Tuesday, March 12, 2013

የመግባባት (Communication Skill) ችሎታ





የመግባባት ችሎታ ለመሪነት ብቻም ሳይሆን ለአንድ ሰው የህይወት ስኬት እጅግ ቁልፍ ከሆኑ ክህሎቶች አንዱና ዋነኛው ነው እንኳን መሪ ይቅርና አንድ ሰው በህይወት ውስጥ የሚፈልገውን ማንኛውንም ነገር በቀላሉ ሊያገኝና በሚፈልገው መንገድ ለመኖር የመግባባት ክህሎት አስፈላጊ ነው

የስነ - ልቦና ባለሙያዎች እንዳረጋገጡት የመግባባት ችሎታ ለመሪው እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ችሎታዎች አንዱ ሲሆን ተግባቦት (Communication) የሚባለው ነገር 64 በመቶው በአካላዊ እንቅስቃሴ መግባባት የሚካሄድበት ሲሆን የተቀረው 36 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በንግግር በፅሁፍና በስእል መግባባት የሚደረግበት ነው መሪም እነኚህን የመግባባት መንገዶችን ጠንቅቆ ማወቅ ሲኖርበት ይህንን የመግባባት ችሎታን ያልተረዳ መሪ ግን ሊያስተላልፍ የሚፈልገውን መልእክት ሳያስተላልፍ ይቀራል መልእክቱን በአግባቡ ካላስተላለፈ ደግሞ ለመምራት ያለውን እድል ይቀንሰዋል

አንድ መሪ በአራትና በአምስት አቅጣጫ መግባባት መቻል አለበት ከበታቾቹ ጋር ከእርሱ ትይዩ ካሉ እኩዮቹ እንዲሁም ከበላዮቹ ጋርና እንዲሁም ከደንበኞቹ እንዱሁም በአጠቃላይ ከሚያገለግለው ህዝብ ጋር ሌላው ቀርቶ አንድ መሪ ከጋዜጠኞች ጋር ያለው ግንኙነት ሁሉ ለስኬቱ ወሳኝነት አለው በተለይም በእንዲህ አይነቱ ግንኙነት ወቅት ከአለባበሱና ከአነጋገሩ ጀምሮ ስነ - ስርአትን በጠበቀ መልኩ ግንኙነትን መፍጠር አለበት ከስርአት ውስጪ የሆኑ ባህሪያቶችን ማስወገድ አለበት ይህም በሌሎች ሰዎች ዘንድ ቅሬታን ሊፈጥር ስለሚችል ሌሎችን እንደናቃቸውና ዝቅ እንዳደረጋቸው አሰድርገው እንዳይወስዱት ያደርገዋል

ከዚህም በተጨማሪ ስኬታማ ለሆነ የቡድን ስራ ተግባቦት እጅግ አስፈላጊ ነው በቂ ተግባቦት የሌለባቸው የስራ ከባቢዎችመግባባት ከማጣት የታወኩና ውስጥ ውስጡን የማያቋርጥ የእርስ በእርስ ሽኩቻ የሚደረግባቸው ናቸው

ለጥሩ ተግባቦች መሪው ራሱን በቅጡ ማወቁ እጅግ አስፈላጊ ነው ለምሳሌ መሪው የራሱን እሴቶችን አስተሳሰቦችን እውነት ብሎ የያዛቸውን ሀቆችን እንዲሁም የራሱን የተዛቡ አስተሳሰቦችንም  ጭምር የሚያውቅ መሪ ከሌሎችን ጋር በቀላሉ መግባባት ይችላል ራሱን በሌሎች ሰዎች ቦታ አድርጎ የመመልከት ልማድ መሪው የሌሎችን ፍላጎትና አላማና ችግር በቀላሉ ለመረዳት ያስቸግረዋል ።ሌሎችንም እንዲሁ ማወቅ አስፈላጊ ነው የሌሎችን ስሜት ፍላጎት ሀሳብ መረዳትም እንዲሁ ለተሳካ ተግባቦት አስተዋፅኦን ያደርጋል

መሪዎች አወዛጋቢ ከሆኑ የስልጣን እድሜአቸውን ያሳጥራል አወዛጋቢ መሪዎች በስልጣን የመቆየት እድሜቸው አጭር ነው መሪዎች አወዛጋቢ ከሆኑ ብዙ ተቃዋሚዎችን ስለሚያፈሩ ሌሎች ሰዎች በዚያ ስልጣን ሊያቸው አይፈልጉም ብዙውንም ጊዜ ለሀላፊነታቸው እንዲለቁ ግፊት ይደረግባቸዋል መቼ ነው ከስልጣን የሚለቁት የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄም ይቀርብላቸዋል በእርግጥ ሁሉም ጠላታቸው ይሆናል ማለት ባይሆንም ነገር ግን ለስራቸው መቃናት ግን እንቅፋትን ይፈጥርባቸዋል

ለአመራር ብቃት አስፈላጊ ክህሎቶች


የሚተማመኑበት (Dependable) መሆን

          እንኳን ግለሰብ መሪዎችን ትተን ፣ በአለማችን ላይ ከትላልቆቹ ኩባንያዎች ፣ መንግስታት ፣ ባንኮች እና መሰል ተቋማት ስራቸውን መስራት የሚችሉት መልካም ስማቸውን እስጠበቁ ድረስ ነው ። ተቋማትም ህልውናቸው የተመሰረተው ከዚህ እምነት ላይ ነወው ። ተአማኒ መሆን ለአንድ መሪ የስራ ስኬት እጅግ አስፈላጊ ነው ። አንድ መሪ በተከታዮቹም ሆነ በተቀረው ወገን ሌሎች ሰዎች የሚተማመኑበት መሆን መቻል ይኖርበታል ። አንድ መሪ የሚመራውን ተቋምንም ሆነ የራሱን መልካም ስምና ዝናን መጠበቅ አለበት ።

