዳይ ላይ ትናንሾቹ እኛም በበኩላችን ደሴቶቹ ይገባናል ባዮቹ ቬትናምና ፊሊፒንስ እና ሌሎቹም ቻይናን የሚቋቋም ወታደራዊ አቅም የሌላቸው አገራት የአሜሪካንን ጣልቃ ገብነት ለመጠየቅ ተገደዋል ።

የወንዶች አለም



ይህ አለም «የወንዶች አለም» መሆኑ በበርካታ «ፊሜኒስት» ፀሀፍት ተደጋግሞ የተገለፀ ነው ፡። በእርግጥ ይህ አለም «የወንዶች አለም» መሆኑ ባያከራክርም ለምን የወንዶች አለም ሆነ የሚለው ጉዳይ ምላሽን የሚሻ ነው ። ይህ አለም የወንዶች አለም ሆነበት የራሱ ምክንያት አለው ። ይህ አለም የሚመራው በጉልበት ወይም በስሜት ሳይሆን በምክንያት ፣ በቁጥርና በስሌት እንዲሁም በአመክንዮ «ሎጂክ» ነው ። ስልጣኔ እድሜው እየጨመረ በሄደ ቁጥር የሳይንስ ስሌትና ምክንያታዊነት የበላይነቱን እየያዘ መጥቷል ። በጥንት ግሪክና ሮማ የነበሩ ህዝቦች አማልክቶቻቸው በሴት ፆታ ነበረ የሚመስሏቸው ። አፍሮዳይት፣ቬነስ፣ሜርኩሪ፣አቴና የመሳሰሉት በሙሉ በሴት ፆታ ይጠሩ የነበሩ እና በጥንታዊ ሰዎች እንደ አምላክ ይመለኩ የነበሩ ናቸው ።

     አንዳንድ ፊሜኒስቶች «የሴቶች ጠላቶች፣ ራሳቸው ሴቶች ናቸው» የሚል አቋም አላቸው ። ይህም በአንድ በኩል ራሳቸው ሴቶችን በመጨቆን ፣ ራሳቸው ሴቶች ዋነኛ ጨቋኞች ሲሆኑ ነው ። ሴት «ማህፀን ነች» የሚለው አባባል የሴትን ልጅ ደረጃ ዝቅ እሚያደረግ ነው ። ይህም የተዋልዶ አካል ናት ፤ የሰውን ዘር ለማስቀጠል ብቻ ነው የተፈጠረችው እንደ  ማለት ነው ። በዚህ አስተሳሰብ ከሄድን ወንድም ዘሩን ለማባዛት ብቻ ነው የተፈጠረው ወደሚል አስተሳሰብ ያመራናል ።

በነገራችን ላይ የሴቶች ስኬት ከአገር አገር ይለያያል ። እንደ ስዊድን ባሉ የሰሜን አውሮፓ ሀገራት ላይ የሴቶች ስኬትና የኑሮ ደረጃ እጅግ ከፍተኛ ሲሆን ፣ በአንፃሩም በእስያ ሀገራትም እንዲሁ ሴቶች ለከፍተኛ የመሪነት ቦታዎች የሚታጬ ናቸው ። እንደ አሜሪካ ባሉ አገራት ግን ሴቶች እምብዛም ለከፍተኛ የፖለቲካ ወንበር ላይ አይታዩም ፣ ለዚህም ምክንያቱ እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገራት ፡ ለመመረጥ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስፈልግ ሲሆን እንደ አሜሪካ ባሉ የምእራብ ሀገራት ለመመረጥ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማግኘት ስለማይችሉ በፖለቲካውም መስክ ስኬታማ ሊሆኑ አልቻሉም ። 

