Tuesday, April 16, 2013

የኤርትራ የወደፊት እጣ ፈንታ




በምስራቅ አፍሪካ ካሉ ሐገራት ያላት መልከአ-ምድራዊ አቀማመጥ ስልታዊ የሆነችው ኤርትራ ነፃነቷን ካገኘች ወዲህ የሄደችበት አቅጣጫ ብዙዎችን አስገርሟል ። እንደ አንድ በቅርቡ ነፃ እንደወጣ ሐገር ነፃነቷን ካገኘች ወዲህ በእርጋታና በጥንቃቄ ትጓዛለች ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ፤ በአንፃሩ የዚያች ሐገር አካሄድ ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ ሆኖ ቆይቷል ። አደገኛ በሆነው በአካባቢው የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ራሷን በሰፊው የከተተችው ኤርትራ ፣ ሀያላንንም ጭምር በሚጨምረው በዚህ አደገኛ ጨዋታዎች ውስጥ መግባቷ ውሎ አድሮ ለአለም አቀፍ ማእቀቦች ፣ ከአለም አቀፍና ከአካባቢያዊ ድርጅቶች መገለልን ፣ በዲፕሎማሲ አለም አቀፍ መገለልንና መነጠልን «Isolation» አስከትሎባታል ። 


ከጎረቤቶቿ ጋር በሙሉ መሳሪያን የተማዘዘችውና ከዚያም አልፋ ከሳኡዲ አረቢያ በስተቀረ ከየመንም ጭምር ጋር የተጣላችው ፣ እንዲሁም በሱማሊያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ራሱን የአልቃኢዳ ክንፍ ነኝ ብሎ ለሚጠራው ለአልሸባብም ጭምር ድጋፍን ስታደርግ የቆየችው ይህቺው አገር ፣ ከውጪ ለሚመለከቷት ተመልካቾች ወደ መንግስት አልባነት «Failed State»  ደረጃ ትወርዳለች ተብሎ አስግቷል ።

ምንም እንኳን ኤርትራ የቆዳ ስፋቷ ከኢትዮጲያ እጅግ ያነሰ ቢሆንም ፣ ያላት ከአንድ ሺ ማይል በላይ የሆነ በአለም ዋነኛ የንግድ መስመር በሆነው በቀይ ባህር ጠረፍና ለመካከለኛው ምስራቅ ያላት ቅርበት ተፈላጊ ያደርጋታል ። በአንድ ወቅት እንደውም አሜሪካኖች ከኢትዮጲያ ይልቅ ለኤርትራ ነው የሚያደሉት ይባሉ ነበር ። ካላት እጅግ ስልታዊ ከሆነ መልከአ ምድራዊ አቀማመጧ የተነሳ ፣ የውጭ ሀይሎች በዚህችው አገር የውስጥ ጉዳይ መግባታቸው የማይቀር ነው ። ከጎረቤቷ ሱዳን ፣ መካከለኛው ምስራቅ አረብ ሀገራትና ግብፅ ጭምር እንዲሁም እንደ አሜሪካን ያሉ ሀያላን በዚያች ሐገር የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን አይሰዱም ማለት አይቻልም ።

ኤርትራ በነፃነት ትግል ወቅት ኤርትራን ነፃ ለማውጣት እንደ ጀብሀን የመሳሰሉ የነፃ አውጭ ድርጅትች የነበሩ ቢሆንም በትግል ወቅት ጀብሀ ተሸንፎ ከትግል ሜዳ በሀይል ነው የተወገደው ። ይህችው አገር ውስጣዊ አንድነት ራሱ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ የሚችል ነው ። ከአስር በላይ ብሄር ብሄረበሰቦች ያሏት ይህችው አገር የአሰብ ወደብ ባለቤት ጭምር የሆነው የአፋር ፣እንዲሁም የብሌን ፣ የሳሆ ፣ የቤጃን የመሳሰሉ ብሄር ብሄረሰቦች አገር ነች ።


በአንፃሩ በስልጣን ክፍፍል እኚህ አናሳ ብሄረሰቦች ተገቢውን የስልጣን ውክልና አላገኙም ። ኤርትራን ነፃ በማውጣት በኩል አሸናፊ ሀይል ሆኖ የወጣው በአብዛኛው በክርስትያኖች የበላይነት የሚንቀሳቀሰው ሻእቢያ ነው ከዚህም በተጨማሪ በእስልምና እና በክርስትና እምነት ተከታይ ኤርትራውያንም የቆየ የስልጣን ትግልም እንዳለ በነፃነት ትግል ወቅት ጀምሮ የታወቀ ነው ። ስለዚህ በዚያች ሐገር ያለው መንግስት ሀገሪቱን ማስተዳደር ቢያቅተው ሊከተል በሚችለው የስልጣን ክፍተት አደገኛ የሆነና ለብዙ አሰርት አመታት የቆየው የተዳፈነው የስልጣን ሽኩቻ ሊቀሰቀስ ይችላል ። ካላት እጅግ ስልታዊ ከሆነ መልከአ-ምድራዊ አቀማመጥም የተነሳ የውጭ ሀይሎችም በሰፊው እጃቸውን ሊሰዱ ይችላሉ ።

የዚህ ውጤትም ለአፍሪካ ቀንድ የባሳ አለመረጋጋትን ሊፈጥር ሲችል ፣ ገና በእግሯ መቆም ከጀመረችው ሶማሊያ ሌላ መንግሰት አልባ የሆነ አገር ሊፈጠር ይችላል በሚል ምእራባውያንን ክፉኛ አሳስቧል ። ከዚህም በተጨማሪ ከኢትዮጲያ ጋር ያለው የድንበር ውዝግብ ገና መቋጫ ያላገኘ ከመሆኑ አንፃር ከኢትዮጲያ ጋር ያለው ሁኔታ ወዴት ሊያመራ  እንደሚችልም አንዱ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው ።

No comments:

Post a Comment