መልካም ስምናንና ዝናን (Reputation) ለመገንባት አመታትን የሚፈጅ ነገር ሲሆን በአንፃሩ አንዴ ካመለጠ ግን መልሶ ለመገንባት የበለጠ ጊዜን ይወስዳል ፤ የጠፋውንም ስም ለመገንባት ፈፅሞ ላይመለስም ይችል ይሆናል ፣ በቅርብ ጊዜ ወዲህ በዚህ መስክ እየወጡ ያሉ ጥናቶች  እንደሚጠቁሙት በበርካታ ማህበረሰቦች ውስጥ (Ethical) በስነ - ምግባር የስነ -  ባህሪ ውድቀትን በስፋት መረዳት ችለዋል ፤ ነገር እየሳሳ እንደመጣ በበርካታ በዘርፉ ጥናት ያጠኑ አጥኚዎች መስክረዋል ። ይህም እጅግ አሳሳቢ ሲሆን መተማመንን ፣ መልካም ስምን በመጠበቅ ፋንታ በሌላው ማላከክን ፣ ከተጠበቀው በታች አገልግሎትን ወይንም ሸቀጥን ማቅረብን ፣ ወይንም ለምሳሌ የባጀት ፍላጎትን አጋኖ ማቅረብን የመሳሉት ሲሆኑ በተለይም የበታች ሰራተኞች የበላይ መሪዎቻቸው የዚህን አይነት ባህሪን በሚያሳዩበት ወቅት ወደ ተቀረው ሰራተኞች እንደሚስፋፉና የመሪዎቹንም ሆነ የድርጅቶቹን መልካም ስም እንደሚሸረሽር ተመራማሪዎቹ በጥናታቸው ተረድተዋል ። 


በተለይ በአሁኑ ወቅት የትላል ኩባንያ ሀላፊዎች ፣ እንደዚሁም እምነታቸውን መጠበቅ ይገባቸው የነበሩ በርካታ ሰዎች እምነታቸውን ሲጥሱና ፣ በዛም ተጠያቂ ሲደረጉ ማየትና መስማት የተለመደ ሆኗል ። የምእራቡ አለም የገንዘብ ተቋማት ተአማኒነታቸው በመሸርሸሩ ኀላፊዎቻቸው ሲጠየቁ መመልከት የተለመደ ነው ። ይህም በተቋማቱ ህልውና ላይ ጥቁር ጠባሳን የተወና በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነው ።


ሀላፊነትን ለመውሰድ ዝግጁ መሆን
አንድ መሪ ለራሱም ሆነ በሱ ስር ያሉ ተከታዮች ለወሰኑት ውሳኔና ድርጊቶት ሀላፊነተቱን ራሱ መዉሰድ ይኖርበታል። እርሱ ሳያውቅ እንኳን እርሱ በሚመራው ተቋም ስር አንድ ነገር ቢፈጠር ፣ ምንም እንኳን ያን ነገር አር እርሱ ራሱ ባያደርገውም ራሱ የሚመራውውን ተቋም መቆጣጠርና የሚደረገውን ነገር ማወቅ መቻል አለበት ። እንጂ በበታቾቹ የሚያላክክ መሪ እንደ መሪ አይቆጠርም ፣ ወይንም ሀላፊነትን እንደመሸሽ ይቆጠርበታል ። ጥፋትን ወደ ሌሎች የሚያከላክክ ከሆነ ፣ ድሎቹን ብቻ  ነው ማለት ነው እኔ ሰራሁ ለማለት የሚፈልገው ማለት ነው ። የዚህ አይነት መሪዎች ለሚያደርጉት ነገር ራሳቸው ሀላፊነትን የማይወስዱ በመሆናቸው ተከታይን አግኝተው ሊቀጥሉ አይችሉም ።


የሚበልጡትን ሰዎች ከጎኑ ለማሰለፍ ዝግጁ መሆን


የአንድ መሪ ችሎታ ከሚለካባቸው ችሎታዎች አንዱ በዙሪያው በሚያሰልፋቸው ሰዎች ብቃት ነው ። አቅም ያላቸውን በዙሪያው ማሰባሰብ የሚችል መሪ ይደነቃል ብቃት ብቻ ሳይሆን ከሱ የሚበልጡ ሰዎችንም ጭምር በዙሪያው ማሰለፍ የሚችል መሪ ብልህ መሆኑን ያሳያል ። አንዳንድ ግዜ መሪዎች ከእነሱ የሚበልጧቸውንና ከነሱ ጎልተው ሊታዩ የሚችሉ ሰዎችን በዙሪያቸው ለማሰለፍ አይፈልጉም ይህም በሌሎች መበለጥን ዋጥ የማድረግ ችሎታን ይጠይቃል ። ብዙውን ጊዜ በሌሎች እንጋረዳለን ብለው የሚሰጉ ሰዎች ፣ የሚበልጧቸውን ከጎናቸው ለማሰለፍ ያመነታሉ ።
ነገር ግን ይህ በብዙ የአፍሪካ ሀገራት የተለመደ ነገር አይደለም ። በመሪዎችና በምሁራኖችና በሳይንቲስቶች መሀከል መቀራረብና አብሮ የመስራት ነገር ብዙም አይታይም ፣ ነገር ግን መሪዎች የባለሙያዎችን ምክር እንደ ግብአት ቢጠቀሙበት ለውሳኔያቸው ይበልጥ ጠቃሚ ሆኖ ያገኙታል ። በባለሙያዎች በኩልም የመሪዎቹን ደረጃ ጠብቀው መልካም ግንኙነትን ለመፍጠር ጥረትን ማድረግ ይጠበቃል ። በእርግጥ አንድ ትልቅ የስልጣን ደረጃ ላይ ያለ ሰውን ማገልገል የራሱ የሆነ ጥበብን ይጠይቃል ። ያ መሪ ቢሳሳት እንኳን በቀጥታ ይህን አድርገሀል ላይባል ይችላል ።  
በአብዛኛው በሀገራችንም ሆነ በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ቲንክ ታንኮች (አዳዲስ ሀሳቦችን አመንጪ የሀሳብ ሙዳየ ተቋማት ፣ የሙያተኞች አምባ ) በብዛት የሉም ። ይህ በምእራቡ አለም የተለመደ ስለሆነ መሪዎች በቀላሉ ከብዙ ቲንክ ታንኮች ሀሳቦችን የመውሰድ እድል አላቸው ፣ መሪዎች የመምራት ስራቸውን ያቀልላቸዋል ። እነኒኚህ ተቋማት በምርምርና በጥናት በበርካታ ጉዳዮች ላይ ስለሚመራመሩ ፣ የምርምራቸውንም ውጤት በህትመት ስለሚያሰራጩት በብዙ ሰዎች ዘንድ እንዲደርስ ያደርጋሉ ።