     የአንድ ማህበረሰብ በቅርፅና በይዘት በጊዜ ውስጥ እየተለወጠ ይሄዳል ። በዚህም በፆታዎች መሐከል ያለው ግንኙነትም በዚህ መንገድ እየተቃኘና እየተለወጠ ፣ እየተሻሻለ ይሄዳል ። በዚህም መስክ ሴቶች መብታቸውን ለማስከበር እጅግ የመረረ ትግልን አካሂደዋል ። አሁን በወንድና በሴት መሐከል ያለው የሀይል ሚዛን ፣ የግንኙነት መስፈርትና ሚዛን እዚህ ደረጃ የደረሰው እና አሁን የያዘውን ቅርፅ የያዘው በቀላሉ አይደለም ።  
     ማህበረሰቡ ወንዱ በፈጠረው አለም የሴትን ማፈንገጥና ማመፅ «ሪቤል» አጥብቆ እንደሚፈራው የታወቀ ነው ። ለምሳሌ ግርዛትን ብንወስድ የግርዛት አላማው የሴት ልጅን ወሲባዊ ስሜትን ማዳከም ወይም ታፍኖ እንዲቆይ እና በሙሉ ሀይሉ እንዳይወጣ ለማገድ ፣ ብሎም ሴቷን በቀላሉ ለመቆጣጠርና ተገዢ ለማድረግ ነው ። ሴት በወንዱ አለም ውስጥ በተለያየ መንገድ ፍንገጣዋንና አመፃዋን ትገልፃለች ። የወንድ የበላይነት ስልጣኔ በአለም ላይ ከሰፈነ ወዲህ ፣ ሙሴ ሴት አጥፍታ ብትገኝ «አይንህ እንዳይራራላት» ሲል ለተከታዮቹ ይገልፃል ።

     የካፒታሊዝም ስርአት ለራሱ ህልውና ሲል ለፈጠረው የሸማችነት ስርአትን ብንወስድ ግን ፤ ለሸማችነት  ሴት ተጠያቂ አይደለችም ፣ እንደውም የሸማችነት ሰለባ ነች ። ሸማችነት አንዱ የካፒታሊዝም ስርአት መገለጫ ነው ። በአብዛኛው ሴቶችን እሚያማልሉ ሸቀጧችን ወደ ገበያ በማውጣት ካፒታሊስቶች እጅግ የበዛ ገንዘብን እንደሚያፍሱ ይታወቃል ። የጌጣጌጥ፣ የቅባት ፣ የሽቶ ንግዶች በአለም ላይ ከፍተኛ የበርካታ ቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ የሚንቀሳቀስባቸው ናቸው ። ሸማችነት ከፆታ ጋር የሚያያዝ ነገር አይደለም ለምሳሌ ከፍተኛ የገቢ ደረጃ ባላቸው የአረብ ሀገራት ብንወስደ ፣ የእነኚህ አገራት ህዝቦች ከፍተኛ ገቢ ያላቸው መሆናቸው ይታወቃል ። በእነኚህ ሐገራት በአብዛኛው ዜጎቻቸው ምንም ስራ ስለሌላቸው በየሱቁ እየዞሩ እቃ ሲሸምቱ ነው እሚውሉት ።

የወሲብ ስሜትን «በማፈን» የተገኘው ስልጣኔ



ሲግመን ፍሮይድ ይህ የሠው ልጅ ስልጣኔ የሰው ልጅ «የወሲብ ስሜቱን በማፈን ያገኘው ነው» ሲል እንዲሁም ፍሬደሪክ ኒችም ይህ ስልጣኔ «ራስን በማሰቃየት የተገኘ ነው» ሲል ገልጿል ። ለዚህ የኒች አባባል ማስረጃ የሚሆነው ማርክስ «ዳዝ ካፒታል» በተሰኘው መፅሀፉ በዝርዝር እንደገለፀው ካፒታሊዝም ስርአት በመጀመሪያው የእድገት ዘመኑ እጅግ አነስተኛ ደሞዝ እና በጣም አስቸጋሪ በሆነ የስራ ሁኔታ የሰራተኞችን ብሎም የህፃናትን ጉልበት ጭምር ያለ ምህረት ይበዘብዝ  ፣ እንደነበረ ይገልፃል ።

