Thursday, April 11, 2013

የወንዶች አለም



ይህ አለም «የወንዶች አለም» መሆኑ በበርካታ «ፊሜኒስት» ፀሀፍት ተደጋግሞ የተገለፀ ነው ፡። በእርግጥ ይህ አለም «የወንዶች አለም» መሆኑ ባያከራክርም ለምን የወንዶች አለም ሆነ የሚለው ጉዳይ ምላሽን የሚሻ ነው ። ይህ አለም የወንዶች አለም ሆነበት የራሱ ምክንያት አለው ። ይህ አለም የሚመራው በጉልበት ወይም በስሜት ሳይሆን በምክንያት ፣ በቁጥርና በስሌት እንዲሁም በአመክንዮ «ሎጂክ» ነው ። ስልጣኔ እድሜው እየጨመረ በሄደ ቁጥር የሳይንስ ስሌትና ምክንያታዊነት የበላይነቱን እየያዘ መጥቷል ። በጥንት ግሪክና ሮማ የነበሩ ህዝቦች አማልክቶቻቸው በሴት ፆታ ነበረ የሚመስሏቸው ። አፍሮዳይት፣ቬነስ፣ሜርኩሪ፣አቴና የመሳሰሉት በሙሉ በሴት ፆታ ይጠሩ የነበሩ እና በጥንታዊ ሰዎች እንደ አምላክ ይመለኩ የነበሩ ናቸው ።

     አንዳንድ ፊሜኒስቶች «የሴቶች ጠላቶች፣ ራሳቸው ሴቶች ናቸው» የሚል አቋም አላቸው ። ይህም በአንድ በኩል ራሳቸው ሴቶችን በመጨቆን ፣ ራሳቸው ሴቶች ዋነኛ ጨቋኞች ሲሆኑ ነው ። ሴት «ማህፀን ነች» የሚለው አባባል የሴትን ልጅ ደረጃ ዝቅ እሚያደረግ ነው ። ይህም የተዋልዶ አካል ናት ፤ የሰውን ዘር ለማስቀጠል ብቻ ነው የተፈጠረችው እንደ  ማለት ነው ። በዚህ አስተሳሰብ ከሄድን ወንድም ዘሩን ለማባዛት ብቻ ነው የተፈጠረው ወደሚል አስተሳሰብ ያመራናል ።

በነገራችን ላይ የሴቶች ስኬት ከአገር አገር ይለያያል ። እንደ ስዊድን ባሉ የሰሜን አውሮፓ ሀገራት ላይ የሴቶች ስኬትና የኑሮ ደረጃ እጅግ ከፍተኛ ሲሆን ፣ በአንፃሩም በእስያ ሀገራትም እንዲሁ ሴቶች ለከፍተኛ የመሪነት ቦታዎች የሚታጬ ናቸው ። እንደ አሜሪካ ባሉ አገራት ግን ሴቶች እምብዛም ለከፍተኛ የፖለቲካ ወንበር ላይ አይታዩም ፣ ለዚህም ምክንያቱ እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገራት ፡ ለመመረጥ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስፈልግ ሲሆን እንደ አሜሪካ ባሉ የምእራብ ሀገራት ለመመረጥ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማግኘት ስለማይችሉ በፖለቲካውም መስክ ስኬታማ ሊሆኑ አልቻሉም ። 

     የአንድ ማህበረሰብ በቅርፅና በይዘት በጊዜ ውስጥ እየተለወጠ ይሄዳል ። በዚህም በፆታዎች መሐከል ያለው ግንኙነትም በዚህ መንገድ እየተቃኘና እየተለወጠ ፣ እየተሻሻለ ይሄዳል ። በዚህም መስክ ሴቶች መብታቸውን ለማስከበር እጅግ የመረረ ትግልን አካሂደዋል ። አሁን በወንድና በሴት መሐከል ያለው የሀይል ሚዛን ፣ የግንኙነት መስፈርትና ሚዛን እዚህ ደረጃ የደረሰው እና አሁን የያዘውን ቅርፅ የያዘው በቀላሉ አይደለም ።  
     ማህበረሰቡ ወንዱ በፈጠረው አለም የሴትን ማፈንገጥና ማመፅ «ሪቤል» አጥብቆ እንደሚፈራው የታወቀ ነው ። ለምሳሌ ግርዛትን ብንወስድ የግርዛት አላማው የሴት ልጅን ወሲባዊ ስሜትን ማዳከም ወይም ታፍኖ እንዲቆይ እና በሙሉ ሀይሉ እንዳይወጣ ለማገድ ፣ ብሎም ሴቷን በቀላሉ ለመቆጣጠርና ተገዢ ለማድረግ ነው ። ሴት በወንዱ አለም ውስጥ በተለያየ መንገድ ፍንገጣዋንና አመፃዋን ትገልፃለች ። የወንድ የበላይነት ስልጣኔ በአለም ላይ ከሰፈነ ወዲህ ፣ ሙሴ ሴት አጥፍታ ብትገኝ «አይንህ እንዳይራራላት» ሲል ለተከታዮቹ ይገልፃል ።

     የካፒታሊዝም ስርአት ለራሱ ህልውና ሲል ለፈጠረው የሸማችነት ስርአትን ብንወስድ ግን ፤ ለሸማችነት  ሴት ተጠያቂ አይደለችም ፣ እንደውም የሸማችነት ሰለባ ነች ። ሸማችነት አንዱ የካፒታሊዝም ስርአት መገለጫ ነው ። በአብዛኛው ሴቶችን እሚያማልሉ ሸቀጧችን ወደ ገበያ በማውጣት ካፒታሊስቶች እጅግ የበዛ ገንዘብን እንደሚያፍሱ ይታወቃል ። የጌጣጌጥ፣ የቅባት ፣ የሽቶ ንግዶች በአለም ላይ ከፍተኛ የበርካታ ቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ የሚንቀሳቀስባቸው ናቸው ። ሸማችነት ከፆታ ጋር የሚያያዝ ነገር አይደለም ለምሳሌ ከፍተኛ የገቢ ደረጃ ባላቸው የአረብ ሀገራት ብንወስደ ፣ የእነኚህ አገራት ህዝቦች ከፍተኛ ገቢ ያላቸው መሆናቸው ይታወቃል ። በእነኚህ ሐገራት በአብዛኛው ዜጎቻቸው ምንም ስራ ስለሌላቸው በየሱቁ እየዞሩ እቃ ሲሸምቱ ነው እሚውሉት ።

No comments:

Post a Comment