ይህም ብዙውን ግዜ አንድ መሪ ከእርሱ ጋር ተመጣጣኝ ወይንም ከተቻለ የበለጡ ሰዎችን ማሰለፍ መቻል ፣ ለመምራት የሚያስችለውን አንድ የልእለ - አእምሮ ቡድንን እንዲፈጥር ያስችለዋል ።ከተለያዩ ሙያዎች የተውጣጡ ባለሙያዎቸን ማሰለፍ  ለመሪው እጅግ አስፈላጊ ሲሆን ፣ እርሱ ብቻውን ሊወጣ የማይችለውን ፣ በሌሎች አቅሙና ልምዱ ባላቸው ሰዎች እገዛ እንዲወጣ ያደርገዋል ። ለምሳሌ ማይክሮሶፍት ኩባንያን በመመስረት ስኬታማ የሆነው ቢል ጌትስ ከፍተኛ እውቀት ያላቸውን ሰዎች በዙሪያው በማሰለፍ ይታወቃል ። በአሜሪካም እንዲሁ አንድ ፓርቲ ተመርጦ ወደ ቤተመንግስት በሚገባበት ወቅት በሚችለው አቅም ከፍተኛ ልምድንና ብቃትን ያላቸውን ሰዎችን በአማካሪነትና የተለያዩ ሀላፊነቶችን በመስጠትስራውን እንደሚጀምር ይታወቃል ።


ነገር ግን ይህን ማድረግ ካልቻለ የእርሱን ፍላጎት በማንበብ ደካማ የሆኑና ጥቅም ፈላጊ የሆኑ ሰዎች ይከቡታል ። ይህም ወይ ጠንካራ ሰዎች ከጎኑ አይኖሩም ፣ ወይም እርሱ እሚፈልገውን ደካማ ፍላጎትን የሚያሟሉ ሰዎች ብቻ ባጠገቡ እንዲገኙ ያደርጋል ።


ይህ ብቻም ሳይሆን ብቃት ያላቸው ሰዎች በመሪው ዙሪያ መኖራቸው በመሪው ላይ ሊኖር የሚችለውን የስራ ጫናን ይቀንስለታል ። ሁሉንም ነገር ራሱ ከሚሰራው ይልቅ በሌሎች ሰዎች ቢታገዝ እርሱ ከዛ የበለጠት ኩረትን ወደ ሚሹ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ማድረግ ያስችለዋል ። በተለይም ሀሳብን በማመንጨትና በመፈፀም በኩል የለሌሎች ሰዎች እገዛ ለመሪው የስራ መቃናት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ። ይህም ብቻ ሳይሆን መሪዎች በስራ ጫናና ሸክም ምክንያት ህመም ላይ እንደሚወድቁም ይታወቃል እንደ ልብ ድካም ፣ ስትሮክ ፣ ማርጀት ፣ መሸበት የመሳሰሉት ህመሞችንና አካላዊ ለውጦችን በብዛት አእምሯዊ የሆነ ከባድ የስራ ሸክም ባለባቸው ሰዎች ላይ በብዛት እንደሚከሰቱ ይታወቃል ። መሪ እንደማንኛውም ሰው ጤናው ይታወካል ፣ በአለማችንም ላይ በርካታ መሪዎች በስራ ላይ እያሉ ህይወታቸውን ያጡ ወይንም ለከባድ ህመም የተጋለጡ በርካታ መሪዎች አሉ ፤ በአብዛኛው ምክንያቱም መሪዎች ካለባቸው የስራ ጫናና የጭንቀት ምክንያት የሚከሰቱ ናቸው ። በተገቢው ሁኔታ የእረፍት ጊዜውን የሚጠቀም መሪ የእረፍት ጊዜውን ከማይጠቀም መሪ ይልቅ ጤነኛ እና ረጅም አመታትን በተሻለ የመኖርና የመስራት እድል ይኖረዋል ።


ዊድሮው ዊልሰን በአሜሪካ ቤተ-መንግስት ውስጥ እያለ ሁለት ጊዜ ስትሮክ የመታው ሲሆን ፣ ኮንግሬሱ ሁለት ጊዜ የጣለው ሲሆን ፣ የናዚዎች መሪ የነበረው አዶልፍ ሂትለርም ናዚዎች እየተሸነፉ በነበረበት የመጨረሻው ዘመን በተደጋጋሚ ስትሮክ እንደመታውና ፣ ከቀኑ ውስጥ ለረጅም ሰአታት በእንቅልፍ ያሳልፍ እንደነበረ የታሪክ ባለሙያዎች የመዘገቡት ነው ። የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶችንም እንዲሁ ከዋይት ሀውስ ሲወጡ ሸብተው እንደሚወጡ ይታወቃል ። ለምሳሌ ማእድን ማውጣትን ብንወስድ ለአደጋ እንዲሁም ለጤንነት አደገኛ ከሆኑ ስራዎች አንዱ ነው ። በእርግጥ መሪነት እዛ ደረጃ ላይ ባይደርስም በአለም ላይ ለጤንነት እንዲሁም ለአደጋ የሚያጋልጡ ስራዎች እንዳሉ ሁሉ መሪነት ለጤንነት አደገኛ ከሆኑ ስራዎች እንደ አንዱ ሊመደብ ይችላል፣ በተለይም ውጥረትና ጭንቀት የሚበዛባቸው የስራ ድባቦችና ሁኔታዎች ለመሪዎችም ሆነ በዙሪያቸው ላሉ ሰዎች ጭንቀትንና ስጋትን ይፈጥራሉ ። 




የትውልዶች ቅብብሎሽ

 