የወሲብ ስሜት ልክ እንደ ማንኛውም እንሰሳ ለሰው ልጅም ራሱን እንዲራባና ዘሩን ተክቶ እንዲያልፍ የሚያስችል ነው ። ብዙውን ግዜ ታላላቅ ሀይማኖቶች ሰው ራሱን እንዲገዛ ከሚያስተምሩባቸው ምክንያቶች በአንድ በኩል የሰው ልጅ የወሲብ ስሜቱን ካልተቆጣጠረ ወደ ሌላ አላማ ሊውል የሚችል እምቅ ሀይሉን ያዳክማል ፣ በሌላ በኩል ግብረ-ገባዊ የሆነና ስርአትና ወግን የተከተለ ማህበረሰብን ለመፍጠር አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራል ። በምእራቡ አለም አንድ የፖለቲካ ሰው ከሚስቱ ውጪ ከማገጠ እና በማስረጃ ከተረጋገጠ የፖለቲካ ህይወቱ ያበቃለታል ። የወሲብ ስሜቱን መቆጣጠር የማይችል ሰው ለከፍተኛ የሀላፊነት ደረጃ አይታጭም ማለት ይሆን ?


የወሲብ ስሜት በሁለት እርስ በራሳቸው ተቃራኒ በሆኑ አቅጣጫዎች የሚመራ ነው፣ አንደኛው የወሲብ ስሜት ሀይል ሲሆን ፣ በአለም ላይ ከፍተኛ ስኬትን የሚቀዳጁ ሰዎች ከፍተኛ የወሲብ ስሜት ያላቸው ሰዎች ናቸው ። አንዳንዶቹ እንደ አይዛክ ኒውተን ያሉት ታላላቅ ሰዎች ደግሞ በድንግልና ኖረው የሞቱ ናቸው ። በተቃራኒው የወሲብ ሰሜት ካልተገራና ወደ ሌላ ጠቃሚ ወደ ሆነ ነገር ካልተለወጠ በስተቀር ፣ የሕይወት ብክነትን ይፈጥራል ።
የወሲብ ስሜት እንደ ማንኛውም እንሰሳ ለሰው ልጅ የተሰጠው ራሱን እንዲያራባበት  ነው ። ይህም ማለት የወሲብ ስሜት አንድ እምቅ ሀይል ነው ። ይህ ሀይል አለልክ ሲባክን የዛን ሰው የህይወት ግብ ያመክናል ። ሲታፈን ደግሞ እንዲሁ የተቆጣና የተናደደ ሰውን ይፈጥራል ። ናፖሌዎቸን ሂል የተባለው ፀሀፊ እንዳስቀመጠው «አንድ ሰው ከአርባ አመቱ በፊት ስኬታማ አይሆንም» ፣ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አንድ ሰው ከአርባ አመት እድሜው በፊት የወሲብ ስሜቱን መቆጣጠር ስለማይችል ነው ።

በዝግመተ-ለውጥ አስተሳሰብ መሰረት አንድ ሰው ወጣትና ለተቃራኒ ፆታ መስህብ የሚኖረው በወጣትነቱ ዘመን ብቻ ነው - ይህም ለመራባትና ራሱን መተካት አንዲያስችለው ነው ። የወጣትነቱ ዘመን ሲያልፍ ተፈጥሮ እንሰሳው ወይም ተክሉ ራሱን አንደተካ በማመን ለእርሱ እምትሰጠውን እንክብካቤ ማለትም ወጣትነቱንና ሀይሉን ውበ አማላይ አካላዊ ገፅታውንና ጥንካሬውን በአጠቃላይ የአንድ ሰው ትልቁ ፀጋ እሚባለውን ወጣትነቱን ቀስ በቀስ ትወስድበታለች ። ከዚያም እያረጀ ፣ እያረጀ ይሄድና ወደ ተፍፃሜ - ህይወቱ ማለትም ወደ ሞት ያዘግማል ።