ወጣት ችግርም ሲመጣ መስዋእትነትን የሚከፍለው እሱ ስለሆነ ያገሩ ጉዳይ ከሌሎቹ የትውልዱ አካላት በበለጠ ሊያሳስበው ይችላል ።በሀገራችን በ1950ዎቹና 60ዎቹ ብዙ ጊዜ የነበረው ትውልድ ይደነቃል ። ሆኖም ሁሉም ትውልድ የየራሱ የሆኑ ታሪካዊ ግዴታዎችና ሀላፊነቶች አሉበት እንደየዘመኑና ወቅቱም ይለዋወጣሉ ።በአንድ ወቅት የነበረ ችግር በሌላ ጊዜ ላይኖር ይችላል፣ ወቅቱ የሚጠይቀው ፈተናም እንደዛው ለየቅል ነው ። ሁኔታዎች ስለሚቀያየሩ የሚፈልጉትም መፍትሄ እንደዛዉ ይለያያል።


ቻይናውያን ሰፊ የአመራር ልምድ ያላቸው ሲሆኑ የመተካካት ባህላቸው እድሜን እያስቆጠረ የመጣና ሲሆን መተካካቱም በመንግስት ስልጣን ላይ ብቻ ሳይሆን በፓርቲውስጥም እስካሉት ከፍተኛ የአስፈፃሚዎች ድረስ ነው ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማካይ በየአስር አመቱ የፓርቲው ከፍተኛ ስራ 9 ከሚሆኑት ውስጥ 7 ወይም 8 የሚሆኑት ይተካሉ ስለዚህ ይህ በፓርቲው ውስጥም ሆነ በመንግስት ውስጥ የሚደረገው የአመራር ለውጥ ከዋናዎቹ መሪዎች ጀምሮ ነው ።


ይሁን እንጂ በመሪነት ውስጥ እሚመከረው ከሶስቱም ትውልዶች የተለዩ ትውልዶች ሰዎች መኖር አለባቸው ። ከወጣትም፣ ከመካከለኛው እድሜም ፣ እንዲሁም የረጅም ዘመን ልምድ ካላቸው የተውጣጣ እንዲሆን ነው ።ለምሳሌ የረጅም ዘመን ልምድ ያላቸው ሰዎች ከሌሉ ለወጣቶቹ ተሞክሮን እሚያስተላልፍላቸው አይኖርም ፣ መሀል ላይ ያለውም ባይኖር በእድሜ ከበለፀጉት በቅርብ ሊረከብ የሚችል አይኖርም ። የረጅም ዘመን ልምድ ያላቸው ሰዎች ብቻ ቢኖሩ ከአዲሱ ለውጥ ጋር ለመጓዝ አስቸጋሪ ይሆናል ። ስለዚህ ትውልድ ሰንሰለት ነው እንደሚባለው ሁሉ በመሪነት ውስጥም እንደዛው ሰንሰለቱን ጠብቆ እየተተካካ መሄድ አለበት ።

ታክቲክና ስትራቴጂ

አንድ ነገር እየተደረገ ካለበት ጊዜ ይልቅ ካለፈ በኋላ ይበልጥ ጥሩነቱ ወይንም መጥፎነቱ መሆኑ ጎልቶ ይታያል ። መጥፎ ስራ ጊዜ እያለፈ በሄደ ቁጥር መጥፎነቱ ይበልጥ እየጎላ ይሄዳል ሲሄድ በአንፃሩ ደግሞ ጥሩ ስራ ከሆነ ደግሞ ጊዜ ጥሩነትን ይበልጥ እያጎላው ይሄዳል ። ለዚህም በርካታ መጥፎ ስራዎች መጥፎነታቸው ተደጋግሞ የሚነሳና በርካታ አመታትም ካለፉም በኋላም ቢሆን መጪውም ትውልድ ጭምር የሚያፍርባቸው ሲሆኑ ፣ ጥሩዎቹም ዘመን ባለፈ ቁጥር ጥሩነታቸው እየጎላና ህብረተሰቡ የሚኮራባቸው ነው ። ስለዚህ የሚያደርጋቸውን ነገሮች የአጭርነ ና የረጅም ጊዜ አንድምታ ለይቶ ማወቅ አለበት ። እነኚህም የሚከናወኑት በታክቲኮችና በስትራቴጂዎች አማካይነት ነው ።


አንድ መሪ በተለይ ግቡን ለማሳካት ስታራቴጂዎችንና ታክቲኮችን ማወቅ አለበት ። አንድ መሪ ስትራቴጂንና (Strategy) እና ታክቲክን (Tactic) ለይቶ ማወቅ ሲኖርበት ፣ ስትራቴጂ ማለት የመሪው ዋነኛው የረጅም ጊዜ ግቡ ወይም በረጅም ጊዜ እደርስበታለሁ ብሎ የሚያስበው ሲሆን ፣ በአንፃሩ ግን ታክቲክ ማለት ስትራቴጂውን እሚያስፈፅምበት የአጭር ጊዜ ብልሀቶችና መንገዶች ናቸው ። ስለዚህ የታክቲኮች ስኬታማነት ተሰባስቦ የስትራቴጂን ውጤማነትን ያረጋግጣል ። የታክቲኮች መውደቅም የስትራቴጂውን አለመሳካት ሲያመለክት ።


ይሁን እንጂ (the End Justifies the Means)የሚል አቋም ያላቸውና አንድ መሪ ስትራቴጂውን ለማሳካት ማንኛውንም ነገር ማድረግ አለበት ብለው የሚያምኑ አሉ ። መጨረሻ ግቡ ትክክል እስከሆነ ድረስ ፣ መሪው ግቡን ለማሳካት ማንኛውንም ነገር ወንጀል ሊሆን የሚችልንና ሌሎች ሰዎችን ሊጎዳ የሚችል ነገርን ጨምሮ መፈፀምና አላማውን ማሳካት አለበት ብለው የሚያምኑ ናቸው ። ነገር ግን ይህ አስተሳሰብ እጅግ አደገኛ ሲሆን ሊያስከትል የሚችለው ቀውስ ከባድ በመሆኑ ከፍተኛ የማመዛዘን ችሎታን ይጠይቃል ። ታላቁ ስትራቴጂ ወይም ዋነኛው ግብ የሚባልም አለ ። 

የአጭር ጊዜ የታክቲክ አዋቂ መሆንና የረጅም ጊዜ የስትራቴጂ ቀያሽ መሆን በጣም የተለያዩ መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል ። ብዙ ጊዜ የአጭር ጊዜ ታክቲኮች ረጅም መንገዶችን የማያስኬዱ ሲሆኑ ለአጭር ጊዜ ጥቅምን ሊያስገኙ ቢችሉም በረጅም ጊዜ ግን ጉዳታቸው አመዛኝ ነው ። የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ ግን የረጅም ጊዜ ግብን ወይም ስኬትን አልሞ የሚጓዝ ሲሆን በሂደትም አንድ መሪን ከመንገዱ ከሚያጋጥሙ ከብዙ አላስፈላጊ ችግሮች የሚጠብቅ ነው ነው ። የአጭር ጊዜ ታክቲክ ከረጅም ጊዜ ስትራቴጂው ያፈነገጠ መሆን የለበትም ። ብዙውን ጊዜ የአጭር ጊዜ ታክቲክን ብቻ የሚጠቀሙ ሰዎች  ረጅም ርቀት መሄዳቸው አጠራጣሪ ነው ። መሄድ ከቻሉም ብዙ ዋጋ በሚያስከፍል መንገድ ሊሆን ይችላል ። ይህም በተደጋጋሚ በብዙ መስኮች በታሪክ የታየ አጋጣሚ ነው ።

ለአጭር ጊዜ እሚጠቅም ነገርን ማስፈንና ለረጅም ጊዜ ዘላቂ የሆነ ነገርን ማስፈን በጣም የተለያዩ ነገሮች ሲሆኑ እሚጠይቁት ጥረትና እሚኬድባቸው ጎዳናም የተለያየ ነው ። ብዙ ጊዜ ምእራባውያን የረጅም  ጊዜውን በማየት ነው እሚንቀሳቀሱት ።

በነገራችን ላይ ምእራባውያንም በአንድ ወቅት የአጭር ጊዜ ታክቲክን እንደ ትክክለኛ አማራጭ የሚወስዱበት ጊዜ የነበረ ሲሆን ይህንንም አፍሪካን በቅኝ ግዛት ሲይዙና ከዚያም በኋላም ቢሆን ምንም እንኳን ሀገራቱ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ወጡ ቢባልም ብዙዎች ሀገራት ግን እውነተኛ ነፃነት አልነበራቸውም  በተለይም የኢኮኖሚ ነፃነታቸው በምእራባውያን እጅ ሆኖ ለዘመናት ሲቆይ ፣ ነገር ግን የቀድሞ ታዳጊ ሀገራት በመባል ይታወቁ የነበሩት እነኚህ ሀገራት በምጣኔ - ሀብታቸው እያደጉ ሲሄዱና ፣ በአንፃሩ ግን ምእተራባውያን የምጣኔ - ሀብት የበላይነታቸውን እያጡ ሲመጡ እነኚህ ታዳጊ ሀገራት ነፃነታቸውን ማስመለስ መጀመራቸው ይታወቃል ተጠቅመውበታል።ሆኖም ግን አሁን ጉዳቱን በአመዛኙ ሰለተረዱት እየተውት መጥተዋል ።


የለውጥ አመራር



አንዳንዶች ለውጥ በመሪነት ውስጥ ያለውን ዋነኛ ቦታ በመረዳት መሪነት ማለት ለውጥን መምራት ነው ይላሉ ። አንድን ለውጥ መምራት የራሱ የሆኑ አካሄዶችና መስመሮች ያሉት ተግባር ነው ። አንድ መሪ በመሪነት ዘመኑ ለውጥ የማይቀር ጉዳይ በመሆኑ በዛ የለውጥ ጊዜ በሀላፊነት ስለሚቆይ ለውጡ የሚያስከትለውን አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ጎኖች መረዳት አለበት ።


በዋናነት ለውጥ ከሁለት አቅጣጫ የሚመጣ ነገር ሲሆን ፤ ከላይ ወደ ታች ወይም ከታች ወደ ላይ ሊመጣ ይችላል ።ከላይ ወደ ታች የሚመጣው ለውጥ በመሪዎች ተነሳሽነት የሚጀመር ሲሆን ፤ ከታች ወደ ላይ የሚመጣው ለውጥ ደግሞ በተከታዮች ተነሳሽነት የሚመጣ ነው ። ለምሳሌ በአገር ደረጃ የሚመጡ ለውጦች ከላይ ባሉ መሪዎች የሚደረጉ ሲሆኑ ይችላሉ ፣ ለምሳሌ በጃፓን አገር ፊውዳሎች መሬታቸውን በፈቃደኝነታቸው ለጭሰኞቹ በመልቀቅ ያለ ስር ነቀል አብዮት ለውጥን ማምጣት ችለዋል ።


በአንድ ድርጅት ውስጥም እንዲሁ የበላይ አመራሩ ለውጥን ሊያነሳሳ እና ሊያቅድ ይችላል ። ይህም ብዙሀኑ የማያዩትን ዋናውን ስእል በመረዳት መሆን አለበት ። ይህም ግራንድ ስትራቴጂ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ፣ ለብዙሀኑ ግልፅ ያልሆነውን በማየት መሪው እቅድ ሊያወጣና ሊመራ ወደ ሚፈልገው ወደ ዋናው መንገድ ሊመራ ያስችለዋል ።


ለውጥ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ተቋማትንና ኩባንያዎች በየጊዜው የሚከናወን ድርጊት  ሊያጋጥም የሚችል ነው ፣ ለምሳሌ ኢስትማን ኮዳክ የተባለው የፎቶ ፊልም አምራች ኩባንያ ቴክኖሎጂው ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ተቀይሮ ከዛ ጋር ራሱን ባለማስማማቱ ከዘመኑ የዲጂታል ፎቶ ግራፍ ቴክኖሎጂ ጋር ሊወዳደር ባለመቻሉ ለኪሳራ በመዳረግ መክሰሩን ይፋ በማድረግ የመንግስትን ድጋፍ ለመጠየቅ ተገዷል በአንፃሩ ፉጂ የተባለው የጃፓኑ የፎቶ ፊልሞችም አምራች ኩባንያ በጊዜ ራሱን በተወሰነ ደረጃ ከዘመኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር  በማስማማቱ ህልውናውን ማስጠበቅ ችሏል ።


የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚገልፁት «አዲስ ስርአትን ከመመስረት የበለጠ አደገኛ ነገር የለም» ድንገተኛና ያልተጠበቀ ለውጥ በሰዎች ስነ - ልቦና ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅእኖዎች ከባድ መሆናቸውን በመረዳት ነው ። ሌላው መሪው ለውጥ የሚያስፈልጋቸውንና የማያስፈልጋቸውን ነገሮችን በቅጡ መለየት አለበት ፣ አንዳንዶች የለውጥን በሰዎች ህይወትና አስተሳሰብ ውስጥ የሚፈጥረውን ስሜት ባለመረዳት ጥሩ ሀሳቦችን ፀንሰው ነገር ግን ለውጡን እንዴት መምራት እንዳለባቸው ማወቅ ባለመቻላቸው የታሰቡ ታላላቅ ነገሮች የትም ሳይደርሱ ቀርተዋል ።



ለውጥን ለማካሄድ ነባሮቹም ሆኑ አዲስ መሪዎች በሁለት አጣብቂኝ ውስጥ መገኘታቸው አይቀሬ ነው ። ለምሳሌ የሀገር መሪ ቢሆንየተወሰነ ለውጥ ቢደረግ ፣ ህዝቡ  ተጨማሪ ሊጠይቅና የተጀመረው ለውጥ እንዲቀጥል ሊፈልግ ይችላል ፣ የዚህ አይነት ፍላጎት ካለ ያለው ወቅታዊ የሆነው ነባራዊ ሁኔታ ዘላቂ እንዳልሆነ መገመት ይቻላል ። የተጀመረው ለውጥ እንዲቀጥልና ህዝቡ ሲፈልግ በአንፃሩ ደግሞ ፣ መሪው ለውጡን ከገፋበት የመሪው ስልጣን መሸርሸርንና ብሎም መጥፋትን ያስከትላል ብሎ ራሱ መሪው ሊሰጋ ሲችል ስለዚህ ያለው አማራጭ ምንም አይነት ለውጥን አለማድረግን እንደ አንድ አማራጭ አድርጎ መሪው ሊሰወስደው ይችላል ። ይሄም ግን በራሱ አደጋ አለው ፣ ይኀውም ለውጥ በሚያስፈልግበት ሁኔታ ምንም አይነት ማሻሻያን ሳይወስድ መሪው ዝም ብሎ ጊዜውን ሳይጠቀም ቢቀርና የለውጥ ፍላጎት ገፍቶ ቢወጣ ፣ መሪው ጊዜው ካለፈ በኋላ እንዲነቃና ስርአቱን ማዳን የማይችልበት ሁኔታንና አብዮትን እሚጋብዝበት ደረጃ ሊደርስና ሲችል መሪው ዘግይቶ በሚነቃበት ወቅት ጊዜው ሊያልፍ  ይችላል ።

ነባር መሪዎች ለውጥን ለማካሄድ ቢሞክሩም ፣ ነገር ግን ለመልካም ለውጥ ብለው የጀመሩት ነገር ሀዲዱን ስቶ ሁሉን ነገር አፈራርሶና ንዶት ቁጭ ሊል ይችላል ። የቀድሞዋ የሶቭየት ህብረት ፕሬዝዳንት ጎርባቾቭ ምንም እንኳን በአለም መድረክ ላይ ከምራባውያን ጋር መወዳደር እያቃተው የነበረውን የሶቭየት ህብረትን ስርአትን ጥገናዊ ለውጥን ለማድረግ የተነሱቢሆንም ፣ ጅምራቸው ባልተጠበቀ አቅጣጫ ሄዶ የሶቭየት ህብረትን ኮሚኒስታዊ አስተዳዳር ጨርሶ ሊያፈራርሰው በቅቷል ። 


አዲስ መሪዎችም ተመሳሳይ አጣብቂኝ ውስጥ ራሳቸውን ሊያገኙት ይችላሉ ፤ በአንድ በኩል ከእነሱ ቀድሞ የነበረው መሪ የሄደበትን መንገድ በተወሰነ ደረጃ መለወጥና ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ሊረዱ ሲችሉ እምን ደረጃ ድረስ ነው ለውጥን እሚያካሂዱት የሚለው ራሱን የቻለ እውቀትን ይጠይቃል ። እነሱም ቢሆኑ ለውጥ ማድረግ ስልጣናችንን ሊሸረሽር ይችላል ብለው ካሰቡ ፣ ምንም ሳያደርጉ ቁጭ ሊሉ ይችላሉ ። ጊዜ እያለፈ በሄደ ቁጥርም በዚህ ምክንያት በቀድሞው መሪ ላይ ጭምር የነበረው  ቅሬታ ፣ በጣም በመረረ ሁኔታ ሊመጣባቸው ይችላል ።


በአረቡ አመፅ ወቅት በሶሪያ መሪ በአሳድ ላይ የተነሳው ተቃውሞ ለበርካታ አመታት በአባትየው ዘመን  የነበረው ቅሬታ ጭምር የተገለፀበት ነው ። ልጅየው አሳድ ከአባቱ አሳድ የወረሰውን አስተዳደር ለውጦችንና ማሻሻያዎችን ለማድረግ ጊዜ የነበረው ቢሆንም ምንም ለውጥ ሳያደርግ በመቆየቱ ከቁጥጥር ውጪ የወጣ ህዝባዊ አመፅ ሊቀሰቀስና ስርአቱ ሊያከትምለት በቅቷል ። በሌሎችም የአረብ አገራትም እ.ኤ.አ. በ2012 የተነሱት ህዝባዊ አመፆችና ተቃውሞዎች የዚሁ የለውጥ አስፈላጊነት የቀሰቀሳቸው ናቸው ።


ከመፅሀፍ ቅዱስ ታሪክ ብንወሰድ ጠቢቡ ሰለሞን ከሞተ በኋላ የስልጣን ወራሹ ለነበረው ለልጁ ለሮአብም ዘመን ተገዢዎቹ ቀንበሩ መረረን ፣ እና አቅልልን ሲሉ ይጠይቁታል ። ነገር ግን ሮአብም ከአባቴ በበለጠ እጨቁናችኋለሁ በማለቱ ለእስራኤል ለሁለት መከፈልና ለእርስ በእርስ ጦርነት ተዳርገዋል ። በተለይ ተተኪዎች በለውጥ በኩል ጠንቃቃ መሆን ይገባቸዋል ። ምክንያቱም በቦታው አዲስ በመሆናቸው ፣ ከቀድሞው ተተኪ እንደመሆ ናቸውና በቀድሞው መሪ ዘመን የመጨቆን ስሜት የሚሰማው ህዝብ ወይንም ተከታያቸው አንድ አይነት ለውጥን ከነሱ መጠበቁ አይቀርም ።


ለውጥን መቋቋም ወይም እምቢ ባይነት (Resistance) በራሱ በመሪውም በኩል ሊመጣ ይችላል ። መሪው በዙሪያውና በስሩ ያለውን እውነታ ካለመረዳት የተነሳ ያንን ለውጥ ላይረዳው ይችላል ። ራሱም ለውጥን ላለመቀበል ሊያንገራግር ወይም እምቢ ሊል ይችላል።ለውጡ ራሱ ስልጣኔን ያሳጣኛል በሚል ፣ ወይም ለውጡ ያለኝን ነገር ሀብት ወይም ስልጣን ሊያሳጣ ይችላል ።


ለውጥን ማድረግ ራሱ የተቋሙ አይነት ይወስነዋል ለምሳሌ ፤ የቻይና መሪዎች ምንም እንኳን  ቢለዋወጡም ለውጥን አድርገው ሊከተል የሚችለውን አደጋ ለመጋፈጥ ራሳቸውን ሪስክ ለመውሰድ ፈቃደኞች አይደሉም ። ይህ ግን ውሎ አድሮ በጣም መሰረታዊ በሆነ ሁኔታ ወደ ስር-ነቀል ልውጥ አብዮት ሊያመራ ይችላል ህዝቡ ዝም ብሎ የመሪዎች መለዋወጥ ብቻ ከሆነና መሰረታዊ ለውጥ እንደማይመጣ ሲረዳና ተስፋ መቁረጥ ሲጀምር ። በአንፃሩ እንደ አሜሪካ ባሉ ዲሞክራሲያዊ ስርአቶች ውስጥ ግን መሪዎች በምርጫ ሲለወጡ ለውጥን ማምጣት ቀላል ይሆንላቸዋል ። ለዚህም ምክንያቱ ራሱ ፕሬዝዳንቱም ሆኑ ሌሎቹ የህዝብ ተመራጮች ለመመረጥ የቀድሞውን መሪ ፖሊሲን ለመለወጥ ቃል ገብተው ስለሆነ ፣ እንደተመረጡ የገቡትንና ህዝቡም የሚጠብቀውን ቃል በቀላሉ መፈፀም ይችላሉ ። ለምሳሌ ግብር እቀንሳለሁ ብሎ ቃል ከገባ ፣ ወይም ከዚህ አገር ጦር ሰራዊት አስወጣለሁ የገባውን ቃል መፈፀም ይችላል ።


በጦርነት ወቅት ለውጥን ማካሄድ እጅግ ፈታኝ ነው ። ለምሳሌ ብዙ ጦርነትን የጀመሩ መሪዎች የሚጨርሱት እነሱ ሳይሆኑ ከእነሱ በኋላ የሚመጡ መሪዎች ናቸው ያን ጦርነት እንዲያበቃ የሚያደርጉት ። ለምሳሌ አሜሪካ በኢራቅም ሆነ በቬትናም ጦርነት ወቅት ጦርነቱን የጀመሩትምንም እንኳንበፕሬዝዳንት ኬኔዲ ይመሩ የነበሩት ዲሞክራቶች የነበሩ ቢሆንም ጦርነቱን ያስቆሙት ተቃናቃኝ ከነበረው ፓርቲ ከሪፐብሊካን መሪዎች ሲሆኑ ፣ በኢራቅ ጦርነትም ወቅት ፕሬዝዳንት አሜሪካ ኢራቅ ውስጥ ከባድ መስዋእትነትን እየከፈለችበት በነበረበት ወቅት ከኢራቅ የእንውጣና ጦርነቱ እንዲቆም ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ጦርነቱ ለማስቆምም ሆነ ወታደሮቻቸውን ከኢራቅ ለማስወጣት ፈቃደኛ አልነበሩም ። እርሳቸው ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ፣ የአሜሪካ ወታደሮች ከአፍጋኒስታንና ከኢራቅ አስወጣለሁ የሚል ቃልን ገብተው በተመረጡት በአዲሱ ፕሬዝዳንት አሜሪካ ከኢራቅም ሆነ ከአፍጋኒስታን ጦርነቶች ልትወጣ በቅታለች። ይህም የሚፈጥረው የእልህና የስሜታዊተነት የበላይ አመራሩና መሪዎቹ እስካልተለወጡ ድረስ የፖሊሲ ለውጥን ማምጣት አስቸጋሪ በመሆኑ ነው ።


የጃፓኖች የአመራር ስልት ካይዘን ማለት ቀጣይና ያልተቋረጠ ለውጥን ማድረግ ማለት ነው ። ይህም የዚሁ የለውጥን አስፈላጊነት የተረዳና ለውጥን ማስቀጠልንና ማካሄድን ለማመልከት ነው ። በሀገራችንም እንዲሁ የዚህ አስተዳደር አይነት በተለያዩ ድርጅቶች ተግባራዊ መደረግ የጀመረ ሲሆን ። ይህም ከምእራቡ አለም የኮርፖሬት አስተዳዳር አይነት ለየት ያለ ነው ። እንደ ቶዮታን የመሳሰሉ ግዙፍ የጃፓን ኮርፖሬሽኖች የሚመሩበት እና ስኬታማ የሆነው ይኀው የአስተዳደር ዘዴ ነው ።


ዝርዝር አፈፃፀሞችን ለመረዳት መሞከርና መከታተል አንዱ አስፈላጊ የመሪነት ችሎታ ነው ። የነገሮችን ሂደት አስቀድሞ ማየት መቻል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ልክ በጥንታዊ የግሪክ ተረቶች እንደተጠቀሰው አማልክትና መላእክት ገና ያልደረሰውን ነገር አስቀድመው ያያሉ ብለው ያምናሉ ። ይህም ሊመጣ የሚችለውን እና የሚያስፈልገውን ለውጥ ለማቀድ ይረዳዋል ።
     

 ብዙውን ጊዜ መሪዎች ስህተት የሚሰሩት በድል ወቅት ነው ። በድል ወቅት በሚፈጠር ከልክ ያለፈ የራስ መተማመን ስሜትና የአልበገሬነት ስሜት በመገፋፋት ስሜታዊ የሆነ እርምጃን ፣ እንዲሁም  አለአግባብ ሌሎችን የሚያስቀይሙ ፣ በቀላሉ ከሌሎች አእምሮ ሊፋቁ የማይችሉ ቃላትን ሊናገሩ ይችላሉ ።ንግግሮችን ሊናገሩ ይችላሉ ።


አንድ መሪ ከተከታዮቹ ወይም ከህዝቡ የሚያገኘውን ድጋፍ ለሁልግዜውም እንደሚያገኘው አድርጎ (For Granted) መውሰድ የሌለበት ሲሆን ፣ የተከታዮቹንም ሆነ የህዝብን ድጋፍ እሚያገኘው በትክክለኛው መንገድ እስከመራ ድረስ ብቻ ነው ። ከዛ ውጪ ግን በተሳሳተ ጎዳና ከሄደ ያገኝ የነበረውን ድጋፍ ያለምንም ጥርጥር ያጣል ። ለምሳሌ የፈረንሳይን አብዮትን ብንወስድ የፈረንሳይ ህዝብ ነገስታቱን እጅግ የሚያከብርና የሚወድ ህዝብ እንደሆነ ይነገርለታል ። ነገር ግን ከሉዊስ 14ኛ በኋላ የተነሱት የሉዊስ 14ኛ ልጆችና የልጅ ልጆች እጅግ የሚከበረውንና የሚፈራውን በርቦርን በመባል የሚታወቀው የፈረንሳይ ነገስታት ዘሮች ቢሆኑም የፀሀዩ ንጉስን ዙፋን ቢወርሱም ፣ ድርጊታቸውና በስልጣን መባለጋቸው ፣ የሀገሪቱን ግምጃ ቤት ማራቆታቸው የአያታቸው ገናና ስምና ተወዳጅነት ሊያድናቸው አልቻለም ። በዚህ ምክንያት  በምእራቡ አለም የመጀመሪያው የሆነው የፈረንሳይ አብዮት እ.ኤ.አ. በ1789 ሊካሄድ ችሏል ፣ ከዚህ በኋላም ለተወሰኑ ጊዜያት ዘውዱን ለመመለስ የተሞከረ ቢሆንም ፣ የበርቦን ዘሮች ዳግመኛ ወደ ፈረንሳይ ዙፋን ሳይመጡ ቀርተው ከታሪክ ገፅ ተወግደዋል ።
   

  አንዳንድ መሪዎች ለተከታዮቻቸው እኔ እምለውን አድርጉ እንጂ እኔ እማደርገውን አታድርጉ ላሉ ይሁን እንጂ ተከታዮች መሪያቸው የሚያደርገውን ማንኛውንም ነገር ያያሉ ፣ ከሚናገረውም ነገር ጋር ያስተያዩታል ። ስለዚህ እኔ የምናገረውን ብቻ አድርጉ ፣ የማደርገውን አትዩ ወይም የማደርገውን አታድርጉ የሚለው አያስኬድም ። ይህ ብቻ ሳይሆን በተከታዮቹ ዘንድ ያለውን አመኔታም ክፉኛ ይሸረሽርበታል ። ሌላው ደግሞ መሪዎች በአንድ ዘርፍ ትክክለኛ ነገርን እያደረኩ ስለሆነ ፣ በሌላኛው ዘርፍ ባበላሽም ፣ ብሳሳትም አትጠይቁኝ የሚል አቋም ያላቸው መሪዎች አሉ ። ለምሳሌ የአፍሪካ መሪዎች ምጣኔ - ሀብቱን  እያሳደኩ ስለሆነ በዲሞክራሲ ወይንም  በሰብአዊ መብት ጉዳይ ምንም አይነት ጥያቄን አትጠይቁኝ ሊሉ ይችላሉ ። ነገር ግን ይህ አዋጪ መንገድ አይደለም ፣ ምክንያቱም በአንድ ዘርፍ ትክክል መሆን በሌላ ዘርፍ ስህተትን ወይንም እማይደረገውን ነገር እንዲያደርግ እድልን አይለጠውጠውም ።
     

 ጦርነት የእርስ በእርስ ጭቃ መቀባባትን የሚያስከትል አስቀያሚ ነገር ሲሆን ፣ በአካላዊ ብቻ ሳይሆን በስነ- ልቦናም ጭምር የሚያደርሰው ጉዳት ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ፣ ከጉዳቱም ለማገገም አመታትን ይፈጃል ። ጦርነት የፖለቲካ ልዩነት ተቀጥላ ሲሆን በክላውሽዊትዝ እንደተገለጠው ይህ ብቻ ሳይሆን ፣ በአሸናፊነት ለመወጣት ጦርነት ፍትሀዊ መሆን አለበት ። ጥሎት የሚሄደው በቀላሉ የማይሽር ጠባሳና ሰቀቀን (Trauma) እንዲሁ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ የሚያደርሰው መናጋት ከፍተኛ ስለሚሆን በአመታት ውስጥ በቀላሉ የማይሽር ነው ። አንዱ የመሪው ስራ የግጭት ፍንጮችን በማየት ፣ ገና ብቅ ሲሉ መስተካከል የሚችሉትን ማስቀረት መቻል ነው ። በጣም አስፈላጊ ካልሆነና ማስቀረት የማይቻል ካልሆነ በስተቀር ወደ ግጭት ሊገባ የሚችልበትን መንገድ በሚችለው አቅሙ ማስቀረት መቻል አለበት ።ይህ ብቻ ሳይሆን ጦርነት ንፁሀን የሆኑ ነገር ግን የጦርነቱ ሰለባ የሚሆኑ ሰዎችን ይፈጥራል ። በጦርነት ውስጥ  በሁሉም ወገኖች አስፈላጊ ከሆነው በላይ እርምጃ  የመወሰድ አደጋም አለ ።